ለውጤታማ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ትግበራ

በተለያዩ ምእራፎች የተተገበረው የገጠር ምግብ ዋስትና ፕሮግራም በርካታ ዜጎችንና አካባቢዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። በ1997 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮግራሙ በርካታ ተጠቃሚዎችንና አካባቢዎችን ተደራሽ በማድረግ አራት ምዕራፎችን አልፎ አምስተኛውን ምዕራፍ እያገባደደ ይገኛል። ባለፉት ዓመታት ፕሮግራሙ ሽፋኑን በማሳደግ የተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያስችሉ አያሌ ተግባራትን አከናውኗል።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፤ የፕሮግራሙ የመጀመሪያው ምዕራፍ በስድስት ክልሎች ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ በቀድሞ ደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች፤ ሀረሪ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ያቀፈ ነበር። የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ በመጠቀም የምግብ ክፍተታቸውን በማጥበብ የምግብ ዋስትናቸውን እያሻሻሉ መጥተዋል።

የመርሃ ግብሩ ስራዎችን በሚመለከት በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አማካሪ ወይዘሮ ሰዒዳ ከድር በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በመርሃ ግብሩ የምግብ ክፍተታቸውን ለመሙላት ሲባል ምርታማ የሆኑ የቤተሰብ ጥሪቶቻቸውን እንዳይሸጡ የመከላከል ስራ ተሰርቷል፤ የፕሮግራሙን ተጠቃሚዎች በተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የልማት ስራዎች በመሳተፍ የተራቆቱና ለድርቅ የተጋለጡ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ እና ለምርት አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል፤ በማህበረሰብ የልማት ስራዎች የገጠር መሰረተ ልማት አውታሮችና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታዎችን በማከናወን የአካባቢው ህብረተሰብ ከተገነቡት የገጠር መሰረተ ልማት አውታሮችና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተጠቃሚ ሆነዋል።

የሁለተኛው ምዕራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ1999-2001 ድረስ ባሉት ሦስት ዓመታት በሰባት ክልሎች በ244 ወረዳዎች 7 ሚሊዮን 57 ሺ480 ተጠቃሚዎችን በማቀፍ በምእራፍ አንድ ላይ የተጀመሩ የማህበረሰብ የልማት ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከርና በማስፋት መቀጠሉን ወይዘሮ ሰዒዳ ይናገራሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የሦስተኛው ምዕራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ2002 -2007 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ተተግብሯል። በዚህም ምዕራፍ የሶማሌ ክልልን በመጨመር በስምንት ክልሎች 318 ወረዳዎች 7 ሚሊዮን 574ሺ 480 ተጠቃሚዎችን በማቀፍ ተሰርቷል። በምእራፍ ሁለት ከነበሩት ተጠቃሚዎች በተደረገው አጠቃላይ ልየታ እና 472ሺ 522 የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ተመርቀዋል። በወጡት ምትክ በነበረው የሀብት እጥረት ምክንያት መሳተፍ የነበረባቸውና ያልተካተቱ በዚህ ምዕራፍ እንዲካተቱ መደረጉንም ይጠቅሳሉ።

እንደ አማካሪዋ ማብራሪያ፤ በሁለቱ ምዕራፍ የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የውሃ ማሰባሰብ ስራ እና የአነስተኛ መስኖ ልማት ስራዎች በማስፋፋት የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በተገነቡ የመስኖ ልማት አውታሮች በመጠቀም እና በመስኖ የሚለሙ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን በማምረት በቤተሰብ ደረጃ ተጨማሪ ገቢና ጥሪት በመፍጠር ኑሯቸው እንዲሻሻል ተደርጓል። የቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ፕሮግራሙ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጋር ተሳስሮ እንዲተገበር በማድረግ ተጠቃሚዎች ተጨማሪ ጥሪትና ገቢ እንዲፈጥሩ በማድረግ ኑሯቸው እንዲሻሻል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

በቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ፕሮግራም ለሚታቀፉ ተጠቃሚዎች በግብርና እና ከግብርና ውጪ ባሉ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ለመሳተፍ የሚያስችላቸው የክህሎት ስልጠና በመስጠት እና የብድር አገልግሎት ከሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በማገናኘት የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል። ተጠቃሚዎቹ ባገኙት ብድር በመጠቀም በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢና ጥሪት በመፍጠር 3ነጥብ4 ሚሊዮን (45 በመቶ) የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች እንዲመረቁ መደረጉንም አመልክተዋል።

