ክፍል አንድ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ትውልድ እንዲህ ባለ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሲገኝ በአስተዋይነት አኩሪ ታሪክ ጽፎ ማለፍ ይገባዋል:: ፈታኙን ወቅት በጥበብ ተሻግሮ ሀገርን ከነክብሯ ለልጆቹ የሚያስረክብ ትውልድ ዘለዓለም በበጎ ይወደሳል:: ይህን ያላደረገ ትውልድ ደግሞ ስሙ በመጥፎ ሲታወስ ይኖራል::
የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያንም እንዲህ ባለ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን:: የቀደሙትን የከሸፉ የታሪክ ገጾቻችንን ለጊዜው እንተዋቸውና በቅርብ ጊዜያት እንኳ በ1960ዎቹ እና በ1980ዎቹ መባቻ ያመለጡንን የሚያስቆጩ ዕድሎች መዘንጋት አይገባም::
አገራችንን እየመራ ያለው መንግሥት ሥልጣኑ በቀጣዩ መስከረም ይጠናቀቃል:: ከዚያ ወዲህ ደግሞ ምርጫ ሊደረግ የግድ ነበር:: ካልሆነ ግን በአገሪቱ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ያለው መንግሥት አይኖርም::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአገሪቱ ለማካሄድ እንደማይችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል:: ይህንኑ ተከትሎም ፓርላማው ምርጫውን ማካሄድ የማይቻል ከሆነ አገረ-መንግሥቱን ሊያዘልቁ ይችላሉ ያላቸውን አማራጮች ተመልክቷል::
በዚሁ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፣ ፓርላማውን መበተን ወይም የሕገ-መንግሥት ትርጉም መጠየቅ የሚሉ አማራጮች ቀርበው ሕገ-መንግሥቱን መተርጎም የሚለው አማራጭ በአብላጫ ድምጽ ተመራጭ ሆኗል::
በየአምስት ዓመት በሚደረግ ምርጫ መንግሥት እንደሚመሰረት በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች:: በዚሁ መነሻ ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመሳሳይ ወቅት ላይ ውለዋል::
በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ እነዚህ ሁለት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ምን ዓይነት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ የሚለው ነገር ባለመኖሩ ሕገ መንግሥቱ መተርጎም አለበት በሚል ለሚመለከተው አካል ጉዳዩን ማሳለፉን ተከትሎ ሁኔታው በሁሉም ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል::
በአንድ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት አገርን ከዚህ ከባድ ጊዜ ለማሻገር በአስተዋይነት የመረጠው ቀና መንገድ ስለመሆኑ ይነገራል:: በሌላ በኩል ግን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ በገዥው የብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን መንግሥት ሥልጣን ለማራዘም የተቀመረ ዘዴ ነው የሚሉም አሉ::
ለማሳያነት የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትህነግ/ሕወሓት) ምርጫው መደረግ እንዳለበት ቁርጥ አቋም ይዟል:: ለተፈጠረው ችግር ከሕጋዊ መፍትሔ ይልቅ ዋነኛው መፍትሔ ፖለቲካዊ መሆን እንዳለበት የሚገልፁት ኃይሎች ደግሞ የሽግግር መንግሥትን ያቀነቅናሉ:: የሕገ መንግሥት ትርጉም ሳይሆን ሌሎቹ ሦስቱ አማራጮች መተግበር አለባቸው የሚሉ ሀሳቦችም ይደመጣሉ::
ያም ሆነ ይህ አገር በወሳኝ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች:: ከግራ ከቀኝ የሚደመጡት ሀሳቦች ገሚሶቹ ገንቢ እና ኃላፊነት የተሞላባቸው ሲሆኑ፤ ጥቂት የማይባሉት ግን ሆነ ብለው ሕዝቡን የሚያሳስቱና ሕገ መንግሥቱን ሳይቀር አጣምመው የሚያቀርቡ ግብዝ ሀሳቦች ናቸው::
እኛም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዛሬውና በተከታዩ ሳምንት እትሞቻችን ለአንባብያን በቂ ግንዛቤን የሚፈጥሩና ምክንያታዊነትን የሚያጎለብቱ ገዳዮችን እንዳስሳለን::
ለምርጫ ጉዳይ “አንድ-ላገሩ” ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው!
ትሕነግና ሌሎች አንዳንድ ወገኖች ምርጫ መደረግ እንዳለበት ነው እየወተወቱ ያሉት:: ይባስ ብሎም በትግራይ ክልል ምርጫ እናካሂዳለን በሚል በይፋ እየተገለፀ ነው:: ከወዲህ ማዶ ደግሞ ክልሎች ምርጫ ማድረግ እንደሚችሉ በመግለጽ የሀሳብ እንድነት የፈጠሩ ኃይሎች አልጠፉም::
ይሁንና በሕገ መንግሥቱ መሠረት በመላ አገሪቱ
ምርጫን እንዲያካሂድ ብቸኛ ሥልጣን የተሰጠው አካል ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ነው:: ቦርዱ ደግሞ በመላ አገሪቱ ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል አስታውቋል:: ታዲያ በምን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የትኛውስ አካል ነው ምርጫ ማድረግ የሚችለው የሚል ቁልፍ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም::
በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ተቋቁሟል ይላል ሕገ መንግሥቱ:: ከዚህ ድንጋጌ በግልጽ እንደምንረዳው በየትኛውም የአገሪቱ ጥግ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ እንዲያካሂድ በራሱ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመ “አንድ-ላገሩ” የሆነ ተቋም ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑን ነው::
ይህንን ድንጋጌ ይዘን ታዲያ ምርጫን በተመለከተ ሕግ የማውጣትም ሆነ ያወጣውን ሕግ የማስፈፀም ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው ማን እንደሆነ ማየቱ ጠቃሚ ነው:: በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶችን ለማስፈፀም ቁልፍ መሣሪያ የሆነውን ምርጫን የተመለከተ ሕግን የማውጣት ሥልጣን ያለው የፌዴራል መንግሥቱ ነው::
የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ተወስኗል:: ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች፤ የክልሎችም በፌዴራሉ መንግሥት መከበር እንዳለበትም ተደንግጓል::
ታዲያ በምን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ነው ክልሎች ወይም አንድን ክልል የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ “በምመራው ክልል ውስጥ ምርጫ አደርጋለሁ” ብሎ የሚነሳው!? ሌላውስ ደግሞ “የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል ምርጫን ክልሎች ማድረግ መብታቸው ነው” የሚለን በምን የሕግ መሠረት ነው!?
እስኪ ሕገ መንግሥቱን አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይቶ ያፀደቀውን የሕገ መንግሥት ጉባኤ ቃለ ጉባኤዎችን በወፍ በረር እናስታውሳችሁ:: በወርሐ-ሕዳር 1987 ዓ.ም. ከተደረጉት የጉባኤው ስብሰባዎች እንደምንረዳው ምርጫና ሌሎችም መሰል ለፌዴራል መንግሥቱ የተሰጡት ሥልጣኖች በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ በሰፈረው አግባብ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው::
በዚሁ አመክንዮ ምርጫ ቦርድ ብሔራዊ ተቋም ሆኖ ነው የተቋቋመው:: በመላ አገሪቱም ምርጫን የሚያካሂደው እሱው ብቻ ነው:: በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ደግሞ ሌሎቹ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በተቃውሞ እየታጀቡ ሲፀድቁ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ የሆነው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ግን ያለአንድም ተቃውሞ ነው የፀደቀው::
ከሁሉም በላይ ምርጫን በተመለከተ እንደ አገር የሚቋቋመው አንድ አካል ብቻ ስለመሆኑ፤ ይህም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን፤ ቦርዱም በየወቅቱ ለሚደረጉ ምርጫዎች ወሳኝ አካል ሆኖ ተቋሙም ራሱን በቻለ አዋጅ ሳይሆን በራሱ በሕገ መንግሥቱ እንዲቋቋም መደረጉን በሕገ መንግሥት ጉባኤው ቃለጉባኤ ላይ ለታሪክ ተመዝግቦ እናገኘዋለን::
ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁትና ያፀደቁት የያኔዎቹ ሰዎች ሀሳብ ይህ ከሆነ ከምርጫ ቦርድ ውጭ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ መነሳት ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው:: የሕገ መንግሥቱ ቁልፍ ማጠንጠኛ ከሆነው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት ከሚለው መርህም ያፈነገጠ ነው::
ደጋግመው በሚያወጡት መግለጫ እንደሚገልፁት ምርጫ እናደርጋለን የሚሉ ኃይሎች ሀሳባቸውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሚል የወርቅ ቅብ በማቅረብ ቅቡልነት ያለው ለማስመሰል ይጥራሉ::
እርግጥ ነው በሕገ መንግሥቱ እንደተገለፀው ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራሉ:: የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም የመገንባት ኃላፊነት አለባቸው::
ከዚህ ውጭ ግን ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ባልተገባ ሁኔታ በማቅረብና ሕዝብን በማሳሳት ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ምርጫ ለማድረግ መንቀሳቀስ ሕገ ወጥነት ነው:: ከሁሉም በላይ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተግባራዊ የሚደረገው በሕገ መንግሥቱ አግባብ በፌዴራሉ መንግሥት ሕግና ሥርዓት የሚመራ ምርጫ ተደርጎ እንጂ በሕገወጥ መንገድ በሚደረግ ሕገወጥ ምርጫ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል::
እዚህ ላይ ምርጫ እናደርጋለን ባዮች ጠንቅቀው የሚያውቁት ግን ደግሞ በደንብ ሊገነዘቡት የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ አለ:: የየትኛውም አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ከሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል::
ከዚህ ውጭ ማንኛውም አካል ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ ባለመሆን ተፃራሪ ውሳኔ ካሳለፈ ወይም ከተገበረ ተቀባይነት አይኖረውም:: በመሆኑም የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ክልሎች ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊዘነጉት አይገባም::
ምርጫ ያካሄዱ አገራትን አርአያ ማድረግ ይቻላልን?
ከሕገ መንግሥቱ አንፃር አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በዚህ መልኩ የሚቃኝ ከሆነ ነባራዊ ሁኔታውንም ማየት ያስፈልጋል:: ነባራዊው ሁኔታ በግልጽ እንደሚያሳየን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምርጫ ለማድረግ እንደማይቻል ነው::
በዚህ ድምዳሜ ላይ ብዙ ጊዜ ማጥፋት ተገቢ ባይሆንም ቅሉ፤ ሌሎች አገራት ምርጫ ስላደረጉ እኛም ማድረግ እንዳንችል የሚከለክል ሁኔታ ውስጥ አይደለንም የሚል አሳሳች ሀሳብ ከምርጫ ይደረግ ባዮቹ አብዝቶ ስለሚሰነዘር የዚህን ሀሳብ ሀሰትነት በማስረጃ ማሳየቱ አስፈላጊ ነው::
ከሁሉ አስቀድመን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ምርጫዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንቃኝ:: International Institute for Democracy and Electoral Assistance (International IDEA) የተሰኘው ተቋም መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላው ዓለም ከመጋቢት እስከ ግንቦት ምርጫ ለማድረግ
ውጥን ከነበራቸው አገራት ውስጥ ከ56 የሚበልጡት ምርጫዎቻቸውን አራዝመዋል::
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ድረስ የሚካሄዱ በርካታ ምርጫዎችን ስለማራዘምም አገራት በመምከር ላይ ናቸው:: በአፍሪካ ደግሞ ከስምንት በላይ አገራት ምርጫ አራዝመዋል::
ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታው ይህ ከሆነ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንም ምርጫን ሊያደርጉ የሚችሉበት የተለየ ሁኔታ አይኖርም:: ምክንያቱም ወረርሽኙ ለሁሉም የሰው ዘር በየአገራቱ ውስጥ ተመሳሳይ ሥጋትን ስለደቀነ::
እንዲህም ሆኖ ግን የተወሰኑ አገራት በኮሮና ጥላ ውስጥም ሆነው ምርጫ አካሂደዋል:: ከባህር ማዶ እሥራኤል፣ ደቡብ ኮርያና ሌሎችም፤ ከአፍሪካ ደግሞ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ማሊና ቤኒን በመጋቢትና በሚያዝያ ምርጫ አድርገዋል::
ለእኛ ተጨባጭ ሁኔታ የቅርብ ማሳያ የሚሆነንን የአፍሪካውያኑን ምርጫ እንመልከተው:: በአራቱም አገራት በተደረጉት ምርጫዎች የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደዋል:: የድምጽ መስጫ ስፍራዎች ጽዱ እንዲሆኑ ተደርገዋል፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የግድ ነበር:: እጅ መታጠብና አለመሰባሰብም እንዲሁ::
ነገር ግን በምርጫዎቹ ማግስት በአገራቱ የተፈጠረው ሁኔታ አሳዛኝ ሆኗል:: በአራቱም አገራት ከምርጫዎቹ በኋላ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ወደ አስከፊ ሁኔታ ተሸጋግሯል::
እስካለፈው ሳምንት ድረስ በጊኒ 2600 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው፣ 16 ዜጎች ሞተዋል:: በካሜሩን 3100 በላይ ተይዘው ከ140 በላይ ሞተዋል:: በማሊ 860 ተይዘው 52 ሞተዋል:: በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ደግሞ ሁኔታዎች ወደ አስከፊ ደረጃ እንደሚለወጡ ነው የተተነበየው::
በሥጋትም ውስጥ ሆነው በቴክኖሎጂ በመታገዝ የቫይረሱን ሥርጭት ለማስቀረት ምርጫ እንዳከናወኑት የባህር ማዶዎቹ ስልጡኖች ሳይሆን እነዚህ የአፍሪካ አገራት ከላይ ከተጠቀሱት የጥንቃቄ እርምጃዎች ውጭ እንደወትሮው በረዣዥም ሰልፎች ነበር ምርጫ ያካሄዱት:: ይህ በመሆኑ ውጤቱ አስከፊ ሆኗል::
ሁኔታው ዜጎችን ለቫይረሱ ተጋላጭ ከማድረጉም በላይ ከፖለቲካዊ አንድምታውም አንፃር አሉታዊ ገጽታ ነበረው:: የዚህ ዓይነተኛ ማሳያው በአራቱም አገራት የድምጽ ሰጭዎች ቁጥር ማሽቆልቆሉ ነው::
ለማሳያነት በጊኒ በቀደመው ምርጫ ከተመዝጋቢዎች ውስጥ 68 ነጥብ 4 በመቶ ነበር ድምጽ የሰጠው:: በአሁኑ ምርጫ ግን ድምጽ የሰጠው ከተመዝጋቢዎቹ ውስጥ 58 በመቶ ብቻ ነው:: በማሊም ከ43 በመቶ ወደ 36 በመቶ ወርዷል::
የሸጋ ምርጫ አንዱ መገለጫ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበው ሕዝብ በምርጫው ቀንም በነቂስ ወጥቶ ድምጽ የሚሰጥበት ሲሆን ነው:: የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባህል ባልዳበረባት አፍሪካ ወትሮም ቢሆን ካርድ ወስዶ ድምጽ የማይሰጠው ሕዝብ በርካታ ሆኖ እያለ በኮሮና ምክንያት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ምርጫዎች በመካሄዳቸው “እንኳን ዘንቦብሽ” እንደተባለው ዓይነት ሆኗል::
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ነው እንግዲህ አንዳንዶች ሌሎችም እያደረጉ ስለሆነ በኢትዮጵያም ምርጫ መደረግ አለበት ሲሉ የሚሞግቱት:: ይህ ደግሞ የዜጎችን ነፍስ አስይዞ የፖለቲካ ቁማር እንደመጫወት ስለሚታይ ፍፁም አሳፋሪ አስተሳሰብ ነው::
በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የቫይረሱ ሥርጭት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረና ወደ አስፈሪ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው:: ሕዝቡ በብርቱ ሥጋት ውስጥ ወድቋል::
የሚጠይቀው የለም እንጂ በዚህ ወቅት እያንዳንዱ ዜጋ ቢጠየቅ ቀን ከሌት መንፈሱን ሰቅዞ የያዘው የምርጫ መደረግ ያለመደረግ ጉዳይ ሳይሆን ይህንን አስከፊ ቀን እንዴት እንደሚሻገረው ነው:: የይስሙላ ምርጫ ደግሞ ሕዝቡን አሰልችቶታል::
ከዚህ አስከፊ ጊዜ ማዶ መልካም ቀን ሲመጣ ከቀደሙቱ የተሻለ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚያደርግ ነው ተስፋን የሰነቀው:: እናም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ካላደረግን ሞተን እንገኛለን ማለት ኢሞራላዊነት ከመሆኑም በላይ “ጮሃ የማታውቅ ወፍ የጮኸች እንደሁ ‘እለቁ እለቁ’ ትላለች” እንደተባለው አይነት ይሆናል::
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
በገብረክርስቶስ