ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ፣ የ16ኛ ሰንጥቅ ሜካናይዝድ ብርጌድና በኋላም የሶስተኛው ሜካናይዝድ ክፍለጦር (ሶሜክ) ዋና አዛዥ በመሆን ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ስመጥር ጀግና እና የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳሊያ ተሸላሚ ናቸው። ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በታንከኛ አዛዥነት በምስራቅ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ተሰልፈው መርተዋል። በሰሜን ጦር ግንባር ከሠራዊታቸው ጋር በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሳትፈዋል። በቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ ስመጥር ከነበሩት ጀነራል መኮንኖች ውስጥ አንዱ ናቸው። በ1981 ዓ.ም በጀነራሎቹ በተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው ታስረዋል። ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሊገባ ሲቃረብ ከእስር ቤት ተፈተዋል። በዚህም የተነሳ በፍቅር ከሚወዱት የውትድርና ሙያቸው ተለይተዋል።
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ የሐረር ጦር አካዳሚ 10ኛ ኮርስ ምሩቅ ሲሆኑ፣ ‹‹የጦር ሜዳ ውሎዎች ከምስራቅ እስከ ሰሜን›› የሚለው መጽሀፍ ደራሲም ናቸው። አዲስ ዘመን ከብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ እና የግብጽ መሪዎች ሲያሰሙት በነበረው የጦርነት ዛቻን በተመለከተ ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- ጀነራል እስኪ ከታሪክዎ ትንሽ ይግለጹልን?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- የተወለድኩት ነገሌ ቦረና ነው። ይርጋለም ተማርኩ። በእደማርያም ዩኒቨርሲቲ (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ትምህርቴን ጀምሬ ነበር። አቋርጬ ሐረር ጦር አካዳሚ 10ኛ ኮርስ ገባሁ። የሐረር ጦር አካዳሚ የሀገራችን ምርጥ ወታደራዊ አካዳሚ የነበረ ነው። ሶስት አመት ሰለጠንኩ። እንደ ተመረቅን በም/መ/አለቅነት ማዕረግ ስራ የጀመርኩት ሶስተኛ ክፍለጦር ውስጥ ነበር። ጅጅጋ ላይ በእሥራኤሎች የሁለት አመት ስልጠና ወስጃለሁ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ደህንነት (በአንቲ ሀይጃከርነት) ሰርቻለሁ። ለከፍተኛ የታንክ ትምህርት አሜሪካን ሀገር ሄጄ አንድ አመት ተኩል ተምሬአለሁ። እንደተመለስኩ ሶማሊያ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባቷና ወረራ በመፈጸሟ ወቅቱ ሀገርን የማዳን ፍልሚያ ስለነበር እጅግ ከፍተኛ ትንቅንቅ በተደረገበት በምስራቁ ጦርነት ተሳትፌያለሁ። ቀጥሎም በሰሜን ጦር ግንባር ብዙ ቆይቻለሁ። በ1981 ዓ.ም በተሞከረው የጀነራሎቹ መፈንቅለ መንግስት ተጠርጥሬ ያለፍርድ ታስሬ ቆይቻለሁ። በዚህም ያለውዴታዬ ከምወደው ሙያዬና ከሠራዊቱ ተገልዬ ዛሬ በጡረታ ላይ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለአባይና ስለግብጽ ቢነግሩን?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- ለመነሻ እንዲሆነን ወደኋላ ሄደን ጠቅላላ ሁኔታውን እንመልከት። የአባይ ምንጩ ነጭ አባይና የእኛው ጥቁር አባይ ነው። ሁለቱ አባዮች የሚገናኙት ካርቱም ነው። የአባይ ውሃ 85 በመቶ የሚፈሰው ከኢትዮጵያ ምድር ነው። ወደ እኛው አባይ የሚፈሱ 90 ትናንሽ የራሳችን ገባር ወንዞች አሉ። አፈራችንን ከያለበት ሰብስበው አጥበው ነው አባይ ወንዝ የሚገቡት። ግብጽ ከኢትዮጵያ የምታገኘው 84 ሚሊዮን ኪዩቢክ ውሃ ነው። እንደገናም ከእኛ አራት ሚሊዮን ቶን ለም አፈር እየታጠበ ወደ ሱዳንና ግብጽ ይሄዳል።