በአራተኛው ምዕራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት በስምንት ክልሎች 7 ሚሊዮን 997 ሺ 216 ተጠቃሚዎችን በማቀፍ በሶስተኛው ምዕራፍ ለየብቻ ይተገበሩ የነበሩትን የቤተሰብ ጥሪት ግንባታ እና የሴፍቲኔት ፕሮግራም የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ተሳስረው እንዲተገበሩ ተደርጓል። በዚህ ረገድም ወይዘሮ ሰዒዳ በሦስቱ ምእራፎች የተገኙ ውጤቶች እና የታዩ ለውጦችን በማጠናከር የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሚደረግላቸው የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመጠቀም የምግብ ዋስትናቸውን እያሻሻሉ እንዲመጡ ጥረቶች ተደርጓል ብለዋል።

በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ የሥራ ዘርፍ የድሃ ድሃ ተብለው ለተለዩ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የአንድ ጊዜ የጥሪት መፍጠሪያ የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አመልክተው፣ ይህን ገንዘብ በመጠቀም በተለያዩ የግብርና እና ከግብርና ውጭ ባሉ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንዲመጡና ወደ መደበኛ የብድር ሥርዓት እንዲገቡ ተሰርቷል ይላሉ።

‹‹በ2008 እና በ2009 የተከሰተውን የኢሊኖ ክስተትን በመቋቋም በአራተኛው ምዕራፍ የፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ወቅት የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የምግብ ክፍተታቸውን መሙላት ተችሏል›› ሲሉ ይናገራሉ። በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ የስራ ዘርፍ የሚደረግላቸውን ድጋፍ በመጠቀም በቤተሰብ ደረጃ ጥሪት ፈጥረው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ ከፕሮግራሙ 249 ሺ 516 ተጠቃሚዎች ማስመረቅ መቻሉንም አስታውቀዋል።

በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት በአራቱም ምዕራፎች ከላይ በየምዕራፉ የተጠቀሱትን ጉልህ ውጤቶች ማስመዝገቡ እንደሚታወቅ ተናግረው፤ ውጤቱን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ በየሁለት ዓመቱ ገለልተኛ በሆነ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት የተፅእኖ ግምገማ ጥናት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተካሄደው የአዋጭነት ጥናት ውጤት ጠቅሰው ሲያብራሩም፤ በየተፋሰሶቹ የተሰሩት የባዮ ፊዚካል ስራዎች የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ እያሻሻሉ መምጣታቸው መታወቁን ተናግረዋል። ከአራተኛው ምእራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ጀምሮ የአፈር መሸርሸር በ36 በመቶ መቀነሱን፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ መሻሻል መታየቱን፣ መስኖ በመጠቀም የሰብል ማምረት ተግባር በሶስተኛው ምዕራፍ ከነበረበት 12 በመቶ ወደ 16 በመቶ እድገት ማሳየቱን ያመለክታል ብለዋል።

በጥናቱ የተመላከተውን ጠቅሰው እንዳብራሩትም፤ የገጠር መንገድ ስራ እየተስፋፋ መምጣቱ እና ይህም ለተጠቃሚዎች የግብርና ግብዓቶችን በቅርብ ማግኘት ያስቻለ መሆኑ ተረጋግጧል። በናሙናነት ከተወሰዱ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ውስጥ የሚገኘው የሰብል ምርት በ24 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተለይቷል።

በዚህም ለድህነት ቅነሳ ቁልፍ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል። ሀገራዊ የድህነት መጠንን በሁለት በመቶ በመቀነስ በአፋጣኝ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አበርክቷል። በቆላማው አካባቢም የምግብ ክፍተት በአማካይ በአንድ ነጥብ አንድ ወራት የቀነሰ ሲሆን፣ በደጋ አካባቢ ደግሞ በ0 ነጥብ አምስት ወራት የምግብ ክፍተት በአማካይ ቀንሷል። የፕሮግራሙ ዲዛይን እና ተግባራዊነት ተጠቃሚ ቤተሰቦች ወቅታዊ ረሃብን በተሻለ ሁኔታ እንዲቋቋሙ አግዟል።

