የንግዱ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረግ ዘርፈ ብዙ ፋይዳና ስጋት

በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የንግድ ዘርፎች ከውጭ ኢንቨስትመንት ተከልለው እንዲቆዩ የሚያደርግ አሠራር ሲተገበር ቆይቷል:: ይህም የተደረገው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ውድድር ጫና እንዲጠበቁ በማድረግ ሀብት እንዲያፈሩ ዕድል ለመስጠት፣ ከዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲቀስሙ እንዲሁም በውስጥ አቅም ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት ታልሞ ነው::

ይሁንና አሠራሩ ዓላማውን ማሳካት እንዳልቻለ ተጠቁሟል:: የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የተደረጉት ዘርፎች ዝግ በመደረጋቸው የሚፈለገው ዓላማ ተሳክቷል ማለት አይቻልም::

ይልቁንም ዘርፎቹ ለውጭ ውድድር ያልተጋለጡ በመሆናቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በሚፈለገው መጠን እና ጥራት እሴት ወደሚጨመሩ አምራች ኢንቨስትመንቶች የተሸጋገሩበት ሁኔታ በጣም ውስን መሆኑ ታይቷል:: ከለላ በተሰጣቸው ዘርፎችም ሰፊ የአገልግሎት ተደራሽነት፣ የጥራት እና የብቃት ችግሮች አጋጥመዋል:: ለሕገወጥ ድርጊት በሰፊው መጋለጣቸውም አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል::

በቅርቡ የሀገርን እና የሕዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩ የንግድ ኢንቨስትመንት መስኮችን ለውጭ ባለሀብቶች መከፈት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል:: የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በኢንቨስትመንት ደንብ 474/2012 ላይ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩት እነዚህ የወጪ (Export trade)፣ የገቢ(import trade)፣ የጅምላ(wholesale trade)ና የችርቻሮ((retail trade) የንግድ ሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል::

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርአያስላሴ በመግለጫው ላይ ባለፉት ዓመታት የግል ዘርፉን ሚና በማሻሻል ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢ ሁኔታን ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ለውጦች መደረጋቸውን አስታውሰዋል:: ከእነዚህ ዋና ዋና ተብለው ከሚጠቀሱት ለውጦች መካከል አንደኛው በኢንቨስትመንት ሕጉ ላይ የተደረገው ለውጥ መሆኑን አመልክተዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከ2012ዓ.ም በፊት ብዙ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው ቆይተዋል:: በ2012ዓ.ም የወጣው ኢንቨስትመንት አዋጅ ደግሞ ብዙ አዳዲስ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ አድርጓል:: በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት የፕራይቬታይዜሽንና ሌብራይዜሽን እርምጃዎች ተወስደዋል:: ይህ የሆነበት ምክንያት ቀደም ሲል ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ወይም ደግሞ ለመንግሥት ብቻ ተከልለው የቆዩትን ዘርፎች በመክፈት የተሻለ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ነው::

ተወዳዳሪነት ለሕዝቡም ሆነ ለሸማቾች የተሻለ ውጤት ያስገኛል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ አጠቃላይ የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢ ሕጉን ለማሻሻል ብዙ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል:: ይህም ማሻሻያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚው የተያዙትን እቅዶች ለማሳካት መንግሥት ከሚወስዳቸው ርምጃዎች መካከል አንዱና ወሳኙ መሆኑን አስታውቀዋል::

የኢንቨስትመንት አዋጁን ቁጥር 1180/ 2012 ተከትሎ በወጣው የኢንቨስትመንት ደንብ 474/2012 ላይ ለውጭ ባለሀብቶች የተከፈቱ እና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተከለሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ስለሚከናወኑ ዘርፎች መቀመጡንም አመላክተዋል::

የኢንቨስትመንት ደንብ 474/2012 ለዚህ ፖሊሲ ማሻሻያ መነሻ የሆኑት የወጪ፣ የገቢ፣ በጅምላና የችርቻሮ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰጠውን ከለላ አስመልክቶ ኮሚሽነሯ ገልጸዋል:: በችርቻሮ ንግድ በአጠቃላይ የራስ ምርትን ከመሸጥና ከኤሌክትሮኒክስ ችርቻሮ ንግድ በስተቀር የተቀረው በሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች የተፈቀደ አልነበረም ወይም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተከልሏል፤ በጅምላ ንግድ ደግሞ ነዳጅና ተዛማጅ ምርቶችን ማቅረብ፣ ሀገር ውስጥ የተመረተ የራስ ምርትን በጅምላ መሸጥና በኤሌክትሮኒክ የሚካሄድ የጅምላ ንግድ ከሚለው በስተቀር ሌላው በሙሉ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተከለለ ሆኖ ቆይቷል ሲሉ ያብራራሉ::

