* የመሬት ወረራ ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታጥሮ የተያዘና ለረጅም ጊዜ ሳይለማ የቆየ 1 ሚሊዮን 383 ሺህ 223 ካሬ ሜትር ቦታ ማስመለሱን የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡ በከተማዋ አሁንም የመሬት ወረራ መኖሩን ቢሮው አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን ግርማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ አግባብ የተያዙና ለረጅም ጊዜ ወደ ልማት ሳይገቡ የቆዩ 143 ቦታዎች ይገኛሉ፡፡
ቢሮውም በቅድሚያ የተለዩትን ቦታዎች የሊዝ ውል የማቋረጥ ሥራ የሠራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 90ዎቹ በቀጥታ ቦታዎቹ ፈርሰው ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የቀሩት ደግሞ በቅሬታ ላይ ያሉና ተለይቶ መፍትሔ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡
ቦታዎቹ ከ10 ዓመታት በላይ ታጥረው የቆዩ በመሆናቸው በተያዘላቸው ጊዜ ቢለሙና አገልግሎት ላይ ቢውሉ በኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ላይ የሚኖራቸው አወንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ቦታዎቹ ሳይለሙ በመቆየታቸው በህዝብ ላይ እንዲሁም በመንግሥት ላይ ያደረሱት ኪሳራ ሰፊ እንደሆነ የተናገሩት ኢንጂነር ሚሊዮን፤ ምንአልባት በገንዘብ ለማስቀመጥ ቢያስቸግርም ይህን ያክል ሰፊ መሬት ለረጅም ዓመታት አጥሮ ማቆየቱ የሚያመጣውን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡
ቦታዎቹ ለቀጣይ በምን ዓይነት ሥራ ላይ መዋል እንደሚኖርባቸው በከተማ አስተዳደሩ በኩል እየተወሰነ ለላቀ የሕዝብ ጥቅም ሊውሉ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚወሰንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የትኛው ቦታ ለምን አገልግሎት በዘላቂነት ቢለማ የተሻለ ይሆናል የሚለው ገና እየታየ ነው ያሉት ኢንጂነር ሚሊዮን ይህ ተወስኖም መሬት በሚተላለፍበት መንገድ መንግሥት የሚያለማው ከሆነ ለመንግሥት አልያም በግለሰብ ኢንቨስተር የሚለማ ከሆነ ለእነርሱ የሚተላለፍበት ዕድል እንደሚፈጠርና ይህም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ተወስኖ በቀጣይ ወደ ሥራ እንደሚገባበትም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን ቦታዎቹ በከተማ ውስጥ ያለውን የተሽከርካራ ማቆሚያ ችግር ለመቅረፍ እየዋሉና በትክክልም መፍትሄ መስጠት መቻላቸውን የተቆሙት ኢንጂነር ሚሊዮን ወጣቶችም ተደራጅተው ፓርኪንግ እየሰሩ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንና ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ አንፃርም ትልቅ ድርሻ እንዳበረከቱ መመልከት ተችሏል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የሕገወጥ መሬት ወረራ አሁንም ቢሆን ለከተማ አስተዳደሩ የራስ ምታት እንደሆነ ኢንጂነር ሚሊዮን ጠቁመዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል አስተዳደሩ ቁርጠኛ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት በየክፍለ ከተማው እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የማስፋፊያ አካባቢዎች በሚበዛባቸው ቦሌ፣ አቃቂ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የካ እንዲሁም ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ችግሩ በስፋት መኖሩን የጠቆሙት ኢንጂነር ሚሊዮን በነዚህ አካባቢዎችም ሕገወጥነትን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ ግን የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት እርምጃ በወሰደበት አግባብ በሕገወጥ መንገድ የሚያዙ ቦታዎችም ላይ ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት ይንቀሳቀሳል ያሉት ኃላፊው የመሬት ወረራ ችግሩ ሰፊ ቢሆንም ችግሩን ለማቃለል የከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ የሆነ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ቅድሚያ የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና በተቀናጀ መንገድ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ስለሆነም በተመሳሳይ መንገድ መሬት ወረራ እየተደረገ መቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ አይኖርም፤ በዚህ መሠል ድርጊት ተሳታፊ አካላትን በሕግ ተጠያቂ የማድረጉና እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማሻሻያ እየተደረገበት ያለው የሊዝ አዋጅም የነበሩ ችግሮችን ትርጉም ባለው ሁኔታ እንደሚያቃልልና አዋጁ ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ ችግሮች ለመቅረፍ መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሊዝ አዋጅ 721/2004 ተግባራዊ ተደርጎ ሲሰራበት በነበረባቸው ጊዜያትም የነበሩ ጉድለቶች መሰብሰባቸውንና በአተገባበር ሂደት አዋጁ የለያቸው፣ ሊታረሙ የሚገቡና ያልተሟሉ ነገሮችን በማካተት አዋጁን የማሻሻል ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
በፍዮሪ ተወልደ