በአማራ ክልል የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች ይገኛሉ። ክልሉ በወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ የድንጋይ ከሰል፣ ጂብሰም፣ የኖራ ድንጋይ እና ሌሎች በርካታ ማዕድናት ይገኙበታል፡፡ እስካሁን በክልሉ ከ40 በላይ ማዕድናት (የኢንዱስትሪ፤ የኮንስትራክሽን፤ የከበሩ ጌጣጌጥ፣ የኢነርጂ የማዕድን ውሃ እና ጂኦተርማል ማዕድናት) ክምችት እንዳለ በጥናት ተረጋግጧል፡፡
የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ክልሉ ካሉት እምቅ የማዕድን ሀብቶች መካከል እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች የተለዩት 70 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ ጥናቱ የሚሸፍነው የክልሉ የቆዳ ስፋት ከ33 ነጥብ 3 በመቶ በታች ያህሉ ነው፡፡ አሁን ላይም ተጨማሪ አካባቢዎች ላይ ጥናት የማካሄዱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ እስካሁን 40 የሚደርሱ ማዕድናት በጥናት ተለይተዋል፡፡ በጥናቱ ከተለዩት መካከል ኦፓል፣ ወርቅ ፣ ጂብሰም፣ የድንጋይ ከሰል ፣ ቤንቶናይት ፣ ሁሚስት፣ የኖራ ድንጋይ እና መሰል የማዕድን አይነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት በጥናት ከተለዩት መካከል ‹ሲሊካ ሳንድ › የተሰኘ ማዕድን ተገኝቷል። ‹ሲሊካ ሳንድ › የተሰኘው ማዕድን ለማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን በጥናት የተለዩትን ማዕድናት ማልማት ለሚችሉ አልሚ ባለሀብቶችም ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል። በዘጠኝ ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትም እንደሚከተው ቀርቧል፡፡
የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት
በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በክልሉ ያሉትን ወርቅ፣ ኦፓል፣ አጌት፣ ጃስፐር የማዕድናት ክምችት ለማወቅ በተደረገ የፍለጋ ጥናት ከነበረበት 90 ነጥብ ስምንት ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ወደ 138 በላይ ካሬ ኪሎ ሜትር ለማሳደግ የሚያስችል የፍለጋ ጥናት ተካሂዷል፡፡
በዚህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የነባር ፕሮጀክቶች በ 10 ካሬ ኪሎ ሜትር በተመረጡ ወረዳዎች የወርቅ ማዕድን ጥራት፣ ስርጭትና ክምችት ጥናት መካሄዱ ተመላክቷል፡፡ የጥናቱ የናሙና ውጤት በላብራቶሪ ተረጋግጦ 46 ነጥብ ሶስት PPM (Part Per Milion) የሆነ የወርቅ ማዕድን ክምችት እንዳለ ታወቋል፡፡ ይህም በአካባቢው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የወርቅ ክምችት ያለ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡
በተጨማሪም በ2015 ዓ.ም በሰሜን ወሎ ዞን የከበሩ ማዕድናት ላይ በአምስት ካሬ ኪሎ ሜትር በተደረገ ጥናት የኦፓል ማዕድን መገኘቱ ተመላክቷል።
በሌላ በኩል ይህን ግብ ለማሳካት አምስት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በመፈጸም 48 ካሬ ኪሎ ሜትር ለማጥናት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን በጀት ባለመፈቀዱ ምክንያት ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻለ አስታውቋል ፡፡
ኢንዱስትሪ እና ኮንስትራክሽን ማዕድናት
በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪ እና ኮንስትራክሽን ማዕድናት ላይ 3973 በላይ ካሬ ኪሎ ሜትር ሲደረግ የነበረው ጥናት ወደ 4053 በላይ ካሬ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም በ2014 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን የሸክላ አፈር ማዕድን ፍለጋ በተካሄደው ጥናት በአምስት ካሬ ኪሎ ሜትር መስፈርት ሶስት ሜትር ጥልቀት እና 15 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ክምችት ጥራት ያለው የሸክላ አፈር ማግኘት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በ2015 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን የፑሚስ ማዕድን ፍለጋ በተደረገው ጥናት መስፈርት በ200 ካሬ ኪሎ ሜትር የተካሄደው ሲሆን፤ በ126 ካሬ ኪሎ ሜትር 30 ሜትር ጥልቀት ያለው የፑሚስ ማዕድን ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
በሌላ በኩል ይህን ግብ ለማሳካት በአራት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም 80 ካሬ ኪሎ ሜትር ለማጥናት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በጀት ባለመፈቀዱ ሥራው እንዳልተሠራ ተመላክቷል፡፡
የብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት
የብረትና ብረትነክ ማዕድናትን (ወርቅ፣ኒኬል፣ ኮፐር እና የመሳሳሉት) ፍለጋ በ277 ነጥብ 5 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የተካሄደ ሲሆን፤ ጥናቱን 387 በላይ ካሬ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
