የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጤናና ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ቀውስ ከፍተኛ ነው። በሌሎች ማህበራዊ ክንውኖች ላይም ተጨማሪ ብዙ ምስቅልቅል እየፈጠረ ነው። በመዝናኛ እና በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይም እያሳደረ ያለው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነዚህ ሥራዎች መዝናኛ የሚሆኑት ለእኛ ለታዳሚዎች እንጂ ለሰሪዎች የህልውና ጉዳይ ናቸው፤ መደበኛ ሥራዎቻው ናቸው። የገቢ ምንጫቸውም በእነዚህ መደበኛ ሥራዎቻቸው ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እነዚህን ሥራዎች ለመከወን ደግሞ ከፍተኛ የገንዘብ እና የሰው ኃይል ወጪ ይጠይቃሉ።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የእነዚህ ባለሙያዎች ሥራ ላይ መጋረጃውን ጥሏል። አጀንዳ አስቀይሯል። ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎች ሳይቀሩ በከፍተኛ አድናቆት እየተዋወቁ በነበሩበት ሁኔታ ድንገት እንዲረሱ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ በወርሃ የካቲት የዳዊት ጽጌ ሙዚቃ መነጋሪያ ሆኖ ነበር። አጀንዳ የሆነበት ምክንያት በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲወቀስ የነበረውን ነገር በመሰባበሩ ነው። ዘፈኖቹ የኮምፒዩተር ፈጠራ እስከሚመስሉ ድረስ የዘፋኞች ድምጽ የማይታወቅ ሆኖ ነበር። በዚያ ላይ ማታ ተሰምቶ ጠዋት የሚረሱ ዘፈኖች በዝተው ነበር። በባላገሩ አይዶል የመድረክ ታዳሚዎችን ብቻ ሳይሆን በየቤቱ ሆኖ ቴሌቭዥን የሚከታተለውን ሁሉ ያስጨበጨበው ዳዊት ጽጌ፤ አልበም ይዞ ሲመጣ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ነበር።
ዳዊት በሚወዳደርበት ጊዜ አንደኛው ዳኛ የተናገረው ትዝ አለኝ። ‹‹እስኪ የምንገመግመው ሳይሆን ዝም ብለን የምንሰማው አንድ ዝፈንልን›› ብሎት ነበር። በችሎታው ተደምሞ ማለት ነው። በዚህ የዳዊት ዘፈን አፍላነት ውስጥ ነው የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን የገባው።
ሌላኛውና በዝርዝር የምናየው የኮሮና ወረርሽኝ የጋረደው እንሳሮ ፊልም ነው። የአገራችን ፊልም ችግሩ የሰሪዎች ብቻ አይደለም፤ የተመልካቹም ጭምር ነው። ተመልካቹ ሲባል የግድ ሲኒማ ቤት ገብቶ የሚያየው ሳይሆን በአጠቃላይ ፊልም ተመልካች ነኝ የሚለውን ማለት ነው። በዚህ በኩል ስርቆትን ያወግዛል፤ በዚያ በኩል ራሱ ይሰርቃል። መስረቅ ማለት የግድ በራስ እጅ መስረቅ አይደለም። የተሰረቀውን መጠቀም ወይም እያዩ ዝም ማለት እንደ ስርቆት ይቆጠራል።
‹‹እንሳሮ›› ፊልም ገና ከመውጣቱ ተሰረቀ። አንድ ፊልም ለመሥራት ምን ያህል ገንዘብና ጊዜ እንደሚወጣበት ለማወቅ የግድ የፊልም ባለሙያ መሆን አይጠይቅም። ለዚያውም እንደ እንሳሮ አይነት ከአዲስ አበባ ውጭ የሚሰራ ፊልም ደግሞ ብዙ ገንዘብ፣ ጊዜ እና የሰው ኃይል ይወስዳል። የፊልሙ ታሪክ ከአዲስ አበባ እስከ እንሳሮ ይዘልቃል። እንሳሮ ከገባ በኋላ በረሃ ውስጥ ነው የሚገባው። ገደል እና ዋሻ ይበዛበታል። በዚያ ቦታ ላይ እንኳን ፊልም አንድ ዘገባ እንኳን ለመሥራት ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
ፊልሙ የተሰረቀው ምንአልባትም ወቀሳ ከሚበዛባቸው ፊልሞች ለየት ያለ ስለሆነ ይመስላል። የኢትዮጵያ ፊልሞች የሚወቀሱት ከጭፈራ ቤትና ከቪላ ቤት አይወጡም በሚል ነው። እንዲህ ወጣ ያለ ፊልም ሲገኝ ደግሞ ፈተና ብዙ ነው ።
‹‹እንሳሮ›› ሲልም በ‹‹ዩ ትዩብ›› ብዙዎች አጭበርብረውበታል። እንደሚታወቀው በዚህ ዘመን ‹‹ዩ ትዩብ›› ገንዘብ መሰብሰቢያ ሆኗል። ገንዘብ የሚከፈላቸው በሚያገኙት ተመልካች (Views) መጠን ነው። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ርዕስ የሚያጮሁት። ርዕስ የማጮሁ ነገር ሲነቃባቸው አሁን ደግሞ ሌሎች አማራጮች የጀመሩ ይመስላል።
‹‹የተሰረቀው እንሳሮ ፊልም›› ተብለው የተጫኑ ብዙ ናቸው። በዚህ ሀሰተኛ ስም ከአሥር በላይ “ ዩ ትዩቦች” አይቻለሁ። በሁሉም ውስጥ ፊልሙ የለም። በፊልም የደቂቃ ልክ ተጭነው ሲከፈት ግን ሌላ ነገር ነው የሚያወሩት። አንዳንዶቹም ከዚህ በፊት የታዩና የቆዩ ፊልሞችን ናቸው። ዋናው ነገር ሰዎች ሰፍ ብለው እንዲከፍቱት ነው። ከከፈቱት ደግሞ ባይጨርሱትም የተመልካቹ መጠን ይጨምራል። ከከፈቱት በኋላ እንግዲህ ቢነዱ ቢጨሱ የተመልካች ቁጥሩ መጨመሩ አይቀሬ ነው።
እንሳሮ ፊልም ሁለት ጊዜ በደል ደረሰበት ማለት ነው። ብዙ የፊልም አድናቂዎች ‹‹ይሄ ምርጥ ሥራ ቢሰረቅም ሲኒማ ገብተን በማየት መካስ አለብን። እንዲህ አይነት ፊልም ሰሪዎችን በማበረታታት ሞራል በመስጠት ሌሎች ሰሪዎችን መፍጠር አለብን›› ብለው ነበር። ብለውም አልቀሩም የሚመረቅበትንና የሚታይባቸውን ሲኒማ ቤቶች በጉጉት መጠበቅ ጀመሩ። ፊልሙ መጋቢት 3፣ 4፣ 5 እና 6 ተመርቆ መታየት ጀመረ። መጋቢት 4 ቀን የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ገባ። መንግስት በእንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ጣለ። እንኳን መዝናኛ ቤቶች የዕለት ጉርስ የሚሰራባቸው ቦታዎችም በከፍተኛ ጥንቃቄ ሆኑ። የእንሳሮ ፊልም ኪሳራውን ሳያካክስ ዳግም ፈተና ገጠመው። ለማንኛውም የሆነው ሆኗል ወደ ፊልሙ እንግባ።
ፊልሙን የምናየው በፈጣን የወፍ በረር ነው። በጥልቀት ለማየት ፊልሙን ደጋግሞ ማየት ይጠይቃል። እንሳሮ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኝ ወረዳ ነው። የፊልሙ ታሪክ ከአዲስ አበባ እስከ እንሳሮ ስለሆነ በከተማ እና በገጠር መካከል ያለውን ግንኙነት ከነባራዊው ዓለም ጋር እናስተያየው።
የከተማ እና የገጠር ህይወት አንድነትም ልዩነትም አለው። አንድነቱ፤ ሁለቱም የተሳሰሩ ናቸው። የከተማ ነዋሪዎች ሥር – መሰረታቸው ከገጠር ነው። ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገጠር ውስጥ ዘመድ አላቸው። በሌላ በኩል ገጠር ውስጥ ተወልደው ያደጉ ወጣቶች ትምህርት እንደጨረሱ የሚመጡት ወደ አዲስ አበባ ነው። በእንሳሮ ፊልም ውስጥም ይህ አይነት ታሪክ ነው ያለው። ህይወቱ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ፤ ከዚያም ከአዲስ አበባ ወደ ገጠር ትመላለሳለች። የእሱ ህይወት ለከተማ የሥራ ባልደረባውም ይተርፋል።
ፊልሙ የአካባቢውን ገሃዳዊ አኗኗር ያሳያል። በተለይም የሴትን ልጅ ጀግንነት ያሳያል። ብዙ ጊዜ የሴት መብት የሚረገጠውና የሚጨቆነው ገጠር ውስጥ ይመስለናል። ዳሩ ግን ገጠር ውስጥ ሴት ወንድ የሰራውን ሁሉ ትሰራለች። የግብርና ሥራ እኩል ነው የሚሰሩት።
በእንሳሮ ፊልም ውስጥ ሴቷ ክላሽ ታጥቃ ጠላት ፍለጋ በረሃ ለበረሃ በዋሻና በገደል ስትወጣ ስትወርድ ይታያል። በፊልሙ አውቶማቲክ ስትተኩስ ልቦለድ ሊመስለን ይችላል። በፊልሙ ላይ ልቦለድ ይሁን እንጂ እውነታው ግን የአካባቢው ገሃዳዊ ህይወት ነው። ራሴው ያስተዋልኩት አንድ እውነተኛ ታሪክ ልንገራችሁ።
እዚያው ሰሜን ሸዋ ውስጥ ነው። እንደሚታወቀው በብዙ የገጠር አካባቢዎች ሰው ሲሞትና ሌሎች አደጋዎች ሲፈጠሩ ጥይት መተኮስ የተለመደ ነው። የሚተኮሰውም ለፀፀት እና ሰዎች እንዲሰባሰቡ ነው።
እናም በአንደኛው የገጠር አካባቢ ውስጥ አንድ ታማሚ በድንገት ለሞት ማጣጣር ጀመረ። ህመሙ ውሎ ያደረበት ስለሆነ የተለመደው ነው ብለው ሰዎች በየሥራቸው ሄደዋል። ወንድ በአካባቢው የለም። ታማሚው በድንገት አረፈ። በአካባቢው ወግና ባህል ጥይት መተኮስ አለበት። ‹‹ምን ይሻለናል!›› እያሉ ሲጨነቁ አንደኛዋ ሴት ወጣ አለች። የባሏን ክላሽ አንስታ መጣች። ‹‹ኧረ ትፈጅናለሽ!›› እያሉ ሲንጫጩ የጥይቱን ካዝና አስገብታ አከታትላ ተኮሰች። ጥይቱን ሰምተው ሰዎች ተሰባሰቡ። ሌላ ቀን ስትጠይቅ ባሏ ሲፈታታና ሲገጣጥም ልብ ብላ ታየው እንደነበር ተናግራለች።
ጠመንጃውን ከጥይት ጋር ያገጣጠመችው ራሷ ናት። ወንዶች መሳሪያ ሲያስቀምጡ ጥይቱንና ጠመንጃውን ለያይተው ነው። ምክንያቱም ልጅ እንኳን ቢያገኘው እንዳይተኩስ ነው። ጥይቱ የተቀመጠበትን ታውቀው ስለነበር አውጥታ ገጣጠመችው።
እንግዲህ አስቡት! ይቺ ሴት መተኮስ የቻለች (ለዚያውም ያስቸግራል የሚባለውን አውቶማቲክ ክላሽ) በማየት ብቻ ነው። እንዲህ አድርጊ ተብሎ እንኳን ልምምድ ተሰጥቷት አያውቅም። ወንድ ነው መተኮስ ያለበት ለሚባለው ራሱ ለጀማሪ ወንድ አይሰጥም ነበር። ምክንያቱም ጥይት ሲተኮስ ከፍተኛ ንዝረት ስለሚወጣ መሳሪያው ከእጅ ላይ ሊያመልጥ ይችላል፤ አውቶማቲክ መሳሪያ አመለጠ ማለት ደግሞ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ለከፋ አደጋ አጋለጠ ማለት ነው። ይቺ ሴት ግን በማየት ብቻ ያለምንም እንከን በሚፈለገው ልክ ተኩሳ የወጉን አደረሰች።
ሰርግ ላይ ከወንድ ላይ ተቀብለው የተኮሱ ሌሎች ሴቶችንም አስተውያለሁ። እነዚህን ገጠመኞች ያነሳኋቸው ያለምክንያት አይደለም። በፊልሙ ላይ ያለችው የገጠር ገጸ ባህሪ ክላሽ እየፈታታች ስትገጣጥም፣ ከከተማ ለሄደው ወንድ አተኳኮስ እና አነጠጥሮ መምታት ስታለማምደው ልቦለድ ብቻ እንዳይመስል ብዬ ነው። ሴት ወታደሮችንና ታጋዮችን ምሳሌ ያላደረኩት እነርሱ ልምምድ ስለሚሰጣቸው ነው። ሴቶች አስተዋይና አገናዛቢ መሆናቸውን የምንረዳው ያለልምድ በማስተዋል ብቻ የሚሰሩትን በማየት ነው። በትግል ታሪክ ውስጥ የነበሩትን ሴት ተኳሾች እንዘርዝር ከተባለ የትየለሌ ነው።
በነገራችን ላይ የሴት ጀግንነት የሚገለጸው ጥይት በመተኮስ ነው ለማለት አይደለም። ዳሩ ግን ጀግንነት ሲባል ብዙ ጊዜ ለወንዶች ስለሚሰጥና ጀግንነት ማለትም ከተኳሽነት ጋር ስለሚያያዝ ነው። በዚህኛው ትርጉምም ቢሆን ጀግና ናቸው ለማለት ነው።
ሌላው በፊልሙ ውስጥ የምናየው ነገር ለሴት የሚሰጠውን ክብር ነው። በአካባቢው ደም መመላለስ የሚባል አጉል ልማድ አለ። በዚህ ደም የመመላለስ ልማድ ውስጥ፤ ለምን የጠላቱ እናት አትሆንም ሴት መግደል ፈፅሞ አይታሰብም። እንግዲህ ለጠላት እናቱን ከመግደል በላይ በቀል አልነበረም። ከእናቱ ሞት በላይ የሚያናድደው ነገር አይኖርም፤ ግን ፈፅሞ አይደረግም! ፊልሙ ይሄን እውነታ ነው ያሳየን። በፊልሙ ላይ ሴቷን የገደላት በስህተት ነው። የገደላት ደግሞ የወንድ ልብስ ለብሳ ስለነበር ወንድ መስሎት ነው። እሷ መሆኗን ሲያውቅ እጅግ ይፀፀታል።
ሌላው እውነታ ደግሞ ይሄኛው ነው። ከአዲስ አበባ ከሄዱት ጋዜጠኞች አንደኛዋ ሴት ናት። የካሜራ ባለሙያዋ አባቱ ሰው ገድሎ ስለነበር አባቱ የሞተበት ሰውዬ ከአዲስ አበባ መምጣቱን ሰምቶ እየፈለገው ነው። በዚህ አጋጣሚ ምንም የማታውቀው ከተሜዋ ጋዜጠኛ ታገተች። የታገተችው ዋሻ ውስጥ ነው። እዚያ ዋሻ ውስጥ፤ እንኳን አስገድዶ መድፈር ከነ ሕይወቷ ቢቀብራት ራሱ የሚያይና የሚሰማ የለም። የጦር መሳሪያም ሆነ ሌሎች ስለታማ ነገሮች በእጁ ናቸው። ግን አላደረገውም። ሴት ናት ብሎ ተንከባክቦ ነው የያዛት። የያዛትም ለተፈላጊው ፍቅረኛው ወይም ሌላ የቅርብ ዘመዱ መስላው ነው። እንዲያውም ዋሽንት ተጫወትልኝ እያለች በዋሽንት ያጫውታታል። ከዚያ በኋላ የሆነው ነገር አስገድዷት ሳይሆን በራሷ ፍላጎት ነው። አስቀድማ የሳመችውም እሷው ናት።
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ የፊልሙ ታሪክ በሚገባ አልተዳሰሰም። በውስጡ ብዙ ሌሎች ታሪኮች አሉት።
እንዲህ አይነት ፊልሞች ናቸው አገርን የሚያስተዋውቁ። ኢትዮጵያ ማለት በመጠጥ፣ በሴሰኝነት እና በጭስ ብቻ የሚኖርባት አይደለችም። የባላገሩ ህይወትም ድምር ናት። ሴት ወደ ማጀት ወንድ ወደ አደባባይ የሚባልባት ብቻም አይደለችም። ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች የተዋጉ ጀግና ሴቶች ያሏት ናት። እንዲህ አይነት የአገር ባህልና ታሪኮች ለዓለም የሚተዋወቁት በፊልም ነው። የእንሳሮ ፊልም ሰሪዎች የገንዘብ ኪሳራ ቢደርስባቸውም የጥበብ ትርፍ ግን አግኝተዋል። እንዲህ አይነት ፊልም ሰሪዎችን ያብዛልን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