በገቢ ንግድ (ኢምፖርት)እንዲሁ ከቡታጋዝና ከቢቱመን ንግድ በስተቀር ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የተደረገ ዘርፍ አልነበረም ሲሉ አመልክተው፣ በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ዘርፍም ጥሬ ቡና ፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት ፣ ጥራጥሬ ፣ ቆዳና ሌጦ፣ የደን ውጤቶች፣ ዶሮና የጋማ ከብቶችን ከገበያ በመግዛት መሸጥ የሚሉት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩ ዘርፎች ነበሩ ብለዋል::

እንደ ኮሚሽነሯ ማብራሪያ፤ በቀደመው አሠራር እነዚህን ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች መዝጋት ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከለላ በማድረግ የተሻለ ሀብት በማፍራት ካፒታላቸውን ለማሳደግ እንዲችሉ ለማድረግ ነበር:: ዓለም አቀፍ ገበያውን እንዲላመዱት ለማድረግ እድል የተሰጠበት ሲሆን፣ በሂደት የካፒታል እድገታቸውን ተከትሎ አምራች ወደሆኑ እሴት ወደሚጨምሩ ወደ ማምረቻ ዘርፎች መሸጋገር እንዲችሉ ለማድረግ ነው::

ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የታየውን አፈጻጸም ስንመለከት በፖሊሲው ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከለላ መደረጉ ውስን ውጤቶችን ብቻ ማስገኘቱን ነው ኮሚሽነሯ ያመለከቱት:: የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከለላውን ተጠቅመው ተጨማሪ ካፒታል በማግኘት ተጨማሪ እሴት ወዳለው ማምረት ሥራ ይሸጋገራሉ ተብሎ የተቀመጠውን የፖሊሲ ግብ ስንመለከት በእነዚህ የንግድ ዘርፎች የሚገኙ ብዙ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አምራች ወደ ሆነው ዘርፍ ሲሸጋገሩ አልተስተዋለም ብለዋል::

ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ዘርፎች ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው መቆየታቸው ውድድር መገደቡንም ጠቅሰው፣ ለሕዝቡ ወይም ለሸማቹ በጥራት እና በዋጋ ተመጣጣኝ እቃዎችን ለማቅረብ ከፍተኛ ውስንነቶች እንደነበረም አመልከተዋል:: በእነዚህ ዘርፎች የተሻለ ውድድር ለመፍጠር እና ለሸማቹም ለሕዝቡም የተሻለ ውጤት ለማስገኘት ያስችል ዘንድ ዘርፎቹ ለውጭ ባለሀብቶች እንዲከፈቱ ተወሰኗል ሲሉ ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል::

እሳቸው አንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲባል ተከልለው የቆዩ በንግድ ዘርፎች ላይ የነበረውን ውጤት በመመልከት ጥናት አካሂዷል:: በጥናቱም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እና ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፤ ጥናቱንም ለአንድ ዓመት ያህል አካሂደዋል::

በጥናቱም እስካሁን ያለው አጠቃላይ መርህ እና የንግድ ሕግ እንዴት መተዳደር አለበት የሚለው ታይቷል፤ እንደ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ንግዳቸውን ለውጭ ባለሀብቶች የከፈቱ የሌሎች ሀገራትን (ቻይና፣ ህንድ ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳና ቤትናም ) ተሞክሮ በመውሰድ በአራቱም ዘርፎች ላይ ጥናት ተደርጓል:: ከባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይት ተካሂዷል:: በዚህ ላይ በመመስረት የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ ዘርፎቹ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲደረጉ ውሳኔ አስተላልፏል::

