
በሙያው ታታሪ የሆነና በሥራዎቹ ጥራት የተመሰገነ አንድ አናጢ ከከተማ ወጣ ባለ ሥፍራ ይኖር ነበር። ይህ አናጢ ለአንድ ባለሀብት ተቀጥሮ ዕድሜውን ሙሉ ሲያገለግለው ይኖርና የጡረታ መውጫ ዕድሜው ላይ ይደርሳል። በዚህን ጊዜም አናጢው ወደ አሰሪው ቀርቦ «ጌታዬ ሆይ ዕድሜዬን ሙሉ በታማኝነት ለሥራዬ ትኩረት ሰጥቼ ሳገለገልዎት ቆይቻለሁ። አሁን ግን ዕድሜዬ ገፍቶ እየደከመኝ ስለሆነ የጡረታ መብቴን አክብረውልኝ ያሰናብቱኝ ዘንድ በአክብሮት እጠይቅዎታለሁ» ሲል ይጠይቃል።
አሰሪው ይህንን ሃሳብ በሰማ ጊዜ ትጉህ ሠራተኛውን ሊያጣው መሆኑን አስቦ እጅጉን ያዝንና «ዕድሜህን ሙሉ በታማኝነት ያገለገልከኝን አንተን የመሰለ አናጢዬን በማጣቴ እጅጉን አዝናለሁ። የዕድሜ ጉዳይ እንደመሆኑ ደክሞሃልና ምንም ማድረግ አልችልም። ጥያቄህን ተቀብያለሁ። ይሁንና ለመጨረሻ ጊዜ አንድ የማስቸግርህ ነገር አለ። እሱም ለአንድ ደንበኛዬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ላደርስ ቃል የገባሁለት ቤት አለና ይህቺን ብቻ በፍጥነት ሰርተህ አስረክበኝና ጡረታህን ውጣ።» ብሎ ለመነው።
አናጢውም የአለቃውን ጥያቄ ተቀብሎ ቤቱን ለመስራት ተስማማ። ይሁንና ከዚህ በኋላ በደንብ ሰራሁ አልሰራሁ ምን ይጨምርልኛል? ከሥራው እንደሆነ መሰናበቴ ነው በማለት ቤቱን ከማይረቡ ቁሳቁስ ጥንካሬና ውበት በሌለው ሁኔታ እንደነገሩ ሰርቶ ጨረሰና ለአሰሪው እንዲረከበው ጠየቀው። አሰሪውም ይህንን በሰማ ጊዜ ጥያቄውን ተቀብሎ በፍጥነት በመስራቱ አመሰግኖ «ዕድሜህን ሙሉ በታማኝነት ስታገለግለኝ ስለኖርክ ይህ አሁን የሰራኸውን ቤት ላንተ በስጦታ አበርክቼልሃለሁ እነሆኝ የቤቱን ቁልፍ ተረከብ» ብሎ ያስረክበዋል።ይህንን በሰማ ጊዜ አናጢው ክው ብሎ ቀረ «ምን ዓይነት ሰው ነኝ? ቤቱን የሰራሁት እንደነገሩና ለይሰሙላ ነው። እናም በዚህ የደከመ ቤት ነው ቀጣይ ዕድሜን የምኖረው» ብሎ ተጸጸተ።
ይህ ታሪክ ሁላችንንም ይመለከታል። ምክንያቱም ዛሬ የምንኖረው ትናንት በሰራነው ልክ ሲሆን የነገ አኗኗራችንም የሚወሰነው ዛሬ በምንሰራው ሥራ ነውና። ዛሬ ክፋትና ተንኮልን ከዘራን ነገ የምናጭደው የዚህኑ እኩይ ፍሬ ሲሆን መልካምነትን ከዘራንም እንዲሁ ነገ የምናፍሰው ሰናይና ህይወትን የሚለግሰን ፍሬ ይሆናል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ጽሁፉ «ዛፍን ለመትከል ምርጡ ጊዜ የዛሬ ሃያ ዓመት፤ ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ ደግሞ ዛሬ ነው» ይላሉ ቻይናዎች ሲል አስነብቧል። አባባሉ ትልቅ እውነት አለው። ነገ የሚገነባው ዛሬ ነውና! ዛሬ እንዲኖረን የምንፈልገውን ዛፍ ከሃያ ዓመት በፊት ተክለነው ቢሆን ኖሮ ዛፉ አድጎ ዛሬ ለፍሬ በበቃና በጠቀመን ነበር።
ነገ እንዳናያቸው የምንፈልጋቸውና ዛሬ የምንሰቃይባቸውን ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ መጥበብ፣ ግጭትና መፈናቀል መቆም ካለባቸው ይህን ፍሬ የሚያሳፍሰውን ሥራ መስራት ያለብን ዛሬ ላይ መሆን አለበት። ያለዚያ በምኞት ብቻ የምንፈልገው ነገር በምንም ተዓምር ነገ ላይ ሊከሰት አይችልም። አሁን እየተቸገርንባቸው ያሉ የጭፍን ጥላቻ፣ የመገፋፋትና የመጥበብ እኩይ ተግባራት የትናንት ሥራዎቻችን ውጤት መሆናቸውም ፈጽሞ መዘንጋት የለበትም። ከዛሬ 50 እና 60 ዓመት ጀምሮ ያለውን ፖለቲካችንን ብናይ የሴራ፣ የመጠላለፍ፣ የመገፋፋትና የመገዳደል እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው። ይህ ትናንት የተሰራው ሥራም ጥላቻን ወልዶ አሁን ያለውን ትወልድ አበሳውን እያሳየው እንዳለና ፖለቲካችንንም አስቀያሚ ገጽታ እንዲላበስ እንዳደረገውም ከማንም አይሰወርም።
እርግጥ ነው መልካም ፍሬ የሚያስገኝ ነገር ተረጋግቶ መሥራትንና ትዕግስትን እጅጉን ይፈልጋል። ወደዚያ ለመድረስ የሚደረገው ጉዞም በውጣ ውረድ የተሞላ መሆኑ አይቀሬ ነው። ነገር ግን ዕይታችንን የዛሬው ችግር ላይ ሳይሆን ነገ የምናፍሰው ምርት ላይ ካደረግን ከምንፈልገው ግብ ላይ መድረሳችን አይቀሬ ይሆናል። «እኛ ግን በብዙ መሰናክሎች ተከቦ፣ ሜዳልያውን እያሰበ፣ ወደ ሩጫው ፍጻሜ እንደሚገሰግስ ሯጭ ከፊታችን ያለውን ውብ ቀን እና በጥረታችንም የምናስመዘግበውን ጣፋጭ ድል እያሰብን በጽናት ልንሮጥ ይገባል፡፡ በጊዜያዊ እና አልፎ ሂያጅ ነገሮች ላይ ማተኮር ውጤታችንንም ታሪካችንንም ጊዜያዊ አድርጎት ይቀራል:: በልፋታችን፣ በትግላችን እና በብርታታችን የምንቋደሰው ድል የሁላችንም የመሆኑን ያህል ተግዳሮት እና ፈተናውም የሁሉም ኢትዮጵያ ልጆች እንቅፋት መሆኑን በመረዳት እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር እና በመደመር ልንሻገረው ይገባል፡፡» የሚለው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የጥምቀት በዓል መልዕክትም ይህን ሃሳብ በሚገባ የሚያጠናክር ነው።
ስለሆነም የነገውን ፍሬ አስበን የምንዘራውን ዘር ዛሬ ላይ በጥንቃቄ መምረጥና ፍሬ እስኪያፈራም በትጋት መንከባከብ ይገባናል። ስላለፉት ነገራት በማውሳት አሁን ላይ መተከዝ፣ መቆዘምና ማዘኑ አይጠቅምም። ሽሚያው መሆን ያለበት ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ እንዳያልፍ ነውና መስራት የሚገቡንን ሰናይ ነገሮች ሁሉ አሁኑኑ መስራት እንጀምር። እየደጋገሙ መተከዝና እየደጋገሙ ማልቀስ ለአገር ሰላምና ዕድገት እንደማይጠቅም አውቆ ትናንትን ከመርገም መውጣትም ብልህነት ነው። ስለሆነም ዛሬ ላይ መሆን ያለበት ነገር የጥንቱን የኢትዮጵያዊነት ፍቅርና መተሳሰብን ማምጣትና ይህንኑ ለማጠናከር መስራት ነው። ይህን ካደረግን የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ዕውን የማድረግ ጉዟችንን አሳመርን ማለት ነው።
ልጆቻችን እኛ ባለፍንበት የድህነትና የንተርክ መንገድ ደግመው እንዲሄዱበት ፈጽሞ አንፈልግም። ይልቁኑ ፍቅርና መተሳሰብን እንዲላበሱ ብሎም አንዱ የአንዱን ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት እያከበረ በሰላምና በተድላ የሚኖሩበትን ጊዜን እንመኛለን። ይህን እውን ማድረጉም በእጃችን ያለ ዕድል ነውና በታላቅ ሀገራዊ የኃላፊነት መንፈስ ነገን ዛሬ ላይ አሳምረን እንስራ እንላለን።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011