የኢራን መንግሥትን የተቃወመው ሙዚቀኛ ሞት እንደተፈረደበት ጠበቃው ተናገረ

መንግሥትን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ የታሰረው ኢራናዊ ራፐር በሞት እንዲቀጣ በፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉን ጠበቃው ገለጸ።

ቱማጂ ሳሊህ የተባለው ሙዚቀኛ ከሁለት ዓመታት በፊት በኢራን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በመደገፍ የራፕ ሙዚቃ አውጥቶ ነበር።

በወቅቱ በመላው ሀገሪቱ ማሻ አሚኒ የተባለች ሴት ሂጃብ በአግባቡ አልለበሽም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ አገሪቷን ያናወጠ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።

ሙዚቀኛውም ይህንን ድርጊት የሚኮንን የራፕ ዘፈን አውጥቶ ነበር። ከሙዚቀኛው ጠበቆች አንዱ የሆነው አሚር ሬሲያን ራፐሩ የተላለፈበትን ብይን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል። በዚህ ጉዳይ ከኢራን መንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።

ሙዚቀኛው ሳሊህ ከሁለት ዓመት በፊት ጥቅምት ወር በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት የሚደረገውን ተቃውሞ በመደገፍ ንግግር ሲያደርግ ተይዞ በርካታ ክሶች ተመስርተውበታል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት ስድስት ዓመት ከ3 ወር እንዲታሰር ተወስኖ ነበር።

ሆኖም በዚህ ዓመት ጥር ላይ የኢራን አብዮታዊ ፍርድ ቤት በሙዚቀኛው በተመሠረቱት ክሶች ላይ አዲስ በመጨመር ለፍርድ አቁሞታል ሲል ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሻራቅ ለተባለ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኛ ትናንት ረቡዕ አስተያየቱን የሰጠው ጠበቃው ሬሲያን አብዮታዊ ፍርድ ቤቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ወደ ጎን ማለቱን ተናግሯል። ይህንን “አስከፊ ቅጣት” ከማስተላለፋቸው በፊት አዲስ ክስ እንደተመሠረተበትም ጠቁሟል።

ሙዚቀኛው በትጥቅ በታገዘ አመፅ እና መንግሥት ላይ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ከቀረቡበት ክሶች አንዱ እንደሆነም ተናግሯል። ሙዚቀኛው ይግባኝ የመጠየቂያ 20 ቀናት ተሰጥቶታል።

ሙዚቀኛው ሳሊህ በቅርቡ ከተቀሰቀው ተቃውሞ ቀደም ብሎም መንግሥትን በአደባባይ በመተችት ይታወቃል። በዚህም ሳቢያ በኢራን መንግሥት የተለያዩ ሙዚቃ ድግሶች ላይ እንዳይሳተፍ ታግዷል።

በሙዚቃ ሥራዎቹም መንግሥትን በሙስናና ሠላማዊ እንቅስቃሴዎችን በመገደብ አጥብቆ ተችቷል። በሐምሌ ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 6 ዓመት ከተፈረደበት በኋላ በዋስ ተለቆ ነበር።

ሆኖም መንግሥት ላይ ያለበቂ ማስረጃ ሐሰተኛ ውንጀላዎችን በማቅረብ በሚል በተለቀቀ በቀናት ውስጥ ታስሯል። ይህ የሆነው በእስር ላይ እያለ ስቃይ እና እንግልት ደርሶብኛል የሚል ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከጫነ በኋላ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You