አዲስ ዘመን፡- በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ያሉት ሀገሮችስ?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- በአባይ ሸለቆ ተፋሰስ ውስጥ 12 ሀገሮች አሉ። ሁሉም በእርሻና በግብርና የሚተዳደሩ ናቸው። እኩል ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው ግብጽ በብቸኝነት የአባይን ውሃ ለዘመናት በሞኖፖል ይዛ ብቻዋን ተጠቃሚ ሆና ኖራለች። ሌሎቹ የበይ ተመልካች ነበሩ። ግብጽ ካለ አባይ መኖር እንደማትችል የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ያውቃል። የተፈጥሮን ሂደትና የውሃውን ፍሰት የምናግድበት ነገር የለም። እኛ የአባይ ወንዝ ውሃ ዋነኛው አመንጪ ሆነን ሳንጠቀምበት ኖረናል። አሁን የአባይ ወንዝ ውኃችን የመብራት ኃይል
እንዲያመነጭ፣ ለልማት እንጠቀምበት ስንል የግብጽ እብደትና ንዴት አይገባኝም፤ የትም አይደርስም። በመሰረቱ የሚጎዳት ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የግብጽ መሪዎች ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የጦርነት ቀረርቶ እያሰሙ ነው። የግብጽ ሠራዊት የጦርነት ታሪክ ምን ይመስላል? ጦርነት ለመክፈትስ ይበቃሉ?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- ከጥንት ጀምሮ በጣም የራቀውን ልተውና መለስተኛውን ብወስደው የግብጽ መሪ የነበረው ከዲቭ እስማኤል በአንድ ወቅት የድፍረቱ መጠን ያኔ አጼ ቴዎድሮስ እንግሊዞችን በያዙ ጊዜ ኤሽያዎችም ያልቻሏቸው ስለሆነ በአስቸኳይ እንድትፈታ ብሎ ለእንግሊዝ ሞጋች ሆኖ ነበር የቆመው። አጼ ቴዎድሮስ በተረጋጋ ሁኔታ ስላልነበሩ እንጂ ሊወጉት ሁሉ እየተዘጋጁ ነበር። ከእርሳቸው ሞት በኋላ ሁኔታዎች ባልተረጋጉበት ይኸው ሰው ሙዚንገር የሚባል አንድ የእንግሊዝ አሰልጣኝን በመጠቀም በ1871 ዓ.ም ያሰለጠነውን ጦር አስከትሎ አሰብን ያዘ። ሀረርም ሄዶ ይዟል። ከአሰብ ወደ መሀል ሀገር ለመምጣት ሙከራ አድርጎ አፋሮች ሙሉ በሙሉ ነው ሠራዊቱን የደመሰሱበት።
በዚያኑ ወቅት 3 ሺህ ሠራዊቱን ከምጽዋ አንስቶ ወደ ከረን ሲገባ የአጼ ዮሐንስ ሠራዊት በራስ አሉላ የጦር መሪነት እንዳለ ነው ከረን ላይ የደመሰሱት። እንደገና
በ1875 ዓ.ም ሚዚንገር 15 ሺህ ሠራዊት አሰልፎ ኩአቲት ላይ ዘመቻ ሄደ። በዚህ ውጊያ የአጼ ዮሀንስ ሠራዊት 7 ሺህ የሚሆነውን የግብጽ ሠራዊት ደመሰሰው። የተረፈውን 8 ሺህ ምርኮኛ ተደርጓል። ሁለተኛ ከኢትዮጵያ ጋር አንዋጋም ብሎ ለምኖ ቃል አስገብተው ነው ወደመጣበት የሸኙት። ይሄ ነባራዊ ሁኔታ ነው። ዛሬ አይደለም ጥንት ጀምሮ የግብጾች ፍላጎት አባይን ከምንጩ ከመሰረቱ እንያዘው የሚል ነው። ይሄ እንደማይሆንና እንዳልተሳካላቸው ያውቃሉ።
አዲስ ዘመን፡- ግብጾች ኢትዮጵያ ላይ በሞከሩት ተደጋጋሚ ጦርነት ተሸንፈው ተመልሰዋል። ከታሪካዊ ሽንፈትና ውድቀታቸው አልተማሩም ማለት ነው?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- ግብጾች ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ስናየው ኢትዮጵያውያንን በጦርነት እንደማያሸንፉ አውቀዋል። አሻጥር ወደ መስራት በስፋት ሄዱ። ጀብሀ የሚባለው በኤርትራ የነበረ ፓርቲ ሲመሰረት ቢሮ የሰጡት፤ ከአረብ ሀገራት ጋር በስፋት ያስተዋወቁት እንዲደገፍ ያደረጉት የግብጽ መሪዎች ናቸው። ሻዕቢያንና ወያኔን በዚህ መልኩ ሲረዱ የነበሩት ግብጾች ነበሩ። ማንኛውንም የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ የተነሳን ኃይል በገንዘብም በማቴርያልም ሲደግፉ የኖሩት አሁንም የሚደግፉት ግብጾች ናቸው። ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ኢትዮጵያን እንድትወር ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በማስታጠቅ በከፍተኛ ደረጃ ስትረዳ የነበረችው ግብጽ
