ቱሪዝም ለአንድ አገር አንዱ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ በዓለም ላይ ቱሪዝምን ለእድገታቸው በማዋል ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ በርካታ አገራት ይገኛሉ፡፡ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እየተባለ በሚጠራው በዚህ ዘርፍ በዓለም ላይ ከ1 ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት እ.አ.አ በ2018 ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለማችን ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን ከሚያስተናግዱ አገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ስፔንና አሜሪካ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሲሆን፤ ከአፍሪካ ደግሞ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካና ቱኒዚያ በግንባር ቀደምትነት ይገኛሉ፡፡ አገራቱ ከቱሪስት ፍሰቱ የሚያገኙትን ገቢ ስንመለከትም ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ትልቁን ስፍራ ትይዛለች፡፡ አሜሪካ በየዓመቱ ከ244 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመሰብሰብ ቀዳሚ ስትሆን ስፔን ደግሞ 68 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ፈረንሳይ 60 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ ለኢኮኖሚያቸው እድገት እያዋሉት ይገኛሉ፡፡
ከአፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ 8ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ ቀዳሚ ስትሆን፣ ግብጽ ደግሞ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ትሰበስባለች፡፡ ሞሮኮ 7ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ከቱሪስቶች በመሰብሰብ ከአፍሪካ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በ2007 ዓ.ም 3ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡
ከላይ እንደገለጹት ቱሪዝም ትልቅ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ ይህንን ዘርፍ በአግባቡ ማንቀሳቀስና መጠቀም ከተቻለ ለአገር እድገት የሚኖረው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም፡፡ በዓለም ላይም በቱሪዝም ገቢያቸው ያደጉ በርካታ አገራት እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ያም ሆኖ ግን የአገራችን የቱሪዝም ሁኔታ ሁለት ተፃራሪ ጉዳዮች የሚታዩበት ነው፡፡ በአንድ በኩል ለቱሪስት መስህብ የሆኑና በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም የተመዘገቡ በርካታ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከዘርፉ መጠቀም በሚገባት ልክ እየተጠቀመች አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ከአፍሪካ በህዝብ ቁጥሯ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለምትገኘውና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ለሆነችው ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡
ሰሞኑን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የከተራና የጥምቀት በዓላት ተከብረው መዋላቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ በዓላት ደግሞ ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነታቸው ባሻገር በርካታ ቱሪስቶች የሚስተናገዱባቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ በነዚህ በዓላት ላይ ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶችን ስንመለከት ይህንን ዘርፍ በአግባቡ ብንጠቀምበትና ብናስተዋውቀው ማግኘት የሚገባንን ጥቅም እንድናገኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት መገመት አያዳግትም፡፡ ለዛሬም ይህንን አጋጣሚ ምክንያት በማድረግ በአገራችን በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ቅርሶች ጥቂቱን በማስታወስ በዚህ ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት በስፋት እንዲሠሩበት ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በመመዝገብ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እገዛ የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታትም 43 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በአፋጣኝ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ቅርሶቻቸውን ካስመዘገቡ አገራት በአፍሪካ በቀዳሚ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የቱሪዝም ኢንዱስትሪን በ1950ዎቹ መጨረሻ ያቋቋሙ ሲሆን ኢትዮጵያም በወቅቱ ዘርፉን ካቋቋሙ አገራት አንዷ ነበረች፡፡ በአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መመስረትን ተከትሎ ወደ አገራችን የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ መድረክ ማስመዝገብ ተጀመረ፡፡ ይህም ፍሬ አፍርቶ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባህልና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርሶቹን መመዝገብ ጀመረ፡፡ ይህም ቅርሶቹን ለማስተዋወቅ ከመጥቀሙም በላይ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግም አግዟል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ በተለያዩ የስነፅሁፍ ቅርሶችም የበለፀገች ናት፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመፅህፍትና ቤተመዛግብት ካሰባሰባቸው የመረጃ ሃብቶች ውስጥም 12 የስነጽሁፍ ቅርሶች በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ መሰረት ያላቸው ሲሆኑ፣ በብራና ላይ የተፃፉት መጽሐፈ ሄኖክ፣ መጽሐፈ ታሪክ ነገሥት፣ መጽሐፈ ግብረ ህማማት እና አርባዕቱ ወንጌል ይጠቀሳሉ፡፡ ከነዚህም ባሻገር አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ የፃፉት ደብዳቤ፣ የሸዋው ንጉሥ ሳህለሥላሴ ለእንግሊዝ ንግሥት የላኩት ደብዳቤ እና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለሞስኮ ንጉሥ ኒኮላስ ቄሳር 2ኛ የላኩት ደብዳቤ በቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ መዝሙረ ዳዊት፣ በግዕዝ የተፃፈ መጽሐፍ ቅዱስና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ታሪክም በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል ይገኙበታል፡፡
ከነዚህ ውጪ ደግሞ አብዛኛው የአገራችን ህዝብ በስም የሚያውቃቸው ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ በአካል የማየት ዕድሉን ያገኙባቸው ልዩ ልዩ የሥልጣኔ መገለጫ የሆኑ ቅርሶችም አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የአክሱም ሐውልት ነው፡፡ የአክሱም ታሪክ ሲነሳ የአገራችን ቀደምት ሥልጣኔም አብሮ ይነሳል፡፡ ይህ ትልቅ የአገራችን የቀደምት ሥልጣኔ አሻራ በጣሊያን ወረራ ወቅት በፋሽስት ኢጣሊያ ተወስዶ ከ68 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደአገሩ መመለሱ የሚታወስ ነው፡፡
አክሱም ከአዲስ አበባ 1025 ኪ.ሜ ላይ ትገኛለች፡፡ በከተማዋ አክሱም ፅዮን ቤተ ቤተክርስቲያን፣ የአክሱም ሐውልቶችና የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎች የአክሱም ሥልጣኔ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በጊዜው ከተማዋ የሥልጣኔ፣ የእምነትና የአስተዳደር ማዕከል እንደነበረችም ታሪክ ይናገራል፡፡
በዘመኑ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው የታነፁት እነዚህ ሐውልቶች የአክሱምን የሥልጣኔ እና የእድገት ምህንድስና የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ቦታዎቹ እ.አ.አ በ1980 በቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡ ሐውልቶቹ 1700 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው ይገመታል፡፡
ሌላው የሥልጣኔያችን መገለጫ ደግሞ ላሊበላ ነው፡፡ ሮሃ ወይም የአሁኗ ላሊበላ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት መቀመጫ ነበረች፡፡ በከተማዋ የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በንጉሥ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት የተሠሩ ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያኖቹ ከአንድ አለት ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩ ሲሆን ቁጥራቸውም 11 ይደርሳል፡፡ ቤተክርስቲያኖቹ በ12ኛውና በ13ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሠሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ግንባታውም 24 ዓመታትን እንደወሰደ ይገመታል፡፡ በአስደናቂነታቸውም በዓለም ደረጃ በ8ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እየሩሳሌምን ተምሳሌት አድርገው የተሠሩ ሲሆን፤ በ1978 በዩኔስኮ በቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡
የጎንደር ቤተመንግሥትም በአገራችን ታላላቅ ቅርሶች ስም ሲጠራ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ቅርሶች አንዱ ነው፡፡ በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መቀመጫ የነበረችው ጎንደር በአፄ ፋሲለደስ ዘመን ነበር የተቆረቆረችው፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኙት ቤተመንግሥቶች 900 ሜትር ርዝመት ባለው ግድግዳ የታጠሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቀደምት መገለጫ የሆነው የፋሲለደስ ግቢም በ1980 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ ግቢው 5 ቤተመንግስቶችና ብዛት ያላቸው ህንጻዎች ያሉት ሲሆን 12 በሮች አሉት፡፡
ከነዚህ በተጨማሪም በአገራችን ገና ያልተመዘገቡና የአገራችንን የቆየ የሥልጣኔ አሻራ የሚያሳዩ በርካታ የሥነጥበብና የሥነህንጻ ውጤቶች ይገኛሉ፡፡ የጅማ አባጅፋር ቤተመንግሥት፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሼህ ሆጀሌ ቤተመንግሥት፣ የሐረር ግንብና አምስቱ በሮቿ፣ የንጉሥ ጦና መኖሪያና ሌሎችም በርካታ ቅርሶች የአገራችንን የቱሪዝም ሀብት ስፋት የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የአገራችን ልዩ ተፈጥሮአዊ ገጽታ ከለገሰን የቱሪስት መስህቦች ውስጥ ደግሞ ፓርኮቻችን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአገራችን የሚገኙ ፓርኮች ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋትን የያዙና በርካታ አገር በቀል እፅዋት ያላቸው፤ በአቀማመጣቸውም ልዩ ገጽታና ውበትን የተላበሱ በመሆናቸው ለቱሪስቶች ልዩ ደስታን የማጎናፀፍ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ በዩኔስኮ ተመዝግበዋል፡፡
በዚህ መሰረት በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ብሄራዊ ፓርኮቻችን ውስጥ አንዱ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ነው፡፡ ይህ ፓርክ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኝ ሲሆን፣ በውስጡም በአገራችን በርዝመቱ ትልቁ የሆነውንና በአፍሪካ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የራስ ዳሽን ተራራ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውስጡ 1500 የሚሆኑ ገደላማ ስፍራዎች አሉ፡፡ ጭላዳ ባቡን፣ ሰሜን ቀበሮ፣ ዋልያ አይቤክስና መሰል ብርቅዬ እንስሳትም መኖሪያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እፅዋትም መገኛ ነው፡፡ ፓርኩ በ1978 በዩኔስኮ ተመዝግቧል፡፡ ሆኖም በ1996 በአደጋ ውስጥ ካሉ ፓርኮች አንዱ ተደርጎ ተመዝግቧል፡፡ ለዚህም ሰዎች በፓርኩ ውስጥ መኖራቸው ትልቁ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
የታችኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንዱ ድንቅ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ በአፋር ክልል የሚገኘው ይህ ስፍራ በተለይ በሰው ልጅ መገኛነት ከሚታወቁ ስፍራዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ እስከ 3ነጥብ9 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ የሚገመት ቅሪቶች መገኛ እንደሆነ የሚጠቀሰው ይህ ስፍራ በርካታ ጥናቶች የሚካሄዱበት ነው፡፡ የሉሲ መገኛ ስፍራም ነው፡፡ አሁንም በርካታ ጥናቶች ይካሄዱበታል፡፡ ከድንቅነሽ 150ሺህ ዓመት የምትቀድመው ሰላምም የተገኘችው በዚሁ ስፍራ ነው፡፡ ይህ ስፍራም በ1980 በቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
ከእነዚህም በተጨማሪ የባሌ ተራራዎች ፣ የአቢያታ ሐይቆች፣ የኦሞ፣ የማጎ፣ የጨበራ ጩርጩራ፣ ያንጉዲ ራሳ፣ ገራኢሌ፣ የዳቲ ወለል፣ ያቤሎ፣ ጊቤ ሸለቆ እና የቃፍታ ሽራሮ ብሄራዊ ፓርኮች በአገራችን ከሚገኙ ፓርኮች በርካታ አዕዋፋት፣ ብርቅዬ እንስሳትና እፅዋት የሚገኙባቸው የመስህብ ስፍራዎች ናቸው፡፡
በአገራችን በተፈጥሮአዊ አቀማመጣቸውና በጥንታዊ ሰው ሰራሽ ክንውኖችም የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የኮንሶ ባህላዊ የመሬት አቀማመጥና እርከን ሥራ ነው፡፡ 55 ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍነው የኮንሶ ባህላዊ መሬት አቀማመጥና በድንጋይ የተሠራው የእርከን ሥራ ለአራት መቶ ዓመታት የዘለቀ ነው፡፡ ሥራው የአካባቢውን ህብረተሰብ እሴትና ማህበራዊ ትስስር እንዲሁም ምህንድስናን እንደሚሳይ ዩኔስኮ በመዝገቡ አስፍሯል፡፡ በአንድ ቦታ እስከ አምስት ሜትር ከፍታ ያለው እርከንም ይገኛል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የእንጨት ቅርፃ ቅርፆችም አሉት፡፡ እነዚህ እንጨቶችም የአካባቢውን የተከበሩ ሰዎችና ጀግኖች የሚወክል ነው፡፡ ስፍራውም እ.አ.አ በ2011 በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
ከአ.አ. ደቡባዊ ዞን 90 ኪሎሜትር ላይ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋይም በአገራችን ከሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ 36 ሐውልቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 32ቱ በተለያዩ ቅርፆች ያጌጡ ናቸው፡፡
ከእስልምና ማዕከልነትም ባሻገር የንግድ ማዕከል ሆና ለዘመናት ያገለገለችው የምስራቋ ኮከብ የሐረር ከተማም በአገራችን ከሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች አንዷ ናት፡፡ ከተማዋ በግንብ አጥር የተከበበች ሲሆን፣ ይህም በኤሚር ኑር ኢብን ሙጃሂድ የተገነባ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ግንባታው በወቅቱ ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል ታስቦ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ግንቡ 3ነጥብ5 ኪሎሜትር ርዝመትና 4 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ ከተማዋ እ.አ.አ በ2006ዓ.ም በዓለም ቅርስነት ተመዝግባች፡፡
ከላይ በጥቂቱ ከተጠቀሱት የአገራችን የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችና ሰው ሰራሽ የፈጠራ ውጤቶች በተጨማሪ በአገራችን በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ይህ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2003 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ኮንቬንሽን ወይም ስምምነት እንደሚገልጸው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸው አድርገው የተቀበሏቸውን ድርጊቶች፣እውቀቶች፣ ሥነጥበባት፣ ህግጋት፣ እምነቶች፣ ማህበራዊ ክንዋኔዎችና ሥነ ሥርዓቶች ክብረ በዓላት የሚያካትት ነው፡፡
በዚህ ረገድ በዓለም ላይ እ.አ.አ እስከ 2018 ድረስ 300 የሚጠጉ ቅርሶች ተመዝግበዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 30 የሚጠጉት የአፍሪካ ሀገራት ናቸው፡፡ አገራችንም እስካሁን ድረስ የመስቀል ደመራ በዓልን፣ ፊቼ ጨምበላላንና የገዳ ሥርዓትን በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡
በአገራችን ከነዚህ በተጨማሪ በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ሃይማኖታዊ መሰረት ያለውና በርካታ ክንዋኔዎችን የሚያቅፈው የከተራና የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ የሚከበር በዓል ሲሆን፣ በርካታ ቱሪስቶችም የሚሳተፉበትና የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ እየሳበ የሚገኝ በዓል ነው፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የጠቃቀስኳቸው የቱሪስት መስህቦቻችን በአገራችን ከሚገኙ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አገራችን ከነዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ያላት አገር ናት፡፡ በርካታ ቱሪስቶችም ወደ አገራችን ሲመጡ በሚያዩት ነገር ተደምመውና ተደስተው የሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህን በእጃችን የሚገኙ፤ ምንም አይነት ኬሚካልም ሆነ ጭስ የሌላቸው የተፈጥሮ ኢንዱስትሪዎች በአግባቡ መጠቀም ለኢኮኖሚያችን እድገት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ዛሬ አገራችን ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለመፍታት ይህንን ሀብቷን በአግባቡ ልትጠቀም ይገባል፡፡ በሌላም በኩል የአገራችን ዜጎችም ቢሆኑ አገራቸውን ማወቅ ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ በአገራችን የሚገኙትን ትላልቅ ቅርሶች ሌላው ቀርቶ በዩኔስኮ የተመዘገቡትን እንኳ ስንቶቻችን እናውቃቸዋለን? የምናውቀውንስ ምን ያህል ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች እናስተዋውቃለን፡፡ በዚህ ዙሪያ ሁላችንም ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አገራችንን ለመውደድም ሆነ ለመጥቀም በቅድሚያ ስለአገራችን በአግባቡ መረዳትና ማወቅ የግድ ነውና፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
ውቤ ከልደታ