ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በህብረተሰብ፣ ብሎም በሀገር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖዎች አሉት። ይህም በግለሰብ ላይ ህመምና ሞት፣ የማምረት/የመስራት አቅም መቀነስ፣ የህክምና ወጪ መጠን መጨመር፣ በህመም ምክንያት ከሥራ/ ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ ስነ ልቦናዊ ችግሮች ያስከትላል። ኤች.አይ.ቪ.ኤድስ የቤተሰብ የጤና ችግርም ነው፤ በሽታው ሚስት፣ ባልን፣ ልጅን ሊመለከት ይችላል፤ የማምረት ችሎታ ማጣት፣ ኀዘንና የሚወዱትን ሰው ማጣት፣ የቤተሰብ ኃላፊነት በልጆች ላይ መውደቅ፣ መገለልና መድልዎ በቤተሰብ ሊከሰት ይችላል። በተመሳሳይ በአገር ላይ የአምራች ሠራተኛ ኃይል መቀነስ፣ በአገሪቱ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ ጫና መፍጠር፣ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው በህመምና በሞት መለየት ምክንያት በሁሉም የኢኮኖሚ ክፍሎች ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርሳል።
በአገር ደረጃ ለተያዘው በ2030 ኤድስን የማቆም ግብ ስኬታማነት በወቅቱ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ በማድረግ ራስን ማወቅ ከፍተኛ ሚና አለው። የኤች.አይ.ቪ ምርመራ በማድረግ ራስን ማወቅ ከየትኛውም በላይ በርካታ ጥቅሞች አሉት። መመርመር ህይወትን ለመምራትና ለመቆጣጠር ያስችላል፤ በሚኖረው ህክምና በበሽታው ከመጎዳት ይከላከላል፤ ህይወትንም ይታደጋል። ምናልባትም አንድ ግለሰብ እንደሚያስበው አሳሳቢ የቫይረስ ደረጃ ላይ ላይገኝ ስለሚችል በወቅቱ ራስን ማወቅ ተገቢ ነው።
የኤች.አይ.ቪ የደም ምርመራና የምክር አገልግሎት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ስርጭት ለመግታት አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ተመርምሮ የኤች አይ.ቪ ሁኔታን ማወቅ ያለውን ጠቀሜታ በዝርዝር ስንመለከት የመጀመሪያው በወቅቱ መመርመር ማለት ህይወትን ማዳን ማለት ነው። ሰዎች የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ህክምና መድኃኒት የሚጠቀሙት ተመርምረው በደማቸው ቫይረሱ መኖሩን ሲረዱ ብቻ ነው። በዩ.ኤን.ኤይድ መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ 9.4 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከኤች አይ ቪ ጋር መኖራቸውን አያውቁም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ተመርምሮ ራስን ባለማወቅ ነው።
በሁለተኛነት ቀድሞ መመርመር ወይም በጊዜ ህክምና መጀመር ማለት ነው። ይኸውም አንድ ሰው ቫይረሱ በደሙ መገኘቱን ቀድሞ አወቀ ማለት ህይወቱን ለመታደግ የሚያስችለውን ህክምና ቀድሞ ይጀምራል ማለት ነው። እንዲሁም ቫይረሱ በደሙ ከተገኘ በኋላ በመጀመሪያው አካባቢ የኤች.አይ.ቪ ህክምና ከጀመረ ውጤቱም የተሻለ ይሆናል። በወቅቶ ራሱን አውቆ በወቅቱ የተመረመረ እና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ የወሰደ ሰው ረጅም እና ጤናማ ህይወት መምራትም ይቻለዋል።
በሦስተኛነት በወቅቱ ተመርምሮ የሉበትን ሁኔታ ማወቅ ከቫይረሱ ነፃ ከሆኑም ነፃ እንደሆኑ ለመቆየት ዕድል ይከፍታል። በሌላ በኩል ቫይረሱ በደም ውስጥ ከተገኘ እንደ ቫይረሱ ደረጃ ሁኔታ ራሳቸውን እንዲሁም የሚወዱትን ቫይረሱ የሌለበትን ሰው እንዳይያዝ ይከላከላል።
በአራተኛነት በጊዜ ራስን ማወቅ ተገቢ እንክብካቤ ለማድረግ ጥሩ ዕድል ይፈጥራል። ተመርምሮ ራስን ማወቅና ተገቢውን እንክብካቤ ማግኘት ደግሞ ትልቁ ኤች አይ ቪን የመከላከል መሳሪያ ነው። ይኸውም ህይወትን ማዳን እና ስርጭቱን መከላከል በመሆኑ የኤች አይ ቪ ህክምና የቫይረሱን የጉዳት መጠን እንዲሁም በታማሚው አካል ላይ ያለውን የቫይረስ መጠን በምርመራ በማይገኝበት ደረጃ ያደርሰዋል። ኤች አይ ቪ በምርመራ የማይገኝበት ደረጃ ሲደርስም ቫይረሱን ወደ ሌሎች የማስተላለፍ አቅም አነስተኛ ይሆናል።
በአምስተኛነት በወቅቱ ተመርምሮ ራስን ማወቅ ቫይረሱን ከእናት ወደ ህፃን የማስተላለፍ ሁኔታ ማቆም ነው። ቫይረሱ በደሟ የሚገኝና በእርግዝና ላይ የሆነች ወይም እያጠባች ያለች እናት ከቫይረሱ ነፃ የሆነና ጤነኛ ልጅ እንዲኖራት ማረጋገጥ ትችላለች። ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ተመርምራ ራሷን ማወቅ ስትችል ብቻ ነው።
በስድስተኛነት ያለውን ጥቅም ስናይ በጊዜ ተመርምሮ ራስን ማወቅ በጤንነት የመኖርን መብት ማወጅ ነው። የራስን ሁኔታ ተመርምሮ ለማወቅ በመወሰን የቻሉ ሰዎች ስለጤናቸው ያላቸውን መብት ለመምረጥም አቅም ያገኛሉ።
በተጨማሪም የኤች አይ ቪ ምርመራ በማድረግ በወቅቱ ራስን ማወቅ በህይወትና በጤና ለመቆየት ያስችላል፤ ሌሎች በሽታዎችን በጊዜ ለማወቅ ዕድል ይከፍታል። በመሆኑም እንደ ሳንባ ነቀርሳ/ቲቢ፣ የጉበት ብግነት/ሄፓታይተስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ የመሳሰሉትን ችግሮች በጊዜ ለማወቅም ያስችላል።
ስለዚህ አንድ ሰው ቫይረሱ በደሙ እንደሚገኝ ካላወቀ ህክምናውን አይጀምርም፤ የትኛው የመከላከል አማራጭ እንደሚያስፈልገውም መረዳት አይችልም። በዩ.ኤን.ኤይድ መረጃ መሰረት ማንኛውም ተመርምሮ የኤች.አይ.ቪ ሁኔታውን ለማወቅ የሚደረግ ውሳኔ የግለሰቡ ውሳኔ ብቻ ነው። የቤተሰብ፣ የሥራ ባልደረባ፣ የዶክተሮች ወይም ማንኛውም አካል ለምርመራ ማስገደድ አይችልም። አንድ ሰው ክሊኒክ ሄዶ ምርመራ ከማድረጉ በፊትም ስለምርመራው ለማወቅ ከካውንስለር ወይም የምክር አገልግሎት ሰጪ አካላት ጋር የመነጋገር አጋጣሚ ይኖረዋል።
ስለውጤቱና ውጤቱ ስለሚያመለክተው እንዲሁም ስለማንኛውም ስጋቶች ለመወያየትም ዕድሎች ይመቻቻሉ። ከምርመራ በኋላም በምርመራው ውጤት መሰረት ያለውን አማራጭ ለመረዳት ቀጣይ ምክርም ያገኛል። ስለዚህ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆኑ ወይም በፍርሃት የሚመጣውን አሉታዊ አስተሳሰብ እና መገለልን ማስወገድም ያስፈልጋል።
ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች የምናሳያቸው ባህሪያቶችና መደምደሚያዎች ከፍተኛ ተፅዕኖ አላቸው። ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ የሚመጣ አድሎና መገለል የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የሚፈልጉትን ሰዎችንም ያሸሻቸዋል። የጤና አገልግሎት ሠራተኞችም ሁሉንም የግለሰቡን የጤና መረጃ በአስተማማኝነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት የምርመራ ውጤትና ማንኛውም ስለውጤቱ ያለው ውይይት ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ ነው። በመሆኑም ራሱን በምርመራ ያወቀ ሰው ብቻ ከሚፈልገው ሰው ጋር ውጤቱን የማጋራት መብት ይኖረዋል።
ከጤና ተቋማት መዋቅሮች አካባቢ ያለውን ከኤች አይ ቪ ጋር የተያያዙ ችግሮች ማስወገድ ለተጋላጭነቱ ቅርብ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ወይም ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩት እንቅፋቱን በማስወገድ የምርመራ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። ስለዚህ በጤና ተቋማት አካባቢ ያለውን ለወንድም ሆነ ለሴት ምቹ የሆነ የአገልግሎት ሁኔታዎች ማመቻቸት ማለት ራሱን የቻለ በቂ የምክር አገልግሎትን ጨምሮ ለኤች አይ ቪ ምርመራ ምቹ ሁኔታ መኖር አለበት።
በመረጃዎች መሰረት ወንዶች ከሴቶች ይልቅ አነስተኛ በሆነ መልኩ የጤና ተቋማትን ይጎበኛሉ። ለዚህም ለወንዶች በአቅራቢያ ጤና ተቋማት አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ ምክንያት የሆነው የጤና አቅርቦቶች ለወንዶች ምቹ አይደሉም ብሎ የማሰብ ሁኔታ ነው። ከዚህም መካከል የጤና ማዕከላቶች ለተገልጋዩ ክፍት የሚሆኑበት ሰዓት በቅጥር ህይወት ላይ ላሉት ከሥራ ጊዜያቸው ጋር ግጭት መፍጠሩም ይጠቀሳል። እንዲሁም የወንዶች አገልግሎት ተጠቃሚነት ውስንነት መኖር ማህበራዊና ባህላዊ እምነቶች እና ባህሪያቶች የራሳቸው ምክንያት የሚሆኑበት ጊዜም አለ። በመሆኑም በርካታ ወንዶች ሳይመረመሩ ቆይተዋል። በመሆኑም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወንዶች ሳይመረመሩ በመቆየታቸው ምክንያት የህክምና አገልግሎትና እንክብካቤ ዘግይተው ለማግኘት ይገደዳሉ።
ግብረሰዶም የሚፈጽሙ ግለሰቦች የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ፣ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች፣ በእስርቤቶች ያሉና ሌሎች ተቀራራቢ ሁኔታዎችም አካባቢ ለምሳሌ ስደተኞች የምርመራ አገልግሎት ተጠቃሚነት አነስተኛ ነው። በነዚህ አካባቢዎች ደካማ የጤና አገልግሎት ሽፋንና የአቅርቦት ችግር በመኖሩ እንዲሁም የአቅርቦትና አገልግሎት ተቀባይነቱ አለመኖርም ተደራራቢ ችግር ነው። ይህም እየተንጸባረቀ ያለው ተደጋጋሚ የጤና ምርመራ አገልግሎት የማግኘት ፍራቻ፣ የመገለል ችግር የመሳሰሉት ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ የጤና ምርመራ አገልግሎት ማድረግ እንዳይቻል አድርጓል። በማጠቃለያም አንድ ግለሰብ በደሙ ውስጥ ኤች.አይ.ቪ መኖር አለመኖሩን የደም ምርመራ በማድረግ ማወቅ ይችላል።
ይህም ግለሰቡ ቀጣይ ህይወቱን ጤናማ በሆነ መልኩ ለመምራት እንዲችል ግንዛቤና መልካም አጋጣሚ ይፈጥርለታል። የምክር አገልግሎት ሳያገኙ በደም ምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያረጋገጡ ሰዎች በሥነ ልቦናቸው ላይ የሚደርስባቸውን ፍርሃት፣ አለመረጋጋት መቋቋም ያቅታቸዋል። ስለዚህ የምክር አገልግሎት ከኤች.አይ.ቪ የደም ምርመራ ጋር ማግኘት እጅግ ጠቃሚ ነው። የኤች.አይ.ቪ የደም ምርመራና የምክር አገልግሎት የኤች.አይ.ቪ ኤድስን ስርጭት ለመግታት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል። በደም ምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያረጋገጡ ሰዎች በሚያገኙት ምክር ታግዘው ከቫይረሱ ጋር ለረጅም ጊዜ እንዴት መኖር እንደሚችሉና የወደፊት ህይወታቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው እቅድ በማውጣት ራሳቸውን ያዘጋጃሉ። የባህሪ ለውጥን ለማምጣትም ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ።
በደም ምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሌለ ያረጋገጡ ሰዎች ደግሞ ወደፊት እንዳይያዙ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የባህርይ ለውጥ እንዲያመጡ ያግዛቸዋል።
ስለዚህ በዩኒቨርሲቲው ክሊኒክ እና በየጤና ድርጅቱ የሚሰጠውን የኤች.አይ. ቪ.የደም ምርመራና የምክር አገልግሎት በማግኘት ራሳችንን ማወቅ እና የወደፊት ህይወታችንን ጤናማ በሆነ መልኩ መምራት ይገባናል። በተለይም ወጣቶች ከጋብቻ በፊት ከትዳር አጋር ጋር የኤች.አይ.ቪ የደም ምርመራና የምክር አገልግሎት ማግኘት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶችም ኤች.አይ.ቪ ወደ ህጻኑ እንዳይተላለፍ ለመከላከል ወደ ጤና ድርጅት በመሄድና የኤች.አይ.ቪ የደም ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011