የተጠናከረ የፍትህ ስርዓት መኖር ለተረጋጋ ሰላም፣ ዋስትና ላለው ደህንነት ብሎም ለኢኮኖሚ ዕድገትና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ ነው። በአንፃሩ ህዝብ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት አጣ ማለት በመንግሥት ላይ ያለውንም አመኔታ ጥያቄ ውስጥ ይከታል። በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ ባካሄደው የውይይት መድረክ በክልል ያሉ ፍርድ ቤቶችና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀናጅቶ አለመሥራት ዜጎችን ለእንግልት እየዳረገ መሆኑ ተነስቷል። የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በህግ የተደነገገ የየራሳቸው ስልጣንና ኃላፊነት ያላቸው ቢሆንም የሚያገናኟቸውም ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ከእነዚህ መካከል የክልል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የሰበር ችሎት ውሳኔ መተግበርና የባለጉዳዮችን መዝገብ በአግባቡ በመላክ በኩል ሰፊ ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ ተቀራርበው መሥራትና የጋራ መፍትሔ መፈለግ እንዳለባቸውም ተገልጿል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ተክሊት ይመስል እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የተለዩ ችግሮች መኖራቸው ተነስቶ መፍትሔ እንዲያገኙ የተጀመሩ ሥራዎች ነበሩ። እነዚህ ችግሮች በወቅቱ ባለመቀረፋቸውና አዳዲስ ዳኞችም በየወቅቱና በየደረጃው ስለሚገቡ ችግሮቹ ዛሬም ድረስ ዜጎችን ለእንግልትና ለተዛባ ፍትህ እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ ሠላሳ ሰባት ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባው ፍትህ የማግኘት መብት እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ሳይስማማው ከቀረ እስከ ፌዴራል ይግባኝ የማለትና መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞም ከሆነ እንዲታይ የማድረግ መብት አለው። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለባቸውን ማናቸውንም ጉዳዮች በመላው ሀገሪቱ የሰበር ሰበርን ጨምሮ የማየት ስልጣን አለው። ነገር ግን ይሄ ፍትህ የማግኘት ህገ መንግሥታዊ መብትና ፍትህ የመስጠት ህገ መንግሥታዊ ግዴታ ትርጉም የሚኖረው ለዜጎች ተደራሽ ወጪ ቆጣቢና በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውሳኔ መከናወን ሲችል ነው። በዚህ ረገድ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ሆኖ ህዝብን ለእንግልትና ለተዛባ ፍትህ እየዳረገ ይገኛል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተለያዩ ክልሎች በይግባኝ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ውሳኔ ለመስጠት በስር ፍርድ ቤት የተወሰነው ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ለመወሰን መዝገብ እንዲቀርብ ያደርጋል። በዚህ ሂደት የሚቀርቡ የውሳኔ ግልባጮች በአብዛኛው ተሟልተው አለመቅረብ የፍትህ ሂደቱን እያስተጓጓለው ይገኛል። ከእነዚህ መጓደሎች መካከል በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ክሱ ምን እንደነበር ባጭሩ አለመጻፍ፣ የግራ ቀኙን ክርክር በአግባቡ አለመመዝገብና በስር ፍርድ ቤት የቀረቡ እንደ (ፎቶ፣ ቪዲዮ፣ ሰነድ) የመሳሰሉት መረጃዎች አሟልቶ አለመላክ በተደጋጋሚ ከሚስተዋሉት የክልል ፍርድ ቤቶች ችግሮች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው። በተለይ ከመሬትና ማህበራዊ ዳኝነት እንዲሁም ከአንዳንድ የሸሪያ ፍርድ ቤት ለሰበር የሚመጡ ጉዳዮች ውሳኔው በአንድ ዓረፍተ ነገር ተጽፎ ስለሚመጣ ምን ማስረጃ ቀርቦ እንዴት እንደተወሰነ ማወቅ አይቻልም። በመሆኑም በስንት ውጣ ውረድ ከሩቅ ቦታ ጉዳዩን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያደረሰ ይግባኝ ባይ መዝገቡ እንዲሟላ ተመልሶ ይላክና ለተጨማሪ እንግልት ወጪና የጊዜ ብክነት ይዳረጋል።
በክልል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ብይኖች ውሳኔዎችና ትዕዛዞች ተነባቢ ካለመሆን ጋር በተያያዘ የሚነሱ መሰረታዊ ችግሮችም አሉ። በአንድ በኩል በፌዴራል የሥራ ቋንቋ የሚሠሩ ፍርድ ቤቶች የአንዳንድ ዳኞች የእጅ ጽሑፍ የማይነበብ በመሆኑ የውሳኔውን ይዘት ከግራ ቀኙ የክርክር ይዘት እንዴት እንደተነሳ ስለማይታወቅ የተሳሳተ ድምዳሜ እንዲሰጥ ያደርጋል። በተመሳሳይ አንዳንዶቹ በፎቶ ኮፒ የሚልኩ ቢሆንም ከወረዳ ዞን፣ ከዞን ክልል ድረስ በተደጋጋሚ ኮፒ ስለሚደረግ ተመሳሳይ ያለመነበብ ችግር በስፋት ይገጥማል።
በፌዴራሉ ቋንቋ የማይጠቀሙ ክልሎችም የውሳኔ ግልባጮችን ወደ ፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ሲተረጎሙ በርካታ ስህተቶች ሲፈፅሙ ይስተዋላሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ቋንቋውን በሚገባ በማያውቁና የህግ እውቀት በሌላቸው ሰዎች ሲተረጎም ከህጉ ፅንሰ ሃሳብ በራቀና ለውሳኔ በሚያሳስት መልኩ ተተርጉሞ ይቀርባል። አንዳንዱ ረጅም ውሳኔ ባጭሩ የሚጽፍ ሲሆን፤ ይህም ተርጓሚዎች በፍርድ ሂደቱ ሚና እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ የሰበር ፍርድ ቤቱን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እየመራው ይገኛል። አንዳንድ ግለሰቦችም ውሳኔውን እነሱ በፈለጉት መልኩ እንዲተረጎም አድርገው ለፍርድ ቤት እያቀረቡ ይገኛሉ።
በአንዳንድ ክልሎች ያሉ የስር ፍርድ ቤቶች ደግሞ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዝገብ እንዲልኩ ሲጠየቁ ማንገራገርና በተያዘው ቀጠሮ አለማቅረብ፤ የእግድ ትዕዛዞችን ተቀብሎ ተፈጻሚ አለማድረግ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።
የሰበር ችሎት በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሀገር ደረጃ ተመሳሳይ ለሆኑ ጉዳዮች ተመሳሳይ ትርጉም እየሰጠ ወጥነት ያለው የፍትህ ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል። ምንም እንኳ እስከአሁን በርካታ ውሳኔዎች በሰበር ችሎት የተላለፉ ቢሆንም ከክልሎች ተመሳሳይ ለሆኑ ውሳኔዎች ተመሳሳይ ትርጉም እየተሰጠ በተደጋጋሚ ወደ ሰበር ሲመጣ ይታያል። በህጉ መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝና ሰበር ሰሚ ትዕዛዞችና ውሳኔዎች በመላው ሀገሪቱ መተግበር ቢኖርባቸውም በአንዳንድ ክልሎች በተደጋጋሚ ያለመቀበል የማጓተት አካሄድ መኖሩ ተነግሯል። በዚህ በኩል ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም አስር ዓመት የሚደርሱ ጉዳዮችም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ተደራሽ እንዳይሆን እያደረጉት ይገኛሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የክልል ፍርድ ቤቶች የሰበርን አስገዳጅና ገዢ ውሳኔዎችን አለመጥቀስና የሰበር ፍርድ ቤት አስገዳጅ ውሳኔዎችን በዝምታ ማለፍም በአንዳንድ ክልሎች ይታያል። ይህም የፌዴራል የሰበር ሰሚ ችሎትን የመዝገብ ፍሰት እየጨመረው ይገኛል። እንደ ኬንያ ባሉ ሀገራት በአስር የሚቆጠር ፋይል ለሰበር ሲቀርብ በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቀርብ መሆኑ ለዚህ እንዱ ማሳያ ነው። በህግ አተረጓጎምና አተገባበር ረገድም ህጎች ከወጡበት አግባብ አንፃር መተርጎም ቢኖርባቸውም ዛሬም ድረስ ለተመሳሳይ ጉዳይ በፌዴራልና በክልል ብሎም በክልሎች መካከል የተለያዩ ትርጓሜዎች በመስጠት የተዛቡ ውሳኔዎች ሲተላለፉ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል ይላሉ ዳኛ ተክሊት።
