እውነትንና ሀቅን ይዘው መጓዝ ይመርጣሉ። በዚህ ባህሪያቸው ሰዎች እንዲረዷቸውና እንዲያውቋቸው ይፈልጋሉ። ዛሬ ላሉበት ደረጃ የደረሱት ብዙ ነገሮችን በእውነተኛነት አሸንፈው መሆኑን ያምናሉ። ለቤተሰቦቻቸው ልፋትም ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ። ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ ቢከተሉ ያስደስታቸዋል። በተለይም በእርሳቸው የትውልድ አካባቢ ያሉ ሴቶች ብዙ ፈተና አለባቸውና ያንን ተጋፍጠው ለትልቅ ደረጃ ቢበቁ ደስታቸው ወደር እንደሌለው ይናገራሉ። የዛሬዋ ‹‹የህይወት ገጽታ›› እንግዳችን የሴቶች፤ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኦሞድ።
የተወለዱት ከጋምቤላ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። ጎግ ወረዳ ጀንጀር ቀበሌ ትባላለች። በዚህች ቦታ እትብታቸው ተቀበረ እንጂ አላደጉባትም። ኑሮዋቸው ከቤተሰባቸው ጋር ጋምቤላ ሆነ። ስለዚህ ስለ እድገታቸው ስናነሳ ጋምቤላ ላይ ብቻ ከትመን ትዝታቸውን እንቃኛለን።
ለወይዘሮ አለሚቱ ጋምቤላ መምጣት መንስኤ የሆኗቸው እዛ ቦታ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሴት አያታቸው ናቸው። አያታቸው የትዳር አጋራቸው ልጆቻቸው በደንብ ሳያድጉ በማረፋቸውና ብቻቸውን ለማሳደግ በመቸገራቸው ሰርቶ ለመኖር በማሰብ ለአካባቢው እንግዳ ወደ ሆኑበት ከተማ ገቡ። ግን ማንንም አያውቁምና ብዙ ተቸግረዋል። ‹‹ ሳይደግስ አይጣላም›› እንዲሉ ሆነና ከደጋጎች ቤት እግር ጣላቸው።
አቶ አመንቴና ወይዘሮ ረጋቱ የሚባሉ ባልና ሚስቶች ከወለጋ መጥተው ኑሯቸውን በጋምቤላ አድርገዋል። ልጅ ስለሌላቸው የተቸገረ በመርዳትና የሌሎችን ልጆች በማሳደግ ነበር የሚኖሩት። እናም የወይዘሮ አለሚቱም አያት እነዚህ ደጋግ ቤተሰቦች ቤት ዘንድ ተቀላቀሉ። ከተቀበሏቸው በኋላ በሰፊው ግቢያቸው ቤት ሰርተው እንደሰጧቸው ከእናታቸው የሰሙትን ታሪክ በማንሳት አውግተውናል።ወይዘሮ አለሚቱም ከወላጅ እናታቸው ጋር ብዙም ሳይቆዩ ወደ አያታቸው በመምጣት ከእነዚህ ቤተሰቦች ጋር የመቀላቀሉን እድል አገኙ።
በክርስትና ልጅነት የተመሰረተው ዝምድና ሁሉንም ቤተሰብ እንዳደረገውም አጫውተውናል። ይህ ደግሞ የሁለት ብሄረሰቦችን የአኗኗር ባህል ልቅም አድርገው እንዲለምዱና እንዲኖሩት እንዳደረጋቸው ያወሳሉ። በተለይም መተጋገዝንና ለሰዎች በችግር ጊዜ መድረስን ከእነርሱ እንደተማሩም ነው የሚያነሱት። በዚህ ቤት ውስጥ ማደጋቸው ሌላም መልካም ነገር እንዳስተማራቸው ይናገራሉ። በሁለቱም ወገን የሚመጣውን ሰው ባህሪና ማንነት እንዲለምዱ።
የአያት ልጅ ቅምጥል እንደሚባለው ብቻ አይደለም እርሳቸው ያደጉት። ከዚያ ላቅ ባለ ሁኔታ ነው እንክብካቤ ያገኙት። ምክንያቱም እናታቸውን ያሳደጉ ሌሎች ዘመዶችም አሏቸው። ሁለት አያት፤ ብዙ ቤተዘመድ፤ ብዙ ወንድምና እህት ባለበት ቤት እንዲያድጉ እድል አግኝተዋል። እናም በልጅነታቸው ያገኙት ደስታ በምንም የሚለካ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ነፃነት የተሞላበት እንደነበርም ያስታውሳሉ። በተለይም በሁለት ብሔረሰብ መካከል ባለ ልምድ ማንነትን መገንባት የተለየ ስሜት አለው ይላሉ።
የተወለዱበትም ሆነ ያደጉበት አካባቢ በተለያዩ ልማዳዊ ድርጊቶች ይታወቃል። እርሳቸው ግን ለዚህ ልማዳዊ ድርጊት ተጋላጭ አልነበሩም። ይልቁንም በአቅማቸው ልክ መስራትን እየተለማመዱ እንዲያድጉ ነው የሆኑት። እያንዳንዱን ተግባር ማንም ጫና ሳያደርግባቸው ፈቅደው እንዲሰሩም ይደረጋሉ። ግን በግዳጅ አንድ ነገር አድርጊ ከተባሉ ኃይለኛ እንደሆኑም አይረሱትም። በዚያው ልክ ደግሞ በፈቃድ በሚሰሩት ስራ ላይ መለምን አያውቁም። እንዳውም ቀድመው ቤቱ የሚያስፈልገውን በመረዳት ስራ የሚሰሩት እርሳቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
በቤት ውስጥ በየቀኑ ለእያንዳንዳቸው ልጅ የሥራ ክፍፍል ይደረጋል የሚሉት ባለታሪኳ፤ የሴት የወንድ ሥራ ተብሎ ልዩነት አይታወቅም። ሁሉም የተሰጠውን በኃላፊነት በሚገባ ይወጣል። ይህ ደግሞ ሁላችንም እኩል መሆናችንን እያሰብን እንድናድርግ አድርጎናል ብለውናል።
በእነ ወይዘሮ አለሚቱ ቤት ሌላው የተለመደው ነገር በራሳቸው ሰርተው ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ መደረጉ ሲሆን፤ መሬት ታርሶ ይሰጣቸውና የፈለጉትን ይዘራሉ። ከዚያ እስከምርቱ ድረስ ራሳቸው ሁሉንም እንክብካቤ በማድረግ የተሻለ ምርት በማግኘት ገንዘቡን ለፈለጉት ነገር ያውላሉ። ይህ ደግሞ በልጆቹ መካከል የውድድር ስሜት ይፈጥር እንደነበርም አይዘነጉትም። ይህ ሲሆን ግን የከበደው ካለ ማገዝም ግዴታቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ የሆኑት ባለታሪኳ፤ በባህሪያቸው ዝምተኛ የሚባለው አይነት ናቸው። ከሰው ጋር ሳይጋጩ መጫወት ይወዳሉ። ነጋዴና ገበሬ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ በማደጋቸው ደግሞ የንግዱንም ሆነ የግብርናውን ሥራ በሚገባ ማከናወን ያዘወትራሉ። በተለይ በግብርና ሥራ ላይ አብዝተው ቢሰሩ እንደሚወዱና ቤተሰቡንም በዚህ ስራ ቢያግዙ እንደሚመርጡም አጫውተውናል።
በአካባቢው ባህል ዘንድ ገንፎ ዋነኛ ምግብ ሲሆን፤ እንግዳችን ምግቡን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ነገሮችን ሁሉ አከናውነዋል። ለአብነት ወፍጮ ባለመኖሩ የተነሳ በቆሎውን በሙቀጫ ከመውቀጥ ጀምሮ በድንጋይ ወፍጮ እስከማድቀቁ የሚደርስ ስራን ይሰሩ ነበር። ይህ የመስራት ልምዳቸው ታዲያ ዛሬም ልምድ ሆኖ አሁን በጋምቤላ ትንሽ የጓሮ እርሻ ስላላቸው በማረስ ምርቱ የተሻለ እንዲሆን እንደሚያደርጉ ነግረውናል።
የአካባቢያቸው ለምለም መሆን በግብርና ሥራው ልቀው መውጣትን በልጅነታቸው እንዲመኙ አድርጓቸዋል። ህልማቸውም ያ ነበር። የአካባቢው ማህበረሰብ ልጅ የለኝም ብሎ አያውቅም። ምክንያቱም የፈለገውን ልጅ መላክ፤ ማዘዝ ይችላል። በዚያ ላይ የአካባቢው ልጆች ሁሉ የእርሱ ናቸውና የተባሉትን ያደርጋሉ። በተለይ በጋ ሲመጣ ውሃ ለማግኘት ስለሚያስቸግር ልጅ የሌላቸው ሰዎች ውሃ መቅጃቸውን ይዘው ወንዝ በመውረድ ውሃ እየቀዱ ይጠብቃሉ። የአካባቢው ልጅም የራሳቸውን ትተው የእነርሱን ቤታቸው ያደርሳሉ። እኔም ይህንን እያደረኩ ነው ያደኩት ይላሉ።ይህ ደግሞ ታላላቆችን ማክበር፣ ለሰዎች መታዘዝን እንዳስተማራቸው ይናገራሉ።
ዘልማዱ ሲሰበር
በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ሴት ልጅ እድሜዋ ለጋብቻ ከደረሰ አግብታ ጥሎሽ ማምጣት እንዳለባት ይታመናል። ከዚያም በላይ ወንድሟ እንዲያገባ ከተፈለገ ቅድሚያ እርሷ ማግባት ግዴታዋ ነው። አለበለዚያ ግን ወንድሟ ቆሞ ቀር ይሆናል። እርሳቸው ያደጉበት ቤት ግን ከዚህ የተለየ ነው። መማር የበለጠ ለውጤት እንደሚያበቃ ይታሰባል። ከቤት ውስጥ ሥራ ይልቅ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩም ይበረታታል። ስለዚህ የመማር እድሉን አግኝተዋል።
አያታቸው ከማህበረሰቡ ጎጂ ባህል ጋር በእጅጉ የሚቃረኑ በመሆናቸው ልጆቻቸው በዚያ እንዲያልፉ አድርገዋል። ይህ ደግሞ ወይዘሮ አለሚቱን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አውቀው፤ በራስ መተማመንን አዳብረው እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። በትምህርታቸውም ለመጎበዝ ያስቻላቸው ይህ ልምዳቸው እንደነበር ይናገራሉ። በተጨማሪ ደርግ አስገድዶም ቢሆን ሴቶች እንዲማሩ እድል ሰጥቷል፤ የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተሉ አደረጃጀቶችንም በየወረዳው ፈጥሯል። ይህ ደግሞ እርሳቸውንና መሰሎቻቸውን እንዲማሩም እንደረዳቸው ያስረዳሉ።
በማህበረሰብ ውስጥ ባህሉ በጥቂቱም ቢሆን መቀየሩና የተማረችዋ ሴት ብዙ ፈላጊ ስላላት ተማረች የተለየ ጥሎሽ ታስገኛለች መባል መጀመሩ ይበልጥ ትምህርት ወዳዶች እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በጋምቤላ ከተማ ራስጎበና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ተማሪና የደረጃ ተማሪ በመሆናቸው ሁልጊዜ ሽልማቱን እርሳቸው ይወስዳሉ። በተለይም በዚህ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ብዙዎች ያደንቋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጋምቤላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፤ እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትለዋል። ከዚያ ውጤታቸው የመረጡትን የነርስ ትምህርት ለማጥናት ቢያስችላቸውም በመውለዳቸው ምክንያት እንደተጨናገፈ ነገር ግን ሌላኛውን የልጅነት ህልማቸውን የአጠቃላይ ግብርና ትምህርት ለመማር ችለዋል። ትምህርቱን የተከታተሉት ደግሞ በግብርና ኮሌጁ ሲሆን፤ በራሳቸው ከፍለው በሰርተፍኬት ነበር የተመረቁት።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው ወደ ዲፕሎማው ያሸጋገራቸው ሲሆን፤ በሰው ሀብት አስተዳደር የትምህርት መስክ ተምረዋል። ዲግሪያቸውን ደግሞ በማህበረሰብ ልማት የትምህርት መስክ ለአመራር ሴቶች በተሰጠው የትምህርት እድል ያገኙት ሲሆን፤ ከአለም አቀፉ የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የጋምቤላ ግብርና ኮሌጅ ትምህርቱ እንዲሰጣቸው በማድረጉ እርሳቸውም መማር እንደቻሉ አውግተውናል። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርታቸውን አልቀጠሉም። የተለያዩ ስልጠናዎችን ከመውሰድ ውጪ። ሦስት የትምህርት መስኮችንም በመማራቸው በሶስቱም አገራቸውን ለማገልገል እየሰሩ መሆናቸውንም ነግረውናል።
