አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሚታዩትን ግጭቶች ለማስቆም ወጣቱ በውይይት የሚያምንና በምክንያት ላይ የተመሰረተ ሥራ ሊያከናውን እንደሚገባ ተገለፀ፡፡ በሃይማኖት በዓላት ላይ የሚታየውን አንድነትም ግጭቶችን ለመፍታት መጠቀም እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሻለሙ ስዩም፣ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናሩት፤ በአገሪቱ የሚታየውን ግጭት ለማስቆም ወጣቱ የተለያዩ የአገሪቱ ጉዳዮችን በመተንተን ለግጭት ሊያደርስ የቻለውን ነገር በምክንያት ላይ ተመስርቶ በመለየት ችግሮችንም በውይይት መፍታት አለበት፡፡ በሃይማኖት በዓላት ወቅት ወጣቱ የሚያሳየውን መተባበርና አንድነትም የግጭት መፍቻ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ይገባል፡፡
«አሁን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ግፈኛን አውርዶ ሌላ ግፈኛ የማምጣት ነው፤» የሚሉት አቶ ሻለሙ፤ ወጣቱ ውይይት ከማድረግ በተጨማሪ ተቃርኖን ሊቀበል የሚችል ስብዕና ሊገነባ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ አንዱ ያነሳውን ሀሳብ ሌላው እንዲያነሳው መፈለግ የቅራኔ ምንጭ ሊሆን ስለሚችል ወጣቶቹ ሲወያዩ ተቃርኖ ካለ ያንን ተቃርኖ በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ሻለሙ አባባል፤ የኃይል እርምጃ መጠቀም የሚገባው አማራጭ ሲታጣ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ከኃይል እርምጃ በፊት ውይይት ማድረግ እና የተለያዩ መንገዶች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች በውይይት ማመን፤ ምክንያታዊም መሆንና የመረጃ ምንጮቻቸውን መፈተሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የብሄር ፖለቲካ የዘመኑ ሃይማኖት በመሆኑ አንድ አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች የተለያየ ብሄር ስላላቸው ሲጋጩ እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል፡፡ ብሄርተኝነትን በማጠንከር ፖለቲካ ወይም ኢኮኖሚ እና ሌሎች ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ከተለያየ ብሄር የመጡ ሰዎች በአንድ ዓይነት ሃይማኖት ሲኖሩ እንደሚታየ በመጠቆም፤ ይሄንን ማጎልበት ወጣቱ ወደ ውይይት እንዲመጣና ነገሮችን ሰከን ብሎ እንዲያስብ ሲደረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካው ለውጥ ሲስተካከል ፖለቲካ ላይ ያሉ ሰዎች እንዲለወጡ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ሻለሙ፤ ነገር ግን ህዝቡ በተግባር የሚጠቅመው የኢኮኖሚ መደላደል ሲኖር እና በልቶ ያላደረው በልቶ ሲያድር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከብሄር ጋር ማስተሳሰር ሲቆም ለውጦች እንደሚመጡ ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
በመርድ ክፍሉ