ከሌማት ተርፎ ማቀነባበሪያ እየጠየቀ ያለው የወተት ምርት

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሠረቱ የወተት መንደሮች መካከል አንዱ በሆነው በእነ አቶ ሣሕሌ በርታ መንደር ተገኝተናል፡፡ አቶ ሣሕሌ በርታ በእንድብር ከተማ ልዩ ስሙ የሰሚ የተባለ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የባንክ ሠራተኛ ነበሩ፤ ጡረታ ከወጡ በኋላ የጡረታ ገንዘብ ብቻ መጠበቅ አልተመቻቸውም፤ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ያስባሉ፡፡

ለእሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው የሚሆን ሥራ ለመሥራትም ከልጆቻው ጋር ይመክራሉ፤ ማኅበር ያቋቁማሉ፡፡ በ2013 ዓ.ም የነበረቻቸውን አንዲት የተሻሻለ ዝርያ ያላት ላም መነሻ በማድረግ የወተት ሃብት ሥራ ለመጀመር ለከተማው አስተዳደር አመልክተው መሬት አገኙ፤ ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ደግሞ 150 ሺ በብር ተበደሩ፤ በዚህም ጊደሮች ገዝው የወተት ሃብት ልማቱን ማስፋፋቱን ተያያዙት፡፡

አቶ ሣሕሌ አሁን ከነጥጆቹ 12 የወተት ላሞች አሏቸው፤ ከእነዚህ መካከልም ስድስቱ ናቸው። ከእያንዳንዷ ላም በቀን ከ20 ሊትር በላይ ወተት በማለብና በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ሣህሌ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም ቤተሰቤን ለማስተዳደር የገቢ አቅሜ ይፈትነኝ ነበር፤ አሁን ግን በወተት ምርቱ በማገኘው ገቢ በአስተማማኝ ሁኔታ ቤተሰቤን ከማስተዳደር አልፌ ኢኮኖሚዬንም እያሳደኩኝ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ፤ በቀጣይም የተሻሻሉ ላሞቻቸውን ቁጥር ከፍ በማድረግ የወተት ልማታቸውን የማስፋፋት እቅድ አላቸው፡፡

አቶ ሣሕሌ ለዚህ ለመድረሳቸው የወረዳው አስተዳደር በተለይም የግብርና ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ እንደነበረም ጠቅሰው፣ ‹‹በተለይ ሕክምና የሚሰጡ የግብርና ባለሙያዎች ሌት ተቀን ሳይሉ በፈለግናቸው ጊዜ ሁሉ እየተገኙ ድጋፍ ያደርጉልናል፤ ለዚህም ነው ምርታማነትን በተሳካ ሁኔታ ማምጣት የቻልነው›› ይላሉ፡፡

አቶ ሣሕሌና ቤተሰቦቻቸው አሁን በየቀኑ የሚያልቡትን ወተት ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለካፍቴሪ ያዎች በማከፋፈል ይሸጣሉ፡፡ ሰባት የሚሆኑት ላሞች እርጉዝ በመሆናቸው የሚቀጥለው ዓመት የላሞቻቸው ቁጥር በእጥፍ ያድጋል፤ የወተት አቅርቦታቸውም በዚያው ልክ ከፍ ይላል፡፡ ይህ ሁኔታ አቶ ሣሕሌን ቢያስደስታቸውም፣ የላሞቻቸው ብዛት እየጨመረ እንዲሁም የሚመረተው ወተት መጠን ከፍ እያደረጉ በመጡ ቁጥር ወተቱን የሚረከባቸው እንዳያጡ ሰግተዋል፡፡

‹‹የወተት ሃብት ልማቱን የማስፋፋት ፍላጎት ቢኖረንም፤ ብዙ ባመረትን ቁጥር የሚወስድልን እንዳናጣ እንፈራለን፤ አሁንም ቢሆን የወተት መንደሩ እየተስፋፋ በመምጣቱ የወተት አቅርቦቱና ፍላጎቱ የሚመጣጠን አልሆነም›› ይላሉ፡፡ በአካባቢያቸው የወተትና የወተት ተዋፅዖ ማቀነባበሪያ ቢከፈት ወተታቸውን የሚረከባቸው እንደሚያገኙ ጠቅሰው፣ ይህ ሲሆን ከስጋት ነፃ እንሆናለን፤ ተጠቃሚነታችንም ያድጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ‹‹የእኛ ተጠቃሚነት ባደገ ቁጥር ከተማችንንም እናሳድጋለን›› ሲሉ ይገልፃሉ።