ነበረች።
በምስራቁ ጦርነት ጊዜ በ1969 ዓ.ም ጅጅጋ ነበርኩ። ቅኝት ወጥተን የማረክነው ሐኪም የተባለ የግብጽ ጦር መሳሪያ ነበር። በዛው ጦርነት ወቅት ግብጾች ሶማሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ እጅግ ደስተኞች ሆነው በፊት ከሰጧቸው ሌላ ታንክ መድፍ ቢ.ኤሞችና የተለያዩ ጦር መሳያዎችን ይረዱ ነበር። በዚህም ሳይወሰኑ አረብ ሀገራትን አግባብተው ገንዘብና ሌሎች እርዳታዎችን ለሶማሊያ እንዲሰጡ አድርገዋል። የዚያን ጊዜ በነበረን መረጃ ይሄን ሁሉ እናውቅ ነበር።
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት ጦርነት በአንድ ወቅት የቲ 55 ታንክ ጥይት እጥረት ነበረባቸው። ምክንያቱም ሶቪየት ህብረት ነበረች የምትረዳቸው። እነሱን ከሶማሊያ ሲያባርሩ ሌሎች አረብ ሀገሮች ናቸው ያንን ጥይት መስጠት የነበረባቸው። ጥይቱን በቦይንግ 707 አውሮፕላን ጭነው ናይሮቢ (ኬንያ) አርፈው ከናይሮቢ ወደ መቋዲሾ ሊሄዱ ነበር። የኢትዮጵያ ደህንነትና ወታደራዊ መረጃ ከፍተኛ ክትትል ያደርግ ስለነበር ደርሶበት ለኬንያ መንግስት አስታውቆ የኬንያ መንግስት ያንን እዛው ይዞ እንዳይሄድ አደረገው። የእነሱ ሴራ እስከዚህ ድረስ ነው። ጎረቤት ሀገሮችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሲፈጽሙ የነበረው ሴራ እጅግ በጣም ብዙ ነው። ሲወጉት፤ ሲያቆሰሉት፤ሲገድሉት የኖሩት የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው። ሶማሊያ ኢትዮጵያን እንድትወር እንድትወጋ ግፊት ያደረጉት ግብጾች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጾች በኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ ለመፍጠር ሰፊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ በስፋት ይታወቃል፤ እንዴት ይመለከቱታል?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- ይሄ የኖሩበት ስራ ነው። በቅርብ ጊዜ ስታያቸው አንዳንድ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶችን፣ አክቲቪስት ነን የሚሉ ለሆዳቸው ያደሩ በገዛ ሀገራቸውና ሕዝባቸው ላይ የዘመቱ የተገዙ ባንዳዎችን ከሚገመተው በላይ ገንዘብ እያፈሰሱላቸው ሀገር ውስጥ ትርምስና ብጥብጥ እንዲሁም ሁከት እንዲነሳ ሲሰሩ ቆይተዋል፤ ዛሬም እየሰሩ ነው። ወደ ሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ስንመለስ የግድቡን ውሀ አሞላል በተመለከተ ተስማምተውበት ያለቀ ነገር ነበር። አሁን በኢትዮጰያ ውስጥ አለመረጋጋት አለ፤ ይሄን እድል እንጠቀምበት በሚል ነው እየዘመቱብን ያሉት። ግብጽ ይሄን አጋጣሚ ልጠቀምበት በሚል ነው እየሰራች ያለችው። የትም አይደርሱም። ኢትዮጵያ ሁሉንም ሴራ በጣጥሳ በአሸናፊነት ትወጣለች።
አዲስ ዘመን፡- የግብጽ መሪዎች እንደሚዝቱት ድንበር ስለማንጋራ የፊት ለፊት ጦርነት መግጠም አይችሉም። በምን መልኩ ነው ስለጦርነት የሚያወሩት?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- የግብጽን ወታደራዊ ሁኔታ ካየነው እልፍ መሳሪያ ሊታጠቁና ሊሸከሙ ይችላሉ። የራሳቸውን ስናይ በረሀ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን እንኳን ማሸነፍ አልቻሉም። የግብጽ ሠራዊት ከእሥራኤል ጋር በነበረው የስድስቱ ቀን ጦርነት እንደገናም በዮም ኪፑር ጦርነት እኤአ በ1971 ታይቷል። ተዋጊነት የላቸውም። እኛ ኢትዮጵያውያን ጦርነትን በተመለከተ በተፈጥሯችን ተዋጊዎች ነን። የፈለገው ነገር ቢመጣ ግብጾች ደፍረው የኢትዮጵያን መሬት አይረግጡም። በጦርነት ውስጥ አሸናፊ የሚያደርግህ ተዋግተህ መሬትን መያዝ ነው። እነሱ ያሉት በረሀ ውስጥ። እኛ ያለነው ተራራ ላይ። እንኳን ግብጽ ጣሊያን ያንን ሁሉ መርዝ ረጭቶ ታንክ፣ መድፍና አውሮፕላን አሰልፎ ያውም በዛ ዘመን እኛን ማሸነፍ አልቻለም። የአባቶቻችን ተጋድሎ ታላቅ ነው። ሶማሊያ በግብጽ ዋነኛ አጋዥነት ያንን ሁሉ እጅግ ዘመናዊ የተባለ የሰማይና የመሬት መሳሪያ አንጋግቶ በኢትዮጵያ መሬት ረግፎ መቀበሪያው ሆነ እንጂ አልወጣም። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ ትናንትናው ቁጥሩ ትንሽ አይደለም። በእኛ ጊዜ ያልነበሩ እጅግ ዘመናዊ የአየርና የምድር መሣሪያዎችንና ሚሳኤሎችን የታጠቀ ሠራዊት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ ግዙፍና ትልቅ ሠራዊት ነው። 110 ሚሊዮን ለሀገሩ የሚዋጋ እና ለመሞትም የተዘጋጀ ጥቃትና መደፈርን የማይቀበል ጀግና ሕዝብና ሠራዊት አለን። እንኳን
በከፍተኛ ደረጃ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ታጥቆ በአራቱም ማዕዘናት ሀገሩን እየጠበቀ ያለው ሠራዊታችን እያለ በሀገር ላይ አንድ ነገር ተነሳ ቢባል አሁን ያለው የቀድሞው ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ገብቶ ይዋጋል። ስለዚህ የግብጾች ልፈፋ ከንቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአየር ውጊያ ግምት ውስጥ ይገባል?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- ይሄ ሁሉ አይሆንም። ኢትዮጵያ ድረስ በተዋጊ ጀቶች ለመምጣት አይችሉም። አየር ላይ ነዳጅ የሚሞላ አውሮፕላን የላቸውም። የእኛ አጎራባች በሆኑ ሀገሮች ላይ የጦር ሰፈር ለመገንባት አቅደው መሬት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ነበር። አላማቸው ምን እንደሆነ ኢትዮጵያ ታውቃለች። ግብጾች የጦር ሰፈሮችን ለመገንባት ሱዳንን፣ የመንንና ሶማሊያን መሬት ጠይቀዋል። ለዚህም ብዙ ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጧቸው በመግለጽ ሲያግባቧቸው ነበር። መሬት ካገኙ ለጦር ጀቶቻቸው ማረፊያና መነሻ እንዲሁም የተለያዩ ተዋጊ ክፍሎችን ማለትም እግረኛ፣ ታንከኛ፣መድፈኛ፣ ሜካናይዝድና የአየር መቃወሚያ ባትሪዎችን በኢትዮጵያ አጎራባች ሀገራት በማስፈር ኢትዮጵያን በ360 ዲግሪ የከበባ ቀለበት ውስጥ አስገብተው በፈለጉ ሰዓት ጦርነት ለመክፈት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ለማድረግ ነበር እቅዳቸው። ይሄንን የምታውቀው ኢትዮጵያ ምንጊዜም ዝግጁ ነች። ግብጾች ኢትዮጵያ ላይ በዚህ መልኩ ጦርነት ካሰቡ ግብጽ የምትባል ሀገር ጭርሱንም አትኖርም። ከሱዳን በለው ከየመን ወይንም ከሶማሊያ መሬት በመነሳት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት ማሰብ አለም አቀፍ ወንጀል ነው። ሀገራቱ ግብጽ ኢትዮጵያን እንድትወጋ ፈቅደው የጦር ሰፈር ከሰጡ ትልቅ ወንጀል ነው የሚሆነው። በሌላ መልኩ የአየር ድብደባ ቢያስቡ እንኳን የኢትዮጵያን ድንበር ከራዳር እይታና ቁጥጥር ውጭ ሁነው ሊያልፉት አይችሉም። ይሄንንም ተወው። አይሆንም እንጂ ገና የግብጽ ጀቶች ኢትዮጵያን መደብደብ አስበው ከካይሮ ወይ ከአሌክሳንደርያ ሲነሱ በደቂቃዎች ውስጥ የአስዋንና የናስር ግድቦች ከመኖር ወደ አለመኖር ይለወጣሉ። ግብጽ ነበረች የምትባል ሀገርና ታሪክ ሆና ትቀራለች። በኢትዮጵያ ላይ ዝንተ አለም ሲሰሩት የነበረው ሴራ በዚሁ ይደመደማል። አላርፍ ካሉ ሌላም ከባድ መሳሪያ አለን። የራሳችንን ለአባይ ውሃ የሚሰጡ 90 ገባር ወንዞቻችን በሙሉ በያሉበት ቆርጠን ለልማት እናውላቸዋለን። አሁንም ቢሆን ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ ሲሰሩት የኖሩትን ወንጀል ማቆም አለባቸው። ከዚህ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም ተከባብረው መኖር ነው የሚበጃቸው። ይሄ ሁሉ መወራጨት ኢትዮጵያን ካለማወቅ የተነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጾች የሚራወጡት ኢትዮጵ ያን በሚገባ ካለማወቅ የተነሳ ነው ያሉትን ቢገል ጹት?