ከጎግ እስከ አዲስ አበባ
በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ጊዜ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ሴቶች ናቸው። ይህ የሆነውም የመማር እድሉን ባለማግኘታቸው ነው። በዚያ ላይ ትችያለሽ የሚላት የለም። ስለዚህም ሁል ጊዜ ጥገኛ ሆና ትኖራለች። በዚህም ሁሌ ለምን የሚል ስሜት ይሰማኝ ነበር። እኔ ምንም ጫና ስላልተደረገብኝ ለዚህ በቅቻለሁ። ሌሎች ሴቶችስ እንደእኔ ለምን እንዲሆኑ አላደርግም የሚለው አዕምሮዬ ውስጥ ስላለ በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩት ሥራ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ። ይሁንና ከዚህም ቅድሚያ የሚሰጡት የልጅነት ህልማቸው በመሆኑ ግብርናውን የመጀመሪያ ሥራቸው አድርገዋል። በግብርና ምርምር ውስጥ በአስተዳደር ዘርፍ የሪከርድና ማህደር ክፍል ኃላፊ ሆነውም ስራን በቅጥር ‹‹ሀ›› ብለው ሰርተዋል።
በዚህ ሥራ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ከሰሩ በኋላ ደግሞ ወደ ግብርና ሥር በሚተዳደረው የኢኮኖሚ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የገጠር ሴቶች ጉዳይ ቡድን ሴቶችን ያደራጅ ነበርና እርሳቸው እንዲያደራጁ ወደ ጎግ ተመድበው ጉዞ መጀመራቸውን የነገሩን እንግዳችን፤ እትብታቸው የተቀበረበትን ቦታ በሚገባ ያወቁት በዚህ ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ። የእናትና አባቶቻቸው ዘመዶች፤ አጎቶቻቸው ነበሩናም ብዙም ሳይቸገሩ መስራት ችለዋል።
ቤተሰቦቻቸውን ያወቁት እነርሱ ጋር ስለሚመጡ እንደነበር የሚያወሱት ወይዘሮ አለሚቱ፤ ከአንድ አጎታቸው ልጅ ጋር መኪና ላይ ተገናኝተው ቤት ወስዳ ቦታውን እንዳለማመደቻቸውም አጫውተውናል። በእርግጥ ወደዚያ ቦታ የተመደቡት ብዙ ሰው ተመድቦ አልሄድም ስላለ ነበር። እርሳቸው ግን ህዝብ ማገልገል ምርጫቸው ስለነበር በደስታ እንደተቀበሉት ያስታውሳሉ።
በጎግ ወረዳ ላይ ሲሰሩ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በደል እጅጉን ያማቸው ነበር። ሴት ልጆች በግዳጅ ይዳራሉ፤ ትምህርት መማር አይፈቀድላቸውም፤ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ሳይወዱ በግድ ይፈጸምባቸዋል። እናም ጥያቄ የሌለው ተግባር ነበር የሚከናወንባቸው። እናም እዚያ ተመድበው መስራታቸው የሚያስደስታቸውም ጉዳቱን መገንዘብ በራሱ ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ብለው በማሰባቸው ነው። ምክንያቱም ቀደም ሲል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በእኛ ላይ ቤተሰቦቻችን እንዳይፈጸም ያደረጉት ጎጂነቱን ስለተረዱ እንጂ የተማሩ ስለሆኑ አይደለም። ፊደል መቁጠር ብቻ በቂ ሊሆን አይችልም። እናም ሀሳቡን ደግፈው አያቶቻችንን የመሰሉ እናቶች ነበሩና ብዙ ነገሮችን ለማሸነፍ እንደቻሉም ያነሳሉ።
እንግዳችን፤ ብዙ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰትባቸው በማድረጌ ለአካባቢው ሴቶች ተስፋ የጫርኩ ያህል ይሰማኛል። በአደጉበት አካባቢ በማህበረሰቡ ዘንድ ሴት ልጅ መማር አይፈቀድላትም። ጥሎሽ ማምጣትም ነው ዋነኛ ስራዋ። ግን ከአካባቢው ሰዎች ጋር መስራት በመቻሌ ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል። ማህበረሰቡ አምኖ ልጆቹን እንዲማሩ ፈቅዷል ይላሉ።
ከዚያ በተጨማሪ ትምህርት ያቋረጡ እንዲቀጥሉ፤ አቅመደካሞች እንዲደገፉና በቀላሉ መስራት የሚችሉትን ሥራ እንዲሰሩ፤ ሁሉ ነገር ተመቻችቶላቸው መንገዱን ያላወቁ ሴቶችም ራሳቸውን የሚያወጡበት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን በማከናወን የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት እንዲጀምሩ ማድረጋቸውንም ይናገራሉ። በተመሳሳይ በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት እያለ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁት እንዲቀጥሉ በማድረግ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻላቸውንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን አውግተውናል።
‹‹በቦታው ብዙ ለመስራት የሚያስችሉ ነገሮች አሉ። ግን መንገድ የሚያሳይ ሰው አልነበረም። ስለዚህም ቤተሰቤን ከተማ ላይ ትቼ እነርሱን ለማገልገል ዓመታትን አሳልፌያለሁ። ስራው ደግሞ የመስክ በመሆኑ መቋረጥ ስለማይችል ነፍሰጡር ሄኜ እስከምወልድበት ጊዜ ድረስ ከማንም ያላነሰ ሥራ ሰርቻለሁ። በዚህም ብዙዎች ወደ ሥራ እንዲገቡና ከችግራቸው እንዲወጡ ላደርግ ችያለሁ›› ይላሉ።
የገጠር ሴቶች ጉዳይ ቡድን አስተባባሪ በመሆን ወደ ጎግ ወረዳ የሄዱት ወይዘሮ አለሚቱ፤ ይህንን ተልኳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀጥታ ወደ ጋምቤላ ነበር የመጡት። ከዚያም ንግድ ኢንዱስትሪ ቱሪዝም ቢሮ ነበርና በዚያ የቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲሰሩ ተደረገ። ከሦስት ዓመታት የስራ ላይ ቆይታ በኋላ ደግሞ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ አንድ ላይ በመደረጉ በቀጣይነት ይህንን ቦታ እንዲመሩ ሆኑ።
ቀጣዩ ሥራቸው የክልሉ ሴቶች ጉዳይ የቢሮ ኃላፊነት ሲሆን፤ ለሦስት ዓመታት ሰርተውበታል። በዚህም በርካታ ተግባራትን ከውነዋል። በተለይም ገጠሩ ላይ ሰርተውበት ለውጥ ያዩበት ጉዳይ ላይ በስፋት ሰርተው ብዙዎችን መለወጥ እንደቻሉ ለራሳቸው ይመሰክራሉ።
