
ለአንድ አገር እድገት መሬት፣ ካፒታልና የሰው ሀብት መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት እና በርካታ የተማረና በመማር ላይ ያለ የሰው ኃይል እንዳላት ይታወቃል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ገና ስራ ላይ ያልዋለ ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት ያላት ሲሆን 70 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧም እድሜው ከ29 ዓመት በታች ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም ግማሽ ያህሉ እድሜው ለስራ የደረሰ ወጣት ኃይል ነው፡፡
በሌላ በኩል በአገራችን የካፒታል አቅም ማነስ ዋነኛው የመንግሥት ፈተና እንደሆነም ይታወቃል፡፡ በተለይ አነስተኛ በሆነው ኢኮኖሚያችን ላይ የሌብነትና የአሰራር ድክመቶች ተጨምሮበት እድገታችንን አዝጋሚ አድርጎታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረትም በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለፅ የቆየ እውነታ ነው፡፡
መንግሥት ይህንን የካፒታል አቅም ለማሳደግና በተለይ በውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታዩ ድክመቶችን ለመቅረፍ ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የወጪ ንግድን ማበረታታትና የውጭ ቀጥተኛ ድጋፍ ነው፡፡
በሌላ በኩል በአገራችን በተለይ የውጭ ምንዛሬን የምናገኝባቸውና የአገር ውስጥ ኢኮኖሚያችንን የምንደጉምባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚሳዩት አገራችን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ካላቸው የአፍሪካ አገራት በግንባር ቀደምትነት ትገኛለች፡፡ በአገራችን በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶች ይገኛሉ፡፡ ከታሪክም አንጻር ኢትዮጵያ የበርካታ የጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ የሆኑ ታሪኮች መገኛ ስፍራ ናት፡፡ በተፈጥሮአዊ አቀማመጧም ቢሆን ኢትዮጵያን ተመራጭ የሚያደርጓት በርካታ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች አሉ፡፡ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ አእዋፋትና እፅዋትም ከምቹ አየር ንብረት ጋር ተዳምረው የቱሪስቶችን ቀልብ የመግዛት አቅም ፈጥረዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን አገራችን በዘርፉ ያላትን ሀብት ያክል በአግባቡ አለመጠቀሟ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል የቱሪዝም ዘርፉን በአግባቡ አለማስተዋወቃችን በሌላ በኩል ደግሞ ዘርፉን ለማሳደግ ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱ እንደ ምክንያት ይነሳል፡፡
በመሆኑም ከዘርፉ የሚገባንን ጥቅም ለማግኘትና ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር የቱሪስት መስህብ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን መሰረተ ልማት አገልግሎት ይበልጥ ማሳደግ፣ አገራችንን ያላትን የቱሪዝም ሀብት በስፋት ማስተዋወቅና የሌሎችን አገራት ልምድ በመውሰድ ዘርፉ የሚያድግበትን መንገድ መቀየስ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ ሊታይ ይገባል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በቅድሚያ የአገራችን ህዝብም ስለራሱ አገር የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ሊረዳ ይገባል፡፡ በተለይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎች ስለአገራቸው የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ የሚረዱበትን መንገድ መፍጠርና በሚሄዱበት ቦታ ስለአገራችው የሚያስተዋውቁበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡
የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሙኒኬሽን ስራ ውጤታማ የሚሆነው በተለያዩ መንገዶች መረጃዎችን ማዳረስ ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከኢትዮጵያ ውጭ ለስራም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች የሚጓዙ ዜጎች ለአገራቸው አምባሳደር ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ ስለአገራቸው ጠንቅቀው መረዳትና በሚሄዱበት ቦታ ምን እና እንዴት መረጃ መስጠት እንዳለባቸው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን በአብዛኛው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎች አንድም ስለአገራቸው በቂ መረጃ ሳይኖራቸው በሌላም በኩል ስለሚያውቁትም ነገር ለሌሎች እንዴት ማካፈል እንዳለባቸው በቂ እውቀትና ግንዛቤ ሳይይዙ ስለሚሄዱ አንዳንድ ጊዜ የአገራቸውን ገጽታ ከመገንባት ይልቅ አበላሽተው የሚመለሱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ከዚህም ባሻገር በስራ ምክንያት በውጭ አገራት በአምባሳደርነትም ሆነ በአታሼነት የሚሄዱ ባለስልጣናትም ቢሆኑ ስለአገራቸው በቂ ግንዛቤና ስለቱሪዝም ሃብታችን በቂ እውቀት ይዘው ሊሄዱ ይገባል፡፡ አምባሳደርነት አገርን መወከል በመሆኑ በሚመደቡበት ስፍራ ሁሉ ስለአገራቸው የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅ ቱሪስቶች አገራችንን እንዲጎበኙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አንድን ቱሪስት ወደ አገር ቤት መላክ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት በመሆኑ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የላቀ ነው፡፡
በሌላ በኩል በአገራችን አሁን አልፎ አልፎ የሚታየው አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ ችግሮች የአገራችንን ገጽታ የሚያበላሹና ቱሪስቶችንም የሚያሸሹ በመሆኑ ሰላምን ለማምጣትም መረባረብ ተገቢ ነው፡፡ እኛ ስንዋደድና ስንከባበር ሌሎቹም ያከብሩናል፤ ወደእኛም ለመምጣት ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ስለሰላማችን ደጋግመን ልናስብበት ይገባል፡፡
በተለይ ሰሞኑን የተከበሩትን የከተራና የጥምቀት በዓላት ምክንያት በማድረግ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን መግባታቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ቱሪስቶች ከሚያስገኙት ገቢ የበለጠ ይዘው የሚሄዱት ስምና ገጽታ ለቀጣይ የቱሪዝም እድገታችን ወሳኝ በመሆኑ ተገቢውን እንክብካቤ ልናደርግላቸው ይገባል፡፡ ባገኘነው አጋጣሚም ሁሉ ለነዚህ ቱሪስቶች ስለአገራችን የመስህብ ስፍራዎች፣ ስለኢትዮጵያ መልካም ገፅታዎች መረጃ መስጠትና በቀጣይም ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቱሪስቶችን ጨምረው እንዲመጡ ማስቻል ይጠበቅብናል፡፡
የታክሲ፣ የሆቴል እና ሌሎች አገልግሎቶችን የምንሰጥም አካላት የውጭ ዜጋ ሲመጣ ገንዘብ ጭኖ የሚመጣ አድርገን ማሰብ አይገባንም፡፡ የውጭ ዜጋ በሚመጣበት ወቅት ለሱ የምንሰጠው መልካም መስተንግዶ ነገ ይዞ የሚመጣው የተሻለ በረከት በመሆኑ ተገቢው አገልግሎት መስጠት ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011