ዳኛ ተክሊት ለተነሱት ችግሮች መፍትሔ ያሉትንም ሃሳብ ሲያቀርቡ የፌዴራልና የክልል ዳኞች በተመረጡ ጉዳዮች የጋራና የተናጠል ስልጠና መስጠት፤ የበጀት እጥረትን ተከትሎ የሚፈጠሩትን ክፍተቶች ለመቅረፍ የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ ማድረግ፤ ለተርጓሚዎች የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት በየፍርድ ቤቱ መንግሥት በህጉ መሰረት ተርጓሚ ማስቀመጥ፤አቤቱታ አቀራረብ የክርክር አመራር የማስረጃ አመዘጋገብን የሚደግፉ ዝርዝር ማኑዋሎች ማዘጋጀት። የየክልሉ ፍርድ ቤቶች እየተከተሉት ያለውን የተለያየ የውሳኔ አፃፃፍ ስርዓት ወደ አንድ ማምጣትና የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በኔት ወርክ ማገናኘት ችግሩን እንደሚያቃልለው ይጠቁማሉ።
የጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኦባንግ ጁሉ በበኩላቸው በክልሉ የውሳኔ አጻጻፍና አላላክ ስርዓት ላይ ችግር እንዳለ ይናገራሉ። እንደ አቶ ኦባንግ ማብራሪያ ወደ ፌዴራልም ሲላክ ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች መዝገቦች ሲቀርቡ የተጻፈውን ነገር አንብቦ ለመረዳት ከፍተኛ ችግር አለ በአንዳንዶቹ ጉዳዮች ደግሞ የግድ ዳኛውን ሥራ አስፈትቶ እስከማናገር ይደረሳል። ይሄ ሊፈጠር የቻለው በክልሉ ያሉት አብዛኛዎቹ ዳኞች በመደበኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ሳይሆን ከግል ኮሌጅ የተመረቁ በመሆናቸው የብቃት ችግር በመኖሩ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያንዳንዱ ዳኛ ያስተላለፈውን ውሳኔ በኮምፒውተር ይጻፍና መልሶ እንዲያየውና እንዲያረጋግጠው እየተደረገ ይገኛል። ይሄም ቢሆን በኮምፒውተር እየተጻፉ ወደ ፌዴራል የሚላኩት የውሳኔ ክፍል ብቻ መሆኑ አሁንም ያልተሻገርነው ችግር ነው። በአንዳንድ ፍርድ ቤቶች በፎቶ ኮፒ ለመላክ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ከጥራት ጋር በተያያዘ አመርቂ አይደሉም። የሰበር ውሳኔ አስገዳጅነት ላይ በተመለከተም የሰበርን ውሳኔ ሳይጠቅሱ የሚሠሩ ዳኞች አሉ የሚሉት አቶ ኦባንግ ከሰበር የሚመጡ ለተመሳሳይ ጉዳይ የተሰጡ የተለያዩ ውሳኔዎች መኖራቸውን በማስታወስ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ራሱን መፈተሽ እንዳለበት ያሳስባሉ።
«የሰበር ውሳኔ የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች የክልል ፍርድ ቤቶች የማይመለከቷቸው ካለማወቅና ከቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን ተደራሽ ስለማይሆንም ነው» የሚሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ማሂር አብዱል ሰመድ ናቸው። እንደ አቶ ማሂር አብዱል ሰመድ ማብራሪያ የሰበር ውሳኔዎች በየወቅቱ ታትመው ለክልል ሲደርሱ አይታዩም ይልቁንም ከፍርድ ቤቶቹ ቀድመው ጠበቆች እጅ ይገባሉ። በመሆኑም የፌዴራል የመጨረሻው ትርጉም የሰጠበት በየወቅቱ እንዲደርስ ቢደረግ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ከትርጉም ጋር በተያያዘ የሚነሳው ችግር በተደጋጋሚ የሚከሰትና ህዝብንም ለእሮሮ የሚዳርግ ነው። ነገር ግን ችግሩ የሚፈታው በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ማስከበር ሲቻል ነው። በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 20 ተገልጋዮች ክርክሩ በመንግሥት ወጪ እንዲተረጎምላቸው ያስቀምጣል። ይሄ ማለት ደግሞ እያንዳንዱ ክልል ተገልጋዩ በሚፈልገው ቋንቋ ተርጉሞ ተደራሽ የማድረግ ህገ መንግሥታዊ ግዴታ አለበት ማለት ነው። በመሆኑም የክልል ፍርድ ቤቶች የወሰኑትን ውሳኔ በፌዴራል ቋንቋ አስተርጉመው መላክ እንዳለባቸው ይገልጻሉ።
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ወቅት በበተለያዩ ቦታዎች ተገልጋዩ ገንዘብ ከፍሎ ሲያስተረጉም ስህተት እየተፈጠረ ፍትህ እየተዛባ በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የራሱ የትርጉም ማዕከል ማቋቋም አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