ኮሮና ከምድረገጽ ጠፍቶ ወደ ቀደመ የህይወት ዘይቤው ለመመለስ የማይጓጓ ሰው የለም:: ታዲያ ሁሉም ሰው አንድ አይነት ጉጉት የለውም:: ወደ ስራ መመለስን የሚናፍቀው ብዙ ነው:: መሰባሰብ ፣ መጨባበጥና መተቃቀፍም ያማረው በገደቡ ምክንያት ተማርሯል:: ጥሬ ስጋ ለመብላት የሚቋምጥም አለ:: መሸታ ቤት ለማንጋት አልነጋለት ያለው አፍጣጭስ? ጉዳዩን በጾታ አይን ካየነው ግን ይለያል:: ይህ ሁሉ የጉጉት አይነት ተጠቃሎ በአንድ ሐረግ ይገለጻል:: ውጪ ውሎ የመግባት ጉጉት! በኮሮና ምክንያት “የኔ” ከሚሏቸው ሰዎች ጋር ቤት ውስጥ መዋል ለጥቃት ያጋለጣቸው ሴቶች ብቸኛ ጉጉት ይህ ነው::
ዩኤን ዉሜን በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ በመገደዳቸው ሳቢያ በሴቶች ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ያመለክታል:: ሪፖርቱ አገራት ከጣሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በፈረንሳይ 30 በመቶ፣ በአርጀንቲና ፣ በሲንጋፖርና በሳይፕረስ ደግሞ ከ 25 እስከ 30 በመቶ መጨመሩን ለሴቶች ጥቃት የአደጋ ጥሪ ከተዘጋጁ የስልክ መስመሮች በተገኘ መረጃ የተሰሩ ጥናቶች ማሳየታቸው ተጠቅሷል::የቤት ውስጥ ጥቃቶች ተዳፍነው በሚቀሩባቸው ኢትዮጵያን በመሰሉ አገራት ቁጥሩ ምን ያህል ሊያሻቅብ እንደሚችል አስቡት::
በዓለማችን ሴቶች በየመስኩ የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ ነው በሚባልበት ዘመን ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተበራክተዋል። በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ይህንኑ የሚያመላክት ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 11 ሴት ሚኒስትሮችን ሾመዋል:: አዎ! ከጠቅላይ ሚኒስትሩ 20 የካቢኔ አባላት መካከል 11ዱ ሴቶች ናቸው:: የአገራችን ርዕሰ ብሔር ሴት ናቸው:: የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢም ሴቶች ናቸው:: ክልሎችም ባደረጉት ሹም ሽር በርከት ያሉ ሴት አመራሮች የተለያዩ ቢሮዎችን በመምራት ላይ ይገኛሉ:: አንዳንዶች “የሴቶች ዘመን” እያሉ በሚጠሩት ባለንበት ወቅት የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መጨመራቸው እየተነገረ ነው::
አንጋፋው ገጣሚ “በቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ናት” በሚባልላት አገር የስጋ ዋጋ አልቀመስ ማለቱ ገርሟቸው
ፍየል ሞልቶ ፍየል ተርፎ ፣
ላሙ ሞልቶ በሬው ተርፎ ፣
በጉ ሞልቶ …
ምን ቢመጣ ዐዲስ ታምር ፣ ዐዲስ ነገር፣
ከብት ይወደድ በከብት ሀገር !