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- አዎ የተሳሳተ ግምት ነው ያላቸው። ሊሆን የማይችል ነገር ነው። የአውሮፕላን ድብደባን ከወሰድን የተወሰነ ትንሽ ቦታ ላይ ነው የሚያርፈው። ሀገር የሚያጠፋ ነገር አይደለም። ለዚህ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ደርግ ጊዜ አይደለም። በከፍተኛ ደረጃ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚወነጨፍ ሚሳኤልና ድንበሩንም በራዳርና እጅግ በመጠቁ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በሆኑ አየር መቃወሚያዎች አጥሮ ነው የሚጠብቀው። የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ የመግባት ድፍረቱና ብቃቱ የላቸውም። እኛ በ1969 ዓ.ም ከሶማሊያ ጋር ስንዋጋ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሚግ 21 የሚባል የጦር ጀት ከኤፍ 5 በጣም የበላይ የሆነ አውሮፕላን ስለነበር በዛ ነው የሶማሊያን አውሮፕላኖች ከአየር ላይ አጥፍተን የበላይነታችንን ያረጋገጥነው። በፍጹም አያደርጉትም። የበለጠ ተጎጂዎቹ እነሱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጾች በውክልና ጦርነት ኢትዮጵያን ከጥንት እስከ ዛሬ በጀት መድበው ሲወጓት እንደኖሩ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሄን እንዴት ያዩታል?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- በዚህ ጉዳይ ረዥም ዘመን ሲሰሩበት ኖረዋል። ዛሬም አላረፉም። በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱን በሁለት አምድ ነው መውሰድ ያለበት። ትልቁና ዋነኛው የዲፕሎማሲ ጦርነቱን በከፍተኛ ደረጃ ማካሄድ አለበት። በዚህ ረገድ ከድሮ ጀምሮ የራሳችንን በየመስኩ የነበሩ ብቁ ባለሙያ ዜጎች ያላቸውን አቅም በሚገባ ያለመጠቀም ችግር አለብን። ኢትዮጵያ ብዙ ብዙ የበቁ ሰዎች አሏት። ዘመን ሲቀየር ከባድ የሆኑ ሰዎችን ወደኋላ ሄደን አምጥተን ምክራቸውንና አስተያየታቸውን አንቀበልም። ለምሳሌ ዶክተር ምናሴ ኃይሌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። የታወቁ ምሁር ናቸው። ዛሬም በሕይወት አሉ። ዶክተር
ጎሹ ወልዴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበሩ። በጣም አንደበተ ርቱዕና የሰከኑ ዲፕሎማት ናቸው። ዶክተር አሻግሬ ይግለጡ እንዲሁም ዶክተር ካሳ ከበደ አለ። ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስም አለ። በጣም ብዙ ነባርና ታዋቂ ዲፕሎማቶች አሉን። ኢትዮጵያ አይደለም እውቀታቸውን ሕይወታቸውን ለሀገራቸው የማይሰስቱ ብዙ ሚሊዮን ልጆች ያሏት ሀገር ነች። እነዚህንና ሌሎችንም በጡረታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ጠርቶ ተወያይቶ ለዲፕሎማሲው ስራ በአለም ዙሪያ ማሰማራት ነው። እድሜ ዘመናቸውን ግብጽንና ሴራዋን ጠንቅቀው ያውቃሉ። የምዕራቡን አለም ዲፕሎማሲ ኖረውበታል። እነዚህና ሌሎችም ነባር ዲፕሎማቶች በአለም ዙሪያ ተሰማርተው ስለታላቁ ሕዳሴ ግድብና የኢትዮጵያን ሕጋዊ የመልማት መብት ለአለም በማስረዳት ከፍተኛ ድጋፍ ለኢትዮጵያ በማስገኘት ረገድ ትልቅ ስራ መስራት ይችላሉ።
አሁን ካሉት ጋር ተነጋግሮ መጀመሪያ አንድ የልኡካን ቡድን በተፋሰሱ ሀገሮች ሄዶ ማስረዳት አለበት። ሁለተኛ ለአፍሪካ ሕብረት፣ ሶስተኛ ጊዜው እንደ ደርግ ጊዜ እንደሆነው አይደለም። የቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ነው። አሜሪካ፣ ቻይና እና ራሽያ አሉ። አሜሪካ ብትጠላን የምንታከከው የምንጠጋው ወዳጅ አለን።
ወዳጆቻችን በሆኑ ሀገሮች ላይ ሁሉ ሰፊ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ማድረግ አለብን። በውጭ ሀገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በያለበት የአባይን ግድብ በተመለከተ ለሀገሩ ዲፕሎማት ሆኖ መስራት፤ አውሮፓ ሕብረት ላይም መድረስ አለበት። እነሱ የሚበልጡን በዚህ ነው።
ይቅርታ ይደረግልኝና አምባሳደር የሚባሉ ሰዎች ይሄንንና ኢኮኖሚ ነክ ነገሮችን ነው መስራት ያለባቸው። ነባር አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እውቀትና ልምዳቸው ለሀገር ይጠቅማል። እነሱን አሰባስቦ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንዲያግዙ፣ እንዲያማክሩና አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ ለሀገርም ለመንግስትም ይጠቅማል። የሀገር ሀብት ናቸው። ከዲፕሎማሲ ግንባሩ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቁ ነገር መከላከያውን የሚመለከተው ነው። ከፍተኛ በጀት ሊመደብለት ይገባል። አሁን ካለበትም በላይ መደራጀት አለበት።
የበለጠ አቅሙን ዝግጁነቱን እያጎለበተ እያሣደገ መሄድ አለበት። ዋናው የጦርነት መርህ በሰላም ቀን ያለማቋረጥ ለጦርነት ተዘጋጂ የሚለው ነው። ሌላው በሰላም ቀን በትምህርትና በማያቋርጥ ወታደራዊ ስልጠና ውስጥ የሚፈሰው ላብ በጦርነት ውስጥ ሊፈስ የሚችለውን ደም ይቀንሳል የሚለው ነው። ዘመኑ የሳይበር ቴክኖሎጂ ጦርነት ዘመን ነው። ብዙ ነገር ተለውጦአል። ከዚህ አንጻር እየበቁ መሄድ ነው። አሜሪካ ሱዳንን ሽብርተኛ ብላ የፈረጀቻት ጉዳይ ነበር። ሳኡዲ አረቢያ ደግሞ ግዴለሽም እኔ ወዳጅ ስለሆንኩ አሜሪካንን አሳምኜ ውሳኔውን አስነሻልሻለሁ፤ ከኢትዮጵያ ገለል በይ ከግብጽ ጎን ቁሚ እረዳሻለሁ የሚል ማባበያ እየሰጠቻት ነው። በዚህ ምክንያት ነው ሸርተት እያለች ያለችው። ምንድነው ማድረግ ያለብን ስንል ሱዳን ሸርተት ስትል በአሁኑ ሰዓት በአካል ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ወስደን ጠረፋችን ላይ ማስቀመጥ አለብን። ከወዲያም አሻጥር ለመፈጸም ግዳጅ ተቀብለው የሚገቡ አሉ። በዚህ መልኩ ሱዳንንም እንድታስብ ታደርጋታለህ ማለት ነው።
በአሁኑ ሰዓት በያኔው የማምታታት ነገር የተነሳ የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ መሬት ውስጥ ካለ በአስቸኳይ ውጣ ተብሎ 12 ሰዓት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት እንዲወጣ ማድረግ ነው። ካልወጣ ክበበውና አምጥተህ እሰረው። ይሄም አንድ መደራደሪያ ነው። ይሄንን አስቀድመህ ካስቀመጥክ እንዲያስቡ ታደርጋቸዋለህ። መልዕክቱ ኢትዮጵያውያኑ ከተነኩ የማይመለሱ መሆኑን ያሳያል። በተዋጊነትም ያውቁናል። ሁለተኛ የኢትዮጵያን ሕዝብ በትክክል ልትነግረው ይገባል። እንዲህ እንዲህ ለማድረግ ግብጾች ያሰቡት ነገር ስላለ በአለህበት ቦታ ተዘጋጅ፤ ውስጥህ የሚሽለኮለኩትን ባንዳዎችን አጋልጥ ተብሎ ጥሪ ሊደረግለት ይገባል።
ሕዝቡ በአካባቢው ያለውን ነገር ያውቃል። ተከታትለህ ያዝ፤ ለመንግስት አሳልፈህ ስጥ ቢባል የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ያደርገዋል። ቀጥሎ መደረግ ያለበት በዚህ የሚነግዱትን ባንዳዎችና አክቲቪስቶችን አደብ ማስገዛት ነው። እነዚህን ሰዎች በተመለከተ በቂ ማስረጃ ስላለ ያለይሉኝታ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ይገባል። ምን እስኪያደርጉ ነው የሚጠበቀው። ሀገርና ሕዝብ እያባሉ፤ ሰላሙን እየነሱ፤ ሽብርና ሁከት እየነዙ እስከመቼ ይቀጥላሉ? መረጃ አሳልፈው ይሰጣሉ። ገንዘብ እየበተኑ አሁንም በተለያየ ቦታ እያደራጁ ነው። ይሄ ስውሩ የእነግብጽ እጅ ነው። ይሄ መልእክት ለእነሱም ይደርሳል።
ሌላው ነገር አባይ ግድብ ላይ ብቻ አይደለም
ትኩረት የሚሰጠው። ስትራቴጂክ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። እዚህ ላይ የሀገር ምስጢር ስለሆነ ይሄ ቦታ፤ ይሄ ቦታ ብዬ አልናገርም። መከላከያ ቢጠይቀኝ ልናገር እችላለሁ። እኛ ዛሬ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለነው። ሀገሪቷ በቂ ሠራዊት አላት። እኔ ያኔ በጦርነት ጊዜ ከታጠቁት የተሻለ መሳሪያ አለ። የተሻለ አውሮፕላን ከሁሉም በላይ ደግሞ ትልቁ ኢትዮጵያዊ ወኔ አለ። ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሄር ነች። ማንንም ጎድታ አታውቅም። የዛሬውን አትመልከት። እንግሊዝ ረሀብ በገባበት ጊዜ እኮ ስንት ፓውንድ እንደሆነ አላውቅም ኢትዮጵያ ረድታለች። ለጆርዳን ለሊቢያ ረድታለች። ይሄ ተጽፎ የሚገኝ ነው። ለሌላም ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የረዳች ሀገር ነች። ደቡብ አፍሪካን፣ ዚምባቡዌን፣ ደቡብ ሱዳንን በወታደራዊ ኃይል ያሰለጠነች፤ ለነጻነታቸው ያበቃች ታላቅ ሀገር ነች ኢትዮጵያ።
አዲስ ዘመን፡- ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚነዛውን የግብጽ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ በተመለከተ ሕዝቡና ወጣቱ አንድነቱንና ሕብረቱን ጠብቆ እንዲሄድ ምን ማድረግ አለበት?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- እኔ በወጣቱ ላይ ትልቅ እምነት አለኝ። በብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች በሀገር ላይ አደጋ ሲጋረጥ ዳር ከዳር ሕዝቡ በአንድ ላይ ተነስቶ የመቆም ጠላቱን የመመከት የካበተ ልምድ አለን። ይሄ አሁን የሚታየው የእርስ በእርስ መጠላለፍና መቃረን የትም አይደርስም። ይቆማል። የትልቅ ሀገር ልጆች እርስ በእርስ ልንባላ አይገባም። በኢጣሊያ ወረራ፣ በሶማሊያ ወረራ ጊዜም የሆነው ይሄው ነው። አሁን ያሉት ተቃዋሚዎች በሀገር ሕልውናና ደህንነት ላይ ከተነሱ ሕዝቡ አንቅሮ ይተፋቸዋል። የሚከፋፍለንን ማንንም አንቀበልም።
በመንግስት በኩል የሚጠበቀው ለሀገር ሕልውና አደጋ የሚሆኑትን ለሕዝብ ማሳወቅ ነው። ሕዝቡ በግልጽ ሲያውቅ ሙሉ በሙሉ በአካል ይሰለፋል። ተቸግሮም ቢሆን ጦርነት እንኳን ቢነሳ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ይሄንን በተለያየ ጊዜ በተግባር አይተነዋል። የኢትዮጵያ ልጆች በሀገር ሕልውና ላይ ችግር ሲመጣ ልዩነቶቻቸውን ሁሉ ወደጎን ጥለው በአንድነት ይቆማሉ። በአንድነት ይዘምታሉ። ይዋጋሉ። ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ይሰጣሉ። ወኔያቸውም የላቀ እንደ እሳት ወላፈን የሚጋረፍ ነው። የእሥራኤልና የግብጽን የስድስት ቀን ጦርነትና የዮም ኪፑርን ውጊያ አንብቤዋለሁ። ፊልሙንም አይቼዋለሁ። በጦርነቱ የተካፈሉት እሥራኤሎች አስተምረውኛል። በብቃት፣ በተዋጊነት፣ በጀግንነት፣በሞት አይፈሬነት ግብጾች ኢትዮጵያውያን አጠገብ አይደርሱም። እውነቱ ይሄ ነው። አይመጡም እንጂ ኢትዮጵያ ከመጡ መቀበሪያቸው ነው የሚሆነው። ይቅርታ ይደረግልኝና ባለፈው በአባይ ውሃ ላይ ድርድር ተብሎ አሜሪካን መሄድ አልነበረብንም። ማነች አሜሪካ? በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ያጋለጠችን ነች። በሶማሌ ጦርነት አሳልፋ የሰጠችን ያስወጋችን ሀገር ነች። አሁን ደግሞ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አደራዳሪ ሆና ገብታ የያዘችውን አቋም አይተናል። የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሩን ጥቅምና ሕልውናለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን እያሳየ ነው። እንዲህ ቁርጥ ያለ አቋም ሲይዝ ሁላችንንም ጨምሮ ቆራጡና ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዘብ ይቆማል፤ ይሰለፋል።
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ሕዝቡ ያለውን አዋጥቶ፣ እናቶች ከመቀነታቸው ፈተው የገነቡት ነው፤ ኢትዮጵያውያን ነን እያሉ ከግብጽ ጋር ያበሩትን እንዴት ያዩአቸዋል?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉትን መቀሌ እየሮጡ የሚሄዱትንም አይተናል። አበል እየተከፈላቸው ትልቅ ገንዘብ እያገኙ ነው የሚሄዱት። ይሄ ንግድ ነው። ሰው በሀገሩ ላይ እንዴት እንዲህ ያደርጋል? በቀድሞው ሠራዊት ውስጥ ስማርና ስሰለጥን ከራስ በላይ ለሀገር መቆም እንዳለብን ነው የተማርነው። ሁልጊዜም ቅድሚያ የምንሰጠው ለሀገር ነው። የግል ጥቅም ከታች ነው። ለሀገር የሚሰሩ ከሆነ እንዴት ከጠላት ጋር ያብራሉ? እንዴትስ ከጠላት ገንዘብ ይቀበላሉ? ይህ የትም አይደርስም። ለኢትዮጵያ እስካልበጁ ድረስ መንግስት ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል። በሀገር ጉዳይ ለሚመጣ ነገር ምንም ምህረትና ይሉኝታ የሚባል ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዘመን ጦርነት አዋጪ ነው?
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- በእኛ በኩል ዲፕሎማሲያችንን በከፍተኛ ብቃት ከተጫወትን ይሄ ውሃ ከኢትዮጵያ እየመነጨ ኢትዮጵያ ድሃ ሆና 65 በመቶ ሕዝባችን የኤሌክትሪክ ኃይል የሌለው በተዳፈነ ጨለማ ውስጥ የሚኖር ሆኖ እያለ ግብጽ ኢትዮጵያን ልውጋ ብላ ብትነሳ ከአለም ሀገሮች ሁሉ ውግዘት ይደርስባታል። አይቀበሏትም። ግብጾች ጦርነት እንደማያዋጣቸው ስለሚያውቁ በማስፈራራት፤ በውስጣችን ቅጥረኞችን በመግዛት ትርምስ ፈጥሮ የተጀመረውን የእድገት ጎዳና ወደፊት እንዳይገፋ ለማድረግ ነው እየሰሩ ያሉት። ግብጾች አረብ ሀገራት ለኢትዮጵያ እንዳይረዱ ጭምር ያግባቧቸዋል። በጃንሆይ፣ በደርግ ዘመን ዛሬም ይኸው ነው ስራቸው። ኢትዮጵያ አድጋ በልጽጋ ለምታ ማየት አይፈልጉም።
አድገን እያንዳንዱን ጠብታ ውሃ የምንሸጥ ነው የሚመስላቸው። ይሄ የኢትዮጵያውያንን ባሕሪ አለማወቅ ነው። የእኛ ሕዝብ ደግ፣ ያለውን የሚያካፍል፣ አብሮ መብላትማ መጠጣት የሚወድ ነው። ማጣቱ ነው እንጂ የሚይዘው ቸርና ለጋስ ሕዝብ ነው። የዛኑም ያህል ደግሞ በሀገሩ ከመጡበት ተዋጊና ጀግና፣ ለሕይወቱ የማይሳሳ፣ ምንም ነገር የማይበግረው፣ ብርቱ፣ ጠንካራና ጦረኛ ሕዝብ ነው። ግብጾች እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ስግብግብነት አለባቸው። ኢትዮጵያ እሳትም እሳተ ገሞራም ነች። አይችሏትም። ገና ከዚህም በላይ የምትሄድ፤ የምታድግ ሀገር ነች። በእኛ ዘመን የኢትዮጵያን ታላቅነትና ትንሣኤ እናየዋለን። ለመንግስት የምመክረው ከአሁኑም የበለጠ ቆራጥ አቋም እንዲይዝ ነው። ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክሮ ይስራ። ጠረፎቻችንን በምድርም በአየርም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይጠብቅ። ለሕዝቡ በደምብ ይንገረው ተዘጋጅ ይበለው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።
ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
ወንድወሰን መኮንን