እንደ መግቢያ
ሕይወት በየፈርጇ አስገራሚ ዑደቶችን ይዛ ትሄዳለች። የዛሬ ‹እንዲህም ይኖራል› አምድ እንግዳ ሠላማዊት ገብሬ የዚሁ አካል እንደሆነች ከህይወት ተመክሮዋ መገመታችሁ አይቀሬ ነው። ሰላማዊት ገብሬ እና ቤተሰቦቿ ቀደም ሲል መርካቶ አራተኛ በልዩ አጠራሩ መንዝ በረንዳ በሚባለው አካባቢ ነበር የሚኖሩት። አባቷ በሕይወት ዘመናቸው ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ የነበረው በርኖስ በመስራት ነበር። በሕይወት እስከ 1998 ዓ.ም በቆዩበት ወቅትም በአካባቢው ዝነኛ በርኖስ ሰሪ ነበሩ። ግን አባቷ ሲሞቱ በርኖስ ሥራውም አብሯቸው ሊሞት ሆነ። ይህን የተረዳቸው ሠላማዊት የአባቷን ሥራ ተረክባ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በርኖስ መሥራት ጀመረች። ታዲያ ከአባቷ ንብረት ሳይሆን ሙያ በቀዳሚነት በመውረሷ የቀድሞ ደንበኞቿን ላለማጣት ወሰነች።
አባቷ ቀደም ሲል በርኖስ ሲሠሩ የሰሜን ሸዋ አካባቢ ሰዎች በተለይም መንዝ እና አጎራባች ወረዳዎች ግብዓት አቅራቢዎች ነበሩ። የበርኖስ ግብዓቱን (የበግ ፀጉር) ሸልተው አሳምረው ልክ እንደ ብርድ ልብስ ቅርፅ አስይዘው እያስረከቡ ይሄዱ ነበር። ይህን ሁሉ ታዲያ በሚገባ ስትከታተል አድጋለች። ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ድክ ድክ እያለች ነገሮችን መመልከት የጀመረችው ይህች ባለ ታሪክ ዛሬ ላይ የኑሮ ዋስትና የሆኑትን ጥበብ ከአባቷ ስለመቅሰሟ ትናገራለች። በዚህ ውስጥ ግብዓት እጥረትም ሆነ የገበያ እጦት አልነበረባቸውም። የመንዝ ሰዎች ይህንን ጥበብ ተክነው አሰማምረው ለአባቷ አስረክበው ይሄዱ ነበር። ታዲያ የመንዝ በረንዳ በልማት ምክንያት ሲፈለግ ቤታቸው ስለፈረሰ አሁን ወደምትኖርበት ካራ አካባቢ ለመሄድ ይገደዳሉ።
በርኖስ አሰራር
መጀመሪያ የበግ ፀጉር ይሸለታል። ከዚያ እንደ ጥጥ ይባዘታል። በመቀጠል በእንዝርት ይፈተላል ከዚያም ወደ ፈትል ይቀየራል። በመቀጠል ፈትሉ ልክ እንደጋቢ እየተወረወረ ይደወራል። በመቀጠል ወንዝ ይወሰድና ይረገጣል። ከዚያ የበጎች ፀጉር እየተነሰነሰበት ጥቅጥቅ እያለ ይረገጣል። አንድ በርኖስ ለመሥራት በትንሹ እስከ 10 በጎች ቆዳ ላይ የተሸለተ ፀጉር ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ በባህላዊ መንገድ ለመሥራት የሚታለፍበት መንገድ ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቆዳ ፋብሪካዎች የቆዳ ውጤቶችን ለመስራት ሲሉ ፀጉርን በኬሚካል እና በዘመናዊ ማሽን ይሸልቱታል። ከዚያ ፀጉሩን በርኖስ የሚሰሩ ሰዎች ይጠቀሙበታል። በርኖስ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ እንዲሁም በጎጃም እንደ ባህል ልብስ የተለመደ ሲሆን በለቅሶ፣ ሠርግና ዓመታዊ ክብረ በዓላት በሰፊው እንደሚለበስ ትናገራለች።
አባቷንም ሥራዋንም የምትወድ ሠላማዊት ይህን ሥራዋን ከአባቷ ነው የተማረችው። አባቷ በዚህ ሥራ ቤተሰባቸውን ማስተዳደራቸውንና እጅግ ሥራ ወዳድ እንደነበሩ ታስታውሳለች። በዚህ ሂደት ሁሉ ታዲያ የአባቷን ጥንካሬ ታደንቃለች። ሥራ ወዳድ ስለመሆናቸውም ትመሰክራለች። እርሷ ከአባቷ የቀሰመችውን ሥራ ታከብራለች አባቷንም በታታሪነታቸውና በባህል ወዳድነታቸው ታደንቃለች። በአጭር አገላለፅ ሰላማዊት አባቷንም ሥራዋንም ትወዳለች። ምንም እንኳን ሥራው በአሁኑ ወቅት ታዋቂና ዝነኛ ባያደርጋትም በቢዝነሱም ባይሳካላትም ከእርሳቸው የወሰደችውን መልካም ልምድም ለማስቀጠል ደፋ ቀና ትላለች።
ሠላማዊት አልፎ አልፎ ቴሌቪዥን ስታይ አንዳች ነገር በአዕምሮዋ ብልጭ ይላል። አፄ ምኒልክን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ነገስታት በርኖስ ለብሰው ተውበው ስትመለከት ደስታዋ ወደር የለውም። አርበኞችና ጀግኖች በርኖስ ለብሰው በቴሌቪዥን መስኮት ሲንጎራደዱ ልቧ ድቤ ይመታል። ከባህል ላፈነገጡት እጅ አንሰጥም የሚሉ ወጣቶች በርኖስ ተከናንበው ቀብረር ሲሉ ልቧ በሀሴት ይሞላል። በርኖስ የነገስታት ልብስ ክብር አገኘ ስትል ፈገግ ትላለች። በአሁኑ ወቅትም ቢሆን የአገር መሪዎች ጃኖ እንደ ስጦታ ሲበረከትላቸው ደስ ይላታል።
ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር)፣ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ብሎም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለሃብቶች ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን በሄዱ ጊዜ በአክብሮት ሲሸለሙና ሲሰጣቸው የነበረው በርኖስ ነው። ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በዚህ የክብር ልብስ (በርኖስ) በቀጣይም የነገስታትና የአገር መሪዎች የክብር ልብስ እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች። ግን ደግሞ ትኩረት ካልተሰጠው ይህ ‹‹ነበር›› መባሉ አይቀርም ባይ ናት። ዋናው ነገር ግን ሠላማዊት ይህን ሥራ ስትሠራ ሠላም ስለሚሰጣት ደስተኛ ናት።
ኑ! ተማሩ
ነገስታት የከበሩበት፤ የአገር መሪዎች የተዋቡበት፣ አርቲስቶች የደመቁበትና በርካቶች የተዋቡበት በርኖስ አሰራርን ሁሉም ሰው ቢያውቀው ቢተዋወቀው ምኞቷ ነው። እባካችሁ ከእኔ ዘንድ ኑ! ተማሩ፤ እውቀትም ቅሰሙ ስትል የባህል አድናቂዎችን አገር ወዳዶችን፣ የጥበብ አፍቃሪዎችን የቢዝነስ ሰዎችን ትለምናለች- ወጣቷ። ከገቢ አኳያም ቀላል የማይባል ስላልሆነ ትምህርቱ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ኪስ የሚሞላ ገንዘብ ለማግኘትም ያግዛል ትላለች። ግን ሥራው አድካሚ በመሆኑ ይህን በሚገባ ማለፍ የሚፈልግ ልበ ፅኑ ውጣ ውረዶችን በትዕግስት ለማለፍ የሚተጋ ሰው መሆን አለበት ትላለች። ‹‹በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የሚለበሰውን በርኖስ ከእኔ ውጭ ማንም ሰው እንደማይሰራ መረጃው አለኝ›› ስትል በእርግጠኝነት የምትናገረው ሠላማዊት፤ በቀጣይ ይህ ሥራ አስታዋሽ እንዳያጣ ባህሉም መና እንዳይቀር ትምህርቱን ከእርሷ ዘንድ ሄደው እንዲቀስሙ ትመክራለች።
አድካሚው ሥራ
ሦስት ልጆቿንና ቤተሰቦቿንም በዚህ ሥራ ነው የምታስተዳድረው። ከዚህም ባሻገር ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮቿን የምትከውነውና የምትሸፍነው በዚሁ ሥራ በሚገኘው ገቢ ነው። በርኖስ አዘውትረው የሚለብሱ ሰዎች ባይኖሩም ብዙ ጊዜ ለጥምቀትና ገና ላይ ብዙ ሰዎች ይፈልጉታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት የመርካቶ ልጆች በቡድን መጥተው 60 በርኖስ ስሪልን ብለው እንደጠየቋትና ብዙ ሥራ እንደሰራች ታስታውሳለች። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን ከሌሎች ጋር ተመካክሮ እና ተቀራርቦ ለመስራት ማሰብ ጀምራለች። ግን ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ እንዳሰበችው አልተሳካላትም። እናም በዚህ ረገድ ብዙ ያለመሄዷ የሚቆጫት ቢሆንም ወደፊት ግን ጠንከር አድርጋ ልትገፋበት ታስባለች። ግን ወደ እርሷ ዘንድ ሄዶ ‹‹አብረን እንስራ›› የሚላት ሰው ካገኘች ደስታዋ ወደር እንደሌለው ትናገራለች።
ተማፅኖ፤ ፈተና እና ምኞት
በአሁኑ ወቅት ይህን ሥራ የምታከናውነው በጠባቧ መኖሪያ ቤቷ ነው። ይህ ደግሞ ቤት ውስጥ መተፋፈግ ስለሚፈጥር ለህፃናቶች ጤንነት ትጨነቃለች። ሥራው በባህሪው ሰፋ ያለ ቦታ ስለሚፈልግም ችግርን በቀላሉ ልትወጣ አልቻለችም። በዚህ ላይ ደግሞ ባህሉ ትኩረት ካልተሰጠውና ሰዎች ካልሰሩት ሊጠፋ ይችላል የሚል ሥጋት አላት። ታዲያ ይህን ችግር ለማቃለል መንግሥት ትኩረት ቢሰጠኝ ባይ ናት። ባህሉን ለማቆየት ሲባል የሚመለከታቸው የትምህርት ተቋማት፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባህል ወዳጆችና የአገር ተቆርቋሪዎች ወደ እርሷ ይመጡ ዘንድ ትጋብዛለች።
ሠላማዊት በርኖስ የሚሰራ ሰው ይጠፋ ይሆን ስትልም ትጨነቃለች። አሁን በርኖስን ሥራዬ ብለው የሚሰሩ ሰዎች ባይኖሩም ተጠቃሚዎች ግን ከየት እናጋኛለን ብለው አፈላልገው መግዛታቸውን አላቆሙም።
ትልቁ ፈተና የሆነው ግን ምርቱን የሚፈልጉ ሰዎች እና ምርት አቅራቢዎች በቀጥታ አለመገናኘትም ነው።
ለአብነት እርሷ አንድ በርኖስ በ700 ብር ትሸጣለች። ከእርሷ ወስደው የሚሸጡ ነጋዴዎች ግን ከ 2000 እስከ 3000 (ሁለት ሺ እስከ ሶስት ሺ ብር) በከፍተኛ ደረጃ አትርፈው ይሸጣሉ። ይህም እርሷ ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርጓታል። ግን የመሥሪያ እና መሸጫ ቦታ ቢኖራት ከራሷ ተርፋ ሌሎችንም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደምትችል ትናገራለች።
በርካታ ውጣ ውረዶችን እያለፈች ከዛሬ ላይ የደረሰች ሲሆን ነገም ፈተናዎችን የማለፍ ውጥን አላት ምንም እንኳን ባሰበችው ፍጥነት ነገሮች እየተሳኩ ባይሆኑም። ከአባቷ የሥራ ወዳድነትና ታታሪነትን የቀሰመችው የበርኖስ ጥበበኛዋ ነገ ሥራዋን ለማዘመንም ትሻለች። በአንድ ወቅት ከቻይና ይመጣ ስለነበር ገበያው በመሃል አቀዛቅዞት ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያን ምርት መተካት የማይችል በመሆኑ በርካቶች ወደ አገራቸው ምርት መመለሳቸውን ታስታውሳለች። ግን በዚህ ሁኔታ አንድ ቀን የበርኖስ ሥራ እንዳይጠፋም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ትመክራለች። ብቸኛዋ በርኖስ ሥራ የምትከውነው ይህች ወጣት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም በዚሁ ሥራ አጠናክራ መቀጠል ትፈልጋለች።
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር