የቤት ሠራተኝነት በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ለመሥራት በሕጋዊ ውልና በቃል ስምምነት የሚፈፀም የሥራ መስክ ነው። የቤት ዕቃዎችንና አልባሳትን ማጠብ፣ የቤት ወለልና ጣሪያን ማፅዳት፣ ምግብ ማብሰል፣ መኖሪያ ግቢን ማፅዳት፣ አልጋ ማንጠፍ፣ በመመገቢያ ጊዜ እጅ ማስታጠብና ምግብ ማቅረብ፣ ሕፃናትን መንከባከብና ት/ት ቤት ማድረስ በቤት ውስጥ ከሚሠሩ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ናቸው።
የቤት ሠራተኞች ለሚሰሩት ሥራ ወርሃዊ የደመወዝ ክፍያ ይከፈላቸዋል። ይህ ክፍያ በውል ስምምነቱ ወቅት ከተተመነውና በተለምዶ ሲከፈል ከነበረው ጋር ተነፃፅሮ ይከፈላል። የቤት ሠራተኞች የሥራ ብርታታቸው፣ ቆይታቸውና ሥነ-ምግባራቸው እየታየ ብዙ አሠሪዎች የደመወዝ ጭማሪ ያደርጉላቸዋል።
የቤት ሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎታቸው ከአሠሪዎች ይሟላላቸዋል። ምግብ፣ አልባሳት፣ ሕክምና፣ ትምህርትና መኖሪያ ቤት በአሠሪዎች ከሚሟሉ መሠረታዊ ነገሮች መካከል ናቸው። ይህ አገልግሎት በውል ስምምነት ወቅት በአብዛኛው ባይገለፅም በውስጥ ታዋቂነት ይካተታል።
የቤት ሠራተኝነት በመንግሥት ሕጋዊነት ያለው የሥራ መስክ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ የቤት ሠራተኞች ከአሠሪዎች ጋር በቃል ብቻ ይስማማሉ። በቃል መስማማት ደግሞ ከሥራው ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ አምባጓሮዎች የሕግ እርማት ለመውሰድ አመቺ አይሆኑም። ለምሳሌ፦ ከስምምነት የተተመነው ወርሃዊ የደመወዝ ክፍያ ሳይከፈል ቢቀር በሕግ ለመጠየቅ አይመችም። አሠሪዎችንም ሆነ ሠራተኞች ለሚተላለፉት ሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ሕጋዊ የውል ስምምነት መኖሩ ለአሠራር አመቺ ነው።
የቤት ሠራተኞችና አሠሪዎችን ለማገናኘት በተለምዶ አሠሪና ሠራተኛን አገናኝ ደላላዎች የሚባሉ አሉ። እነዚህ ደላላዎች ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው ሲሆኑ የቢሮ አደረጃጀት አላቸው። የቤት ሠራተኞችና አሠሪዎች የሚፈልጉትን ዓይነት አሠሪና ሠራተኛ ቢሮ መጥተው ያሳውቃሉ። ደላላው ፍላጎታቸውን አይቶ ይጣጣማሉ የሚለውን ገምግሞ የአሠሪና ሠራተኛ ውል ያስገባል። አንዳንዴ አሠሪዎች ዘመዶቻቸውንና ከሚያውቋቸው ሰዎች ጥቆማ የቀረበላቸውን የቤት ሠራተኛ ይቀጥራሉ። ከአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ደላላዎች ውጪ የሚፈፀም ስምምነት በአብዛኛው ሕጋዊነት የለውም። ቢሆንም በዘልማድ የቤት ሠራተኛ የሚቀጥሩ ብዙዎች እንዳሉም ይታመናል።
የቤት ሠራተኝነት የሥራ መስክ በመሆን ለብዙ ሰዎች ብቸኛ የኑሮ መተዳደሪያ ነው። ጥናት ተደርጎ ምን ያል ዜጎች በኢትዮጵያ በቤት ሠራተኛነት እንደሚተዳደሩ ባይታወቅም ለብዙዎች ግን እንጀራ መብያ መሆኑ አይካድም። ብቸኛ የገቢ ማግኛና ቤተሰብ ማስተዳደሪያ የሆነላቸውም ብዙዎች ናቸው። በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው በመስራና በመማር ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ እንዳሉም የሚታወቅ ነው። አንዳንድ ሰፊ ቤተሰብ ያላቸው ግለሰቦች የቤት ሠራተኞች የቤት ሠራተኝነትን እንደ ዋነኛ የሕይወት መስተጋብር ይወስዳሉ። ለዚህም የቤት ሠራተኞች የቤት ሠራተኝነትን እንደ ሥራ አስከብሮ መኖር ላይ አይደራደሩም። በዚህም ሕጋዊነት የሌለው የቤት ሠራተኝነትም ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው አድርጓል።
የቤት ሠራተኞች አንዳንዴ ችግር ፈጣሪዎች ይሆናሉ። ከሥራ ስምምነቱ ውጪ የውል መተላለፍ ያደርጋሉ። ከእነዚህ መካከል፦ ዕቃና ገንዘብ መስረቅ፣ ጠቃሚ ነገሮችን ማባከን፣ በቤተሰብ መካከል ግጭትን መቀስቀስ፣ የዕለት-ተዕለት ሥራዎችን በወቅቱ አለማከናወን እና ብልሹ ሥነ-ምግባር ማሳየት የተለመዱና የሚታዩ ግድፈቶች ናቸው። ቴሌቪዥን ዲሽና ዋይፋይ ያለበት ቤት መሆን አለበት ብለው የሚደራደሩ እንዳሉም ይወራል። ዋነኛ ጉዳያቸው ሥራ ሰርቶ የሚገባቸውን ክፍያ ማግኘት ቢሆንም የወንደላጤ ቤት ካልሆነ አልሰራም፤ ባለትዳር ቤት አልፈልግም የሚሉ አልጠፉም። የእንዲህ ዓነቶቹ ቅምጥል የቤት ሠራተኞች ዓላማ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የቤት ሠራተኞችን የሚያሠሩ አሠሪዎች የበለጠ ችግር ይፈጥራሉ። ከእነዚህ መካከል፦ ወርሃዊ የደመወዝ ክፍያ አለመክፈል፣ ድብደባ መፈፀም፣ ምግብ መከልከል፣ አልባሳት አለመግዛት፣ ንቀት ማሳየት፣ ከቤተሰባዊ ጉዳዮች ማግለል እና ከልክ ያለፈ የጉልበት ብዝበዛ ማከናወን የሚጠቀሱ ግድፈቶች ናቸው። ጾታዊ ጥቃት ማድረስና መደፈርም በብዛት እንደሚደርስባቸው በቤት ሠራተኝነት የተሰማሩ ሴቶች በብዛት የሚገልጹት ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቤት ሠራተኝነት ጋር የተያያዘ አጋጣሚ ለአብነት አንድ ጉዳይ ላንሳ። አንድ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖር ሐብታም ዘመዴ ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ አነሳለሁ። ይህ ዘመዴ ሦስት የቤት ሠራተኞች አሉት። እነዚህ የቤት ሠራተኞች በቤተሰብ አማካኝነት የተገኙ ናቸው። ከድሃ ቤተሰብ የመጡ በመሆናቸው ሃሳባቸው በዚህ ሐብታም ሰውዬ ቤት ረጅም ጊዜ ለመሥራትና ለመኖር ነበር። የእኔ ዘመድ የአምስት ልጆች አባትና ባለትዳር ነው። ባለቤቱ የቤት እመቤት ናት። ባለቤቱ ከቅንጡ ቤተሰብ የተገኙ በመሆናቸው ለቤት ሠራተኝነት የሚሠጡት ግምት በጣም ዝቅተኛ ነው። በዚህም ለሦስቱ የቤት ሠራተኞች ጥሩ ፊት አየሳዩም ለሰውነታቸው እንኳን ተገቢው ክብር የላቸውም። አንድ ቀን ማታ ላይ ወ/ሮ ስህን እግራቸውን ሳይታጠቡ የሳሎኑ ሶፋ ላይ ተኝተው ነበር። ወ/ሮ ስህን ከእንቅልፍ ሲነቁ አንድ ነገር ተገነዘቡ። በእንቅልፍ ላይ ሳሉ የቤት ሠራተኞች እግራቸውን አለማጠባቸው። በዚሁ ተናደው የቤት ሠራተኞችን ሙሉ ለሙሉ ከቤት አባረሯቸው። የቤት ሠራተኞችም ወርሃዊ ደመወዛቸውን ሳይቀበሉ ጓዛቸውን ሸክፈው ተሰናበቱ።
የቤት ሠራተኞች በምሽት ከቤተሰብ አርፍደው ይተኛሉ። ቀድመውም ከእንቅልፍ ይነሳሉ። ቤተሰብ ከተመገበ በኋላ ምግብ ይመገባሉ። ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ አይበረታቱም። ትምህርት እንዲማሩም አይበረታቱም። አቤቱታ ካላቸው አይደመጡም። ባላቸው የኑሮ ደረጃ ፍትሃዊ ቦታ አይሰጣቸውም። ከላይ እንደጠቀስኩት የቤት ሠራተኝነት ብዙ ጣጣዎችን ይዟል።
ይሁን ሥራው ካለው ፋይዳ አንጻር በሕግ ቢደገፍና በአሠሪዎችና ሠራተኞች መካከል ሚዛናዊ የሆነ ሕግ ወጥቶለት ሁለቱንም ወገኖች በፍትሃዊ የሚዳኝ ቢሆን እንደአገር ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ሥራው በቂ ትኩረት እንዲያገኝ ማስቻል፣ የቤት ሠራተኞች ማህበር ማቋቋም፣ የሕግ ማዕቀፍ መቅረፅ እና ስለሥራው ግንዛቤ ማስጨበጥም በደንብ ሊሰራባቸው የሚገቡ ሁነኛ መፍትሄዎች ናቸው እላለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
በላይ አበራ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