በሰፈራችን ያገኙትን መመረቅ የሚወዱ አንድ አባት ነበሩ። «ደግሞ ይስመርላችሁ…አምላክም ይስማኝ እንጂ ልጆቼን እናንተን ለመመረቅ ለምን ብዬ እሰስታለሁ?» ይላሉ። ፈገግ ካሉላቸው መመረቅ ነው፣ ዞር ካሉላቸው መመረቅ ነው፣ አቤት ካሏቸው መመረቅ ነው። ነጋዴ አይደሉም፤ ሽበት የተጎናጸፉ፤ እድሜ ያስከበራቸው ደግ አባት ናቸው። እኛ ደግሞ ሲመርቁ እንዳያመልጠን፤ ቶሎ አሜን አሜን ማለት።
አንድ ወዳጃችን ታዲያ አብዝቶ ይወዳቸዋል። ምርቃታቸው የሠራለት ነገር ኖሮ እንደሆነ አላውቅም፤ ብቻ እኛ ጓደኞቹ ከምንወዳቸው በላይ ነው እርሱ የሚወዳቸው። እናም ይህን ፍቅሩን ለመግለጽ በዓል አስታክኮ፣ የእኛን ቦርሳና ኪስ በመዋጮ ስም ፈትሾ፤ ነጣ ያለ ጋቢ ገዝቶ አበረከተላቸው። መረቁት! መቼም የእኛ ነገር! ጥቅም ሲያገኙ አብዝተው የመረቁት ይመስለን ይሆናል? ግን አይደለም። እንደወትሮው ሳያደሉ፤ ሳይጨምሩ ወይም ሳይቀንሱ መረቁት። «አትጣ! አግኝ!» አሉት።
ምርቃታቸው እያንዳንዱ ፍሬ እንዳያመልጠው ከስር ከስር በ«አሜን» እየለቀመ ቆየና፤ «አባብዬ… እንደው ይሄ አትጣ አግኝ ብለው የመረቁኝ ነገር ምኑን ነው?» አላቸው። እርሳቸውም ነገሩ ጨዋታ መስሏቸው ፈገግ ብለው፤ «ምንስ ቢሆን የኔ ልጅ? ሰላምም ቢሆን ጤና፤ ፍቅርም ቢሆን አንድነት፤ በጎውን የልብህን መሻት ሁሉ እንድታገኝ ነው ምርቃቴ» አሉት።
እርሱ ግን ፊቱን ቅጭም አድርጎ፤ «እንደው ወደላይ አስፈጻሚዎች ጋር ሲደርስ ለመምረጥ እንዳይቸግራቸው፤ «ትራንስፖርት አግኝ…ታክሲ አትጣ!» ብለው ለይተው ቢጠቅሱልኝ ብዬ ነው» አላቸው። ነገሩ ቀልድ ነው ተብሎ በዛን ሰሞን በሰፈራችን እንደ ጉድ ተሳቀ። እርሱ ግን ከልቡ ነበር፤ ተማሯላ!
ባለፉት ቀናት የነዳጅ መጥፋት ድፍን አዲስ አበባ እንዴት የገበያ ማዕከሏን መርካቶን እንደመሰለች አላያችሁም? ግን እኔ የምለው፤ ለነዳጅ እንዲህ ከሆንን…ሰላም ጨርሶ የጠፋች ቀን ምን ሊውጠን ነው። ነዳጅና ሰላም ምን አገናኛቸው እንዳትሉኝ። ሰዎች! ሁሉም ነገር ፖለቲካ መሆን የለበትም። ግን አንዳንዴ አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል ብዬ ነው። አርቀሽ አስበሽ ልብሽ ውልቅ ብሏል! በሉኛ! ይሁን እተወዋለሁ።
ግን እውነቴን ነው፤ አትጡ! አግኙ። ለምን? በትራንስፖርት ማጣትና ማግኘት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ስትመለከቱ ራሳችሁን ታያላችሁ። ባለመኪና ከሆናችሁ ደግሞ እኛን መኪና አልባዎቹን ታዩናላችሁ። ለምሳሌ አሁን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ቀን ረዥም ዘንዶ የሚያስንቅ ሰልፍ ይዘን አውቶብስ ጥበቃ ላይ ታድመናል።
ከስንት አንዴ የሚመጣውን ባስ «ሰለፉ ከእኔ ነው የሚጀምረው» በሚል ንትርክ ጥቂት አቆየነው። ከዚህ ቆይታ በኋላ ሰላማዊና ሰልፋዊ ግፊያ ተደርጎ ተሳፈርን። ማን እንደመረቀኝ ባላውቅም ወንበር አገኘሁ። እማማ አፍሪካ! በየክፍሏ ለወንበር የሚራኮትባት መቼስ ብዙ ነው። ብቻ እድሜው ገፋ ያለ፤ «ኧረ እርስዎ ይቀመጡ» የሚባል ዓይነት ሰው በአካባቢዬ ስላልነበር ተደላድዬ ሃሳቤን ጥዬ ተቀመጥኩ።