ኮሚሽነሯ፤ የጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች ምንድናቸው? ለዚህ ውሳኔ ያደረሰንስ ምንድነው? የሚሉትን አጠቃላይ ሁኔታዎች አሉታዊና አወንታዊ ጎናቸው ከታየ በኋላ ጠቀሜታው ጎልቶ መታየቱንም አስታውቀዋል:: የንግድ ዘርፎቹ መክፍቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ የተሻለ አዎንታዊ ውጤት እንደሚያስገኝ አመላክተዋል::

ኮሚሽነሯ የንግዱ ዘርፍ እስካሁን ተከልሎ የቆየ ዘርፍ በመሆኑ አሁን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ሲሉም ጠቅሰው፣ የውጭ ባለሀብቶች በእነዚህ ዘርፎች ላይ ሲገቡ በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል:: የንግድ ሥርዓቱምን ለማዘመን በጣም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፣ አጠቃላይ ውጤቱ ሲታይ አዎንታዊ ሚናው ያመዝናል ብለዋል ::

በሌላ በኩል በዘርፍ ላይ የሚሰማሩት የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ሰፊ ልምድ ያላቸው እንደሚሆኑ ይጠበቃል ሲልም ገልጸው፣ እቃዎች ለሚያቀርቡ አቅራቢዎች የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል:: ከእነዚህ ተቋማት ለሚገዙ ለሸማቶችም ቢሆን በጣም የተሻሉ አቅርቦቶችን የሚያገኙበት እንደሚሆን ነው ያስታወቁት::

እሳቸው እንደገለጹት፤ የንግድ ዘርፎቹ ለውጭ ባለሀብቶች መከፈት ሌሎች ፋይዳዎችም ይኖሩታል:: በሸቀጦች ዋጋ ላይ የመቀነስ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል:: በመንግሥት ገቢም ላይ እንዲሁ አወንታዊ ውጤት ይኖራል::

ዘርፎቹ ሲከፈቱም ለእያንዳንዱ ዘርፍ የተቀመጡ ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉም የጠቆሙት ኮሚሽነሯ፤ የውጭ ባለሀብቱ በዘርፎቹ ላይ ለመሰማራት ሊያሟላ የሚገባው ቅድመ ሁኔታ በዝርዝር መቀመጡንና ተፈጻሚ እንደሚረግም ተናግረዋል::

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታው እንዳለው መኮንን በበኩላቸው፤ ተክልለው የቆዩት ዘርፎች መፈቀዳቸው በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተለየ ጫናን አይፈጥርም ይላሉ:: በተለይ በቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር የተቀመጡበትና በጣም የተገደቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ልምድ ያለውና ቅድመ ሁኔታዎቹን ሊያሟላ የሚችል የውጭ ባለሀብት ብቻ ነው ወደ ዘርፉ ሊገባ የሚችለው ብለዋል:: ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከገበያ እንደማያስወጣ ተናግረው፣ ሀገሪቷ የሚያስፈልጋትን አቅርቦት ለመጨመር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል::

በገቢ ንግድ ከማዳበሪያና ነዳጅ ንግድ በስተቀር የውጭ ባለሀብቶች በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ የንግድ ዘርፎቹ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያስገኛል ሲሉ አስገንዘበዋል።

የመንግሥት ዋና ፍላጎት እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች በአራቱም ዘርፎች ተሰማርተው ገበያውን እንዲለምዱ እና በሂደት ደግሞ ገቢ የሚደረጉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት እንዲችሉ እድል እንደሚፈጥር ያመላክታሉ:: እነዚህን ምርቶች በሀገር ውስጥ ሲያመርቱም የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ፣ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት እንዲያመርቱ ይደረጋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል::

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉትም፤ መንግሥት ዝግ ሆነው የቆዩትን ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች መፈቀዱ ብዙ ጠቀሜታዎች ሊያስገኝ ይችላል:: በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ባለሀብቶች የዳበረ ልምድ፣ አቅምና እውቀት እና ቴክኖሎጂ ያላቸው እንደሚሆኑ ይጠበቃል:: ይህም የንግድ አሠራሩ የተቀላጠፈና የተሻለ አሠራር እንዲከተል ያስችላል:: የተሻለ የአገልግሎት ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል:: ባለሀብቶቹ ይዘውት እንደሚመጡ የሚጠበቀው እውቀትና ቴክኖሎጂም ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል:: የሥራ እድል ለመፍጠር ያስችላል::