በአካባቢው እንደመብራት፣ ውሃና መንገድ መሠረተ ልማት ያሉት አቅርቦት ችግር መኖሩም ሌላው ስጋታቸው ሆኗል፡፡ ችግሩ እንደእሳቸው በወተት ሃብትም ሆነ በሌላ የግብርና ኢንቨስትመንት ለመሠማራት የሚፈልጉ ግለሰቦችን እንደማይጋብዝም ነው ያመለከቱት፡፡ ‹‹በተለይ የመብራት ጉዳይ አንገብጋቢ ነው፤ በእኛ መንደር ብቻ ሰባት የወተት ማኅበራት አሉ፤ የዶሮና የንብ መንደሮችም እየተስፋፉ ነው ያሉት፤ ይሁንና በቂ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት እኛም ልማታችንን ለማስፋፋት፤ አዳዲሶቹም እኛን አይተው እንዳይገቡ እንቅፋት እየሆነ ነው፤ ስለሆነም የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በሌላ በኩል የተሻሻሉ ዝርያዎች አባለዘር እና ለማባዛት ሥራው ወሳኝ ግብዓት የሆነው የናይትሮጂን አቅርቦት በዞኑ ከፍተኛ እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፣ አርሶአደሩ በሚፈልገው ጊዜ የማዳቀል ሥራ ለመሥራት መቸገሩን አቶ ሣሕሌ አመልክተዋል፡፡ ይህም ከወረዳው አቅም በላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሌሎች አካላት እገዛ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሙደሲር እንደሚሉት፤ የሌማት ቱሩፋት መርሐ-ግብር በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም በይፋ እንደሃገር ከተጀመረ ወዲህ በዞኑም የወተት፣ የዶሮ፣ የማርና ሥጋ መንደሮችን የማቋቋም ሥራ በስፋት ተከናውኗል፡፡ ከዚህም ባሻገር የዓሣ እርባታ በተለየ መንገድ በአካባቢው የማስለመድ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በተለይም የወተት መንደር ልማት ሥራው በዞኑ ባሉ 10 ወረዳዎች፣ አምስት ከተማ አስተዳደሮችና 185 ቀበሌዎች ላይ 525 የወተት መንደር ለመመሥረት ታቅዶ ነው እየተሠራ ያለው፡፡

‹‹ለዚህም 60 የሚሆኑ ማኅበራት ተደራጅተው በወተትም በዶሮ እርባታም፤ በንብ ማነብና የሥጋ ከብት ልማት ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ነው›› የሚሉት ኃላፊው፤ የወተት ሃብት ልማት ሥራ የሌማት ትሩፋቱ ከመተግበሩ በፊት በሦስት የማዳቀል ዘዴዎች በመሥራት የተሻሻሉ የወተት ላሞችን የማስፋፋት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በዞናችን ያሉ አርሶአደሮች ቢያንስ አንድ የተሻሻለ ዝርያ ሊኖራቸው ይገባል ብለን እየሠራን ነበር›› ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

በዚህም በዞኑ ካሉ የቀንድ ከብቶች ውስጥ 23 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የተሻሻለ ዝርያ እንዳላቸው አቶ መሐመድ ተናግረው፣ ቀሪው 77 በመቶ የሚሆነው የከብት ሃብት ዝርያ ለማሻሻል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በየዓመቱ 10 በመቶ የሚሆነውን ከብት ዝርያ ማሻሻል አለብን ብለን ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው፤ በዚህ ዓመት 22 ሺ የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ አሻሽለናል›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የሌማት ትሩፋት መርሐግብር ዋና ዓላማ በምግብ እህል ራስን መቻል እንደመሆኑ በተለይም የዞኑን አርሶአደሮች የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የተመጣጠነ ምግብ እንዲኖራቸው በማድረግ መቀንጨርን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡

አሁን ባለው መረጃ በወተት ሃብት ወደ 120 ሺ የዞኑ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በዶሮ ልማት ደግሞ 69 ሺ ፤ በሥጋ ሃብት ደግሞ ወደ 80 ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህ ግን ለወጣቶች የተፈጠረውን የሥራ ዕድል እንደማያካትት አንስተው፤ ባለፈው ዓመት በተከናወነው ሥራ የእቅዱን 50 በመቶ ዞኑ ማሳካቱን ይጠቅሳሉ፡፡ መርሐ ግብሩ ለአራት ዓመታት ለመተግበር የታቀደ እንደመሆኑ ልማቱንም ሆነ ተጠቃሚነቱን የማስፋት ሥራ ከዚህም በላይ ይሠራል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ፤ የአርሶአደሩን ገቢ ከማሳደግ አኳያ በመርሐ-ግብሩ አርሶአደሩ በምግብ እህል ራሱን እንዲችል ከማድረግ በዘለለ የገቢ አቅሙን ከፍ የሚያደርጉ ልማቶችን እያከናወነ ነው፡፡ ዛሬ ዶሮ የሚያረባው አርሶ አደር እንቁላል ሸጦ ከብት እየገዛ ነው፤ ሃብቱን እያሰፋና ኑሮውን እየለወጠ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከእርዳታ ጠባቂነት ተላቆ ሌሎችን የሚጠቅም እንዲሆን፤ ሃገሩንም የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር የዞኑም ሆነ የክልሉ መስተዳድር በመቀናጀትና በመናበብ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ናቸው፡፡

እነአቶ ሣሕሌ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በሚመለከት ለቀረባለቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም ‹‹የተነሱ ጥያቄዎች ትክክል ናቸው፤ እኛም ሥራውን በቅርበት እየተከታተልን ስለሆነ እናውቃቸዋለን፤ በተለይም የክልልና የፌደራል መንግሥት መውሰድና መፍታት ያለበት ችግር የአባላዘርና የናይትሮጂን አቅርቦት ችግርን ነው፤ ክልላችን ውስጥ ሆሳዕና ላይ ብቻ አንድ ማዕከል አለ፤ እሱም ከተበላሸ በክልሉ ዞኖች በሙሉ ሥራ ያቆማሉ›› ይላሉ፡፡ በተለይም ላሞች የኮርማ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ ቶሎ የማዳቀል ሥራ ካልተሠራ በትንሹ ለ21 ቀናት ያህል የወተት ምርቱም የሚከስርበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ይህም የወተት አልሚዎቹን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የዞኑ አስተዳደር ለክልሉም ሆነ ለፌደራል መንግሥት የናይትሮጂን ማዕከል ግንባታ እንዲከናወን ጠይቋል፤ ይሁንና እስካሁን ችግሩ አልተፈታም፡፡ በተመሳሳይ በዞኑ የዝርያ ማሻሻያ ማዕከል የነበረ ቢሆንም የማሻሻያው ማሽን በመበላሸቱ ላለፉት ሰባት ዓመታት አገልግሎት አልሰጠም፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው የመንግሥት አካል የናይትሮጂን ማዕከላት በየአካባቢውና ለአርሶ አደሩ በሚቀርቡበት ሁኔታ እንዲገነባ ድጋፍ ማድረግ፤ የዝርያ ማሻሻያ ማሽኑንም ማሽን መጠገን፤ አልያም በአዲስ የመተካት ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡

‹‹አርሶአደሩ ያነሷቸው የመንገድ፤ የውሃና መብራት ጥየቄዎችም ቢሆኑ ትክክለኛ ናቸው፤ እኛም ይህን ጉዳይ እንደ አንድ የልማት አጀንዳ ይዘን እየሠራን ነው›› የሚሉት አቶ መሐመድ፣ በተለይም ኮረብታማና ዳገታማ አካባቢዎችን ለማስተካከልና ለልማትና እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ በዞኑ አቅም የሚቻለውን ሁሉ ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ከመብራት ጋር ተያይዞ የትራንስፎርመር ተከላ ጥያቄውም ዞኑ ተገቢነቱን እንደሚያምን ተናግረው፤ ይህንንም ጉዳይ በተደጋጋሚ በደብዳቤም ሆነ በቃል ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማቅረቡን ያስረዳሉ፡፡ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝም ከክልሉ ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የውሃ መሠረተ ልማት ችግርም እንዲሁ ከተማ አቀፍ መሆኑን አንስተው፣ ይህንንም በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ ከገበያ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ ግን ብዙም የሚያሳስብ አይደለም፤ ከዚህ ቀደም በዚህን ያህል መጠን ይመረት ስላልነበር ተረካቢ አካል ስጋት ይሆናል ተብሎ አልታሰበም›› ሲሉ ገልጸው፣ የመርሐ ግብሩም ዋና ዓላማ የእያንዳንዱን ቤተሰብ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና የተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፤ የእኛም ትኩረታችን እዚህ ላይ ነው›› ብለዋል፡፡ በቀጣይ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር የማስተሳሰር ሥራ በመሥራት ስጋቱን እንዲቀረፍ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀው፣ በአካባቢው ቢያንስ አንድ ማቀነባበሪያ እንዲገነባ ለባለሃብቶች ጥሪ እያቀረብን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአርሶአደሮቹ የተነሱትን ጥያቄዎች አስመልክተው ሲገልጹ፤ ‹‹የወተት ምርት ጉዳይ በሁለት መንገድ መመለስ መቻል አለበት የሚል እምነት አለን›› ብለዋል፡፡ እሳቸው እንዳብራሩት፤ አንደኛው እንደተባለው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በየአካባቢው ማስፋፋት፤ በሁለተኛ ደረጃ የስርጭቱን ማስፋፊያ መንገድ መቀየስ ይሻል፡፡

የሚያመርተው አካል መሸጥ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል ሲሉም ጠቅሰው፣ ምክንያቱም የግብርና ልማታችን አንዱ አጀንዳ ኅብረተሰባችን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ ነው›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹አንዳንድ ቦታ ላይ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ሃብታም መሆን ጀምረዋል፤ የተለያዩ ምርቶችን ያመርታሉ፤ ግን ምርቱን አይጠቀሙትም፤ የሰው ለውጥ ደግሞ የሚታየው መጀመሪያ እሱና ቤተሰቦቹ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሲችል ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን እንደ ክልል እየተሠራ ያለ ነገር አለ፤ ጥያቄያቸውም ትክክል ነው ብለን ነው የምንወስደው›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩልም አቶ እንዳሻው እንደተናገሩት፤ በመሠረተ ልማት ረገድ የክልሉ በጀት በፈቀደ መጠን የገጠርም ሆነ የከተማ መንገዶች እየተሠሩ ነው፡፡ አንዳንድ የመንገድ ግንባታዎች አምስትና ከዚያ በላይ ዓመታት የፈጁ አሉ፤ አሁን በተቀመጠው አቅጣጫ 95 በመቶ በላይ ያለቁ ጉዳዮች እነሱን ማስጀመር ነው። አንዳንዱ መንገዱ ይያዝና ድልድይ የለውም፡፡ግን መንገድ የሚባለው ድልድዩን ጨምሮ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ጉድለቶች ነበሩ፤ እሱን የማስተካከል ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሆኖም ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር ግን የሚቀረን ብዙ ነገር አለ፤ እሱ ላይ ተረባርቦ መሥራት ይገባል፡፡

‹‹በውሃ ላይ በብዙ ቦታ በደንብ እየተሠራ ነው፤ ከከርሰምድር የማውጣት፣ የማጎልበት፣ የማስጠናት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፤ ሰው አማራጭ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ጥሩ ናቸው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ለምሳሌ የወልቂጤ ከተማ በወር አንዴ ነበር ውሃ የሚያገኘው፤ አሁን ቀኑን አሳጥረነዋል፡፡ በአስር ቀንና ከዚያ በታች ውሃ ያገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ሆቴል ያደረ ሰው ውሃ የማያገኝበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ግን ቢያንስ በባልዲ የሚያገኝበት ሁኔታ አለ። አሁንም አቅም በፈቀደ መጠን የኅብረተሰቡን ጥያቄ እንመልሳለን ብለን እናስባለን›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You