የአዳሪ ትምህርት ቤቱ የስልሳ ዓመት ጉዞ

በሱዳን ሚሽኖች አማካኝነት በተመሰረተውና ወላይታ ሶዶ በሚገኘው ሆስፒታል ሃኪም ናቸው። ዶክተር ገበየሁ ጋላሶ ይባላሉ። እኒህ ሰው የማጅራት ገትር በሽታ ተቀስቅሶ የአካባቢውን ህጻናት ለአይነ.ስውርነት ሲዳርግ የእርሳቸውም የበኩር ልጅ የሆነው ደሳለኝ የገፈቱ ቀማሽ ነበር። ስለ ልጃቸው ትምህርት ቤት መግባት ሲያስቡ የአይነስውራን ትምህርት ቤት በአካባቢያቸው ላይ መኖሩ ግድ እንደሆነ ተሰማቸው። ለዚህም ስለሰበታ መርሃ እውራን ትምህርት ቤት የሰሙት መልካም አስተዋጾ ለእርሳቸው ልጅና መሰሎቹ እፎይታን እንደሚሰጥ አመኑ።

ዛሬ ነገ ሳይሉ በወላይታ ምድርም ለመተግበር አብረዋቸው የሚሰሩትን ሚሽነሪዎች አስተባበሩ። 1957ዓ.ም ላይም ህልማቸውን ጮራ ፈንጥቆ በወላይታ ሶዶ ላይ የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን እንዲከፈት አደረጉ። በሚሽነሪዎችም ዘንድ ጥያቄያቸው መልስ በማግኘቱም ተጨማሪ ነገር አገኙ። ይህም የሶዶ ክሪስቲያን አካዳሚ ዳይሬክተር ካናዳዊት ሚስ ኒውፈልት ጋር በመሆን አዲስ አበባ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት መጥተው ስለአይነ ስውራን መማር ማስተማር ሂደት ልምድ የቀሰሙበት ነው።

የወላይታ ሶዶን ቃለ- ህይወት ቤተ- ክርስቲያን ጽህፈት ቤት ስለጉዳዩ ሲያናግሩት ደስ ተሰኝቶም በአካባቢው ለሚገኙት 12 ክፍለ-ማህበራት ከአባሎቻቸው ውስጥ አንዳንድ አይነ-ስውር እንዲልኩ ደብዳቤ ጻፈና የትምህርት ቤቱን መመስረት እውን አደረገ።

የተሰናዳውን ትምህርት ቤትንና የሞቀ ክፍያን ትተው ከእቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት ወደ ወላይታ የመጡት ሲስተር ሙሉነሽ ገብረ-ማርያምም የአይነ-ስውር እህትና ወንድሞቻቸውን ህይወት ለማቅናት ቆርጠው ተነስተዋል። በኦቶና አይነ-ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትም ለማስተማርና በትምህርት ቤቱ የተሳለጠ የትምህርት ስርዐት እንዲኖር ለማድረግ ሽተዋል። በተቻላቸው መጠንም ፍላጎታቸውን አሳክተዋል።

መምህርቷ “ትምህርት ቤቱ ገና ሲወጠን ከጠራ ህልምና ጽናት ከተሞላበት ተስፋ በቀር ምንም አይነት ግብዐት አልነበረውም።›› ያሉትን ይዤ ትምህርት ቤቱ ሲከፈት የመጀመሪያው ተማሪ የነበሩትንና በአሁኑ ሰዓትም በትምህርት ቤቱ ውስጥ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙትን ማሞ ማዴቦን በወቅቱ የነበረውን ሂደት እንዲያወጉኝ ጠየኳቸው።

ለስሙ አዳሪ ትምህርት ቤት ይባል እንጂ የተስተካከለ ሁኔታ ካለመኖሩ የተነሳ ወለሉ ላይ ሳር ጎዝጉዘው ሰሌን በማንጠፍ ይተኙ ነበር። ቀለብም ቢሆን ከወላጆቻቸው ስንቅ እየተመላለሰላቸው ሦስት ዓመታትን በችግር ለማሳለፍ የግድ ሆኖባቸዋል። በእንዲህ መልኩ እየኖሩ ሳለ የሚስ ኒውፈልት ዘመዶች ለጉብኝት በመጡበት አጋጣሚ ያሉበትን ደረጃ ተገነዘቡና የመፍትሄ አቅጣጫ ተቋማት፤ እሷም ጊዜ ሳታባክን ወደጀርመን ሃገር በመጓዝ “ሲቢዔም ክሪስቶፎል ብላይንድ ሚሽን” የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅትን አናግራ ዘላቂ ብልሃት ዘየደች። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በየሳምንቱ ሁለት ብር ከሰማኒያ ሳንቲም እየተሰጣቸው ዳገታማውን የትምህርት ህይወት መግፋት ያዙ። ግን ሁነኛ የተባለው ሃሳብ ከዳር ደርሶ ትምህርታቸውን አላስጨረሳቸውም።

ምን ገጠማችሁ? አልኳቸው የሚነግሩኝ ታሪክ ስሜቴን ሰቅዞ ይዞት። እርሳቸውም ‹‹አራተኛ ክፍል ስንደርስ ከዚህ በላይ መቀጠል እንደማንችል በዳይሬክተሯ ሚስ ኒውፈልትና በወላይታ ሶዶ ቃለ-ህይወት ቤተ-ክርስቲያን ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች በኩል ተነገረን። ምክንያቱ ደግሞ ‹በሳይንሱ ከዚህ በላይ ብትገፉ ሃይማኖታችሁን ትተዋላችሁ። ስለዚህም እደ-ጥበብ እናስተምራችሁና በእሱ ትተዳደራላችሁ›” የሚል ነበር ሲሉ የነበረውን ክስተት አብራሩልኝ። እኔም ቀጠል አድርጌ እናንተ ምን ወሰናችሁ? አልኳቸው። አይነ-ስውራኑ አልተስማሙም ፣ ሃሳባቸውን ተቃወሟቸው፤ በዚህም ሰበብ በ1968 ዓ.ም መዘጋቱን አጫወቱኝ።

ብዙኃኑ ተማሪ በቤተሰብ እጅ መልሶ ሲወድቅ ማሞ ማዴቦና ሌሎች ሦስት ጓደኞቻቸው ግን ትምህርት ቤቱ የሚከፈትበትን መንገድ ሲያፈላልጉ የኢትዮጵያ አይነ-ስውራን ብሄራዊ ማህበር ከአውራጃው አስተዳዳሪ አቶ ስምዖን ጋሎሬ ጋር በመነጋገር ዳግመኛ 1971 ዓ.ም ትምህርት ቤቱን ከፈቱትና የጠወለገ ተስፋቸውን አለመለሙትም። ይሁን እንጂ ይህ ተስፋም ከረጅም ዓመታት በኋላ መልሶ ስጋት ላይ ወደቀ። የትምህርት ቤቱን ከፍተኛ በጀት ይደጉም የነበረው ‹‹ሲቢዔም›› እጁን ሰበሰበ። ተማሪዎቹ ለርሃብና ለርዛት ተዳረጉ። ዛሬ ላይ ቆሞ የያኔውን ሁነት ሲያስታውሰው የመከራ ሰንበር ፊቱን ይገርፈዋል የትምህርት ቤቱን ርዕሰ-መምህር ኑሩ በድሩን።

በስንት ማባበል ‹‹ሲቢዔም›› በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ድጋፉን ቢቀጥልም አመርቂ ውጤት ሳያመጣ አሁንም በአጭር ተቀጨ፤ ተስፋ ያልቆረጠው አቶ ኑሩም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የ‹‹ዩዔስዔአይዲን›› ድጋፍ ማግኘት ቻለ፣ ድጋፉ ዘላቂ ሆኖ ከጭንቀት ባይገላግለውም። በችግሩ ግዝፈት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ያስተምር የነበረው የትምህርት ቤቱ ቁመና ወደ አራት ዝቅ አለና ጭራሹኑ እንዳይዘጋ ከንፈር ተመጠጠለትም። ኑሩ ግን ለወጀቡ እጅ አልሰጠም። ይልቁንም ሌሎች አማራጮችን ወደማፈላለጉ ገባ። ከ ‹‹ቢላቭድ›› ሃገር በቀል ድርጅት ጋር ተነጋገረ። ተቀናጀቶም በድን የሆነውን ትምህርት ቤት ስጋና ነፍስ ዘራለት። በዚህና መሰል ፈተና ውስጥ ያለፈው ትምህርት ቤት አሁን 60ኛ ዓመቱን ለማክበር አበቃው። ለቀጣይስ ዋስትናው ምንድነው? አልኩት ሃሳቤን እየጠቀለልኩ። እርሱም የጀመሩትን የከብትና የዶሮ እርባታ እንዲሁም የትምህርት ቤቱን ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች በማልማት የውስጥ ገቢን ለማሳደግ ተጨባጭ ጥረት መኖሩን ገለጸልኝ።

የኢትዮጵያ አይነ-ስውራን ብሄራዊ ማህበር የአካቶ ትምህርት ክፍል ሃላፊ የሆነው አቶ ከተማ ባይለየኝም የንግድ ስፍራዎችን ገንብቶ ከማከራየት ባለፈ የተማሪዎቹን የዕደ-ጥበብ አቅም በማጎልበት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በማግኘት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በጅምር ያሉ ስራዎች መኖራቸውን አያይዞ አጫወተኝ።

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You