ታዲያ ከገባን በኋላ፤ «እዛጋ ተጠጉ…እዚህ ጋር አለፍ በሉ» ልመና ጀመረ፤ ውጪ ያለው ተሰላፊ። «ከዚህ በላይ ወዴት ልጠጋ?» ንጭንጭ ያሰማል ተሳፋሪ። «ቆይ ሰው ሌላ ባስ አይጠብቅም እንዴ? ሞልቶ እያዩት እዚህ ተፋፍኖ ለመሄድ መጋፋት ምንድን ነው?» ይላል፤ ለባሱ መጨረሻኛ ሆኖ የገባው ሰው። ሁሉም ብቻ የየራሱ የሆነ አስተያየት ይሰጣል።
ብቻ መሙላት አይቀርም ባሱ ሞልቶ ተንቀሳቀሰ። ልክ ሲንቀሳቀስ ባሱን የተሳፈረ ሁሉ በመስኮቱ አሻግሮ የተሰለፈውን ሰው እያየ ከንፈሩን መምጠጥ ይጀምራል። «በስመ አብ ሰልፍ! አሁን ስንት ሰዓት ነው ይህ ሁሉ ሰው ቤቱ የሚገባው?» ይላል። ተጋፍቶና ተጣልቶ በባሱ የተሳፈረው ሰው፤ ለገፋውና ለታገለው ለጣለውም ሰው መልሶ ያዝናል።
እናላችሁ! መቼም ሀብታም ሰው ነው ለምስኪን ደሃ ሲያዝን የሚያምርበት፤ እኛ ቀንቶን የተሳፈርን ሰዎችም ገና ሰልፍ ላይ ላሉት ሀዘን ገባን። እኔም ራሴ አዘንኩ፤ እውነት እላችኋለሁ ሰልፉ ላይ እኔ የነበርኩ እስከማይመስለኝ ድረስ ነው የተሰለፉት ሰዎች ያሳዘኑኝ። አሃ! እኔ አገኘሁኛ! ይሄኔ ይህ ተከታዩ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፤ ለካ መተሳሰባችንን የሰረቀው ድህነት ነው። ብዙ አውቶብስ ቢኖረን ኖሮ፤ መንገዱ ቦርቀቅ ቢልልን ኖሮ፤ ከየምንሠራበትና ከየምንማርበት አፈስ አድርጎ ካሰብነው የሚያደርሰን ባለመኪና ዘመድ ቢሰጠን ኖሮ፤ መንገዱን እንጃ እንጂ ራሱ መኪና ቢኖረን ኖሮ፤ ይሄ ሁሉ ይኖር ነበር? አይኖርም።
አትጡ አግኙ…አንጣ እናግኝ ያልኩት ለዚህ ነው። በየትራንስፖርቱ ማንነታችን እየታየ ይመስላል። በዛ ቦታ መታገስ የቻለ ትዕግስቱ፣ በዛ ቦታ መሳደብ የቻለ ድፍረቱ፣ በዛ ቦታ መጋፋት የቻለ ጥንካሬው…ሁሉም ቁልጭ ብሎ ይታያል። በቃ! ሰውን የምታውቀው አብረኸው ረጅም ጉዞ ስትሄድ ነው ምናምን የሚሉት ነገር ተለዋጭና አማራጭ አግኝቷል። ወይም «ጓደኛህን ንገረኝና አንተነትህን ልንገርህ» እንደሚባለው፤ «ረጅም የታክሲ ሰልፍ አብሬአቸው ልሰለፍና ስለሀበሾች እነግርሃለሁ» የሚል ብሂል አያይዞ መናገር ይቻላል።
«ሰላምም ቢሆን ፍቅርና አንድነት፤ ሊፍት የሚሰጥ ክፉ ያልገጠመው ደግ ባለመኪና፣ ባዶ ታክሲና አውቶብስ፣ ቅድሚያ ለሴት የሚሉ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች፣ ስታረፍዱ የማይቆጣ…በጊዜ ስትወጡ የማይከፋው አለቃ፣ መኪና ገዝቶ የሚሰጥ ዘመድ፣ በምትንቀሳቀሱበት መስመር የሚሠራ የምታውቁት የሚያውቃችሁ ሹፌር ወይ ረዳት…የመሳሰሉትን ሁሉ አግኙ፤ ይስጣችሁ። እንዲሁም ጠላት አንዳንዴ ያስፈልጋልና እርሱንም ጠራርጎ አያሳጣችሁ።» የሰፈራችን መራቂ አባት፤ አባባ፤ የጓደኛችን ጥያቄ ቀልድ እንዳልነበረ ከተረዱ በኋላ ነው እንዲህ መመረቅ የጀመሩት። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ሊድያ ተስፋዬ