ምድራችን የሰው ልጅ መኖሪያ ከመሆኗ በፊት በተፈጥሮና በእንስሳት ሀብቶች የተሟላችና እጅግ የበለጽገች እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። የሰው ልጅ ሕይወት በምድር ላይ ከሚገኙ እስትንፋስ ካላቸው ነገሮች የእንስሳት፤ የውሃ ውስጥ ፤ የከርሰ ምድር ረቂቅ አካላት ፤ የእፅዋት ዓይነቶች ወዘተ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳሰረ ነው።
በዚህ የሕይወት ዑደት ውስጥ የሚገኘው የሰው ልጅ መሰረታዊ የሆኑ የምግብ፣ የልብስ እና የመጠለያ ፍላጎቶችን ለማሟላት በሚያደርገው ሂደት የብዝሃ ሕይወት ሀብቶች እየቀነሱና እየተመናመኑ መምጣታቸው ይነገራል ። የዓለም ህዝብ ሙሉ በሙሉ ከምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶቹ 97 በመቶውን የሚያሟላው በጥቅሉ መሬት ብለን ከምንጠራው የተፈጥሮ ሀብት እንደሆነና ቀሪውን ደግሞ ከውሃ አካላት እንደሚያገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የብዝሕ ሕይወት ስብጥር የተለያየ ነው። ኢትዮጵያ የተለያዩ መልክአ- ምድር አቀማማጥና የአየር ንብረት ያላት ሲሆን ለቁጥር የሚያታክቱ የብዝሃ ሕይወት ስብጥር አላቸው ከሚባሉት ሃያ ሀገራት ውስጥ የምትጠቀስ ናት። ቫቪሎቭ የተባለ የሩስያ ሳይንቲስትም ከፍተኛ ተለያይነት ያላቸውና መነሻ የሆኑ ሀገራትን ሲለይ በዓለም ከሚገኙ 12 ሀገራት ውስጥ አንደኛዋ ኢትዮጵያ እንደሆነች ይጠቅሳል። ከአፍሪካ በዚሁ ሀብት ከሚታወቁት አምስት ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደምትጠቀስም መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ ልዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲኖራት አድርጓታል ተብለው እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ የፀሀይ ብርሃን ከሚገኝበት የምድር ወገብ አካባቢ በቅርበት መገኘቷ እና ከባሕር ወለል በታች 116 ሜትር /ዳሎል/ እንዲሁም ከባህር ወለል በላይ በተለያየ ደረጃ እስከ 4620 ሜትር ከፍታ /ራስ ዳሸን/ ያላቸው ቦታዎች (altitudinal difference) በስፋት መኖር በንጽጽር ሲታይ የተለያዩ የአየር ንብረቶች እንዲፈጠሩ ማድረጉ ነው። በተጨማሪም በርካታ ወንዞች እና ሐይቆች በመኖራቸው ሰፊና ከፍተኛ የተለያይነት ስብጥር ያለው የብዝሀ ሕይወት ሀብት የሚገኝባት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የብዝሀ ሕይወት ክምችት በስፋት በሚገኝበት የምድር ወገብ አካባቢ ባሉ ሀገራት የጎላ ጠቀሜታ ያላቸው የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች በከፍተኛ ፍጥነት በመመናመን እና በመጥፋት ላይ እንደሚገኙ በየጊዜው የሚወጡ ጥናቶች ያሳያሉ።
በዚህም የተነሳ በዓለም ዙሪያ ብዝሃ-ህይወት በእጅጉ ቀንሷል። የሰው ልጅ የአካባቢ ጥበቃን ሳያገናዝብ የሚያደርጋቸው ተግባራት ተከትለው በተከሰቱት ሁኔታዎች የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ (global climate change)፣ የድርቅ እና ምድረ በዳነት መስፋፋት፣ ከምጣኔ ሀብት ዕድገት ጋር ያልተመጣጠነ የህዝብ ቁጥር መጨመር ወዘተ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ናቸው።
ኢትዮጵያ ባሏት የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ብርቅዬ የብዝሀ ሕይወት መገኛ ሀገር ብትሆንም ይህ የተፈጥሮ ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የመመናመን ችግሮች እየደረሰበት እንደሚገኝ ጥናቶች ያመለክታሉ። በየጊዜው እያደገ ያለውን የሕዝብ ቁጥር ፍላጎት ለማርካት ሲባል ከፍተኛ መጠን ያለው የብዝሀ ህይወት ሀብት ዘላቂነትን ባልተከተለ ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ በተለይም በሀገራችን ብቻ በሚገኙ የብዝሀ ህይወት ሀብቶች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። በይበልጥም የመኖሪያ አካባቢ መለወጥ (habitat change)፣ ከልክ በላይ መጠቀም(over exploitation)፣ የአየር ንብረት መለወጥ (climate change)፣ ብክለት (pollution)፣ ወራሪ መጤ ዝርያዎች (alien invasive species) እና ልውጠ ህያዋን ዝርያዎች (genetically modified organisms) መስፋፋት በብዝሀ ሕይወት ላይ የጎላ ተፅዕኖ በማድረስ ኢኮኖሚንና የሕይወትን መኖር የሚደግፈውን ተፈጥሯዊ ሥርዓት ሊያገግም በማይችልበት ሁኔታ እየጎዱት ይገኛሉ። በተለይ ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ኅብረተሰብ ዘንድ የብዝሀ ሕይወት ጠቀሜታን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ለዚህ ሀብት መመናመንና መጥፋት መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው።
ብዝሀ ሕይወት ለሥነ ምህዳር መጠበቅ፤ አካባቢን ለዘለቄታው ለመጠበቅ፤ የተፈጥሮ ኡደት እንዲቀጥልና የፍጥረታት ህልውና ዋስትና እንዲኖረው በማድረግ የላቀ ሚና ይጫወታል። ዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ስምምነት እ.ኤ.አ በ1992 ከመፈረሙ በፊት ሀገሮች የብዝሀ ሕይወት ሉአላዊነት አልነበራቸውም። የአንዱ ሀገር ብዝሀ ሕይወት ሀብት በዘፈቀደና ያለ አንዳች ፈቃድ ወደ ሌላው ሀገር ይዘዋወርም ነበር። ከስምምነቱ በኋላ ግን ሀገራት የብዝሀ ሕይወት መብታቸውን ማስከበር የቻሉ ቢሆንም የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች በተገቢው ተለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል።
ብዝሀ ሕይወት ምንድን ነው?
ብዝሀ ሕይወት በመሬት ላይ ያሉ ሁሉም ስነ-ህይወታዊ ሀብቶች ፤ እጽዋት ፤ እንስሳትና ደቂቅ አካላት እንዲሁም በውስጣቸው የያዟቸውን ዘረመሎችና እነዚህ የሚፈጥሯቸውን ውህዶች የሚያካትት ነው፤ በዓለም ላይ ያለ ህያው ዝርያን ያካተቱ ዛፎች፤ የሣር ዝርያዎች፤ ቁጥቋጦዎች፤ በራሪ አእዋፅፍት፤ ባክቴሪያዎች፤ ትላትሎች፤ ተሳቢና ተራማጅ እንስሳት፤ በውሃ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታትን ጨምሮ የሁሉም ህይወት ያላቸው አካላት ስብስብን ያካተተ የተለያዩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች መጠሪያ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ በመቋቋም የመኖር ሂደት ሰው-ሰራሽና ተፈጥሯዊ የሆኑ ሥርዓቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚረዱ ተግባራትን ያካተተ ነው። ብዝሀ ሕይወት የሚወሰነው በአየር ንብረት የመለዋወጥ ሁኔታ፣ የቦታው የምርታማነት ሁኔታ፣ ቀደም ብሎ የነበረው የብዝሀ ሕይወት ሁኔታ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች እርስ በራሣቸው የሚኖራቸው ግንኙነቶች መጠንና ተያያዥ የመሆን ሁኔታ ወዘተ ላይ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጸደቀው ዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ስምምነት አገላለጽ መሠረት ብዝሀ ሕይወት በሁሉም የመገኛ ሥፍራዎች ማለትም ከየብስ፣ ከባሕርና ሌሎች ውሃማ ሥርዓተ ምህዳሮች እና በመካከላቸው ባለው ሥነ-ምህዳራዊ መስተጋብር በሚገኙ ሕይወት ባላቸው ነገሮች መካከል ያለው ተለያይነት ነው። ይህም በዘረመል (genes) በተለያዩ ዝርያዎች (Species) እና በሥርዓተ ምህዳሮቻቸው (Ecosystems) መካከል ያለውን ተለያይነት ያጠቃልላል። በዚሁ ዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ስምምነት ከብዝሀ ህይወት አጠባበቅ እና አጠቃቀም ጋር ተያያዥ የሆኑ የማህበረሰብ ባህሎች (social culture)፤ ልምዶች (customs) እና ነባር ዕውቀትም (indigenous knowledge) ለብዝሀ ሕይወት መጠበቅ ያላቸውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው እና የብዝሀ ሕይወት ትርጉም አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል። በመሆኑም ብዝሀ ሕይወት የዘረመል፤ የዝርያ፤ የሥርዓተ ምህዳር እንዲሁም ተያያዥ የማኅበረሰብ ባህል እና ማኅበረሰባዊ እውቀት ጥንቅር መሆኑን ያሳያል።
ብዝሀ ሕይወት ምን ጥቅም ይኖረዋል
ብዝሀ ሕይወት ለሰው ልጆች በቀጥታው ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚገመቱ ነጻ አገልግሎት ይሰጣሉ። ሚዛኑን የጠበቀ ብዝሀ ሕይወት ለእያንዱንዱ የሰው ልጅ በርካታ አገልግሎቶንች ይሰጣል። ብዝሀ ሕይወት እንደነበረ ወይም እሴት በመጨመር መጠቀም ከሚሰጠው አገልግሎት ምግብ ፤ ለመድሃኒት፤ ለጥሬ እቃ አቅራቢነት፤ ለሀይል ምንጭነት፤ ለግንባታ ፤ለልብስ ወዘተ— መጥቀስ ይቻላል።
በተጨማሪም ቆሻሻን በማፅዳት፤ የአየር ሚዛንን በመጠበቅ ፤ኦክስጂንና እርጥበትን በማመንጨት፤ የንጥረ ነገሮች የውሃ ኡደትን በማቃጠል ፤ የአፈር ለምነትን በማስጠበቅ ህይወት በዓለም ላይ እንዲቀጥል አመቺ ሁኔታን በመፍጠር፤ ባህላዊና ማህበራዊና አገልግሎቶች ከሚሰጣቸው ጥቅሞች ጥቂቶቹ ናቸው፡፤
በብዝሀ ሕይወት ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ሂደት እየተከሰተ ያለውን የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ ወይም ተስማሚ ለማድረግ ህዝቡ ለጤናና በምግብ እራሱን እንዲችል በማድረግ የሚያበረክተው አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው።
የብዝሀ ሕይወት የሚጎዱበት ምክንያቶች
የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች ለሰው ልጅ ህልውና ለአካባቢ አየር ምቹነት፤ በተፈጥሮና በሰው ልጅ መስተጋብር ዙሪያ ሚዛን ለመፍጠር የሚሰጡት አገልግሎት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም የሰው ልጆች በሚያደርጉት ያልተገባ ጥቅምና ጠንካራ የአስራር ሥርዓት አለመኖር ምክንያት የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች እየወደሙ ይገኛሉ።
የሰዎች ብዛት እየጨመረ ሲሄድ እና በተፈጥሮ መኖሪያዎቻቸው ላይ መጠበቁ እየሰፋ ሲሄድ ፣ የሰው ልጆች ጥገኛ በሆኑባቸው ሥነ-ምህዳሮች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እነዚህ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች የዕጽዋት፤ የእንስሳትና የደቂቅ ዘአካላት ፤ ተፈጥሮአዊ ሂደታቸውን ተከትለው ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ ሲገባቸው እጅግ በሚገርም ሁኔታ በመጥፋት ላይ ናቸው።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የብዝሀ ሕይወት ዝርያዎች ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ዳግም ላይመለሱ ከምድረ ገጽ እየጠፉ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው የሰው ልጅ የደን መጨፍጨፍ፣ እርሻ፣ ቤት ግንባታንና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ተብለው የሚካሄዱ ምንጣሮና ቃጠሎ ምድራችንን አደጋ ላይ ጥለዋታል። ህገወጥ አደን ፤ የዱር እንስሳት የመኖሪያ አካባቢዎችን መጉዳት፤ የመጤ ዝርያዎች መበራከት፤ የከባቢ አየር ንብረትና ሙቀት መጨመርና የአካባቢ ብክለት፤ የተፈጥሮ ሀብትና የዱር አራዊት ህይወት አደጋ ላይ በመጣል ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
የብዝሃ ህይወት በአግባቡ አለመያዝና አለመጠቀም በሰው ልጆች በእንስሳት በእጽዋት ህልውና ላይ እጅግ አደገኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያመጣል። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ የበሽታ መስፋፋቶች፤ የወራሪ ዝርያዎች መበራከት፤ የነገሮች መለዋወጥ ዑደት መታወክ፤ የሥነምህዳር መዛባት፤ የጀኒቲክ ሀብቶች ውድመት፤ የአካባቢ ብክለት መከሠት፤ የእጽዋት መዳቀል ሂደት መቋረጥ፤ የከባቢ አየር የማስተካከል ሂደት መዛባትና የምግብ ሰንሰለት መዛባት ሳይጠቀሱ አይታለፉም።
ለወደፊት ምን መደረግ አለበት
የብዝሃ ህይወት ለዘላቂ የህይወት ቀጣይነት ብቸኛው መሠረት ነው። በመሆኑም የሚመጥን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ወሳኝ ነው። በዚህም የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች የምግብ፣ የልብስ እና የመጠለያ በተሻለ ሁኔታ ለማሟላት የብዝሀ ሕይወት ሀብትን በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መጠቀም ብቸኛ አማራጭ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ የሚታይ ነው። አንድ ሀገር ያላት የብዝሀ ሕይወት (የዕጸዋት፣ የእንስሳት እና የደቂቀ አካላት) ሀብት ለግብርናው፣ ለኢንዱስትሪው እና ለጤና ዘርፎች በአጠቃላይ እድገትን ለማፋጠን ለሚከናወኑ የልማት ተግባራት አማራጭ የሌለው የግብአት ምንጭ ነው።
የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስቀመጡት የመፍትሔ ሀሳቦች ተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ማንኛውም አደጋ የሰው ልጅን የሚጎዳ በመሆኑ ብዝሃ ህይወትን ለመታደግ ከግለሰብ እስከ የመንግስት ባለስልጣናት ድረስ እያንዳንዱ ሰው ለህልውናው ዋስትና በመስጠት ተፈጥሮን መታደግ እንደሚቻል ይመክራሉ። ለዚህም የምንጠቀመውን ኃይል መቀነስ፣ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግና በመጠቀም፣ አየርን ከብክለት መታደግ፣ ነዳጅ በመቀነስ ሌሎች የኃይል አማራጮችን መጠቀም ከባቢ አየሩን የማይጎዱ ምርቶችን መጠቀም ፤ በአካባቢ ብዝሃ ሕይወት ላይ የሚደርሱ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ጫናዎችን በመቀነስ ፤ በአካባቢው ለሚገኙ ማህበረሰብ ስለብዝሀ ህይወት ጥበቃና ዘላቂ ጥቅም ግንዛቤን በማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዝሀ ሕይወት ቀን ይከበራል። የዘንድሮው 19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብዝሀ ሕይወት ቀን ‹‹ተፈጥሮ የመፍትሔዎቻችን ምንጭ ናት›› በሚል መሪ ቃል ታስቦ መዋሉን፤ ተፈጥሮ ለሚገጥሙን ችግሮች ሁሉ መፍትሔ የሚገኝባት ስለመሆኑ አጉልቶ ለማሳየት የታሰበ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ የሰው ልጆች የተፈጥሮ ሥርዓትን ሲያናጉ አሁን እንደምናያቸው አይነት የበሽታ ወረርሽኝ፣ የጎርፍ፣ የመሬት መደርመስ፣ በረሃማነትና የመሳሰሉት ችግሮች እንደሚከሰቱ ጠቅሰው፤ የሥርዓተ ምህዳር መዛባት፣ ዘለቄታዊ ያልሆነ የብዝሀ ሕይወት አጠቃቀም እንዲሁም መጤ ወራሪ ዝርያዎች የችግሮች ምንጭ ሲሆኑ በተፈጥሮ ደግሞ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል አመላክተዋል።
በመጨረሻም መፍሔዎችን ከተፈጥሮ ለማግኘት በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የደቂቅ አካላት፣ የአዝርዕት፣ እንስሳት እና የደን የተፈጥሮ ሀብቶችን የመጠበቅ ስራዎች ይከናወናሉ ማለቻቸውን ኢንስቲትዩቱ በማህበራዊ ጽረ-ገጽ ላይ አስነብቧል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2012