ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የሚያዘጋጀው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ ሊካሄድ ዝግጅት ከተጀመረ ሰንብቷል። በዓለማችን ምርጥ አትሌቶች ተሳትፎ እና የፉክክር ደረጃ ከታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ የላቀ ግምት የሚሰጠው ቻምፒዮናውን በ2019 እ.ኤ.አ ላይ የምታስተናግደው የኳታሯ ከተማ ዶሃ ነች።
ለንደን ያለፈውን ቻምፒዮና አዘጋጅ እንድትሆን በአይኤኤኤፍ ምክር ቤት የተወሰነላት በ2011 እ.ኤ.አ ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ከለንደን ጋር በመጀመሪያ ለአዘጋጅነት ማመልከቻ አስገብተው የነበሩት ሌሎቹ ከተሞች የስፔኗ ባርሴሎና እና የኳታሯ ዶሃ እንደነበሩ አይዘነጋም። ኳታር የያኔው ዕድል ቢያመልጣትም አሁን አግኝታዋለች። በዚያ ፉክክር ባርሴሎና በመጀመሪያ ዙር ከአዘጋጅነቱ ወጣችና ለንደንና ዶሃ ተፎካከሩ፡፡ በመጨረሻም በ15 ዓመታት ውስጥ አራት ጊዜ የመስተንግዶ ማመልከቻ ያስገባችው ለንደን ተመረጠች፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ከተካሄደው 30ኛው ኦሊምፒያድ በተለይ በዚያን ወቅት በተለያዩ የሽብር ጥቃቶች እየታመሰች የነበረችው ለንደን ትልቁን የአትሌቲክስ መድረክ ማዘጋጀቷ ትኩረት እየሳበ ነበር፡፡
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ የቀድሞ አትሌቶች የመጨረሻ ተሳትፏቸውን ማድረጋቸውም ልዩ ትኩረት ስቦ ነበር። ከእነዚህም መካከል ዩሲያን ቦልት፤ ሞ ፋራህ፤ዴቪድ ሩዲሻ፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ ጥሩነሽ ዲባባ…. ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው እ.ኤ.አ በ1983 በፊንላንዷ ከተማ ሄልሲንኪ ነበር፡፡ ከዚያም በ1987 እ.ኤ.አ ላይ ሁለተኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የጣሊያኗ ሮም እንዲሁም በ1991 እ.ኤ.አ ላይ ሦስተኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአራት ዓመት ልዩነት የጃፓኗ ቶኪዮ አዘጋጅተዋል፡፡ በ1993 እ.ኤ.አ ላይ የጀርመኗ ስቱትጋርት ካስተናገደችው ከ4ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ የሚስተናገድ ሆኗል፡፡
በ1995 እ.ኤ.አ የስዊድኗ ጉተንበርግ፣ በ1997 እ.ኤ.አ የግሪኳ አቴንስ፣ በ1999 እ.ኤ.አ የስፔኗ ሴቪላ፣ በ2001 እ.ኤ.አ የካናዳዋ ኤድመንተን፣ በ2003 እ.ኤ.አ የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ፣ በ2005 እ.ኤ.አ የፊንላንዷ ሄልሲንኪ (ለሁለተኛ ጊዜ) በ2007 እ.ኤ.አ የጃፓኗ ኦሳካ፣ በ2009 እ.ኤ.አ የጀርመኗ በርሊን፣ በ2011 እ.ኤ.አ የደቡብ ኮሪያዋ ዴጉ፤ በ2013 እ.ኤ.አ የሩሲያዋ ሞስኮና በ2015 እ.ኤ.አ የቻይናዋ ቤጂንግ ከ5ኛው እስከ 15ኛው ያለፉትን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በሁለት ዓመት ልዩነት በቅደም ተከተል አዘጋጅተዋል።
በ2017 እ.ኤ.አ ለንደን 16ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ካስተናገደች በኋላ በቀጣይ ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎችን የሚያስተናግዱትን የአይኤኤኤፍ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ በ2019 እ.ኤ.አ ላይ በካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድየም የኳታሯ ከተማ ዶሃ እንዲሁም በ2021 እ.ኤ.አ ደግሞ በሄይዋርድ ፊልድ የአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን 17ኛውና 18ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል ያዘጋጃሉ፡፡ በ2023 እ.ኤ.አ ላይ 19ኛውን እንዲሁም በ2025 እ.ኤ.አ ላይ 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች እነማን እንደሚያ ዘጋጇቸው ግን አይታወቅም፡፡ አፍሪካ በደቡብ አፍሪካ አማካኝነት ታላቁን የእግር ኳስ መድረክ የዓለም ዋንጫን ጭምር በታላቅ ስኬት ያስተናገደች አህጉር ብትሆንም የተሻለ ስኬት ባላት አትሌቲክስ ዕድሉን ለማግኘት ዓለም አቀፍ ማህበሩ እስካሁን እምነት አላሳደረባትም። ታላላቅ የዓለማችንን አትሌቶች እንደማፍራቷ ግን ቀጣዩ ጊዜ የአፍሪካ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ተስፋ ነው።
በርግጥ የአይኤኤኤኤፍ ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮው እንዳስታወቀው የአዘጋጅ አገር ምርጫ አስቀድሞ እንደነበረው ማመልከቻ አስገብቶ በመወዳደር አይደለም፡፡ ማስተናገድ የሚፈልግ አዘጋጅ አገር ጋር የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ልዩ ምክር ቤት በሚያደርገው ውይይት እና መግባባት መስተንግዶው ይፈቀድለታል፡፡ በ2023 እ.ኤ.አ ላይ የሚደረገውን 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በዋና ከተማዋ ቡካሬስት ለማስተናገድ የምስራቅ አውሮፓዋ ሃንጋሪ ከፍተኛ ዘመቻ እያደረገች ነው፡፡
የሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት ወደ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መስተንግዶ ትኩረት ያደረገችው በ2024 እ.ኤ.አ ላይ ኦሊምፒክን ለማስተናገድ የነበራት ፍላጎት ከተበላሸባት በኋላ ነው፡፡ የኦሊምፒክ መስተንግዶው ሊሳካ ያልቻለው ከ250ሺ በላይ ሃንጋሪያውያን ባሰባሰቡት የተቃውሞ ፊርማ ነበር፡፡ ሃንጋሪ በ2023 እ.ኤ.አ ላይ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ማስተናገድ ከቻለች ኦሊምፒክን በ2028 ወይንም በ2032 እ.ኤ.አ ለማዘጋጀት አቅዳለች፡፡ የአፍሪካ አገራት አንዳንድ ከተሞች በ2023 እ.ኤ.አ ላይ ቢያንስ ሃንጋሪን በመፎካከር በ2025 ደግሞ በዋና ተፎካካሪነት እጩ ለመሆን ጥረት ካደረጉ ከሁለቱ አንዱን ቻምፒዮናዎች የማዘጋጀቱ ዕድል ይፈጠራል፡፡ በርግጥ ከሰሜን ሞሮኮ፤ ከደቡብ ደቡብ አፍሪካ፤ ከምዕራብ ናይጄሪያ ከምስራቅ ኢትዮጵያና ኬንያ በተናጠል ወይም በጋራ ለመስተንግዶው መፎካከር ይጠበቅባቸዋል፡፡
በ2007 እ.ኤ.አ ላይ የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናን ያስተናገደችው ኬንያ ከወር በኋላ የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ቻምፒዮና የማዘጋጀት ዕድልም አግኝታ ነበር። በሌላ በኩል የ2017 የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናን የኡጋንዳዋ ካምፓላ ከተማ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ አይዘነጋም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
ቦጋለ አበበ