የከተሞች ፎረሙ ከተሞች ስኬቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ ተሞክሮአቸውን የሚለዋወ ጡበት፣ የምርምር ግኝቶች የሚቀርቡበት፣ የፖሊሲ ውይይት የሚካሄድበት እና በልማት ዙሪያ ህዝባዊ ንቅናቄ የሚፈጠርበት መድረክ ነው፡፡ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ በከተማ ልማትና እድገት ላይ የሚሰሩ አካላትን የእርስ በርስ ቅርርብና ትውውቅን በመፍጠር በአጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎችን፣ የመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና ትብብር በማጠናከር ለከተማ መልካም አስተዳደር እና ድህነት ቅነሳ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል መድረክ ነው፡፡
ዘንድሮ 8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከየካቲት 9 እስከ 14 ቀን2011 ዓ.ም «መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና» በሚል መሪ ቃል በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በጅግጅጋ ከተማ ይካሄዳል። ዝግጅቱም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክና በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጅግጅጋ ከተማ ዋና አዘጋጅነት የሚካሄድ ይሆናል፡፡ከ200 በላይ የሚሆኑ ከተሞች እና ከ20 በላይ ባለድርሻ ድርጅቶች በዝግጅቱ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የጅግጅጋ ከተማና በቅርብ ርቀት የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች በቀጥታ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ዜጎችም ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊና የስምንተኛው የከተሞች ፎረም የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሀኑ ተሾመ እንደሚሉት በዝግጅቱ በአጠቃለይ ከአስር እስከ 12 ሺ ታዳሚ የሚገኝ ሲሆን ከአፍሪካ እህት ከተሞች ከጁባ፣ ናይሮቢ ፣ኪጋሊ፣ ጅቡቲ፣ ሞቃዲሾ፣ አስመራ እና ሀርጌሳም ተሳታፊዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል። በበዓሉ ለመታደም እስካሁን ከ100 በላይ ከተሞች ተመዝግበዋል። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎች አምባሳደሮችና ሚኒስትሮች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ጨምሮ ከ800 በላይ የክብር እንግዶች በሥነሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ኃላፊው ጠቁመዋል።
በዝግጅቱ ወቅቅ «ሲቲ ማርኬቲንግ» በሚል ውድድር የሚካሄድ ሲሆን ራሱን በሚገባ ያስተዋወቀ ከተማ ሽልማትና እውቅና ይሰጠዋል። በተጨማሪም395 የልማት ኃይሎች፣ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በከተማ ሥራ ፈጠራ ስኬታማ የሆኑ ወጣቶች፣ ሴቶችና የአካል ጉዳተኞችም ተወዳድረው ተሸላሚ የሚሆኑበት ስነስረአት የሚካሄድ ይሆናል።
ኃላፊው ጨምረው እንደተናገሩት እስካሁን ፎረሙ የተካሄደባቸው ከተሞች ለዚህ ተብሎ በተሰሩ ሥራዎች ለዋሪውን ዘላቂ የሥራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል። ከነዚህ መካከል በ2007 በድሬዳዋና በ2009 ጎንደር የነበሩት የኢግዚብሽን ሳይቶች ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት በመሆን ለበርካታ የከተሞቹ ነዋሪዎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። በዘንድሮም ለጅግጅጋ ከተማ በዓሉ በሚከበርበትም ወቅት ከትንንሽ እስከ ትልልቅ ነጋዴዎች ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጠራል። ከተማ አስተዳደሩም ያለበትን አቅም በመፈተሽ ለወደፊት ሌሎች ዝግጅቶችን ለማካሄድ የመሰረተ ልማት፣ ሆቴልና በሌሎች ግንባታዎች በኩል ያለበትን ክፍተት እንዲረዳና እንዲያስተካከል ይጠቅማል። ከተሞች ገቢያቸውን እንዴት አሳደጉ በሚል የሚካሄደው ውይይት ደግሞ ለብዙዎች ተሞክሮ የሚሰጥ በመሆኑ በተለይም ዜጎች እንዴት ሀብት ማፍራት እንደሚችሉና ከተፈጠረውም ሀብት እንዴት ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግንዛቤ የሚያገኙበትም ይሆናል።
በጅግጅጋ ደግሞ በቅርቡ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የነበረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የሚያነቃቃና በኢኮኖሚው መሳተፍ ለሚፈልግ ማንኛውም አካል ምቹ ከተማዋ መሆኗ የሚታይበት እንደሚሆን አቶ ብርሀኑ ይናገራሉ። አጠቃላይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተመደበ በመጠቆምም ከዚህ ውስጥ ሚኒስቴሩ 52 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ጠቁመዋል።
«የፎረሙ መካሄድ በከተማዋ ላለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዘረፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው» የሚሉት ደግሞ የጅጅጋ ከተማ መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሰመተር ፈለቀ ናቸው። ኃላፊው እንደሚያብራሩት በአሁኑ ወቅት የኢግዚብሽን ማሳያና የማረፊያ ቦታ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በኢግዚብሽን ዝግጅቱ አንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር ርዝመትና አስር ሜትር ስፋት ያለው የኮብልስቶን መንገድና አራት ሺ ካሬ ሜትር እምነበረድ የማንጠፍ ሥራ፤ የዘጠኝ ሄክታር አጥር ማጠርና አራት ሺ ካሬ ሜትር የአረንጓዴ ልማት ፤ እንዲሁም የውሃ አቅርቦትና የመጸዳጃ ቤት ግንባታ ተጠናቋል። በዚህም ከ1ሺ44 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በጊዜያዊነትና በቋሚነት የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። ከኤሌክትሪክና ከድንኳን ተከላ ጋር በተያያዘ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ለሌሎች ዜጎችም የሥራ እድል የሚፈጠር ይሆናል ብለዋል።
ይሄ በቀጥታ ለበዓሉ በሚደረገው ዝግጅት ወቅት ያለው የሥራ ፈጠራ ሲሆን በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ደግሞ ሆቴሎች የከተማዋና በአቅራቢያው ያሉ ነዋሪዎች የተለያዩ ምርቶችን ለእንግዶች በማቅረብ የገበያ ትስስር የሚፈጠርላቸው ይሆናል። ይሄንን ተከትሎ በከተማዋ ላለው የንግድ እንቅስቃሴ በር ከመክፈቱ ባሻገር በአካባቢው ያሉ ምርቶች እንዲተዋወቁም ያግዛል። የእግዚቢሽን ቦታዎቹ በዓሉ ካለፈ በኋላ ለመዝናኛነት የሚያገለግሉ በመሆኑ በቋሚነት የሥራ እድል የሚፈጠርላቸው ዜጎችም ይኖራሉ። በአካባቢው የሚዘጋጁት የመዝናኛ ስፍራዎችንም ለማህበራት በማዛወር ለሰርግ፣ ለምረቃትና ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል ለወጣቶች ቋሚ የገቢ ምንጭ ማግኛ እንዲሆንላቸው የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በከተማዋ ያልነበሩ በባለሶስት ኮከብ ደረጃ የሚገመቱ ሶስት ሆቴሎችም እቃቸውን አሟልተው እንግዶችን ለመቀበል እየተዘጋጁ ናቸው ያሉት ኃላፊው ይህም ለወደፊት ወደከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ተመራጥ እንደሚሆንም ተናግረዋል። ይሄ እንዳለ ሆኖ አሁን ያለውና የተገነባው የሆቴል ቁጥር ይመጣል ተብሎ ከሚገመተው ህዝብ አንፃር በቂ ባለመሆኑ በከተማዋ ያሉ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንም ለእንግዳ ማረፊያነት ለመጠቀም መታሰቡን ጠቁመዋል። የክልሉ መንግሥት ለበአሉ 63ሚሊዮን ብርና ለአንዳንድ መሰረተ ልማቶች ግንባታ 24 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
የከተሞች ፎረም የሚካሄድበት ዋና አላማ በከተማ ልማት ዙሪያ የሚነሱ አዳዲስ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር መግባባት ላይ ለመድረስና የከተሞችን እድገት ለማፋጠን ነው። እስካሁንም በተካሄዱት ፎረሞች ሚኒስትሮች፣ ከንቲባዎች፣ የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር፣ በከተማ ዙሪያ ጥናት የሚያካሂዱ ተመራማሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ለከተሞች እድገትና ለድህነት ቅነሳ ይጠቅማሉ ያሏቸውን ሀሳቦች አቅርበዋል።
ከነዚህም መካከል የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና፣ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ፣ የከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ ክትትል፣ የከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር፣ የመኖሪያ ቤቶች ልማትና አስተዳደር፣ የተቀናጀ የከተሞች መሠረተ ልማት አቅርቦትና አስተዳደር፣ የከተሞች ፋይናንስ ልማትና አመራር፣ የከተሞች ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ የከተሞች አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም፣ ተደራሽነትንና የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የከተማ ልማት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ጥናቶችና ተሞክሮዎችም ከተሞች በተጨባጭ በእድገት ጎዳና እንዲራመዱ አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ ናቸው። በፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት እህት ከተሞች ተሳትፎ መኖር ደግሞ አለም አቀፍ ተሞክሮዎች በመውሰድ የተሻሉ የፖሊሲ፣ ፕላንና ትግበራ እንዲሁም ሌሎች ተሞክሮዎችን ለመውሰድና ለመተግበር በር የሚከፍት ይሆናል።
የከተሞች ፎረም በ2002 ዓ.ም ‹‹ከተሞቻችን በሥራ ላይ ናቸው›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ አንደኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ቀን የተከበረ ሲሆን፣ በ2003 ዓ.ም ‹‹ፈጣን የከተሞች እድገት ለፈጣን ሀገራዊ ልማት›› በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ፣ በ2004 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ ከተሞች በህዳሴ ጎዳና›› በሚል መሪ ቃል በመቀሌ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ ከከተሞች ቀን ወደ ከተሞች ሳምንት ስያሜውን ቀይሮ ተከብሯል፣ በ2005 ዓ.ም ‹‹ከተሞቻችን የኢንዱስትሪያሊስቶች መፍለቂያ ማዕከላት ናቸው›› በሚል መሪ ቃል በአዳማ ከተማ ለአራተኛ ጊዜ ተከብሯል፣ በ2006 ዓ.ም ‹‹ከተሞቻችን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማዕከላት በመሆን የመለስን ሌጋሲ ያስቀጥላሉ›› በሚል መሪ ቃል በባህርዳር ከተማ ለአምስተኛ ጊዜ፣ በ2007 ዓ.ም ‹‹የተደራጀ የከተማ ህዝብ ተሳትፎ ለሀገራችን ህዳሴ መፋጠን መሰረት ነው›› በሚል መሪ ቃል ከከተሞች ሳምንት ወደ ከተሞች ፎረም ስያሜው ተቀይሮ ለስድስተኛ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ ተከብሯል፤ በ2009 ዓ.ም ‹‹የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል ለሰባተኛ ጊዜ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ተከብሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