እንዳሉት … ሴቶች ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በሚኙበት ዘመን የሚፈጸምባቸው ጥቃት በማባራት ፈንታ ማሻቀቡ ወዴት፣ ወዴት ያሰኛል::
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቷ በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊጨምሩ እንደሚችሉ በማሰብ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው ጊዜያት ከሚያዩዋቸው ጥቂት አስቸኳይ ጉዳዮች ውስጥ የቤት ውስጥ ጥቃት ክስ አንዱ እንዲሆን መመሪያ አስተላልፈዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩም “በሴቶች ላይ የቤት ውስጥ ጥቃት በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም:: በእንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ወቅት የሚያስፈልገው ከመጠቃቃት ይልቅ መደጋገፍ ነው፡፡” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::
ፕሬዚዳንቷና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያና ማሳሰቢያ መስጠት ግድ የሆነባቸው ወትሮውንም ቢሆን በአገራቸው ሴቶች ላይ የሚፈጸመውን የከፋ ጥቃት ጠንቅቀው በመረዳታቸው ነው:: ቢቢሲ ከአንድ አመት በፊት ባወጣው ዘገባ ፣ ባደጉ አገሮች ከአራት ሴቶች አንዷ ጥቃት እንደሚደርስባት ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ ግን ከሁለት ሴቶች አንዷ ጥቃት እንደሚደርስባት ገልጿል:: ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ጎሞራው) ከአስርት አመታት በፊት በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ የሚደርሰው ይህን ጾታዊ ጥቃት ተመልክቶ “ብቻሽን አልቅሺ” በሚል ርዕስ ተከታዩን ስንኝ ቋጥሮ ነበር::
ግማሽ አካሏ ወንድ በትህምክት ሲከዳት፤
ጧ ብላ አለቀሰች አዛኝ ቢደርስላት፤
ጧ ብላ አለቀሰች ፤
ኳ – ብላ ደረቀች ፤
ዷ – ብላ ፈነዳች ፤
ቿ – ብላ ፈሰሰች ፤
ቷ – ብላ ተፈታች ፤
ብሶት ተጫጭኗት ምንም ሰው አልሆነች፤
በቀቢጸ ተስፋ ሕላዌዋንም ጠላች ፤
ያገሬ ጭቁን ሴት መድህን መላ ያጣች ፤
ወንድሽ እንደሆነ ላንቺ ደንታ ቢስ ነው
ሴቶች ቅርብ በሆነ ጓደኛ ወይንም የትዳር አጋር የሚደርስባቸው ጥቃት ከጤናቸው መጓደል ጋር እንደሚገናኝ የአለም የጤና ድርጅት በ2009 ዓ.ም ህዳር ወር ያወጣው መረጃ ያረጋግጣል:: በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ግድያዎች 38 በመቶ
የሚሆኑት የሚፈጸሙት በወንድ የቅርብ ጓደኛ ወይንም የትዳር አጋር ነው፡፡
ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች ለውስብስብ ችግሮች ይጋለጣሉ:: ለአካላዊ ጉዳት ፣ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች፣ ላልተፈለገ እርግዝና፣ ለሥነ-ተዋልዶና ወሲባዊ የጤና ችግሮች እንዲሁም ለሞት ይዳረጋሉ:: የስነ ልቦና ቀውስና የስሜት መጎዳትም ይደርስባቸዋል:: የድብርት ስሜት፣ ብሶት፣ ፍርሃት፣ እራስን መጥላት፣ አለመረጋጋት፣ በራስ አለመተማመን ያጋጥማቸዋል::
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአራት አመታት በፊት ባወጣው መረጃ መሰረት ፣ በቅርብ ሰው አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ከሌሎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው ከማያውቅ ሴቶች በሁለት እጥፍ ውርጃ ይፈጽማሉ ፤ በድብርት ስሜት የመጠቃት እድላቸው ይሰፋል ፤ እንዲሁም በአንዳንድ አገራት 1.5 እጥፍ በኤች. አይ.ቪ የመያዝ እድላቸው ይጨምራል:: ይባስ ብሎ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች በሚኖሩበት ማህበረሰብ መገለል ፣ መወገዝና መጠቋቆሚያ መሆን ይደርስባቸዋል:: በዚህም ምክንያት ተስፋ ለመቁረጥና ራስን ለማጥፋት ይጋለጣሉ፡፡
ፆታን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ማህበረሰቡ ስለ ፆታ እኩልነት ካለው የተዛባ አመለካከት ጋር ይያያዛሉ:: በ2016 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያ የስነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ እንደሚያመላክተው 28 በመቶ ወንዶች ባል ሚስቱን መምታት መብቱ ነው ብለው ያስባሉ:: ከዚህ የከፋው ደግሞ 68 በመቶ ሴቶች በባሎቻቸው መመታታቸውን አግባብነት ያለው አድርገው መቁጠራቸው ነው:: እንዲህ ያሉ የአስተሳሰብ አረሞች ከስር መሰረታቸው እስካልተነቀሉ ድረስ የኢትዮጵያ ሴቶች የሚጎነጩት የግፍ ጽዋ አይጎልም፡፡
ዛሬም ሴቶች ከሸሹት ኮሮና ይልቅ ቤት ውስጥ ባለ ድንቁርና እየተጎዱ ነው:: ውጪውም ውስጡም እሳት ሆኖባቸው ተጨንቀዋል:: የሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፤ ለይቶ ማቆያና ኳራንቲን የማድረጊያ ስፍራዎች እንደተዘጋጁ ሁሉ ፣ የቤት ውስጥ ጾታዊ ጥቃት ለሚደረስባቸው ሴቶች የሚሆኑ መጠለያዎችና የህክምና እና የስነልቦና ድጋፍ መስጫ ስፍራዎች ሊዘጋጁ ይገባል:: ጥቃት አድራሾች ላይም አስተማሪ የሆነ እርምጃ መወሰድ አለበት !
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
የትናየት ፈሩ
ደጁም ቤቱም እሳት የሆነባቸው ሴቶቻችን