
አንድነት ፓርክ በመኪናም ሆነ በእግር የሰርክ መመላለሻ መንገዴ ስለሆነ ትኩረቴን በብዙ ነገሮቹ ይስበዋል። ትኩረቴን ከሚስቡት አንዱ የጎብኚዎቹ መበራከት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ፓርኩ በተለይ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በመዲናችን አዲስ አበባ ሌሎች የጉብኝት ስፍራዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነበት ሁኔታ ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ ከኢኮኖሚ አኳያ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩና የገቢ ምንጭ መሆኑ ነው።
በታሪካዊ ፓርክነቱ ለመዲናችን የበኩር ልጇ የነበረው አንድነት ፓርክ የሚጎበኝበት ሦስት ወቅቶች አሉ። እነሱም ትምህርት ቤት የሚዘጋበት የክረምት ወቅት፤ ካላንደር የሚዘጋባቸው የበዓላት ወቅት እንዲሁም አብዛኞቻችን ሥራ የማንገባባቸው ቅዳሜ እና እሁድ የእረፍት ቀናት ናቸው።
በተለይ በነዚህ ቀናት የፓርኩ ጎብኚዎች ቁጥሩ በብዙ መጠን ይጨምራል። አካባቢው በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይጨናነቃል። ከ12 ሄክታር በላይ በተንጣለለ መሬት ላይ የሰፈረው ጊቢውማ ሰው በሰው ነው የሚሆነው። ከፓርኩ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በበዓላትና ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ ፓርኩን እስከ ሦስት ሺ የሚደርሱ ዜጎች ይጎበኙታል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በዘንድሮ በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች ብቻ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በሚጠጉ ዜጎች ተጎብኝቷል። ከነዚህ ዜጎች መካከል 28 ሺህ የሚሆኑት ጎብኚዎች ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የውጭ ዜጎች ናቸው። ፓርኩ ቀድሞ በመዲናይቱም ከነበሩት የመዝናኛ ስፍራዎችም ሆነ በኋላ እሱን ተከትለው ከኮሪዶር ልማት ጋር በመያያዝ ለጉብኝት ክፍት ከሆኑት የመዝናኛ ስፍራዎች በብዙ በመለየቱ የጎብኚው ቁጥር እየጨመረ ነው።
ለአብነት ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራት ፓርኩን ከጎበኘው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ጎብኚ አፈፃፀም ከዘንድሮ፤ ዘጠኝ ወር አፈፃፀም ጋር ስናነጻጽረው የዘንድሮው ጎብኚ መጠን ከመቶ ሺ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። ፓርኩ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሥነሥርዓት ተመርቆም ለአገልግሎት ክፍት የሆነበት ሰሞንም ቢሆን ፓርኩን በየእለቱ ከአንድ ሺ ሰው በላይ ይጎበኘው እንደነበር ከፓርኩ አስተዳደር የወጣ መረጃ ያመላክታል። ከነዚህ ወቅቶች ባሻገር በሰርክ ቀናቶችም ቢሆን በእያንዳንዱ ቀን ከሺ በላይ ሰዎች የሚጎበኝ ስለመሆኑም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
መዲናችን አሁን በቁጥር አንዱና በቀዳሚው በዚህ አንድነት ፓርክ ብቻ የዚህን ያህል ቁጥር ያለው ዜጋ መያዝ የሚችል መዝናኛ ስፍራ ማግኘቷ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስፍራው ለዓይን ሳቢ፤ ማራኪ፤ ብዙ እውቀት የሚቀሰምበት ታሪካዊ ከመሆኑ አንጻር አበርክቶውም ቢሆን ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በተለይ በውስጡ የሚገኙት ታሪካዊ ቅርሶች በሌሎች ሥፍራዎች የማይገኙ መሆናቸው ፓርኩን የተለየ እና ተመራጭ ያደርጉታል።
ፓርኩን ተመራጭ ከሚያደርጉት መካከል በውስጡ የያዛቸው ሦስት ዓይነት የቱሪስት መስሕቦች ዋንኞቹ ናቸው። ዘመን ተሻግሮ ዛሬ ላይ መድረስ የቻለው ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር ከነበራት ግንኙነት ጀምሮ፤ ታሪካዊው ቤተ መንግሥት በራሱ አንዱ መስሕብ ሲሆን በውስጡ የዓፄ ምኒልክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽሕፈትን ቤት ይዟል።
በተጨማሪም ከዓፄ ምኒልክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት፣ ንጉሥ ምኒልክ እንግዶቻቸውን ያስተናግዱበት የነበረው የምኒልክ የግብር አዳራሽ እንደዚሁም ከ1880ዎቹ ጀምሮ የተገነቡ የነገሥታት መኖሪያ እና ጽሕፈት ቤቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ዓፄ ምኒልክ ከጦር መኮንኖቻቸው ጋር የሚገ ናኙበት ክፍል፣ የዓፄ ምኒልክ የጦር ሚኒስትር የነበሩት የፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) መኖሪያ ቤት፤ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነገሥታትን እና የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶችን ተቀብለው ያስተናግዱበት የነበረ የዘውድ ቤት ሌላው መስሕብ ነው። ባህል፣ ምጣኔ ሀብት እና የሕዝቦችን አኗኗር መሠረት በማድረግ የተገነባው የብሔር ብሔረሰቦች ማንነት የሚንፀባረቅበት ስፍራም በዚሁ ፓርክ ውስጥ ይገኛል።
ይሄን ሁሉ ብለውም ከውጭ ዜጎች ታሪክ ፀሐፊዎች፤ ጋዜጠኞች፤ ተመራማሪዎች፤ የሀገር መሪዎች፤ የፖለቲካ እና የከፍተኛ ትምህርት ምሑራን አመራሮች አብዝተው ይጎበኙታል። ወላጅ ልጆቹን፤ ቤተሰቡን በሙሉ በመያዝ ወደ ፓርኩ ይጎርፋል። በተለይ የሀገር ውስጥ ጎብኚው ዜጋ ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጣ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ የተለያዩ ተቋማት ሠራተ ኞች፤ ወጣቶች፤ በጋራ ወደ ፓርኩ ይሄዳሉ። በተለይ የጋራ መኖሪያ አካባቢ ያሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች የጋራ ጉብኝት ልምዱን ቢያሰፉት ይመረጣል። አሁን ፓርኩ ወዳጅነት ቁጥር አንድ፤ ወዳጅነት ቁጥር ሁለት እንዲሁም የሳይንስ ሙዚየም፤ አንድነት መኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) በመያዝ ወደ አምስት አድጎ ሰፍቷል።
በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ እስካሁን የተከናወኑ እና እየተከናወኑም ያሉ እጅግ ለዓይን ማራኪና ሳቢ የኮሪዶር ሥራ ውጤቶች በሙሉ በአንድነት ፓርክ ከተቀመረ ተሞክሮ የተገኙ ፍሬዎች ናቸው። ፓርኩ በክልሎች ለሚሠሩ የቱሪዝም ሥራዎች ጭምር እንደ ተሞክሮ መቅሰሚያ ተብሎ በገበታ ለሸገር በኩል እየተስፋፋ በመምጣት፤ በገበታ ለሀገር እያለ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጥቶ ከፓርክም በላይ ያለውን የተሞክሮ መቅሰሚያነት ፋይዳ ያስመሰከረ ነው።
ከአንድ ወደ አምስት በማደግ እንደመስፋቱ የሚከተሉት የሙስሊምም ሆነ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና የፕሮቴስታንት ሃይማኖት እምነት ሳይገድባቸው በርካታ ሙሽሮች በአምስቱም ፓርኮች የመስክ ፎቶ እየተነሱ ሠርጋቸው ያስውባሉ። የሠርግ ሥነ- ሥርዓታቸውንም እንደ ባህል እና ወጋቸው ለማክበር የሚያስችላቸው የበዓል ዝግጅት ያደርጋሉ።
አሁን ላይ በመዲናችን ፓርኩ ከመዝናኛነት በዘለለ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ወደ ሥራ በገባበት ሰሞን ብቻ ለ170 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን መረጃዎች ያሳያሉ። አሁን ላይ በፓርኩ ለዜጎች የተፈጠረው የሥራ ዕድል በእጅጉ ልቆ ወደ ሺዎች መግባቱ ይነገራል። 1 ሺ 30 መኪኖች ማቆም በሚያስችለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ብቻ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበሩትን ሥራ አጥ ወጣቶች በሙሉ ሸክፎ ይዟል። አዳዲስ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ የሆኑ ወጣቶችንም የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ አድርጓል።
ፓርኩ ከገቢ ምንጭነት አንፃርም እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ እጅግ ጉልህ ነው። ወደ አምስት አድጎ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ተብሎ ከመጠቃለሉ በፊት በአንድነት ፓርክ ስም እያለ ብቻ ያስገባው ገቢ ምስክር ነው። የፓርኩ ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን እንዴውም ገቢውም ለሌሎች በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ መስሕቦች ግንባታም እየተረፈ እንደሆነም ይነገራል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለጉብኝት ክፍት ከሆነ ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ 66 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር አስገብቷል። ከዚህም በላይ ፓርኩ በዜጎች ጤንነት፤ መልካም አስተሳሰብ እና በሀገርና አካባቢ ግንባታ ላይ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ወጪው ከገቢው በብርቱ የላቀ እንደሆነ ይነገራል።
ለፓርኩ ሠራተኞች ደመወዝ የሚያወጣው ወጪ ሳይታሰብ ፓርኩን እና አካባቢውን ለማስዋብ፤ ለእንስሳት ምግብ እንዲሁም ሕክምና የሚያወጣው ወጪ እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህም ሆኖ ከትንሽ ጊዜ በኋላ እሱም በሌሎች ባደጉ ሀገሮች እንዳሉት ፓርኮች ሁሉ ከኢኮኖሚ አንፃር ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተተንብዮለታል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም