በኬንያ ናይሮቢ በተከሰተ ከባድ ጎርፍ ቢያንስ 32 ሰዎች ሞቱ

በኬንያ መዲና ናይሮቢ በተከሰተ ከባድ ጎርፍ መንገዶች በውሃ ተጥለቅልቀው የታዩ ሲሆን የሀገሪቱ ባለሥልጣን የጎርፉ መጠን “እጅግ በከፋ ደረጃ እየጨመረ ነው” ብለዋል። ባለፉት ቀናት በኬንያ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ መጠነ ሰፊ ውድመት እያስከተለ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቢያንስ 32 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እና ከ40 ሺህ የሚበልጡት ደግሞ በዝናቡ እና ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለመሸሽ መገደዳቸውን ገልጿል።

በኬንያ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የናይሮቢ ተወካይ የሆኑት ኤዲን ሲፉና ባጋሩት ቪዲዮ በጎርፍ የተጥለቀለቀ ሰፈርን አስመልክተዋል።

በቪዲዮው ላይ መውጫ ያጡ ነዋሪዎች የቤታቸው ጣሪያ ላይ ተቀምጠው ይታያሉ። “በናይሮቢ ያለው ሁኔታ እጅግ በከፋ ሁኔታ እየተባባሰ ነው። የከተማው መንግሥት ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል። ሁሉም ሀገር አቀፍ የአደጋ ጊዜ ደጋፊዎችን እንፈልጋለን” ብለዋል።

በናይሮቢና አካባቢው በርካታ የመኖሪያ መንደሮች በአንድ ሌሊት በሚጥል ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ ተጥለቅልቀዋል። ማታሬ በተባለ ከፍተኛ ሰዎች በሚኖርበት አካባቢ ነዋሪዎች ጣሪያ ላይ ለማደር መገደዳቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሀገሪቱ ዋና ዋና መንገዶች ከፍተኛ መጠን ባለው ዝናብ ተጥለቅልቀው የታዩ ሲሆን የትራፊክ መጨናነቅን እያስከተሉ ነው።

የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር “ለረዥም ሰዓታት መውጫ ያጣው ሕጻን በሚታይ ሁኔታ ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ሆኖ ይንቀጠቀጥ ነበር። ደኅንነቱ ተጠብቆ ከአደጋው ተርፎ አቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስዷል” ብሏል።

ኬንያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም ባለፉት ሳምንታት በጣለው ከባድ ዝናብ ተፅዕኖ ውስጥ ወድቀዋል። በብሩንዲ 100 ሺህ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ሲፈናቀሉ በታንዛንያ ደግሞ 58 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1997 እና 1998 በምሥራቅ አፍሪካ በተመሳሳይ በተከታታይ የጣለው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You