በአሜሪካ መኖሪያ ቤት የሌላቸውና ጎዳና የወጡ ሰዎች ቁጥር 770 ሺህ ደረሰ

በአሜሪካ በተፈጥሮ አደጋ፣ በስደተኞችና በኑሮ ውድነት ምክንያት መኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር 18 በመቶ ጨምሮ ከምንጊዜውም በላይ ከፍ ማለቱን መንግሥት ይፋ አደረገ። የቤቶች እና የከተማ ልማት ሚኒስቴር ባለፈው ዓርብ ባወጣው መረጃ መሠረት 770 ሺህ ሰዎች በመጠለያዎች፣ በጊዜያዊ ቤቶች አሊያም ጎዳና ላይ ናቸው ብሏል። ይህ ቁጥር የተሰበሰበው በአውሮፓውያኑ ጥር 2024 በአንድ ምሽት ነው ተብሏል።

የአሜሪካ መንግሥት መኖሪያ ቤት የሌላቸውን ሰዎች መቁጠር የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2007 ነበር። የ2024 ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 12 በመቶ ያደገ ሲሆን የዘንድሮው ቁጥር ደግሞ በታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል። በርካታ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የተጠለሉ ሰዎች ቁጥር ባለመካተቱ መኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል ግምት አለ።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት ይህ መረጃ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል፤ ባለፈው አንድ ዓመት ደግሞ የቤት ኪራይ እና በድንበር የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሏል። መኖሪያ ቤት የሌላቸው አሜሪካውያን ቁጥር 39 በመቶ ያደገ ሲሆን በተለይ በ13 ቦታዎች ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ችግሩ የከፋ እንደሆነ ተገልጿል።

መረጃው በተሰበሰበበት ምሽት ቢያንስ 150 ሺህ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው። ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ መኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ደግሞ ስድስት በመቶ ጨምሯል። በተቃራኒው መኖሪያ ቤት የሌላቸው በውትድርና ያገለገሉ ሰዎች ቁጥር ስምንት በመቶ ቀንሷል። ይህ የሆነው አንዳንድ ከተሞች የቀድሞ ወታደሮችን ከጎዳና ለማንሳት ባደረጉት ጥረት እንደሆነ ተሰምቷል።

የመኖሪያ ቤት ሽያጭ እና ኪራይ ዋጋ ከፍተኛ በሆነባት ሎስ አንጀለስ በሰባት ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር አምስት በመቶ መቀነሱን ሚነስቴሩ አስታውቋል። ዳላስ እና ቼስተር ካውንዲ የተባሉት ቦታዎች እንዲሁ መኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ዝቅ ብሏል። አንዳንድ ባለሥልጣናት እንደሚሉት መኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለው ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው የተገለጸው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ስደተኞች በድንበር በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባት ጥረት አድርገዋል። በሪፐብሊካን የሚመሩት ቴክሳስ እና ፍሎሪዳ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዲሞክራቶች ወደሚመሩት እንደ ኒውዮርክ፣ ቺካጎ እና ዴንቨር ወዳሉት ግዛቶች ልከዋል። በእነዚህ ግዛቶች ስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ማግኘት ይችላሉ ነው የተባለው።

ቢሆንም ካለፈው ጥር ጀምሮ በድንበር በኩል ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር 60 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በርካታ ግዛቶች ድንበሮቻቸውን ዘግተዋል። ሌላቸው ለበርካታ ሰዎች መኖሪያ ቤት አልባ መሆን እንደ ምክንያት የቀረበው የተፈጥሮ አደጋ ነው። በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2023 በሁዋይ ግዛት የተነሳውን ሰደድ እሳት ተከትሎ የተፈናቀሉ 5200 ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እንደሚገኙ የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You