በ2015 ዓ.ም የብረት ማዕድን ለመፈለግ በተደረገው ጥናት በምስራቅ ጎጃም ዞን ሶስት ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ በተደረገ ጥናት ከ 17 ነጥብ 44 እስከ 39 ነጥብ 36 በመቶ የብረት ማዕድን መጠን ያለው እና 505,418,842.5 ቶን የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
በ2015 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን የሊትየም ማዕድን ለመፈለግ በተደረገ ጥናት በ50 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ በአካባቢው ከ0.01 ppm እና በታች መጠን ያለው የሊትየም ማዕድን አዘል አለት ተገኝቷል። በጥናት ውጤት መሠረት በአካባቢው ተጨማሪ ጥልቅ የሊትየም ማዕድን ጥናት ተጠናክሮ እንዲካሄድ ከባለሙያ ምክረ ሃሳብ የቀረበ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በ2015 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ዞን በ50 ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ቦታ ላይ የተጠናው የካኦሊን ማዕድን የዳሰሳ ጥናት በ 7 ነጥብ 497 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ 928,142,150 ሜትር ኩብ የካኦሊን ማዕድን መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የሚጠናና 4 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት መስፈርት ያለው በደቡብ ጎንደር ዞን የብረት ማዕድን ፍለጋ የመስክ ጥናት የተካሄደ ሲሆን፤ በዚህም ብረት፣ ግራናይት፣ አሜቲስት፣ ጃስፐር እና አጌት የተሰኙ ማዕድናት ተገኝተዋል፡፡ የጥናቱን ውጤትም ለክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ቀርቧል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲም እንዲሁ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚጠናና 5 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ የብረት ማዕድን ጥራት፣ ስርጭትና ክምችት የተመለከተ የመስክ ጥናት አጠናቅቋል፡፡ ጥናቱም ጥልቀቱ እስከ 25 ሜትር የሚሆን እና በአማካይ 50 በመቶ የብረት መጠን ያለው ‹ሄማታይት› የተሰኘ የብረት አዘል ማዕድን ማግኘት ችሏል፡፡ ይህንንም የጥናት ውጤት ቢሮው ተረክቧል፡፡
ይሁን እንጂ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም በ110 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ (ወርቅ፣12 ካሬ ኪሎ ሜትር፤ ኮፐር 30 ካሬ ኪሎ ሜትር፣ ብረት 95 ካሬ ኪሎ ሜትር ) ለማጥናት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በጀት ባለመፈቀዱ ሥራውን መስራት ያልተቻለ መሆኑን ተመላክቷል፡፡
የኢነርጂ ማዕድናት
በ2015 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ተጠንቶ የነበረው በአምስት ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ በተካሄደ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ጥናት የካሎሪ መጠኑ 3369 ነጥብ 5 የሆነ እና 3 ሜትር ውፍረት ያለው እንዲሁም ከ lignite A የሚመደብ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ተገኝቷል፤
ሰሜን ሽዋ ዞን የድንጋይ ከሰል ማዕድን ፍለጋና ክምችት ላይ ጥናት ተደርጎ የነበረ ሲሆን፤ በጥናቱም የድንጋይ ከሰል ማዕድን ባለመገኘቱ ሌሎች ማዕድናት ላይ ጥናት እንዲደረግ ተደርጓል። ጥናቱ በኖራ ድንጋይ እና በሲሊካ ሳንድ ማዕድናት ላይ እንዲጠና የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም የተገኘው ማዕድን ክምችትም 35 ሚሊዮን ቶን ኖራ ድንጋይ እና 21 ሚሊዮን ቶን ሲሊካ ሳንድ እንዳለ ታውቋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች
ክልሉ በማዕድናት ልማት ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ማዕድን ነክ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ማዕድናት (ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ብረት፣ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ጂብሰም፣ ግራናይት፣ ማርብል) ላይ እሴት የሚጨምሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፈቃድ ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡ በ2015 በጀት ዓመት 49 የነበረውን የአምራች ኢንዱስትሪዎች ፈቃድ በ2016 በጀት ዓመት ወደ በ75 ለማድረስ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
የማዕድን ነክ ፋብሪካዎች እንዲቋቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ለ13 አምራቾች፣ በዘጠኝ ወራት ደግሞ ለ10 የከፍተኛ ደረጃ የማዕድናት ምርመራ ሥራ ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ ለሰባት ማዕድናት ማለትም (ለሁለት ወርቅ፣ ሁለት ኦፓል፣ አንድ ድንጋይ ከሰል፣ ሁለት ኖራ) ለአምራቾች የምርመራ ሥራ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ይህም የዘጠኝ ወሩ አፈጻጸም 70 በመቶ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የማዕድን ነክ ፋብሪካዎችን እንዲቋቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ለ12 አምራቾች፣ በዘጠኝ ወራት ደግሞ ለዘጠኝ አምራቾች ማዕድናት የማምረት ሥራ ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ (አምስት ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግብዓት የሚውሉ፣ ሁለት የድንጋይ ከሰል፣ አንድ ለጅብሰም ቦርድ ፋብሪካ ግብዓት፣ አንድ ለማርብልና ግራናይት ፋብሪካዎች ግብዓት) አምራቶች የማምረት ፈቃድ አግኝተዋል፡፡ የዘጠኝ ወር አፈጻጸም 75 በመቶ ደርሷል።
በአጠቃላይ በተያዘው በጀት ዓመት የማዕድን ነክ ፋብሪካዎችን እንዲቋቋሙ 26 የምርመራ እና የምርት ፈቃዶችን ለመስጠት ታቅዶ፤ እስከዘጠነኛው ወር ድረስ እስከ 16 አምራቾች ማከናወን የምርመራ እና የምርት ፈቃዶች ተሰጥቷቸዋል፡፡ አፈጻፀሙም 61 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን፤ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ12 ነጥብ 93 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የባለፈው ዓመት አፈጻጸም 48 ነጥብ 57 በመቶ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በዘጠኝ ወራት 18 እሴት ጨማሪ አነስተኛ ደረጃ የኢንዱስትሪዎች የማዕድናት የምርመራ እና የምርት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ ለ26 አነስተኛ ደረጃ የኢንዱስትሪዎች የምርመራ የምርት ፈቃድ መስጠት ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙ ከመቶ በላይ ሲሆን የአመቱ እቅድ 24 እንደነበር ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለ738 በማዕድን ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በአነስተኛ ኮንስትራክሽንና በባህላዊ የማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡
የሥራ እድል
በማዕድን ዘርፉ ለዜጎች ሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት በማዕድን ዘርፉ በሚሰማሩ ባለሀብቶች፣ ኩባንያዎች እና ኢንተርፕራይዞች አማካኝነት ለ33 ሺ 857 ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን ለ16 ሺ337 ሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
በዘርፉ የተገኘው ገቢ
በክልሉ በሚሰጡ ፈቃዶች በበጀት ዓመቱ እስከ ሶስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ በሚሰጡ የማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃዶች የሚመዘገብ የካፒታል መጠን 5 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ 3,327,230,206 ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል። ይህም አፈጻፀም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የባለፈው ዓመት ዓመታዊ በ 12 ነጥብ 93 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡
ማዕድናት ለውጭ ገበያ ከመላክ አኳያ በዘጠኝ ወራት 13 ሺ 617 ኪሎ ግራም ማዕድናትን ወደ ውጭ በመላክ 5,400,000 የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማስገኘት ታቅዶ፤ 19 ሺ187 ኪሎ ግራም ማዕድናት ወደ ውጭ በመላክ 1,217,937 ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡ ገቢው የባለፈው በጀት ዓመት ምርት አንጻር በምርት ቅናሽ አላሳየም፤ ሆኖም ግን ከገቢ አኳያ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር በ35 ነጥብ 16 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ነው የተገለጸው፡፡
በበጀት ዓመቱ 41,578,235 ከሮያሊቲ፤ ከመሬት ኪራይ፣ እና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎት ክፍያዎች ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 30,195,821 (ከሮያሊቲ፣ ከቁርጥ ዋጋ፣ ከመሬት ኪራይና ከሌሎች ተዛማጅ ክፍያዎች ) መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በሚመረቱ የማዕድን ውጤቶች የመተካት አቅምን እስከ ዘጠነኛ ወር ድረስ 562,500 ቶን ምርት በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት 2070347 ዶላር ለማዳን ታቅዶ፤ 114,004 ቶን ምርት በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት 19,392,614 ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ከክልሉ የማዕድን ሀብት ቢሮ በተገኘው መረጃ ተመላክቷል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም