አለማችን ባልጠበቀችው ወቅትና መጠን በኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጤናዋ ከተቃወሰና ልትፋለመው አቅም አንሷት ነዋሪዎቿዋን አሳዛኝ በሆነ መልኩ መነጠቅ ከጀመረች አምስተኛ ወሯን አስቆጥራለች።የጤናው ዘርፍ ጠቢባን ብሎም የምርምር ተቋማትም የሰው ልጅ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ ለከተተው ወረርሽኝ መድኃኒትና ክትባት ፍለጋ ሌት ተቀን መዳከራቸውን ቀጥለዋል።
አገራት የተቃጣባቸውን የቫይረስ ወረራ ለመ ከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ ከሆነላቸውም ድል ለማድረግ መፍትሄ ይሆናል የሚሉትን በተቻላቸው አቅም ከመሞከር አልቦዘኑም።ይህ የቁጥጥር ጥረት የወረርሽኙን ስርጭትና ጉዳት ከመከላከልና ከመቀነስ ትሩፋቱ ባሻገር በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራን መፍጠሩ አልቀረም።
ኮቪድ 19ኝን ለመከላከልና ለመግታት የተላለፉ ውሳኔዎች ከሁሉ በላይ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን ያደረገውን የዓለም ኢኮኖሚ በእጅጉ አናግተውታል። ቀውሱ ለበርካታ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት መዘጋት ብሎም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ አሊያም በከፊል ስራ ማጣት ምክንያት ሆኖ ታይቷል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከትውልድ አገራቸው ርቀው ባህርማዶ የሚኖሩ ዜጎች ስራ አልባ መሆንም፣ ሌት ከቀን ሰርተው አቅማቸው በፈቀደ ወደ ቤተሰብና አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ በእንግሊዝኛ አጠራሩ (remittance) ገቢን በእጅጉ ቀንሶታል።
ከቀናት በፊት ይፋ የሆነው የአለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ አመት በአለም አቀፍ ደረጃ ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እንደሚቀንስ ማረጋገጫን ሰጥቷል። ‹‹የገንዘብ መጠኑ በመቶኛ ሲወራረድም በሃያ በመቶ ዝቅ ይላል›› ብሏል።
ባለፈው አመት ከመላው አለም ወደ ደሃ፣ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት የተላከው የገንዘብ መጠን ማለትም 554 ቢሊዮን ዶላር፣ በታሪክ ከፍተኛና በክብረወሰን ደረጃ የተቀመጠ መሆኑን ያስታወሰው የባንኩ መረጃ፤ ይህ አሃዝ ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ተፅእኖ ወደ 445 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ እንደሚልም አሳውቋል።
የባንኮች መረጃ ፣ ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ተፅእኖ በአለምአቀፍ ደረጃ ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በአውሮፓና በመካከለኛው እስያ በ27 ነጥብ 5 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት በ23 ነጥብ 1 በመቶ፣ በደቡብ እስያ በ22 ነጥብ 1 በመቶ፣በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ በ19 ነጥብ 6 በመቶ፣በላቲን አሜሪካና በካረቢያን የ19 ነጥብ 3 በመቶ እንዲሁም በምስራቅ እስያና በፓስፊክ በ13 በመቶ ዝቅ እንደሚል አመላክቷል።
ባሳለፍነው አመት የሁለት ነጥብ ስድስት በመቶ እድገት አሳይቶ የነበረው የመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ቀጣናም ዘንድሮ በ19 ነጥብ 6 በመቶ ወይንም በ47 ቢሊየን ዶላር እንደሚቀንስ ተጠቁማል።ባሳለፍነው አመት የዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ እድገት ያስመዘገበውና 48 ቢሊየን ዶላር ሆኖ የተመዘገበው ከሰሃራ በታች ወደሚገኙ አገራት የሚላክ ገንዘብ ዘንድሮ በኮሮና ምክንያት በ23 ነጥብ አንድ በመቶ ወይንም 37 ቢሊየን ዶላር ዝቅ እንደሚል ተመላክቷል።
ደሃ፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወደ አላቸው አገራት የሚላከው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከተለያዩ አካላት ከሚሰጡ እርዳታዎች በሶስት እጥፍ የገዘፈ ስለመሆኑ የሚጠቁመው የዘጋርዲያኑ ፊልፕ ኢንም፣ይህ በሆነበት ሁኔታ ወደ አገራቱ የሚላከው ገንዘብ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 110 ቢሊየን ዶላር መቀነሱ ያለጥርጥር ከባድ ጫና እንደሚከስት አፅንኦት ሰጥቶታል።
የፊልፕን ሃሳብ የሚጋሩ የምጣኔ ሃብት ምሁራንም፣የገንዘቡ መቀነስ ከግለሰቦች ተሻግሮ ወደ አገር ህልውና የሚዘልቅ መሆኑንና ይህም በተለይ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከውጭ አገራት የሚላክ ገንዘብ በጉጉት ለሚጠብቁ የአፍሪካ አገራት ከባድ ፈተና መሆኑን አስምረውበታል።
በእርግጥም አህጉራችን አፍሪካ አሉኝ የምትላቸውን ምርቶች ለውጭ ገበያ አቅርባ ብሎም ከቱሪዝም ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ይልቅ ባህርማዶ የሚኖሩ ዜጎች ሰርተው የሚልኩላት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ሆኖ ይስተዋላል።
የተለያዩ ጥናቶች ብሎም ምሁራን እንደሚያ ስረዱትም፤ ከውጭ አገራት የሚላክ ገንዘብ በአፍሪካ ሰማይ ሰር ለዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት ዋስትና ከመሆንም ይሻገራል።ገንዘቡ አፍሪካ በካዝናዋ የውጭ ምንዛሪ እንድታስቀምጥና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት ስለመሆኑ በርካቶችን በአንድ ድምፅ ያስማማል።
ባሳለፍነው አመት ወደ አፍሪካ የተላከው ገንዘብ መጠን በሶስት ነጥብ አምስት በመቶ ከፍ ብሎ 707 ቢሊየን ዶላር መድረሱንና ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የ2 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ ማበርከቱን የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ።
ከአፍሪካውያን መካከልም ግብፅ ከውጭ አገራት የሚላክ ገንዘብ ቀዳሚ ተጠቃሚ ስትሆን ባሳለፍነው አመት የሃያ ሰባት ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝታለች። ናይጄሪያ በሃያ አራት ቢሊየን ዶላር፣ ሞሮኮ በስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ዶላር፣ ጋና በሶስት ነጥብ አምስት ቢሊየን እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ በሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊየን ዶላር ገቢ ከሁለት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ።
ከውጭ የሚላከው ገንዘብ ለአንዳንድ አገራት አጠቃላይ አገራዊ ምርት ሁነኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የተለያዩ መረጃዎችም ከውጭ የሚላከው ገንዘብ ለሌሶቶ 16 በመቶ፣ ለሴኔጋል አስር በመቶ ለናይጄሪያ ደግሞ ስድስት በመቶ የጠቅላላ አገራዊ ምርት አበርክቶት እንዳለው ይመሰክራሉ።
ይህ በሆነበት አፍሪካ ዘንድሮ ከውጭ ከሚላክላት ገንዘብ 37 ቢሊየን ዶላር ያህሉን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ልትነጠቅ እንደምትችል አለም ባንክ ግምቱን አስቀምጧል።የመገናኛ ብዙሃንና ልሂቃንም በተለያዩ ምክንያቶች ከትውልድ አገራቸው ርቀው ባህርማዶ የሚኖሩ ዜጎች ወደ ቤተሰብና አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ መቀነስ በተለይ አፍሪካውያን ላይ የሚያስከትለው ጉዳቱ ከፍተኛ ስለመሆኑ አፅእኖት በመስጠት ሰፊ ትንታኔን በማቅረብ ላይ ተጠምደዋል።
በገንዘቡ መቀነስ በተለይ በውጭ አገራት የሚኖሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚልኩላቸውን ገንዘብ ጠብቀው የሚተዳደሩ የአፍሪካ ልጆች ክፉኛ እንደሚጎዱና ቀውሱም በመቶ አሊያም በሺህ ሳይሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ አባዎራዎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚጎዳ አስገንዝበዋል።
የአለም ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፐስ ‹‹ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በተለይ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ዋነኛ የገቢ ደም ስር፣ ከሁሉም በላይ ለዜጎች የምግብ፣ የጤና ብሎም የመሰረታዊ ፍላጎት ሁነኛ ዋስትና ነው›› ብለዋል።ይህ በመሆኑ ባንኩ በክስተቱ ይበልጥ ተጎጂ ለሆኑ አገራት ዜጎቻቸው የመሰረታዊ ፍላጎት መሟላት ፈጣንና መጠነ ሰፊ የድጋፍ ግብረ መልስ ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
ከገንዘቡ መቀነስ ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ብሎም በሚባባስ ድህነት የበርካቶች ምግብ ዋስትና አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገባ ተመላክቷል።‹‹ቀውሱ የአፍሪካ ምግብ ዋስትና ላይ የሚያሳድረው ጫና የጎላ ነው›› የሚሉት ፀሃፍትና ምሁራኑ፣ እዚህ ላይ በየቀኑ የራሱን ክብደት ያህል የሚመገበው የአንበጣ መንጋ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ የወቅቱ የአየር ጠባይ በፈጠረለት ምቹ አጋጣሚ ግዛቱን እያስፋፋ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ መሆኑም ሲደመር በቀጣናው ነዋሪዎች ላይ የሚከስተውን ጉዳት ይበልጥ እንደሚያገዝፈው አስምረውበታል።
የገንዘቡ ሚና በግለሰብ ደረጃ ወቅታዊ ፍላጎት ወይም ፍጆታ በማሟላት ብቻም አይወሰንም። ከውጭ የሚገባው ገንዘብ መጨመር ለሚላክበትን አገር አጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚያበረክተው አፅተዋጽኦም እጅጉን ግዙፍ ነው።የገንዘብ መቀነስ ውጤት ደግሞ የተገላቢጦሽ።
ይህን እሳቤ የሚጋሩ የፋይናንስ ሊሂቃንም፣የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ችግር በሆነባቸው አገራት በተለይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪውና በንግድ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ከባድ ራስ ምታት መሆኑን አስገንዝበዋል። ‹‹ቀውሱን ተከትሎ የሚፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲመጣ ምክንያት ይሆናል›› ብለዋል።
አንዳንዶች በአንፃሩ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅእኖ የአለምባንክ በዚህ አመት በአለም አቀፍ ደረጃ ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እንደሚቀንስ ያስቀመጠው ግምት ስህተት ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል።‹‹ወረርሽኙን ለመቆ ጣጠር የተወሰኑ ገደቦች እየተቀዛቀዙ መም ጣታቸውና በአንዳንድ አገራት በርካቶች ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸው ይህን እንድንል ምክንያታችን ነው›› ብለዋል።
የአለም ባንክም ቢሆን ምንም እንኳን በወረርሽኝ ግብአተ መሬት አሊያም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በተወሰኑ ገደቦች የቆይታ እድሜ ላይ ቢወሰንም ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በቀጣዩ አመት መሻሻል ሊያሳይ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጣል።
ባንኩ በተለይ ደሀ፣ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት የሚላከው የገንዘብ መጠን በቀጣዩ አመት በአምስት ነጥብ ስድስት በመቶ መሻሻል እንደሚያሳይና በዚህ ረገድ የሚገኘው ገቢም እስከ 470 ቢሊየን ዶላር ከፍ እንደሚል አመላክቷል።
ይህ ተስፋና ግምት ግን በርካቶችን አላስማማም። በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦችና የቆይታ እድሜያቸው በግልፅ ሳይታወቅ የገንዘብ መጠኑ ይሻሻላል ብሎ መናገር ሞኝነት ነው ተብሏል።
ወረርሽኙን ለመግታት ገቢራዊ የተደረጉ ገደቦች ቢነሱ እንኳን የሰዎችም ሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት በፍጥነት ሊመለስ እንደማይችል የሚጠቁሙት የዚህ እሳቤ አራማጆች፤ የቫይረሱ ጥፋት ከሰዎች ጭንቅላት በፍጥነት የሚሰረዝ አለመሆኑም በቀደመው ልክ ስራቸውን እንዳይሰሩ፣ ቀደም ሲል ያገኙት የነበረውን ያህል ገንዘብ ማግኘትና መላክ እንዳይችሉ ሊገዳደራቸው ይችላል››ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት የወረርሽኙ ጉዳት መቋቋም ተስኗቸው ለኪሳራ በመዳረግ ሠራተኞቻቸውን ማሰናበታቸው በቀጣዩ አመትም ቢሆን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ በቀነሰበት እንዲቀጥል ምክንያት እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ መቀነስን በሚመለከት ተስፋም ሆነ ስጋትን ከመግለፅ ይልቅ የክስተቱን የጉዳት ተፅእኖ ለመቋቋም መደረግ ስለሚገባቸው አበይት ተግባራት የሚያስረዱ መገናኛ ብዙሃንና ምሑራን ቁጥርም ቀላል አልሆነም።
በአለም ባንክ የማህበራዊ ደህንነት ኃላፊ የሆኑት ሚኬል ሩቶስኪም፣ የኮሮና ቫይረስ ቀውስ ፈር እስኪይዝ ከውጭ በሚገኝ ገቢ ላይ ኢኮኖሚያቸውን ያስደገፉ አገራት ብሎም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ደሃና አቅመ ደካሞችን መደገፍ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በአለም ባንክ ስመጥር ኢኮኖሚስት ዲሊፕ ራታም፣የወረርሽኙን ተፅእኖ ከግምት ባስገባ መልኩ ሰዎች በቀላሉ ገንዘባቸውን መቀበልም ሆነ መላክ የሚችሉባቸውን የዲጂታል አማራጮች ማስተዋወቅ ግድ እንደሚልም አመላክተዋል።
ከሁሉ በላይ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር ረገድ ጠንካራ መሆንና ጥብቅ ህገ ደንቦችን ማስተዋወቅ ብሎም ማስተግበር እንደሚገባ ተጠቁማል።አገራት ባንክ የማያውቀው በየጓዳው በሰው የሚመነዘርና በጥቁር ገበያው የሚዘዋወር ገንዘብ ወደ መደበኛ የባንክ ስርዓት እንዲመለስ ለማድረግ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን በተለይ ማበረታቻዎቻቸውን ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል›› ተብሏል። ከሁሉ በላይ ግን ከውጭ የሚላክ ገንዘብ በሰዎች በጎ ፈቃድ እንጂ በግዴታ የሚፈጸም ባለመሆኑ አገራት ኢኮኖሚያቸው በእነዚህ ገንዘቦች ላይ ጥገኛ እንዳይሆን ማድረግ እንዳለባቸው አፅንኦት ተሰጥቶታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2012
ታምራት ተስፋዬ