በእነዚህ ዘርፎች ላይ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ማድረግ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አንጻር ለኢኮኖሚ አወንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ በጥንቃቄ ከተሠራ ደግሞ ሕዝቡ ወይም ሸማቹ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ይላሉ::

ዶክተር ሞላ የንግድ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችልም አመልክተዋል:: የውጭ ባለሀብቶች ያፈሩትን ሀብት ወደ ሀገራቸው ሲልኩ ካፒታል ወደ ውጭ እንዲወጣ በር ይከፍታል ሲሉ ይጠቁማሉ:: ለዚህም መንግሥት ጠንከር ያለ ሕግ ሊኖረው ይገባል ይላሉ:: ምን ያህል መቶኛ ካፒታል መውጣት እንደሚቻል የሚያሳይ ግልጽ ሕግ ማስቀመጥ እንዳለበትም ያመለክታሉ:: ይህ ካልሆነ ግን ያፈሩትን ሀብት በሙሉ ወደ ሀገራቸው ሊወስዱ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ፤ ይህ ሁኔታ በሀገሪቱ የገንዘብ እጥረት እንዲያጋጥም እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮችም ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አመልክተዋል::

በሌላ በኩል ሀገር በቀል የሆኑ በማደግ ላይ ያሉ ድርጅቶች እንዲዳከሙ ወይም ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉ ዶክተር ሞላ ያስገነዝባሉ:: እነዚህ ሀገር በቀል ድርጅቶች የዳበረ ልምድ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ ይዘው ከሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች ጋር መወዳደር ስለማይችሉ ከስራ ውጪ የመሆን እድላቸውም ሰፊ ይሆናል ሲሉም ይናገራሉ::

ይህ ሁኔታ ለውጭ ባለሀብቶቹ ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር ሰፊ እድል እንደሚፈጥርላቸውና ሀገሪቱንም ትልቅ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ያመለክታሉ:: ለዚህም የተለያዩ ሀገራትን ልምድ መመልከት እንደሚቻል የሚጠቁሙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ታይላንድና ኢንዶኒዥያ ከዚህ በተያያዘ የገጠማቸውን ችግር በአብነት ያነሳሉ::

በእነዚህ ሀገራት የውጭ ባለሀብቶች ከገቡ በኋላ የፋይናንስ ዘርፉን እና የገቢና የውጭ ንግዱን በቀጥታ በመቆጣጠር ሲሠሩ ቆይተው ከሀገራቱ መንግሥታት ጋር በተከሰተው አለመግባባት ሀገሮቹን ጥለው ሲወጡ የውጭ ባለሀብቶቹን በር ከፍተው ያስተናገዱት ሀገሮች ወደ ቀድሞ ማንነታቸው ስለመመለሳቸው ታሪካቸው እንደሚያስረዳ አብራርተዋል::

እነዚህ ባለሀብቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከተቆጣጠሩ በኋላ በረጅም ጊዜ ሂደት የመንግሥት አስተዳደር እነሱን ያማከለ እንዲሆን እስከ መፈለግ የሚደርሱበት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል አመልክተው፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አስታውቀዋል፤ እነዚህን ባለሀብቶች አስገድዶ ማስቀረት እንደማይቻልም ጠቅሰዋል:: ለዚህም መንግሥት የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ሀገር በቀል ድርጅቶች በማይዳከሙበት ወይም ከሥራ ውጭ ሊሆኑ በማይችሉበት ሁኔታ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ጎን ለጎን ለመጓዝ የሚያስችላቸው ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አመልክተዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የውጭ ባለሀብቶች ሲገቡ ከሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር የውድድር ስሜት መፍጠር ብቻ ሳይሆን የትብብር ስሜት እንዲኖራቸው ማድረግ ላይም መሠራት ይኖርበታል፤ በሁለቱም በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያደርጉ ሕጎችና ስትራቴጂዎች እንዲኖሩ ማድረግም ይገባል::

የቁጥጥር ሥርዓቱን ጠንካራ ማድረግ የሚያስችሉ ሕጎች ፣ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ማውጣት ላይ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል:: ይህ ውሳኔ በሌሎች ሀገራት ላይ ተግባራዊ ተደርጎ ያስከተለው አይነት ክስተት እንዳይታይ አስቀድሞ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You