በስራቸው ብዙዎች የሚደሰቱባቸው እንግዳችን፤ የክልሉ አፈጉባኤ እስከመሆንም ደርሰዋል። በዚህም ክልሉን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ተግባራትን ፈጽመዋል። ጊዜው አነስተኛ ቢሆንም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ግን በብቃት የተወጡበት እንደነበር ያስታውሳሉ። በስምንት ወር ውስጥም ተመስግነው ይበልጥ መስራት ወደሚችሉበት ቦታ እንደተዛወሩ አጫውተውናል። ይህም ቦታ የክልሉ ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሲሆን፤ ከዚያ በስራቸው ሹመታቸው ከፍ ብሎ ወደ ፌዴራል ሴቶች፤ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር መጡ። በሚኒስትር ዴኤታነትም ተመድበው መስራት ጀመሩ። አሁንም በቦታው ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።
ተግዳሮት በሴትነት
በተለያየ መልኩ ፈተና ያጋጥማል። ግን በፖለቲካው ዘርፍ የሚመጡ ፈተናዎች እጅጉን ከባድ እንደነበሩ አይረሷቸውም። በተለይም ሴት ከመሆን ጋር ተያይዞ የአንዳንድ ሰዎች ምልከታ የተሳሳተ ነበር። በዚህም ከባድ የሚባሉ ችግሮች ገጥመውኝ ያውቃሉ። ለአብነት በአንድ ወቅት ለወንዶቹ የስራ ኃላፊዎች የጸጥታ ኃይል ጥበቃ ተመድቦ እኔ ግን ያለምንም ጥበቃ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች እንድሄድ መደረጌ መቼም አይረሳኝም። በእርግጥ ጠባቂው ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ነው።በመሆኑም በሰላም ተመለስኩ። ነገር ግን በእነርሱ ምልከታ መድሎ ተፈጸመብኝ። ግን ሴት ብልህ በመሆኗ በጥበብ ብዙዎቹን ችግሮች ማለፍ ትችላለችና እኔም ተወጥቼዋለሁ ብለውናል።
በተመሳሳይ የማይረሱት አንድ ችግርም ገጥሟቸው ነበር። በክልሉ ብዙ ጊዜ የእርስ በእርስ ግጭቶች ሲከሰቱ ከተለያየ ብሔረሰብ የተመረጡ ወደ አካባቢው ሄደው ሰዎች እንዲያረጋጉና ጸቡን እንዲያበርዱ ተላኩ። ይህንን ቡድን እንዲመሩ የታዘዙት ደግሞ እንግዳችን ናቸው። የተላኩት ያለምንም ጥበቃ ነበር። አንዱ አመራር ብቻ ነው ይህ አይሆንም ያላቸው። ሌሎቹ ግን በጀት የለም፤ ምን አዘጋጅታችሁ ነው ወዘተ ይላቸው ነበር።
ቡድኑን የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው እንግዳችን ግን ለተጓዦቹ ሀሳብ አቀረቡ። ብዙዎቹም ተስማሙላቸው። እናም እርስ በእርስ ለመጠባበቅ ወስነው ወደ ቦታው ሄዱ። እድል ቀናቸውና ሰላም ወረደ። ግን ሴትነትን ዝቅ አድርጎ የሚያየው አመራር መቼም ከአዕምሯቸው እንደማይጠፋ ይናገራሉ። በፖለቲካ ውስጥ እውነቱን ወደ ጎን በመተው ሌላ ተግባር መከወን ይፈጠራል። ያ ደግሞ ታሪክን ያበላሻል። እናም ከሚፈትኑኝ መካከል ሌላው ይሄ ነው ይላሉ። እውነትን ይዤ ስጓዝ ከማላውቀው ወገን እመደባለሁ፤ ሽፍታ ትደግፋለችም ተብዬ ተፈርጄ አውቃለሁ። እናም ይህም ፈተና በጣም የማልወደውና የሚያመኝ ነበር ይላሉ።
ቤተሰብ
አራት ልጆች አሏቸው። ከዚያ በተጨማሪ በጉዲፈቻ የወሰዷቸው መንታ ወንድ ልጆችም ለቤታቸው ውበት አድርገው እያሳደጓቸው ይገኛሉ። እንደውም በቅርቡ ሶስት ዓመት ከስድስት ወራቸውን እንዳከበሩላቸው ነግረውናል። አራቱ ልጆቻቸው እየተማሩ የሚገኙ ሲሆን፤ ሁሉም በትምህርታቸው ጎበዞች ናቸው። በጉዲፈቻ ያመጧቸው ልጆችም በሚገባ ተምረው የእህቶቻቸው ተከታይ ይሆኑ ዘንድ እንደሚመኙ ይናገራሉ።
ወይዘሮ አለሚቱ በቤታቸው ውስጥ ልጆቻቸውን ብቻ አይደለም የሚያስተምሩት የእህቶቻቸውንና የዘመድ ልጆችንም ያስተምራሉ። ምክንያቱም እርሳቸውን በሥጋ ያልተዛመዳቸው ቤተሰብ ተንከባክቧቸዋል። በዚያ ላይ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደጉት። ስለዚህም በጋራ ያለን መካፈሉ ልምዳቸው ሆኖ እንዲቀጥል ይሻሉና ይህንን እያደረጉ መሆኑን ያነሳሉ።
ኮሮና
ዛሬ የመጣብን ፈተና ያለመተጋገዝ የሚታለፍ አይደለም። ስለዚህም አገራችንን ለማኖር ሰዎች ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማቆየት መቻል አለባቸው። ይህ ሲሆን አገር ወዳድነት ይመጣል። በእርግጥ ሁሉም ሰው አንድ አይነት አስተሳሰብ ሊኖረው ይገባል አይባልም፤ አይቻልምም። ግን ሀሳቡንና ምልከታውን ማቀራረብ ይችላል። በተለይም በአገር ላይ ለመጣ ነገር አንድ ለመሆን መጣር ግዴታ ነው። ‹‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ ነው›› እንደሚባለው ለአገራችን ጌጦች ለመሆን በችግሯ ጊዜ አንድ ሆነን ከገባችበት አዘቅት ማውጣት መቻል ይጠበቅብናል። መተጋገዝ በገንዘብ ብቻ አይደለምና ሀሳባችንን በማዋጣትም አገር ከችግሯ የምትላቀቅበትን መፍትሄ እንለግስ መልዕክታቸው ነው።
ኮሮናን ለማሸነፍ መጀመሪያ ለሰው ህይወትና ደህንነት መጨነቅ ያስፈልጋል። ስለሆነም በጆሮ በተሰማው ብቻ ጥንቃቄ ማድረግ ላይ መረባረብ አለብን። ይህንን በንጹህ ልባችን ማድረግ ከቻልን ደግሞ አምላክ ይረዳናል። እስካሁንም በዚህ ደረጃ ላይ ያለነው በእርሱ ቸርነት መሆኑን አምነን በጎነታችንን እንጨምርም ይላሉ።
ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ከኢኮኖሚ ጀምሮ በተለያዩ ነገሮች ተጎጂ ናቸው። ወቅቱ ደግሞ በተለይ ለእነዚህ አካላት የበለጠ ፈተና የሚሆንበት ነው። ስለሆነም ድጋፍ ይሻሉ። በዚህም ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ከተቋቋመው ግብረሀይል ጋር በመስራት እንደተቋም እገዛ እንዲያገኙ እተደረገ መሆኑንም ያነሳሉ። በሶስት መልኩ ተደራሽነታቸው እንዲሰራበት ለማድረግ መሞከሩንም ጠቅሰዋል። በቤታቸው ያሉ፤ በማቆያ የተቀመጡና ጎዳና ላይ ያሉ በማለት።
ችግሮች የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የሚያስረዱት ወይዘሮ አለሚቱ፤ ተግባሩ ቀደም ብሎ የተጀመረም ቢሆን በኮሮና ምክንያት ሳይቋረጥ የውጪ ጉዳይ፤ የመረጃና ደህንነት ድርጅት፤ ትምህርት ሚኒስቴርን የመሳሰሉ ተቋማት ህጻናትን የራሱ በማድረግ እያስተማረ መሆኑን፤ ከውጪ አገር በኮሮና ምክንያት ተመላሽ እየሆኑ ያሉት ሴቶችና ወጣቶች ላይም እየተሰራ መሆኑን ነግረውናል።
እነዚህ አካላት መጀመሪያ ሲቆዩ በማዕከል ውስጥ ገብተው በመሆኑ ብዙ ችግር አይገጥማቸውም። ሆኖም አገግመው ከወጡ በኋላ አለያም ካልተያዙ በቀጥታ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል። በዚህም ተቋሙ ሙያተኞችን በመመደብ የሚያርፉበት ቦታ ድረስ ያደርሳል፤ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ያደርጋል ብለዋል። ተቋማት ላይ የሚቆዩትንም ቢሆን የስነልቦና ጫና እንዳይፈጠርባቸው ባለሙያ በመመደብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አጫውተውናል።
መልዕክተ ስንብት
አገርን ለማቅናት የሰው ግንባታ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት። እግዚአብሔር ለአገሪቱ ሁሉን ነገር አሟልቶ ሰጥቷታል። ሰውንም ቢሆን አሳምሮ ፈጥሮታል። ግን በተቃራኒው እየተጓዘ ችግሮችን አምጥቷል። እናም ከዚህ ስህተቱ ተመልሶ ለራሱም ሆነ ለአገር መዳን የድርሻውን ማበርከት አለበት የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
የተሰጠ ጸጋ እንክብካቤን ይፈልጋል። ዝም ካሉት ሊጠፋ ይችላል። ስለሆነም ጸጋችን ብዙዎችን የሚታደግ ማድረግ ላይም ልንሰራ ይገባል። ችግር ስለመጣ ይህንን አንወጣውም ብሎ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ይልቁንም የሩቁን ተስፋ አድርጎ ያንን ለማየት መስራት ያስፈልጋል። በተለይ አገራችንን ወደኋላ የጎተታት የብሔር ክፍፍሉ በመሆኑ ይህንን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ከአዕምሯችን አውጥተን አገራችን ለሌሎች ምሳሌ የምትሆንበትን መስራት አለብን ይላሉ።
የሰው ልጅ ሁሉም ውብ ተደርጎ የተፈጠረ ነው። ከዚያ ውጪ አኝዋክ፤ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግሬ ወዘተ እየተባለ አይደለም የተፈጠረው። ይህንንም ወዶ ያመጣው ማንነቱ አይደለም። ስለዚህም ይህንን አስቦ አንድ መሆንን አልሞ መንቀሳቀስ ለዛሬ ከችግር ማምለጫችን እናድርገው ሲሉ ይመክራሉ። አንድ ቤተሰብ ውስጥ ባድግ ኖሮ ቤተሰቤን ብቻ መስዬ ነበር የምወጣው። አሁን ግን በተለያየ ብሄር ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ ለማንኛውም ሰው ቤተሰባዊ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ አድርጓል። በተለይ ጎጠኝነት በእኔ አስተዳደግ ውስጥ ቦታ የለውም። ብሄረተኝነት ጎጠኝነት… እንዳይገቡኝም አድርጌያቸዋለሁ። የኢህአዴግ ግምገማ ላይ እንኳን ግልጽ ከማይሆንልኝ ነገር የመጀመሪያው ይሄ ነበር።
የአደግንበት ማህበረሰብ የጥንቱ አሁንም እንዲያንጸን መፍቀድ አለብን። ብቻውን መብላት የማይወድ፤ አብሮ ማደግ ልምዱ የሆነ ነው። ትልቅ ትንሽ ሳይል የሚያከብር፤ ልካችንን የሚረዳም ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አንዱ በአንዱ ማህበረሰብ ጋር አይገናኝም። አይስማማም። የእኔ ልጆች ግን ከሌላ ማህበረሰብ ጋር ተዋደው እየኖሩ ነው። ጓደኛም የሚያደርጉት ብሔራቸውን ፈልገው አይደለም። ስለዚህም ቤተሰብ ስንሰራ ይህንን እያየን መሆን አለበት ዋናው መልዕክታቸው ነው። ከወይዘሮ አለሚቱ ጋር የነበረንን ቆይታ በዚህ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው