የኢትዮጵያ የአጭር መካከለኛ፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራትና የእርምጃ ውድድር ነገ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይጀመራል፡፡ በውድድሩም ላይ በሁለቱም ፆታ ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው ውድድሮች መካከል ሁለተኛውን ከነገ አንስቶ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲያካሂድ፣ በአጭር ርቀት (ከ100 እስከ 400 ሜትር)፣ መካከለኛ ርቀቶች (800 እና 1ሺ500 ሜትር)፣ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራት (ዝላይ፣ ውርወራ) እና የእርምጃ ውድድሮች ፉክክር ይደረግባቸዋል፡፡ በሥልጠና ላይ የቆዩ አትሌቶችም በዚህ ውድድር ወቅታዊ ብቃታቸውን የሚፈትሹ ይሆናል፡፡ በውድድሩ 21 ክለቦች፣ 2 ማሠልጠኛ ማዕከላትና 1 አካዳሚ የሚሳተፉ ሲሆን፤ በሴት 331 ሴት እና 416 ወንድ በድምሩ 747 አትሌቶች እንደሚፎካከሩም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከነገ ታኅሣሥ 22 የሚጀምረው ውድድሩ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ጠዋት ጠዋት ይካሄዳሉ፡፡ ውድድሩን ለመምራትም በዓለም አትሌቲክስ የደረጃ ሥልጠና የወሰዱ ዳኞችን ጨምሮ 170 የሚሆኑ በጎፈቃደኞችና ሌሎች ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውም ታውቋል፡፡
ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች ተሳትፎ ስኬታማ መሆን የቻሉ ታዋቂና ልምድ ያላቸው አትሌቶች የውድድሩ ተሳታፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጌትነት ዋለ፣ ታደሰ ለሚ፣ አብርሃም ስሜ፣ ሳሙኤል ፍሬው፣ መዝገቡ ስሜ፣ መለሰ ንብረት እና አድሃና ካሕሣይ በወንዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሴቶች ደግሞ ጉዳፍ ፀጋይ፣ አክሱማዊት እምባዬ፣ ሳሮን በርሄ፣ ፍሬሕይወት ገሠሠ፣ ወርቅነሽ መለሰ እና ነፃነት ደስታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የዚህ ውድድር ዓላማም ለአጭር መካከለኛ፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራትና የእርምጃ አትሌቶች የውድድር ዕድል መፍጠር ነው፡፡
በእነዚህ የአትሌቲክስ ርቀቶችና ተግባራት የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳትፎ አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ በመሆኑም በክለቦች መካከል የውድድር ዕድል መፍጠር እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትና በሽልማት ማበረታታት የፌዴሬሽኑ ዓላማ ነው፡፡ በመክፈቻው ዕለትም በበርካታ ርቀቶችና የሜዳ ተግባራት ፍጻሜዎች ይከናወናሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በሁለቱም ፆታ የዲስከስ ውርወራ፤ በሴቶች ደግሞ ርዝመት ዝላይ እና 3ሺ ሜትር መሰናክል ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ ውድድሮች ናቸው፡፡ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው የሜዳሊያ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን፤ ለማበረታቻ የሚሆን ገንዘብም ይበረከትላቸዋል፡፡ በቡድን ነጥብ ደግሞ በሁለቱም ፆታ የዋንጫ እንዲሁም በአጠቃላይ የአሸናፊ የዋንጫ ሽልማትም ይሰጣል፡፡
ውድድሩ የሚከናወንበት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም የተጎዳ መሆኑ ለውድድር አመቺ ባይሆንም በሃገሪቷ ካለው የስፖርት ማዘውተሪያ ሁኔታ አንጻር አማራጭ በማጣት እዛው ለማከናወን መገደዱንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የውድድር ማካሄጃ ቁሳቁሶች (ከዘመናዊ ሰዓት መያዣ ታይም ትሮኒክስ በቀር) የተዘጋጁ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ይጠቁማል፡፡ ውድድሩ በቀጣይ ለሚካሄዱ እንደ ኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላሉ ሃገር አቀፍ ውድድሮች አትሌቶችን የሚያዘጋጅ ይሆናል፡፡ ከዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አስቀድሞ ለሚካሄደው የቱር ውድድርም በየክለቡ ሲዘጋጁ የቆዩ አትሌቶችን የሚመዝን ውድድር እንደሚሆንም አብራርተዋል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት 10 የሚደርሱ ሃገር አቀፍ ውድድሮችን ለማካሄድ ያቀደው ፌዴሬሽኑ ይህ ሁለተኛው ነው፡፡ የ30 ኪሎ ሜትር ጎዳና ውድድር ባለፈው ወር የተካሄደ ሲሆን፤ በቀጣይ ደግሞ የ21 ኪሎ ሜትር፣ የማራቶን፣ ሃገር አቋራጭ፣ የታዳጊዎች ምዘና፣ የማሠልጠኛ ማዕከላት ውድድር፣ የወጣቶች ሻምፒዮና፣ የአበበ ቢቂላ የጎዳና ሩጫ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ደግሞ በቀጣይ የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ 42ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ የአትሌቶች ምዝገባ ዛሬ የሚጀመር መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም