የአኗኗር ባህላችን በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ከመሆኑም በላይ ከሥነ- ምግባር ሕግጋት ጋር የተቆራኘ ነው። ለዚህም ማሳያዎቹ የምናንጸባርቃቸው ብሂሎቻችን ናቸው። ለአብነት ‹‹ለ ሰው መድኃኒቱ ሰው ነው፤ አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም፤ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም ወዘተ›› የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስለዚህም በባህላችን አብሮነት ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል ማለት ነው።
አብሮነት በባህላችን እንዴት ይገለጻል ከተባለ ዋነኛውና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው በመሰባሰብ መሠረት ላይ የታነጸው …. እድርና እቁባችን እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይችላል። ቤት ሲቀልሱ በደቦ፤ አዝመራቸውን ሲሰበስቡና ሲወቁ በደቦ፤ ኀዘንና ደስታ (ለቅሶና ሰርግ) በጋራ ማድረግ የሚቻለውም በእነዚህ መስተጋብሮች አማካኝነት መሆኑን ሁሉም ይገነዘባል።
ሰዎች ድርጊቶቹን የሚከውኑት ከውስጣዊ መንፈሳቸው በመነጨ መልኩ ነው። በመረዳዳት፣ በመተባበርና አንዱ ለአንዱ በመቆምም ነው። ነገ ለእኔም ይህ ይሆንልኛል በሚል ስሜትም ይደረጋል። በተለይ ለዚህ አምድ የመረጥነው እድር በለቅሶና በችግር ወቅት የመድረሱ ሁኔታ በሰዎች ዘንድ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል።
እድር ሰዎች ኀዘን የገጠማቸውን ‹‹ጽናቱን ይስጣችሁ! ኀዘናችሁን ያላላላችሁ›› እያሉ ብርታት የሚሰጡበት እንቁ ባህላዊ እሴት ነው። እድሩን ለጊዜው አቆይተነው መንገደኛ እንኳን ኀዘን የደረሰበትን የማያውቀውን ሰው ሳያጽናና አያልፍም፤ በጉዞው ላይ የማያውቀው ለቅሶ ቢመለከት ድንኳኑን ረግጦ አያልፍም፤ ይልቁንም ድንኳኑ ውስጥ ገብቶ ትንሽ ተቀምጦ ‹‹ብርታቱን ይስጣችሁ› ብሎ ይወጣል፤ በዚህም ተጎጂውን ያበረታታል።
ይህ በእድር በሚገባ የሚከወን የቆየ ባህል በኮሮና ምክንያት ሲሸረሸር ይታያል። ምክንያቱ ደግሞ በሽታው ይዞት የመጣው ጣጣ ነው፤ በዚህ ዘመን እንደፊቱ ብዙ ነገሮችን አብሮ ለማድረግ ይከብዳል። ይህ ማለት ግን ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ መተው ማለት እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ይዞ መጓዝ የሚገባ ጉዳይ እንዳለ ማወቅ ይገባል። የእድሮችን ምሰሶ ቆርጦ መጣል አያስፈልግም፤ አሠራርን በማሻሻል በአብሮነት የቆመን ወገንን ማገዝ ያስፈልጋል።
እርግጥ ነው ወቅቱ ድንኳን ጥሎ ኀዘንተኛውን ለማጽናናት አስቸጋሪ የሆነበት ነው። መረዳዳቱ ታዲያ በምን መልኩ ይተግበር? ጥንካሬ የሚሰጠው የኀዘን መርሻ በእድሮች እንዴት ይከወን? የሚሉትንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ የአዲስ አበባ እድሮች ምክር ቤትን፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርንና የእድር ዳኞችን አነጋግረን የሰጡንን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴት ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ እስከዳር ግሩም እንደሚናገሩት፤ እድር አንዱ ማህበረሰባዊና የባህል ተቋም ነው። ሲቋቋም ለመከራ ጊዜ መረዳጃ በሚል ሆነ እንጂ ለልማት እና ለመረዳዳት እንደ እርሱ ተስማሚ የለም። ከዚያም አልፎ ኢኮኖሚክ ሴክተር በመሆን አገር የሚለውጥ ሥራ ይሰራበታል። ምክንያቱም ከሌሎች ተቋማት ይበልጥ አመኔታ የሚጣልበት ተቋም ነው። ሥራው በባህሪው የሚከናወነው ተሰባስቦ መሆኑ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ይገጥሙታል።
የኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ እንዴት በእድሮች ይሰራበት ከተባለ መሠረታዊ መሆን ያለበት መሰባሰብን መቀነስና ተግባሩን ወደ መረዳዳት ማዞር ነው። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከሌሎች ተቋማት በበለጠ መልኩ አንዱ ለአንዱ ይደርስበታል ተብሎ የሚታሰብበት በመሆኑ ተግባሩን ዘመኑ እና ወቅቱ በሚጠይቀው መልኩ በመከወን ከራስ እስከ ሕዝብ ድረስ ዋጋውን ማሳየት ይገባልም ይላሉ።
እድር ከገጠሩ ይልቅ ከተማ ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የሚገልጹት ዳይሬክተሯ፤ በችግሩ የደረሰ ሁሉ ነገ ለእርሱም እንደሚደርስለት ያምናል ይላሉ። ከገጠር ያለው ወይም ከአካባቢው የራቀው ሰው እስኪደርስለት ድረስ እድር ላይ የተሳተፈው ጎረቤቱ ቀድሞ ያጽናናዋል፤ ችግሩንም ይጋራዋል። ስለዚህም ለነገ እኔነቴ ዛሬን ለሌሎች መድረስ ይገባኛል በማለት በእድሩ ላይ ይሳተፋል። ገንዘብ ባይኖረው እንኳን ከዚህ ማህበራዊ ሁነት ውስጥ መውጣትን ስለሚፈራ ተበድሮ መክፈሉን አያቆምም። ስለዚህም ለሰው ደራሽነት በእድር ውስጥ ትልቅ ዋጋ አለው።
አሁንም በዘመነ ኮሮና ይህንን ትልቅ ዋጋ ወደ መረዳዳት ማዞር ያስፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ከእድር አባላትና ከአዲስ አበባ የእድር ምክርቤት ሰብሳቢ እንዲሁም የእድር አመራሮችና የጤና ባለሙያ ጋር ውይይት በማድረግ በሽታው እንዳይዛመት በሚያስችሉ መከላከያዎች ላይ እንዴት መሰራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን ይጠቅሳሉ።
ኅብረተሰቡ በእድር ውስጥ ሲሳተፍ ችግርና ኀዘን ሲያጋጥመኝ ደራሽ አለኝ በማለት እያሰበ የሚጓዝበት በመሆኑም ብዙ ችግሮች በአንድነት እንዲፈቱ ያደርጋል። አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው። ሰውን በቁሙ መርዳት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ተግባራትን ሲከውኑ በተለይም ቀብር ላይና ከቀብር በኋላ በቤት ውስጥ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ግንዛቤ በማስጨበጡ ዙሪያ ከጋራ ምክርቤቱ ጋር እየተሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።
እንደ ባህልና ቱሪዝም ዛሬን ተሻግሮ ነገ ባህላችንን መልሰን እንድንኖረው ለማድረግ ደግሞ በግል ደረጃ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሆኑ የሚያስረዱት ወይዘሮ እስከዳር፤ ዘመኑ የሚጠይቀውን ማድረግ ያስፈልጋልና የማስተማር ሥራ በየአደባባዩ ተጀምሯል። ይህም የሆነው በባህላዊ መንገድ ሲሆን፤ ጥሩንባ በመጠቀምና ሰዎች ነቅተው እንዲያደምጡ በማድረግ ነው ብለዋል።
ኮሮና ዛሬ መለያየቱን በመፍጠሩ ሳቢያ የሥነልቦና ጫናን ፈጥሮብን ይሆናል፤ ይህንን በመረዳዳት ባህላችን ማሸነፍ እንችላለን። እናም ይህ እንዲሆን ቅርብ መሆንን ለማሳየት ሰዎች በጋራ ለችግረኞች የሚደርሱበትን መንገድ እንዲፈጥሩም በተለይም ከእድሮች ጋር በመሆን በማስተማር ላይ እንገኛለን።
ሰዎች በኮሮና ምክንያት ለቅሶ አልደረሱንም ብለው ተጎጂዎች እንዳይቀየሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሯ ያመለክታሉ። ለቅሶ ያልደረሱት እነርሱ ተጠብቀው እኔንም ለማዳን ነው ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንንም በሃይማኖት አባቶችና አገር ሽማግሌዎች በኩል ለማስረዳት አንዳንድ ሥራዎች መጀመራቸውን ያብራራሉ።
አብሮ መብላት፤ ችግርን መጋራት፤ ማስተዛዘን የመሳሰሉት እሴቶች ከኮሮና በኋላ ሳይጠፉ ዳግም እንድንተገብራቸው ለማድረግ ዛሬ እሴቱን መገንባት ያስፈልጋልና እድሮች ያላቸውን አመኔታ ተጠቅመው እንዲሰሩም ለማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶች በቪዲዮ ኮንፍረንስ እየተደረጉ ናቸው ይላሉ። በቀጣይም በዚህ ላይ እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እድሮች ምክርቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት ገብረማርያም በበኩላቸው ‹‹ዛሬ ወቅቱ የሚጠይቀው ‹ሳይቃጠል በቅጠል› የሚለውን ብሂል ተግባራዊ ማድረግ ነው።›› ይላሉ። ይህ አባባል በተለይም በእድሮች ተግባራዊ ከሆነ ማህበረሰቡ ዛሬን እንዲሻገር የሚረዳ መሆኑን ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ እድሩ ላይ መሳተፍ እንዲሁም ቆሞ ሌሎችን ማገዝ የሚቻለው ዛሬ በበሽታው ዙሪያ ቅድመ መከላከልን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው። ለዚህም ተቋሙ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።
ከአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በርካታ ተግባራትን እየከወነ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ በቅርቡ ከተለያዩ እድሮች ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ለችግረኞች እንዲደርስ መደረጉንም ለእዚህ በአብነት ይጠቅሳሉ። በተመሳሳይ በማዕድ ማጋራት ላይም እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፣ እድሮች በእያንዳንዱ ተግባራቸው ኮሮናን ሊከላከሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ማንዋል ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አቶ ታምራት እንደሚሉት፤ እድሮች በሕጉ መሠረት እየሰሩ ናቸው። ይህም ክትትል እየተደረገበት ይገኛል። በከተማ አስተዳደሩ የእድር አሠራሮች ብዙ ለውጦች ማምጣት ችለዋል። ከእነዚህም መካከል ወደ ቀብር ሲኬድ ውስን ሰው ብቻ ማለትም ከ40 ሰው ያልበለጠ የሚሄድበት አሠራር ተፈጥሯል። የእድር አባላት በቀብር ቦታውም የጤና ባለሙያዎች የሚመክሩትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ። ከቀብር መልስ ደግሞ ለማስተዛዘን የሚገባው ሰው እጁን በሳሙና እንዲታጠብ አለያም ሳይኒታይዘር እንዲጠቀም ይደረጋል። በቤት ውስጥ ተራርቀው እንዲቀመጡ ይደረጋል።
የእድር አመራሮች በየእድሮቻቸው ማስክ ማድረግ ግዴታ እንደሆነ ይነግራሉ ያሉት ሰብሳቢው፤ ከላይ የተጠቀሱትን የማያደርግ እድር ወይም እድርተኛ በተዋረድ ቅጣት ይጣልበታል። እድሩን እስከመሰረዝም የሚያደርስ ተግባር ሊፈጸም ይችላል። ሆኖም እስካሁን ይህንን ያላደረገ እድር አልገጠመምና ቅጣቱ ተግባራዊ አልሆነም። ሆኖም ነገሮች እየከበዱ በመምጣታቸው ምክንያት በቅርቡ ማሻሻያዎች መደረጋቸው አይቀርምና ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰዱ አይቀርም ሲሉ ያብራራሉ።
አሁን በከተማው የኮሮና ስርጭት አስጊ ሁኔታ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፣ እድሮች ሰው የሚሰባሰብባቸው በመሆናቸው ሁኔታው እንዲሰፋ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ድርሻ አላቸው ይላሉ። መነካካት ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረው፣ በእዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ከመሆኑ አኳያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራም ይገልጻሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ መሰባሰቡ እንዲቀንስና መተጋገዙ እንዲጠነክር ማድረግ ላይ እንሰራለን ብለዋል። ማዕድ ማጋራት ሥራው ላይ ጠንከር ያለ ሥራ እየሰራን ነው ያሉት አቶ ታምራት፣ ማእድ ማጋራት ላይ የሚሳተፉ እድሮችም እየተለዩ መሆናቸውንና በግለሰብ ደረጃ የሚያግዙትን በማሳተፍ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፤ ምክር ቤቱ ከ700 በላይ ግብረሰናይ ድርጅቶችን ከያዘ ድርጅት፤ በስደት ተመላሾች ላይ ከሚሰራው ድርጅት፣ ከኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ማህበራት፤ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና መሰል ድርጅቶች ጋር እየተሰራ ነው። ችግሩን በቀላሉ መሻገር የማይቻል መሆኑ ታምኖበትም በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረት አማካኝነትም ሀብት በማሰባሰብ ቀጣይነት ያለው ሥራ ለማከናወን እየተሰራ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያው መምህር መክብብ ገብረማርያም ‹‹ወቅቱ የመንግሥትን ሥራ ብቻ የሚጠይቅ አይደለም። ሁሉም ሰው ለሌሎች እንዲደርስ የሚያስገድድ ነው። ራስን ለማዳን ሰዎችን ማገዝ ግዴታም የሆነበት ጊዜ ነው።›› ሲሉ ገልጸው፣ በዚህ መንደር በእድሮች አማካኝነት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በሚኪሊ ላንድ የጋራ መኖሪያ ቤት መንደር ከ50 በላይ የእድር አባላትን በያዘው የመረዳጃ እድር ውስጥ ሰብሳቢ እንደሆኑ የሚገልጹት መምህር መክብብ እንዳሉት፤ በኮንዶሚኒየሙ 96 እድሮች የሚገኙ ሲሆን፣ 30ሺህ ሕዝብና አምስት ሺህ አባዎራዎች ይኖሩበታል።
‹‹በዚህ አካባቢ እድሮች ከቀብር አልፈው ሰዎችን በችግራቸው እየረዱ ናቸው። ወቅቱ መሰባሰብን አይፈቅድም።›› የሚሉት ባለሙያው፣ ከጋራ መሰባሰብ ይልቅ በግል ደረጃ ለሰዎች መድረስን መሠረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ። በተለይም ባለፉት ጊዜያት ሙስሊሙን በማፍጠር ክርስቲያኑን ደግሞ በተቸገረው ሁሉ በማገዝ ጊዜውን እንዳሳለፉ ነው ያብራሩት።
ችግረኞችን አምጡ በሚባልበት ጊዜ በእድሩ አማካኝነት በመምረጥ ድጋፉን ሌሎች እንዳይሻሟቸው ለማድረግ መቻሉን የሚያነሱት ሰብሳቢው፤ ኮሮና ከገባ በኋላ እስካሁን የሞተም ሆነ ለቅሶ የመጣበት ሰው ባለመኖሩ መሰባሰቦች እንዳልተፈጠሩም ይገልጻሉ። የእድር ወርሃዊ ክፍያ በአባላት ላይ እንዳይወዘፍ በሚል በየብሎኩ የሚከፍሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን ይናገራሉ። ከዚህ በተጓዳኝ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራንም እያከናወንን እንገኛለን ይላሉ።
ሰብሳቢው በኮሮና ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል ሚዲያው የሰራው ሥራ ወደር አይገኝለትም። ሁሉም በራሱ የሚጠነቀቅበትን መንገድ ፈጥሯል። ግን አሁንም የመቀበሉና በተግባር የማዋሉ ሁኔታ ችግር አለበት ሲሉ ገልጸው፣ በቅርቡ አስከሬን ላይ ሳይቀር እየተሻሹ የሚያለቅሱ እንዳጋጠማቸውም ተናግረዋል። ‹‹አትነካኩ ቢባልም ተቃቅፎም የሚያለቅስ አለ። ስለዚህም እድሮች ይህንን በማስገንዘብ ላይ ከፍተኛ ሥራ መስራት ካልቻሉ አደጋው የከፋ ይሆናል›› ብለዋል። ችግሩ ለመፍታት በቀጣይ የጤና ባለሙያዎችን ምክር መሠረት ባደረገ መልኩ ለመስራት እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
የሰው ልጅ የተባልከውን ሁሉ ተቀብለህ ተግብር ቢባል እሺ ለማለት ይቸገራል። በተለይም ማህበራዊ መስተጋብሩን በሚያራርቅበት ሁኔታ ላይ በእጅጉ ይፈተናል ያሉት ሰብሳቢው፣ ቅጣት ታክሎበት ወደ ተግባር የሚገባበትን ሁኔታ ልንዘረጋ አስበናል ይላሉ። ዛሬ ስናዝንና ስናጽናና ነገን እያሰብን መሆን ይኖርበታል፤ ይህ ካልሆነ ሁሉም በኀዘን ውስጥ ከወደቀ አጽናኝ አይኖርምና ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። እኛም ነገ ለመተዛዘን መተጋገዛችን ይብዛ በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው