የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ከቤት ዋሉ ተብሏል። በነገራችን ላይ አሁን አሁን ግን ሰዎች ከቤት እየዋሉ አይደለም። እንቅስቃሴዎች ሁሉ ኮሮና ያልተከሰተ ነው የሚመስሉ። ገና እንደገባ እንደ ፋሽን አይተነው ነው መሰለኝ ቤት የመዋል ዘመቻ ተጧጡፎ ነበር። መስሪያ ቤቶችም ወደመደበኛ ሥራዎቻቸው የተመለሱ ይመስላል። ችግሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት ነው። ቤት ዋሉ ቢባል ከቫይረሱ ወረርሽኝ ያላነሰ ችግር ይፈጠራል። ፆም ማደር ይመጣል። ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ በጤና ባለሙያና በህግ አስከባሪዎች በታዘዘው መንገድ መሥራት ይሻላል።
ወደመነሻዬ ልመለስ። ቤት ዋሉ የተባለ ሰሞን (በእርግጥ አሁንም ቤት የሚውል አለ) የፊልም እና የመጽሐፍ ግብዣ ተጧጡፎ ነበር። ‹‹ይሄን ፊልም እዩ፤ ይሄን መጽሐፍ አንብቡ›› እየተባለ በማህበራዊ ገጾች የሀሳብ መለዋወጥ ነበር።
እኔም የዚህ ዘመቻ ተካፋይ ሆንኩ። ብዙም የፊልም ተመልካች አልነበርኩም። መጽሐፍ እንጂ ፊልም አፈላልጌ የማየት ልምድ የለኝም። ፊልም ካየሁም ታሪካዊ ወይም ሙያዊ የሆነ እንጂ ጭፈራ ቤት ተጀምሮ ጭፈራ ቤት የሚያልቅ፣ በጭስ ተጀምሮ በስካር የሚያልቅ፣ በዝሙት ተጀምሮ በመከዳዳት የሚያልቅ… ፊልሞች ይሰለቹኛል። አጀማመራቸውን አይቶ መጨረሻቸው ይታወቃል።
በነገራችን ላይ ወቀሳ ብቻ የሚወርድበት የኢትዮጵያ ፊልም የሚደነቁ ፊልሞችም አሉት። በጣም የመጯጯህ ዕድል ያላቸው ግን እነዚያው የሚወቀሱት ናቸው። ጥሩ የሚባሉት ፊልሞች በብዛት የመታየት ዕድል የላቸውም። ስለዚህ ፊልም ሰሪዎችም የሚያዋጣቸውን ይሰራሉ ማለት ነው።
የውጭው ዓለም ፊልም የሚወደድበት ምክንያት አለው። ፊልሞቻቸው ሙያዊ ናቸው። ራሳቸውን ችለው ማስተማሪያ ናቸው። የኢትዮጵያ ፊልሞች ግን መማሪያ ሳይሆኑ መዝናኛ ናቸው፤ ችግሩ ማዝናናትም የማይችሉ እየሆኑ ነው። እንዲያውም እየተወቀሱ ያሉትም አላስተማሩም ተብሎ ሳይሆን አላዝናኑም ተብሎ ነው። ስለዚህ ፊልም ሰሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ተመልካቹም ተበላሽቷል ማለት ነው። ለዚህም ነው ፊልም ለድብርት ብቻ ተብሎ የሚታይ። ‹‹ምን ያዝናናሃል›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ፊልም ማየት›› የብዙዎች መልስ ሆኗል። የፊልሞች መለኪያ አስቂኝነት ሆኗል ማለት ነው።
የውጭው ዓለም ፊልሞች ግን እንደ ዘጋቢ ፊልም ናቸው። መማሪያ ይሆናሉ። ታሪክ ናቸው፣ ፖለቲካ ናቸው፣ ሳይንስ ናቸው፣ ፍልስፍና ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተለይ ሳይንሳዊ ፊልም አይታሰብም። ኢትዮጵያ ውስጥ ለልጆች ፊልም የሚመረጠው (ከተቻለም የሚከለከለው) ያለ ምክንያት አይደለም። የሚያሳዩት ማጨስ፣ መጠጣት፣ መስከር፣ ዝሙት መሥራት፣ በተማሪነት አርግዞ ከትምህርት ማቋረጥ፤ ከዚያም ሴተኛ አዳሪ መሆን ስለሆነ ነው።
የውጭው ዓለም ፊልሞች የሚወደዱበት ምክንያት ከሁሉም አይነት አላቸው። መዝናናት ብቻ የሚፈልግ አስቂኝ ፊልሞች ያያል፤ ሀሳባዊና ትምህርታዊ የሆኑ ፊልሞችን የሚፈልግ እነርሱን ያያል። እንኳን በዘርፍ በዘርፍ በአንድ ህዋስ ላይ ብቻ ፊልም ይሰራሉ። የጤና ተማሪ እንደ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን እንደ መማሪያ ያየዋል ማለት ነው። መልክዓ ምድር ላይ ብቻ የሚያተኩር ፊልም አለ፤ ይህ ለጂኦግራፊ ሰዎች መማሪያ ነው ማለት ነው። ማህበራዊ ህይወትን የሚመለከት አለ፣ ፀጥታን የሚመለከት ፊልም አለ፣ ወንጀልን የሚመለከት አለ፣ ታሪክን የሚመለከት አለ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ያልሆነበት ምክንያት ሌላ ምንም ሳይሆን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ አለመኖር ነው። ነገሩን ደፈር ብለን እናውራው። ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ የሚገቡት ሰዎች በትምህርት ያልተሳካላቸውና ጥሩ ውጤት የሌላቸው ናቸው። በመልክ ብቻ የሚመረጡ ናቸው። ‹‹ለትወና ችግር የለውም›› ይባል ይሆናል፤ ችግሩ ግን እነዚሁ ሰዎች ናቸው ደራሲ እየሆኑ ያሉት። ለዚህም ነው የፊልሙ ይዘት ከትምህርት ማቋረጥ፣ ከሱስ እና ከሴተኛ አዳሪነት ህይወት የማይወጣ። በፊልም ውስጥ ከሚሳተፉት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ወደፊልም ሙያ የሚገቡ አይመስለንም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየተጀማመረ ነው።
የዶክትሬት ዲግሪ ምርምራቸውን በተለያየ መስክ የሚሰሩ ሰዎች ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ቢገቡ ሙያዊ ፊልሞች ይሰሩ ነበር። ዳሩ ግን እንኳን የዶክትሬት ምርምር ያላቸው ይቅርና ይባስ ብሎ ከ10ኛና ከ12ኛ ክፍል ውጤት አልመጣላቸው ያለ ሰዎችም የሚገቡበት ነው። ዋና መስፈርቱ መልክ ሆኗል። በተለይም አንዳንዶቹ እንደሚሉት ደግሞ በቁንጅና ውስጥ ብዙ ነውር ነገር ይደረጋል። ገላቸውን ሸጠው እንደሚመረጡም ተደጋጋሚ ሐሜት የተነሳበት ጉዳይ ነው።
ይህ ሲባል ግን የሚደነቁ ፊልሞች የሉም ማለት አይደለም። የፊልም ባለሙያ ባልሆንም እንደ አንድ ፊልም ተመልካች ያደነቅኳቸው ፊልሞች አሉ (ራሱን ችሎ እንዳስሳቸዋለን)።
እነዚህ ሙያዊ ፊልሞችም ታዲያ ቅሬታ ይነሳባቸዋል። ይኸውም ተገቢውን ባለሙያ አያማክሩም፤ ብዙ ሙያዊ ስህተት ይበዛባቸዋል የሚል ነው። ለምሳሌ የጤና ባለሙያዎች ይህንኑ ቅሬታ ጽፈው ነበር። በፊልምና ድራማ ውስጥ የሚሰሩ ህክምና ነክ ሥራዎች ሙያዊ ግድፈት ይታይባቸዋል።
በፀጥታ ጉዳይ ላይ በሚሰሩ ፊልሞችም እንዲሁ ቅሬታ ይነሳባቸዋል። አብዛኞቹ ድራማዎች ደግሞ ፖሊስ ይበዛባቸዋል። ይሄ ከነባራዊው ሕይወታችንም ጋር ስለሚገናኝ አያጠያይቅ ይሆናል፤ ግን ደግሞ በሚገባ ባለሙያዎችን ማማከር ያስፈልጋል። እንኳን ለባለሙያዎች ለእኛ ለተመልካቾች እንኳን በግልጽ የሚያስታውቁ ስህተቶች ይታያሉ። የሐኪም ባህሪ ሳይላበሱ ሐኪም ሆኖ መተወን ሙያውን ማቅለል ነው። ትክክለኛ ሐኪም በሽተኛን በሚጠይቅበት ስነ ልቦና መሆን አለበት።
የፀጥታ ጉዳዮችም እንደዚሁ። ቅልጥፍና የሌለው ሰው የወታደርነት ገጸ ባህሪ መያዝ የለበትም። ምናልባት ዝርክርክ ወታደርነትን ለማሳየት ከሆነ ይሁን፤ ወታደራዊ ጥበቃን ለማሳየት ግን ወታደራዊ ስነ ሥርዓቱን የጠበቀ መሆን አለበት። ወታደሮች ላይ በምናየው ባህሪ ማለት ነው።
ሌላው ደግሞ አንድ አካባቢ ላይ የሚሰሩ ፊልሞች ናቸው። ይኸውም ታሪካዊ አካባቢዎችን ለማስተዋወቅ ማለት ነው። በተደጋጋሚ የሚነሳውን ቅሬታ በመስማት ይመስላል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገጠርን መቼት ያደረጉ ፊልሞች እየተሰሩ ነው። እነዚህ ፊልሞች ሊበረታቱና ሊመሰገኑ ይገባል። ልክ ለወቀሳ የተረባረብነውን ያህል ለአድናቆትና ለምሥጋናም ም ላሳችን ይታዘዝ!
አገራት ባህልና ታሪካቸውን የሚያስተዋውቁት በጥበብ ሥራዎች ነው። ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ማለት የአገሪቱን ታሪክና ባህሎች ማስተዋወቅ ነው። ችግሩ ግን የወቀሳውን ያህል ለአድናቆት አንነሳሳም። ለምሳሌ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑት የሐመር አካባቢዎች ፊልም ተሰርቶላቸዋል፤ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ባህል ፊልም ተሰርቶላቸዋል። እነዚህን ፊልሞችም ማስተዋወቅና ማመስገን አለብን። ምናልባት በፊልሞች ውስጥ ሙያዊ ህፀፅ ይኖር ይሆናል። ሀሳባቸውንና ታሪኩን ግን ማመስገንና ማስተዋወቅ አለብን። ‹‹ኢቫንጋዲ›› እና ‹‹እንሳሮ›› ፊልሞችን በኪነ ጥበብ ገጽ በዝርዝር እንመለስባቸዋለን።
ፊልም ልቦለድ ነው። ሁሉን ነገር በቀጥታ ካልገለጸ አይባልም። ለማዝናናት ወይም ቀልብ ለማንጠልጠል ሲባል ብዙ ነገር ይጨመርበታል። ሆኖም ግን መሰረታዊ ይዘቱን ደግሞ የሚያዛባ መሆን የለበትም። የተለየ ጥንቃቄ የሚጠይቀው ደግሞ የሙያ ፊልሞች ላይ ነው፤ ምክንያቱም የሙያ ፊልሞች ከመዝናኛነታቸው ይልቅ አስተማሪነታቸው ይበልጣል። ስለዚህ የዘርፉን ሰዎች በጥልቅ ማማከር የግድ ይላል።
ሌላው በአገራችን ያልተለመደው ነገር ሳይንሳዊ ፊልሞችን መሥራት ነው። ከጭፈራና ከዝሙት ወጣ ያለ ነው ከተባለም የገጠር ሕይወት ወይም ፖለቲካ ነው። ሳይንሳዊ ፊልሞች ደፈር ብለው ይሰሩ። ለዚህ ደግሞ ባለሙያዎች ግቡበት። አንድ ሐኪም የፊልም ስክሪፕት ቢጽፍ ምን ችግር አለው? እንዲያውም የበለጠ ሙያዊ ይሆናል። ለስነ ጽሑፋዊና ጥበባዊ ውበቱ ደግሞ የኪነ ጥበብ ሰው ‹‹ዳይሬክት›› ያድርገው። አንድ ኢንጂነር የፊልም ደራሲ ቢሆን ምንም ችግር የለውም።
እኛም ተመልካቾች ጥሩ ጥሩ ፊልሞችን እናድንቅ!
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
ዋለልኝ አየለ