
በርካታ አካል ጉዳተኞች ‹‹የእኔ›› የሚሉት በውስጣቸው የተሰነቀ ልምድና ችሎታ ባለቤት ናቸው:: አብዛኞቹ ግን ይህን ውስጠታቸውን አውጥተው ለመጠቀም የሚያሥችል ምቹ ሁኔታዎችን ማግኘት የሚችሉ አይደሉም:: እነዚህ ወገኖች ይህን ዕድል በማጣታቸው ብቻ ለዓመታት ‹‹የበይ ተመልካች›› እንዲሆኑ የተገደዱባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው::
ይህ አይነቱ ሐቅ ደግሞ በተለይም ባላደጉ ሀገራት በስፋት የሚስተዋል እውነታ ነው:: ኢትዮጵያን በመሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችም ባብዛኛው የመልካም ዕድል ተጠቃሚዎች አይደሉም:: ይህ መሆኑም ድንቅ ችሎታና ዕውቀት ያላቸው በርካቶች ከተደበቀ መክሊታቸው ጋር ኖረው እንዲያልፉ የሚገደዱበት አጋጣሚ ይስተዋላል::
‹‹ፎከስ ኦን አቢሊቲ ›› የአጭር ፊልም ፌስቲቫል ትኩረቱን በአካል ጉዳተኞች ሕይወትና ማንነት ላይ ያደረገ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ነው:: ተቀማጭነቱን አውስትራሊያ ሲዲኒ ላይ ያደረገው ይህ ፌስቲቫል ሀገራችንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን ተሳትፎ ማጎልበት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ይህ የፊልም ፌስቲቫል በተለይ ኢትጵዮጵያን መዳረሻ አድርጎ ከመረጠ ወዲህ በርካታ አካል ጉዳተኞች የሕይወት ልምድና ችሎታቸውን በአጭር የፊልም ቆይታ በማስቃኘት ማንነታቸው ማሳየት ችለዋል::
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2021 አንስቶ ኢትዮጵያን ማሳተፍ የጀመረው የፊልም ፌስቲቫል የተለያየ ችሎታ ይዘው ዕድሉን ላላገኙ በርካታ አካል ጉዳተኞች መልካም አጋጣሚዎችን ፈጥሯል:: የዚህ ፊልም ፌስቲቫል ተደራሽነትም ሌሎች ባለሙያዎች ጭምር ተሳታፊ እንዲሆኑና እውቅናና ሽልማት ጭምር እንዲያገኙ አስችሏል::
‹‹ፎከስ ኦን አቢሊቲ›› የአጭር ፊልም ፌስቲቫል አካል ጉዳተኞች በኑሮና ሕይወታቸው ዕለት በዕለት የሚራመዱበትን ገሀዳዊ እውነታ የሚተውኑበት ነው:: በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉና ያልተገቡ አመለካከቶችን ለመቀየርም ያግዛል:: በሀገራችን ይህ አጋጣሚ ዕውን መሆን ከጀመረ ወዲህ ጥቂት የማይባሉ አካል ጉዳተኞችና የፊልም ባለሙያዎች ጠንካራ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የአመለካከት ለውጦችን ለማምጣት ሞክረዋል:: በ2021 ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት የፊልም ፌስቲቫል አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ተሸላሚ መሆን ችላለች::
አትሌት ትዕግስት አካል ጉዳተኛ ወጣት ነች:: እንዲህ መሆኗ ብቻ ግን ያሰበችውን ከማሳካት አላገዳትም:: እአአ በ 2021 በነበረው የፓራ ኦሎምፒክ የአንድ ሺህ አምስት መቶ ሜትር ውድድር አሸናፊ በመሆኗ በኢትዮጵያ መድረክ በልዩ ፈጠራ ዘርፍ ለክብር ሽልማት በቅታለች::
አትሌቷ ተዘጋጅቶ በነበረው መድረክ ተገኝታም የአጋጣሚውን በጎነት በስኬት ገልጻዋለች:: ‹‹በርካቶች አካል ጉዳተኞች ‹አይችሉም › ከሚለው አመለካከት ርቀው ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ዕድል ነው›› ስትልም ራሷን በምሳሌነት በመጥቀስ አሳይታለች::
በመጀመሪያው ‹‹ፎከስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጵያ›› የአጭር ፊልም ፌስቲቫል ሀገራችን ስትሳተፍ የግዜው ዋንኛ ትኩረት ክህሎት ነውና ክህሎትን በማክበር ዓላማ ላይ ያተኮረ ነበር:: የመጀመሪያው የሽልማት መድረክም በሀገራችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አካል ጉዳተኞችን ያሰበ ነበር:: በግዜው ብርቱው የሚዲያ ሰው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረማርያም ለዚህ ዕድል የመታጨቱን እውነት በምስጋና ብቻ አላለፈውም:: የተበረከተለትን ሽልማት በኢትዮጵያ ለሚገኙና ቁጥራቸው ከሀያ ሚሊዮን በላይ ለሚገመት አካል ጉዳተኛ ወገኖች ‹‹ይሁንልኝ›› ሲል ይሁንታውን ሰጥቷል:: ተስፋዬ በሙሉ የመተማመን ስሜት ‹‹እኔ አካል ጉዳተኛ›› አይደለሁም ሲልም ይናገራል::
ጋዜጠኛ ተስፋዬ በወቅቱ በሰጠው አስተያየት እሱ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ብቻ የአካል ጉዳተኞችን የሚዲያ ዝግጅት ለማቅረብ ሰበብ እንዳልሆነ ይጠቅሳል:: ለዚህ የሚያነሳው ምክንያት ደግሞ የእሱ በቦታው መገኘት ለብዙሀን ጉዳተኞች እንደምልክት የመሆኑን ሐቅ ነው::
በመጀመሪያው የፎከስ ኦን አቢሊቲ የፊልም ፌስቲቫል ተወዳዳሪዎች መሀል Journey በሚል ርዕስ በቀረበው አጭር ፊልም አሰፋ ዘሪሁን በምርጥ ተዋናይ ዘርፍ አሸናፊ መሆን ችሏል:: The Power Of Tinking በሚለው ፊልም፣ ሳዳም አብዱ፣ Possible በሚለው ፊልም ተዋናይ ፍጹም ልሳን፣ ‹‹ሁሴን›› በሚለው ፊልም ደግሞ አቤል ከበደ እንዲሁም ‹‹ሁለተኛ ዕድል›› በሚለው ፊልም የአብሥራ ዘርይሁን ዕጩዎች በመሆን የውድድሩ አካል ነበሩ::
ከሴት ምርጥ ተዋናዮች መካከልም if I were you በሚል ርዕስ ሜሮን እንግዳ፣ ሕሊና በሚለው ፊልም ሰላም ታምራት፣ ሰንሰለት በሚለው ፊልም ፈትለወርቅ ሽፈራው ዕጩዎች ነበሩ:: ከነዚህ ዕጩዎች መካከልም ሰላም ታምራት የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ በመባል አሸናፊነትን አግኝታለች::
በፎከስ ኦን አቢሊቲ አጭር ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ ከቀረቡት ስድስት ዕጩዎች መካከል ጽዮን አይናለም ‹‹ኢንዱራንስ››በሚለው ፊልም አሸናፊ መሆን ችላለች:: በተመሳሳይም በምርጥ ፊልም ኤዲተርነት ለዕጩነት ከበቁት አራት ባለሙያዎች መካከል አቤኔዘር ማቲያስ ‹‹ሁለተኛ ዕድል ››በሚለው ፊልም ተመርጦ አሸናፊነትን ተቀዳጅቷል::
ከአጭር ፊልም ፌስቲቫሉ ባሻገር ትኩረት ሰጪ ሆነው ለሽልማት ከበቁት መሀል ‹‹ቼሻየር ሆም›› ኢትዮጵያ አንዱ ነበር:: ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ የዓመታት ቆይታው ከአካል ጉዳተኞች ሕይወትና ማንነት ጋር የተገናኘ ግዙፍ ተቋም ነው:: ቼሻየር የአካል ድጋፍን ለሚሹ ወገኖች ሁሉ ምላሽ እንደሆነ ከስልሳ ዓመታት በላይ ዘልቋል::
በወቅቱ በነበረው የ‹‹ፎከስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጵያ›› የአጭር ፊልም ፌስቲቫልም ቼሻየር ሆም ኢትዮጵያ ምርጥ አድቮኬት/ምርጥ የግንዛቤ ሰጪ ተቋም/ በሚል ሽልማት ተበርክቶለታል::
ፎከስ ኦን አቢሊቲ የአካል ጉዳተኞችን ብቃትና ችሎታ ለማረጋገጥ ዝግጁ እንደመሆኑ በርካቶችን የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ አበክሮ ይሰራል:: በዚህም ጥቂት የማይባሉ አካል ጉዳተኞች አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት አስችሏል:: እንደ እ.ኤ.አ ከ2021 ጀምሮ የሀገራችንን ተሳትፎ ያሰፋው ይህ ፌስቲቫል እስከዛሬ በመዝለቅ የበርካታ አካል ጉዳተኛ ወገኖችን ችሎታና ክህሎት በማድመቅ ላይ ይገኛል::
በመልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም