የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የዛሬ አስራ ስድስት አመት ሲቋቋም ዓላማው አድርጎ የተነሳው የግብርና ምርቶች ግብይትን በማዘመን ዘመናዊ የግብይት ስርአትን ለመመስረትና ለማስፋፋት ነው፤ ነጻ የሆነና የተገበያዮችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የገበያ ስርአት መፍጠርና በአነስተኛ ማሳዎች የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ግልጽና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ምርቶቻቸውን ለገበያ አቅርበው የሚሸጡበትን ሁኔታ ማመቻቸትም ሌላው ከአላማዎቹ መካከል ይጠቀሳል። ምርቶቹ ለገበያ ሲቀርቡ ምን አይነት መስፈርት ያሟሉ ናቸው? የሚለውን በማረጋገጥ ውል ማዘጋጀትና ግብይቱን ማካሄድ የተቋሙ ዋነኛ ተልእኮዎች ናቸው።
ተቋሙ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከመወጣት አንጻር ባለፉት አመታት ባከናወናቸው፣ እያከናወናቸው ባሉና በቀጣይ ሊያከናውናቸው በያዛቸው እቅዶች ዙሪያ ያነጋገርናቸው የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአዋጅ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ላለፉት አስራ ስድስት አመታትም ሃያ ሁለት የግብርና ምርት አይነቶች የኮንትራት ውል እየተፈጸመላቸው ተስተናግደዋል።
ምርቶቹ ወደ ግብይት ስርአቱ ከመጡ በኋላ ግልጽ በሆነ ጨረታ ገዢዎችና ሻጮች ውድድርን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲገበያዩ ይደረጋል። ገበያው የሚካሄደው በቅድሚያ ለሸያጭ የሚቀርቡት ምርቶች ወደመጋዘን ገብተው ለአቅራቢው የምርቱን መጠን፤ አይነትና ደረጃ የሚገልጽ ደረሰኝ ከተሰጠ በኋላ ነው።
በአንጻሩ ገዢውም ለመገበያያ የሚሆነውን በቂ ገንዘብ በባንክ ማስቀመጡ ይረጋገጣል። ይህ ከባንክ ጋር የሚደረግ የክፍያ ስርአት በአቅራቢዎች ላይ ከሚፈጸም የደረቅ ቼክ ማጭበርበር ወንጀልና ክፍያ ማዘግየት ማስቀረት ባለፈ እንደ ሀገር ለፋይናንስ ስርአቱ ተአማኒነትም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በዚህም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተቋቋመ አንስቶ ያለ መስተጓጎል የግብይት ክፍያዎች ከሃያ አራት ሰአት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲከፈሉ ያስቻለ ተቋም ሆኖ ቆይቷል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ። የክፍያ ስርአቱ ከሃያ ሶስት ባንኮች ጋር በስምምነት የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አቅራቢዎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ቢሆኑ ገንዘቡ በዚሁ ጊዜ እንዲደርሳቸው ይደረጋል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባንኮች የወጪ ንግድን ለማበረታታት በዝቅተኛ የወለድ መጠን ለግብይት የሚያበድሩት ገንዘብ ለሌላ ጥቅም እንዳይውል ያደርጋል ሲሉ ጠቅሰው፤ ይህ የሚሆነውም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይት ሲፈጸም ባንኮች ብድሩን ከፈቀዱ በኋላ ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለዚሁ በተዘጋጀ አካውንት እንዲገባ ተደርጎ መሆኑን ያብራራሉ። ተበዳሪዎች ምርት ከገዙ ክፍያው እንደሚፈጸም አስታውቀው፣ በማንኛውም ሁኔታ ግዢው ሳይፈጸም ከቀረ ግን የገንዘቡ እንቅስቃሴ የሚወሰነው በባንኩ ፈቃድ ብቻ ይሆናል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ሌላው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲሰራው የነበረውና በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገው ሥራ ወቅታዊ የገበያ መረጃዎችን ለሚፈልጉ አካላት ተደራሽ ማደረግ ነው። ይህ ስራ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ አምራቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግም ነው። ምርት ገበያ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት የመረጃ ክፍተት በመኖሩ ገበያው የሚወሰነው በጥቂት ገዢዎች ብቻ ነበር። በዚህም የተነሳ አምራቹ የመደራደር አቅም ስላልነበረው በአብዛኛው ዋጋ ተቀባይ በመሆን በተቀመጠለት ብቻ ለመሸጥ ይገደድም ነበር።
ምርት ገበያ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ግን የየወቅቱን ገበያ ዋጋ እንዲያውቅ በመደረጉ ዋጋው የማይስማማው ከሆነ ምርቱን ባለበት በማቆየት ከትራንስፖርትና ከውጣ ውረድ ራሱን ለመጠበቅ የሚያስችለው ሆኗል። በየቀኑ በሚለቀቀው መረጃ የትኛው ምርት ? በየትኛው አካባቢ ? በምን ዋጋ ? ለገበያ እየቀረበ እንደሆነ ይገለጻል። ይህም ለገዢና ለሻጭ ብቻ ሳይሆን አምራቾችም ገበያው የትኛውን ምርት እየፈለገ/ እየተቀበለ እንደሆነ እንዲያውቁና ምን ላምርት ? ለሚለው ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ፤ ብሎም ምርታቸውን መቼ በስንት ዋጋ መሸጥ እንደሚችሉ ባሉበት የተረጋገጠ መረጃ እንዲደርሳቸው የሚያስችል ሆኗል።
በዚህ ረገድ በሰሊጥ ሰብል ከታየው የምርት መጨመር ባለፈ በኢትዮጵያ በወጪ ንግድ የማይታወቁ እንደ አኩሪ አተር፤ አረንጓዴ ማሾ፤ የእርግብ አተር፤ የመሳሰሉትን ወደ ገበያው ለማስገባት ተችሏል። አኩሪ አተር በስፋት የሚታወቀው «ፓዊ» አካባቢ ብቻ ሲሆን፤ የዛሬ አራት አመት ወደገበያው ሲቀላቀል ከነበረው በኩንታል 700 ብር ዋጋ በአሁኑ ወቅት እስከ አራት ሺ ብር መድረስ ችሏል። ይህም ከአካባቢው ባለፈ በተለያዩ ቦታዎች በስፋት እንዲመረት ለማድረግ አስችሏል።
በተመሳሳይ ወላይታ አካባቢ ብቻ በትንንሽ መሬቶች ይመረት የነበረው የእርግብ አተርም ዛሬ በክላስተር ደረጃ እየተመረተ ይገኛል። በቅርቡም በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት የተጀመሩ ስራዎች አሉ።
ተቋሙ በየእለቱ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከሰላሳ አምስት በላይ የክልልና የፌዴራል ሚዲያዎችን እንዲሁም ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሁለት አጭር የስልክ ጥሪ መስመሮችን እየተጠቀመ ይገኛል።
በተጨማሪ በመረጃ ተደራሽነት ረገድ ምርት ገበያው ከተመሰረተ ጀምሮ በስሩ የተገበያዩትን አካላትና መረጃዎችን ሰንዶ ያስቀምጣል። መረጃዎቹም በየወቅቱ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ቡና ሲሆን፤ ለቡናና ሻይ ባለስልጣን ይላካሉ።
ይህም ማን ምን ያህል ተገበያየ የሚለውን በመረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ከመሆን በተጨማሪ ለታክስ አሰባሰብም የሚጫወተው የራሱ ሚና አለው። በዚህ ስርአት ባለፉት አስራ ስደስት አመታት 18 ቢሊዮን ብር /ከአስራ ስምንት ቢሊዮን ብር/ በላይ በቫት፤ በዊዝ ሆልዲንግና በሌሎች የታክስ አይነቶች የመንግስት ገቢ እንዲሰበሰብ ማድረግ አስችሏል።
ከዚህ ውስጥ የአቅራቢዎች ሁለት በመቶ ዊዝ ሆልዲንግ እየተያዘ ለክልሎች ስለሚላክ በክልል ያሉ ግብር ሰብሳቢዎችም ይህንን መሰረት አድርገው ገቢ ለመሰብሰብ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተጨማሪም ለውጪ ገበያ የተገዙት ምርቶች በተፈቀደው መሰረት ወደ ውጪ መላክ አለመላካቸውን ለመቆጣጠርም ይረዳል። ለውጪ ገበያ ከሚቀርብ ምርት እስከ ሀያ በመቶ ተረፈ ምርት ስለሚያዝ ይህም ለሀገር ውስጥ ገበያ ሲቀርብ በምርት ገበያ በኩል ቫት የሚሰበሰብበት ይሆናል። እነዚህ መረጃዎች ከጉምሩክና ብሄራዊ ባንክ ከሚሰጡት ጋር ተዳምረው የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር የሚረዱ ናቸው።
ኢትዮጵያ በርካታ የቡና አይነት ያሉባት ሀገር ብትሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ በስም የሚታወቁት የሀረር፤ የሲዳማ፤ የሊሙ፤ ጅማ፤ ነቀምትና የይርጋ ጨፌ ብቻ ነበሩ የሚሉት አቶ ወንድማገኝ፤ እያንዳንዱ ወረዳ የራሱ መለያና ጣእም አለው ይላሉ። ከክልሎችና ከአምራቾች በቀረበ ጥያቄ መሰረት የጉጂ፤ የአርሲ፤ የከፋ፤ የባሌ፤ የኢሉ አባቦራ የምእራብ ወለጋ፤ የቄለም ወለጋ፤ የተባሉ መለያዎች እንዲወጡ ተደርጓል ሲሉም ጠቅሰው፤ ይህም በተለይ ለውጪ ገበያ የሚቀርበው ቡና ከየት አካባቢ እንደመጣና ደረጃውንም ለማሳየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። ደረጃው ከአለም አቀፍ ገበያ ጋርም እንዲናበብ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ መለያው ተሰርቶ የምርት ኮንትራቶች በሚዘጋጁበት ወቅትም የሚቀርበው ምርት ደረጃው ምንድን ነው የሚለው ይሰራል። በዚህም መሰረት የጥራትና የእርጥበት ደረጃው በየወቅቱ እየተፈተሸ የሚገኘው ውጤት ምርቱ ለተነሳባቸው ወረዳዎች ይላካል። ይህ የሚደረገውም ክፍተት ካለ ከአርሶ አደሩ ጋር በመምከር እንዲያስተካክሉት ለማድረግ ነው።
በዚህም መሰረት እስካሁን እጣንን ጨምሮ ለሀያ ሁለት የግብርና ምርቶች የጥራት ደረጃ መወሰኛ በማውጣት የኮንትራት ውል በማዘጋጀት እየተስተናገዱ ይገኛሉ። የግብይት ማእከልም አዲስ አበባ ብቻ የነበረውን ተደራሽ ለማድረግ በክልሎች ማለትም አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ጅማና ጎንደር ማእከላት ተከፍተዋል። እነዚህ ማእከላት በኤሌክትሮኒክ ሲስተም ሁሉም በአንድ ጊዜ መገናኘት የሚችሉ ሲሆን፤ ምርቱም መጋዘን ከገባ ጀምሮ በሲስተም ተመዝግቦ ናሙና ወጥቶለት ኮድ ተሰጥቶትና በላቦራቶሪ የጥራት ደረጃው ታይቶ ለየብቻው የሚቀመጥ ይሆናል።
ድሮ ለቡና ገበያ ምርት ሲቀርብ ማእከላዊ ገበያ ድረስ እንዲመጣ ይደረግ የነበረው አሰራር አድካሚ እንደነበር አስታውሰው፣ በገበያ አማካይነት ገበያውን ለአምራቾች በአካባቢያቸው ተደራሽ ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል። ለዚህም ምርት ገበያው ባሉት ሀያ አምስት ቅርንጫፎች ስር ከስልሳ በላይ መጋዘኖችን አዘጋጅቷል ያሉት ዋና ስራ አስፈጸሚው፣ በመቱ፤ በጎንደር፤ በቡሌ ሆራ፤ በቴፒ፤ ጎንደርና ኮምቦልቻን ከ150 ሺ ኩንታል በላይ መያዝ የሚችሉ ዘመናዊ መጋዘኖች እንዳሉት አብራርተዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በቀድሞው አካሄድ አርሶ አደሩ ምርቱን ገበያ አቅርቦ ካልሸጠ ይዞት ይመለስ ነበር። በዚህም ለከፍተኛ ወጪ ሲዳረግ ኖሯል። ምርቱም ለተለያዩ የጥራት ችግሮች ይጋለጥ ነበር። እነዚህ መጋዘኖች በመቋቋማቸው ግን በአቅራቢው በሚገኙት መጋዘኖች ምርቱን በማስቀመጥ እስከ አንድ ወር ጊዜ የሚፈልገውን ዋጋ ጠብቆ የሚሸጥበት እድል ተፈጥሮለታል። የጥራት ፍተሻው ባሉት ሀያ አምስት ቅርንጫፎች የላቦራቶሪ አገልግሎትን ጨምሮ እየተሰጠ ይገኛል። አገልግሎቱ የሚሰጠው በምርት ገበያው ብቻ ለሚገበያዩት ሳይሆን በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት ለሚያደርጉት የምርት ልውውጥም ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኮሞዲቲ ኤክስቼንጅ እንዲሁም በስቶክ ኤክስቼንጅ ረገድ ያሉ ዘመናዊ የግብይት ስርአት እሳቤዎችን በተመለከተ የእውቀት ሽግግር እንዲኖርም በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ይላሉ። የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከደብረ ብርሃን፣ ባህርዳር፣ ጂማ፣ ቅድስተ ማርያምና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎች የምርምር ስራዎችን እንዲሰሩና ልምድ እንዲወስዱም ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። በተጨማሪም ከስምንት የአፍሪካ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ የቻለ ሲሆን፤ አካዳሚ በማቋቋም ከአፍሪካ ሀገራት የመጡ ተማሪዎችን ጨምሮ አራተኛ ዙር የደረሰ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት በቅቷል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ቡና ለውጪ ምንዛሬ ከፍተኛ ምንጭ በመሆኑና ለሀገር ገጽታም ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው በገበያው በልዩነት የሚታይ ሲሆን፣ ምርት ገበያው ከተቋቋመ በኋላ ከጥራጥሬና ስንዴ ቀጥሎ ገበያውን የተቀላቀለ ምርት ነው። ቡና የተለያየ አይነት ያለው በመሆኑ ማንነትን ገላጭ በሆነ መንገድ መቀመጥ ተአማኒነትን ለማረጋገጥ ለእያንዳንዱ መለያ የእርጥበት መጠን ቅምሻውን የመለየት ስራ ይሰራል። ይህም ገዢው የሚያነሳው ምርት የማን እንደሆነ ከየት እንደመጣ አጠቃላይ መረጃ እንዲኖረው ያስችላል። ገዢዎች ምርቱን ከመሸመታቸው በፊት የምርቱ ወካይ ናሙና በቅርንጫፍ እንዲያዩ ይቀመጥላቸዋል። ከገዙም በኋላ በገዙት ደረጃ መሰረት መሆኑን ማረጋገጥ የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቷል።
በተመሳሳይ አንድ ሻጭ ቡና አዘጋጅቶ ከቤቱ ሲወጣ የምርቱ ደረጃ ይሄ ይሆናል ብሎ የሚገምተው ይኖራል። ነገር ግን ሲቀርብ በሙያተኞች ናሙና ተወስዶ ማለትም በማየት 40 በመቶ በቅምሻ 60 በመቶ ነጥብ ተሰጥቶት ደረጃ ይወጣለታል። ይህ ደረጃ በሁለት ዙር በሁለት ቡድኖች ተመሳሳይ የኤሌክትሪክ መመዝገቢያዎችን በመጠቀም የሚሰጥ ይሆናል። በዚህ ሂደት አልፎም ሻጩ ባሰበው ደረጃ ሳይሆንለት ቀርቶ ቅሬታ ካለው በቅርንጫፍ ወይንም በዋናው መስሪያ ቤት ቅሬታውን ያቀርባል። በዚህም ካልረካ ቡና ከሆነ ቡናና ሻይ ጥራጥሬና ቅባት እህል ከሆነ ደግሞ በተስማሚነት ምዘና የሚታይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እነዚህን መንገዶች በመጠቀም ባለፉት አስራ ስድስት አመታት ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርቶችን በማስተላለፍ ከ382 ቢሊዮን ብር በላይ ማገበያየት ተችሏል። ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት የቀረበው ለውጪ ገበያ ነው።
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ምርት ገበያና በህብረት ስራ ማህበራት ብቻ ይገበያይ የነበረው ቡና አምስት የገበያ አማራጮች እንዲኖሩት ተደርጓል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህ አካሄድ ተገቢነት ቢኖረውም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግን ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሌላው ተለይቶ በየሳምንቱ በሚላክ የመገበያያ ዋጋ ጣራ ተመን ተቀመጦለታል ሲሉ አመልክተዋል። ይህም የነጻ ንግድ ውድድር አካሄዱን ስላዛባው ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በፈረሱላ አራት ሺ ብር ሲሸጥ በሌሎቹ እስከ ሰባት ሺ የሚደርስበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ አካሄድ የንግድ ስርአቱን ፍትሃዊነት ከጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኗል ብለዋል።
ለቀጣይ ምርት ገበያው ያሉትን የወጪ የግብርናና ምርቶችን አጥንቶ ለማስገባት የኢንዱስትሪ ምርቶች ማለትም የምግብና የኢንዱስትሪ ጨውና ጥጥ እንዲሁም በሌሎቹም ለመሳተፍ እቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደ ዋና ከተቀመጡት ሴክተሮች መካከል ማእድን አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የከበሩ ድንጋዮች ሳፋሪ ኦፓል ሲሚንቶ የመሳሰሉትን ለመነገድ ከማእድን ሚኒስቴር ጋር ስራዎች መጀመራቸውንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ወንድማገኝ አመልክተዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም