የዛሬው የእሁድ ገፅ የስፖርት አምዳችን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አደረጃጀት ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚሁ ጉዳይ ላይ ልዩ አጀንዳ ይዞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጎ ነበር፡፡ በዋናነትም የሊጉ አደረጃጀት ምን ዓይነት ቅርፅ እና ይዘት ሊኖረው ይገባል? የሚለው ሃሳብ የተንሸራሸረ ሲሆን፣ የዘርፉ ባለሙያዎችም የየአገራቱን ሊግ ተሞክሮ እና የፕሪሚየር ሊጉን ነባራዊ ሁኔታ በጥናታቸው በመዳሰስ የመፍትሄ አቅጣጫ አመላክተዋል፡፡
የአገሪቷ እግር ኳስ ችግር መፍቻ መፍትሄ አንዱ የሊግ አደረጃጀትን ማሻሻል መሆኑን ያመነበት ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ለውይይት ክፍት አድርጎታል፡፡ እግር ኳሱን ለማዘመን «የሊግ ካምፓኒ» ምስረታ አስፈላጊነት ተወስቷል፡፡
አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የፕሪሚየር ሊጉን አደረጃጀት በተመለከተ ከባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ ጥናት በመስራት አማራጮችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጃቸው የሊግ ውድድሮች የአደረጃጀት እና የአሰራር ችግሮችን በመለየት የማሻሻያ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡
የአደረጃጀት ክፍተትና የሊጉ ፈተና
እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለፃ አሁን ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ አደረጃጀት የአስተዳደር፣ ከደንቦች እና መመሪያዎች አተገባበር፣ የውድድር ዓይነትና የመርሐ ግብር አወጣጥ፣ የገንዘብ እና የገበያ ትውውቅ ሥራ እንዲሁም የክለቦች አደረጃጀት እና አሰራር ጋር በተያያዘ ውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ ይገኛል፡፡
ፌዴሬሽኑ በአድራጊ ፈጣሪነት በሚመራው የኢትዮጵያ እግር ካስ ውስጥ የሚገኙ ክለቦች የአመራርነት እና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ እግር ካሱን እና የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ የሚያደርጉ ህጎች እና ደንቦች አይዘጋጁም፡፡ ውድድሮች እንዴት እንደሚመሩ የሚያሳይ አጠቃላይ ሰነዶች የሉትም፡፡ በተለይ ሥራ አስፈፃሚው የሊግ ኮሚቴዎች እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች የሥራ ግንኙነት እና ኃላፊነት በግልፅ የተለየ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አብዛኛው በእግር ኳሱ ዙሪያ የሚገኙ አመራሮች ሙያዊ ክህሎታቸውን ይዘው የሚሰሩ ሳይሆኑ በአማተርነት ስፖርቱን የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ከዚህ መነሻ የብቃት ማነስ እና የሥነ ምግባር ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች ደግሞ የእግር ኳሱ ማነቆ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ‹‹ተቋማዊ ቅርፅ የለውም›› የሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡ በተለይ መሽቶ በነጋ ቁጥር ህፀፅ የማያጣውን የክለቦች ውድድር በበላይነት ተቆጣጥሮ ትክክለኛውን መፍትሄ ሊያስቀምጥ የሚችል አደረጃጀት አለመፈጠሩ እንደምክንያት ይነሳል፡፡ በሌላ በኩል የቴሌቪዥንና ስፖንሰር መብቶች ጋር በተያያዘ ህጋዊ ስምምነቶች ለመፈፀም የሚያስችል ህጎችም እንደሌለው ነው ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚገልፁት፡፡
‹‹ከዋናው ፕሪሚየር ሊግ ውጪ በርካታ ውድድሮችን በባለቤትነት ይመራል፡፡ ሆኖም ግን ሁሉ መርሐ ግብሮች በብቃት እና በቅልጥፍና የሚያካሂድ ቁመና ስለሌለው ለአቅም ክፍተት ተዳርጓል›› የሚል አስተያየታቸውን የሚሰጡት አቶ ገዛኸኝ አደረጃጀቱን የሊግ ውድድሮች በተያዘላቸው የመርሐ ግብርና የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቁ ይቀራሉ የሚል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
«የእግር ኳስ ክለቦች ከአመሰራረታቸው አንስቶ በፖለቲካ ተፅዕኖ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው» የሚለውን ጉዳይ ጥናት አድራጊው ትክክለኛ ወቀሳና የስፖርቱ ፀር መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አብኞቹ ክለቦች በመንግሥት እና በልማት ድርጅቶች የሚተዳደሩ በመሆናቸው እራሳቸውን በፋይናንስ ሊደግፍ እና በነፃነት ሊመሩ የሚችሉበት ቁመና ላይ አይደሉም፡፡ የፋይናንስ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ችግርም ሌላኛው የሊጉ የአደረጃጀት ፈተና ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የተጫዋቾች ዝውውር አተገባበር ትልቁ ጥያቄ የሚነሳበት ቦታ ነው፡፡
‹‹የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ባስቀመጣቸው መለኪያዎች ሲቀመጡ አሁን ያሉት ክለቦች የክለብነት መስፈርት አያሟሉም›› የሚሉት ጥናት አድራጊው፤ የስፖርታዊ፣ የመሰረተ ልማት፣ የአስተዳደርና የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ እንዲሁም የህጋዊ መስፈርቶችን ተከትሎ አገር ውስጥ ያሉ ክለቦችን ሲለኩ አብዛኛዎቹ ክለብ ለመባል የማይበቃ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡ በተጨማሪም አዲስ አደረጃጀት ማለትም የአክሲዮን እና የግል ሊግ ካምፓኒ አደረጃጀትን ተረድቶ ተግባራዊ የማድረግ ዝግጁነት የላቸውም በማለት እንደ ዳንቴል የተወሳሰበውን የእግር ኳስ ፈተና ጥልቀት መታየት ይኖርበታል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡
የሊግ ካምፓኒ አደረጃጀት
ከላይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊግ አደረጃጀት በተለይ ችግሮቹን በጥልቀት የተመለከተ ዳሰሳ አድርገናል፡፡ አቶ ገዛኸኝም በሳይንሳዊ መንገድ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ችግሮቹን ብቻ ከማንሳት ይልቅ ምን ዓይነት የሊግ አደረጃጀት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ያስፈልጋል? የሚለውን በተመሳሳይ ያብራራሉ፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም በቅድሚያ ሊከናወኑ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ይገልፃሉ፡፡
‹‹ጉዳዩን በጥናት በጥልቀት ለማየት እንደሞከርነው የኢትዮጵያ ሊግ በፌዴሬሽን ስር ሆኖ ክለቦች በራሳቸው የሚያስተዳድሩት የሊግ ካምፓኒ ሆኖ ሊደራጅ ይገባል›› ያሉት ባለሙያው በዚህ አደረጃጀት ፌዴሬሽኑ ሊጎቹ የሚሰሩት ሥራ የተቃና እንዲሆን ከማገዝ በተለየ በክለቦቹ አስተዳደር ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ያስረዳሉ፡፡ ይህን መሰል አደረጃጀት የስፔን፣ የጀርመን እንዲሁም የጣሊያን ሊጎች የሚከተሉት አሰራር ነው፡፡
ባለሙያው የጥናቱን ምክረ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከማድረግ በፊት ሊሰሩ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል አንዱ ክለቦችን ነፃ ሆነው በራሳቸው የአስተዳደር እና የፋይናንስ አቅም እንዲመሩ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ የመንግሥት የገንዘብ ድጋፍን ህልውናቸው ከማድረግ መቆጠብ እና የራሳቸውን የገበያ ስልት መንደፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ፌዴሬሽኑ እና ክለቦች ሊጉን ሊያስተዳድሩበት የሚችሉበት የጋራ መተዳደሪያ ደንብ እና የተለያዩ ሰነዶች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የጋራ ውይይት ማድረግ ከቻሉም በዚህ አደረጃጀት ውስጥ በማለፍ ስኬታማ ሊግ ለመመስረት የሚያስችል ዕድል መፍጠር ይችላሉ፡፡
ቁርጠኝነቱ ምን ይመስላል?
ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ዘመናዊ የእግር ኳስ አደረጃጀት መመስረትን በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚመለከታቸውን አካላት አወያይቷል፡፡ ይህም ጥናት አቅራቢዎቹ የሰጡትን ምክረሃሳብ ባፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበትነው፡፡
ፌዴሬሽኑ ተወካዮቻቸውን የላኩ ክለቦች ለጉዳዩ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገልጽ መሆኑንና ያላሳወቁ ክለቦች እንዲያሳውቁ አሳስቧል። ክለቦቹ የሚወክሏቸውን ባለሙያዎች ሲመርጡ የእግር ኳስ ኢንዱስትሪውን የሚያውቁ፣ ሥራውን በብቃት መወጣት የሚችሉ፣ የጥናትና የሊግ አደረጃጀት ሥራ ለመስራት አቅም ያላቸውን መሠረት ማድረግ እንደሚገባቸው አጽንኦት በመስጠትና የተመረጠውንም አንድ ተወካይ እስከ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በደብዳቤ እንዲያሳውቁ አሳስቧል፡፡ በቀጣይ የሊግ ካምፓኒ መስራች ኮሚቴ ቡድኑ ወደ ሥራ እንደሚገባም ገልጿል፡፡
በፌዴሬሽኑ በኩል ቡድኑ በአፋጣኝ ወደ ዝግጅቱ ለመግባት እንዲያስችለው የመሰብሰቢያ ቢሮ እንደሚመቻችና አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። እንዲሁም የሊግ መስራች ኮሚቴ ቡድኑ የሥራ እቅዱን በማውጣት ተጨማሪ የባለሙያ ድጋፍ የሚያስፈልገው ከሆነ ለጽህፈት ቤቱ ያሳውቃል። በጥናት ሰነድ ዝግጅት በአገኘው ጥሩ ተሞክሮ መሠረት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ባለሙያዎችን ድጋፍ በመጠየቅ እንደሚያሟላላቸው አረጋግጧል፡፡
ሆኖም ጥናት አድራጊው አቶ ገዛኸኝ ይህን አደረጃጀት በሚፈለገው ፍጥነት እውን ለማድረግ የማያስችሉ ፈተናዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ፌዴሬሽኑ እና አንዳንድ ክለቦች ቢያንስ በጅምር ደረጃ ያሳዩት ፍላጎት አለ፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ክለቦች በሚፈለገው ደረጃ ስለጉዳዩ ፍላጎት እና እውቀቱ አላቸው ብዬ አላስብም›› ይላሉ፡፡ አንዱ ችግር የእውቀት ክፍተት በመሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ የክለቦቹ አመራሮች ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ይላሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ትዝብት ግን ከፍተኛ የተነሳሽነት ችግር በብዙሃኑ ክለቦች ላይ ይስተዋላል፡፡
በመግቢያችን ላይ ጠቆም እንዳደረግነው አቶ ገዛኸኝ እና ባልደረቦቻቸው የሊግ አደረጃጀት አመሰራረትን ጨምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ያሉ የአሰራር ክፍተቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት ጥናት አድርገዋል፡፡ በዚህም ዘጠኝ ሰነዶችን ለፌዴሬሽኑ በማቅረብ አሁን ላይ የሚታዩትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ባልነበረ መልኩም ተቋሙ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡ ምክረ ሃሳቦች መሬት ላይ ወርደው እውን እግር ኳሱ ነፃ ይወጣ ይሆን የሚል? ተስፋ ደግሞ የስፖርቱ አፍቃሪ ማህበረሰብ ተስፋን ያዘለ ጥያቄ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ዳግም ከበደ