የቤተሰቡ አባላት ቀን ቀን እንደፈንድሻ ተበትነው ይውሉና ማታ በትንሿ ሳሎን ሰብሰብ ሲሉ ውሏቸውን ይለዋወጣሉ። በአንድ ገበታም ይመገባሉ። አብሮ መብላት አብሮ መጨዋወት ያፋቅራል፣ ያስተሳስባል፣ ውስጥን ለመተዋወቅም ያግዛል።… ይባል አይደል?። ሁሉም በየፌስቡኩ፣ በየጌሙና ፊልሙ ከተተከለ ቤተሰብም ቤተሰብነቱን ያጣና እንደምንሰማው የዓለም ወሬኛ መሆናችን አይቀሬ ነው።
ይሄ በብዙ በተለይ ዘመናዊ ነን በሚሉ ቤተሰቦች እንኳን እየተለመደ መሆኑን ልብ ይሏል። አንዳንዱም የመኝታ ክፍል ይዞ ለብቻ በመሆን ግለኝነት እየመጣ ነው። ከዚህም መለስ ሲል ምን ትዝ አለኝ የኮንዶሚንየም ኑሮ፤ የኮንዶሚንየም በር ከርችሞ ኑሮ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ገብታለች። ሰውና ሰው፤ ጎረቤት ከጎረቤት እየተለያዩ ነው ፤ አንዱ ሲጮኽ ማነው የሚልም ኧረ ጠፋ የሚሉም አስተያየቶች ሰፍተዋል። ብቻ ይሄ ለእኛ አይሆንም፤ አላደግንበትም፣ አልኖርነውም፤ ለመንደር ተልኮ፣ እሳት ጭሮ፣ አብሮ ቦርቆ፣አደራ ተቀብሎ፣ መብላት፣ መጠጣቱ ሁሉም ነገር አብሮ… ተባብሮ ነው።
የእኔ ነገር ከቤተሰቡ የውሎ ሪፖርት ወጣሁ – ልመለስ። ከዛ ልጆች የልጅ ተግባራቸውን ፤ ወላጆችም እንደየስራ ድርሻቸውና ፊናቸው ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ይሰማራሉ። በዚህ መሀል የዋልያ ቢራ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አለ።የአራተኛ ክፍል ተማሪው ልጅም ማስታወቂያውን ከመነሻ እስከ መድረሻ ማለቴ እስከ ተሸላሚዎች ምስክርነት ያለውን ቃል በቃል አብሮ ተወጣው። ድንገት «ዋልያ ምንድነው» የሚል ጥያቄ ተነሳ፤ ልጁ ምንም እንደማይስተው ያውቃልና አሁን ይሄ ይጠየቃል በሚል ስሜት ጭምር ኮራ፣ጀነን ብሎ « ቢራ ነዋ! » ማለት ። አባት አሁንም ጥያቄውን ቀጠለ ዳሽንስ? እሱም ቢራ ነው። ማብራሪያም አለው አብሮት «መቶ በመቶ ጥራት ያለው…»ቀጠለ። ልጁ አይፈረድበትም ማታ ማታ በየቀኑ እንደ ዳዊት የደገመው ይሄንኑ ነው። እንዴት ይጥፋው!።
«ሀበሻስ » ከሌላ አቅጣጫ የተነሳ ጥያቄ ነበር፤ ይሄም ቢራ ነው።ሁሉም ፈገግ አሉ፤ ልጁ ግን አንድም ነገር አልተሰማውም፤በልጁ አይፈረድም «ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሀለሁ» አይደል አባባሉ፤ የእሱ የቅርብ ጓደኛ ቴሌቪዢን የነገረው የቢራ ስም መሆኑን ነው።ቀዝቃዛ ቢራ፣በአረፋ የሞላ ብርጭቆ፤ ግጥም ለውሀ ጥም !? አንድ አይቀመጥም፤ ማን ያልጎመዠ አለ፤ ማለቴ ለሚቀማምሱት ጣዕሙን ላጣጣሙት ትነሱ… ትነሱ..፣ አሁን… አሁን… አይደል የሚያስብለው። በልጆች አእምሮ ደግሞ ምን እንደፈጠረ ያኔ ልጅ በነበርኩበት ወቅት ባየው ኑሮ ዛሬ አስታውሼ እከትበው ነበር።ያኔ ብቸኛው የዶሮ አይን የመሰለው ጠላ፣የማር ጠጅ አይ የኔ ነገር የተረሱትን አነሳሳኋቸው። ወሬን ወሬ ያነሳዋል ማለት እንዲህ ነው።
የቢራ ማስታወቂያችን በአገራችን በሰሜን ተራራ የሚገኘው፣ በብርቅየው የዱር እንስሳ ዋልያ ስም የተሰየመው፣…ቢራ እየተባለ ማስታወቂያ ቢሰራ ኖሮ ልጁ ቢያንስ አብሮ የሚያውቀው፣ የሚያጠናው ይኖረው ነበር፤ በምስል ዋልያን ሰሜን ተራራ ላይ ሲጎማለል ቢመለከትም ዋልያ የሚባለው ብርቅዬ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው እንስሳን በአእምሮው ስለን ባስቀረን ነበር። አሁን ግን እንደምናየው እንደምንሰማው ሆነና ሁሉም ነገር ቢራ። እንድንጠጣ፣ ሽልማትን እያሰብን እንድንሰክር የተጋበዝነው ቢራ በየአይነቱ ነው። ምነው ከልካይ የለም ? ሀይ የሚል ልል አሰብኩና የማስታወቂያ ህግ ፣መመሪያ፣ ደንብ የሚባል የሚዲያ ፖሊሲ አለ ብዬ ልለፈው፤ ግን እኮ እሱም ቢሆን ትውልድን ታዳጊን በሚጎዳ መልኩ እንዳይሆን ማድረጉን ማንን ገደለ አለች አያቴ እኔም ይሄንኑ ደገምኩት። ሀይ የሚል መኖር አለበት ።
«ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሀለሁ» የሚለውን አባባል እውነትም እውነትነት አለው። ሰው ለካ የሚመስለው ማንንም አይደለም ። በአካል ፣ በመልክ፣ በተክለ ሰውነት ማለቴ አይደለም በባህሪ፣ በአለባበስ ፣በስታይል።ኧረ አንዳንዴ አነጋገርም የሚኮርጅ አይጠፉም። ወጣቱ ልጄ ጸጉሩን በአጭሩ ቆርጦ አበጥሮና በየጊዜው ተስተካክሎ ነው የኖረው ። አሁን አሁን እንግዲህ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ሲደረስ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለመመሳሰል ተብሎ ይመስ ላል ወይም የዋሉበት ይጋባባት በሚባለው ስታይል ፀጉር ማሳደግ ፣ማንጨባረር እየለመደ መጥቷል። ምነው ማበጠሪያ ሳይጠፋ ልል አሰብኩና ፋሽን ነው የሚለው መልስ እንደሚከተል አስቤ እኔም አለፍኩ። እንዳውም በተለይ ከክልል የመጡት አብዛኛዎቹ ይሄንን እስታይል ተቆጣጥረውታል አሉ። ፀጉር አለማጎፈር እንዳውም አዲስ አበባዎችን «ፋራ» እያስባለም መሆኑን ሰምቼ ፋራነት በዚህ ከሆነ ይሁና አልኩኝ ለራሴ።
እየሆነ የማየው አንዳንዱ ነገር ምነው ኢትዮጵያውያን የሌለንን ባህሪ አወጣን ወይንስ ድሮም ባህሪያችን ሲፋቅ እንደሚባለው አይነት ነው ለማለት እከጅላለሁ።ማለቴ ሲፋቅ ሌላ እየሆንን ነው።«ኢትዮጵያውያን ስንፋቅ ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣የመን…» ነን እንዴ?
አያቴ ሁልጊዜም የምትለኝ ነገር እኔም እስከ አሁን ድረስ የማየው ሁሉ አይጥፋብን የሚያሰኝ ነው። አሁን አሁን ግን የሚታየውና የሚሰማው እንደጠፋብን አይነት ስሜት አለው። ደግሞ ይሄ ጥፋት ደመቅ ብሎ የሚታየው «የተማሩ» በሚባሉና በወጣቶቹ አካባቢ ነው።
ሰው ያክል ክቡር ፍጡር፣ ታላቅን፣ ሽማግሌን፣ የሀገር መሪ ማዋረድ ፣መስደብ … እንደ ጸያፍ ሳይሆን እንደ ጥሩ እደግልኝ አይነት ምርቃት እየተቆጠረ መሰለኝ ። ክብር ለሚሰጠው ክብር መስጠትን እንጂ መስደብን ማዋረድን ማን አስተማረን? ማን ነገረን? አሁን እንደቀላል «ዴሞክራሲ» የቆጠርነው የኋላ የኋላ ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሀለሁ እንዳይሆን እሰጋለሁ። አንዱ ተነስቶ ሌላውን ብሄር፣ ዘር፣ መሪ… የሚዘልፍና የሚሳደብ ከሆነ ማን ማንን ያከብራል፤ የተሰደበው ብቻም ሳይሆን የተሳደበው መዋረዱን አይቶት ይሆን ?ተገንዝቦታል? ሰዎችን ስንሳደብ ስናንጓጥጥ እኮ ድሮስ ማን ያሳደገው ማን ያስተማረው መባባላችን አይቀርም።
አንድ ሰው አንድን መጥፎ ድርጊት ሲፈጽም እኮ ወይ ጉድ እከሌ እኮ እንዲህ አደረገ ተብሎ ብቻ አይታለፍም። የማን ልጅ ነው? ከየት ክልል የመጣ ነው?አሁን አሁን ደግሞ ኧረ ብሄሩ ሁሉ ይጠየቃል። ይሄ ታዲያ ግለሰቡን ወይም ቡድኑን ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሰዎችም ፣መሪዎችም… የመጥፎ ምሳሌ ተደርገው እንዲቆጠሩ የሚያደ ርግ ይመስለኛል። አንድን የሀገር መሪ ጸያፍ ስድብ መስደብ እነማን ናቸው ይሄን የተናገሩት? ማን አስተማራቸው? ሲሰደብ ያደገ፣ ከተሳዳቢ ጋር የኖረ ፣ተሳዳቢ ያሳደገው እየተባለ እሱን ሲመሩትና ኮትኩተው ሲያሳድጉት እስከነበሩት ታላላቅ ሰዎች ድረስ ውግዘቱ ይቀጥላል «ማን ከማን ምን ይማራል» እንደሚባለው ይሆናል።
አሁን የሚታየውም ክብረ ነክ ነገሮች ለማንም የሚጠቅሙ ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊነታችንን እየረሳን ማን ያሳደጋቸው እየተባልን መሆኑን ያሳያሉ። እንግዳ ተቀብሎ እግር አጥቦ፣ ለራሱ ሳይበላ አብልቶና መኝታውን ለቆ እንግዳ ተቀባይ ማህበረሰብ ውስጥ፣ ይሄንን ሲያይ ሲከተል በመጣ ህዝብ መሀል የሀገር መሪን ያክል ለማዋረድ ያልተገባ ስም መስጠት እንደተባለው ጓደኛህን ንገረኝ አይነት ይሆናል። ምክንያቱም በኢትዮጵያውያን ስነምግባር ውስጥ አልተለ መደማ። የኢትዮጵያዊነት መገለጫም አይደለማ። በኢትዮጵያዊነታችን ጉልበት እስከ መሳም ይዘልቃል አክብሮታችን።
ቅሬታዎች፣ ተቃውሞች፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች፣ አለመስማማቶች … ይኖራሉ። በፊትም ነበሩ፣ አሁንም ፣ወደፊትም ይኖራሉ። እናስ ይሄንን ቅሬታ የምንገልጽበት መንገዱ ኢትዮጵያዊያን ክብርን በሚያዋርድ መልኩ መሆን አለበት? መታወቂያችን እኮ ዕርቅ ፣ይቅርታ ፣ምህረት ነው። የአጠፋ ይቅርታ ጠይቆ የተበደለ ተክሶ ቀጣይ ህይወት ፣ቀጣይ ኢትዮጵያዊነት ወደፊት ሊሆን ይገባል። ከዚህ ስንወጣ ማንነትህን ንገረኝ እንዳንሆን ከስህተታችን እንማር፣ እንመለስ ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
አልማዝ አያሌው