ወይዘሮ ሰዒዳ የምግብ ዋስትናን ከፍ ከማድረጉ እና የድህነት ንረትን የቀነሰና በጥቅሉ የ2018 ዋጋዎችን በመጠቀም በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ቤተሰቦች መካከል በነፍስ ወከፍ በየወሩ የፍጆታ ወጪ በ5ነጥብ6 በመቶ መጨመሩ ከመጡት ለውጦች መካከል አንዱ ነው ሲሉም አብራርተዋል። በምርታማነት እና በዕድገት ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ማሳየቱን ያመለክታሉ። አብነት አድርገውም ‹‹ የምርት እድገትን፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች የሰብል ምርት በአማካይ በሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አበርክቷል›› ይላሉ። በሌላ በኩል ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ተፅዕኖ ማበርከቱን ያነሳሉ።

ከላይ የተመዘገቡ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው በአራቱ የፕሮግራሙ ዓመታት ችግሮች ማጋጠማቸውንም አመልክተዋል። በየደረጃው ያለው የማስፈፀም አቅም ውስንነት፣ የባለድርሻ አካላት በኃላፊነት እና በተጠያቂነት መንፈስ ስራቸውን አለማከናወን፣ ሌሎች የልማት ፕሮግራሞች የሴፍትኔት ተጠቃሚዎችን አካታች አለማድረግ ወይም የፕሮግራም ትስስር አለመኖር ችግር መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ ክስተት እና የብድር አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙንም ጠቁመው፤ በተለይም ተጠቃሚው በስፋት እንዲመረቅና ፕሮግራሙን እንዲለቅ አለመደረጉ፣ በስፋት ማስመረቁ ያለው ሀገራዊ ፋይዳን በጥልቀት አለመገንዘብ፣ በየደረጃው በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ላይ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ፕሮግራሙ በተቀረፀው መሰረት ያስቀመጣቸውን ግቦች በሚፈለገው ልክ ማሳካት እንዳላስቻለ ነው ያስገነዘቡት።

ከባለፉት አራት ምዕራፎች የተገኙ ለውጦችን በማጠናከርና ከታዩት ችግሮች በመነሳት የወደፊት የፕሮግራሙን አቅጣጫ በማስቀመጥ በየደረጃው የሚገኘው አካል በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ መሆኑን ትምህርት በመውሰድ የአምስተኛው ምዕራፍ ዲዛይን እንዲቀረፅ መደረጉን ያመለክታሉ። ‹‹ካለፉት አራት ምእራፎች ከተከናወኑት የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች በጎ ተሞክሮዎች ልምድ በመውሰድ ከ2013-2017 ድረስ የሚካሄድ የአምስተኛው ምዕራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተቀርፆ ወደ ትግበራ ተገብቷል›› በማለት ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይህም ምእራፍ በሰኔ ወር 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል፤ ፕሮግራሙ በአስር ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር (ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ ሀረሪ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደደር) የሚገኙ 489 ወረዳዎችንና 7 ሚሊዮን 997ሺ 216 ተጠቃሚዎችን በማቀፍ ይገበራል።

በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዓመት ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የልየታ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ በዚህም አሰራር የድሃ ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች ፍትሃዊ በሆነ የልየታ አሰራር ተለይተው የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን በአካባቢያቸው ከሚገኙ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በፕሮግራሙ ውስጥ እንደ አንድ ግብ ተካተው እየተተገበሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ የስራ ዘርፍ ለድሃ ድሃ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የሚቀርበው የአንድ ጊዜ ጥሪት መገንቢያ ድጋፍ ሦስት መቶ ዶላር እንዲሆን በማድረግ እና ለተለዩት የድሃ ድሃ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በማሰራጨት ኑሯቸው እየተሻሻለ እንዲመጣ እገዛ መደረጉን ይጠቅሳሉ። በሁሉም የስራ ዘርፎች የስርዓተ ፆታ እና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም ሥርዓተ ምግብ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲተገበሩ እየተደረገ መሆኑም አመልክተዋል።

እንደ አማካሪዋ ማብራሪያ፤ ማሻሻያዎች እና አዳዲስ የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘመንና በማስፋፋት ለመተግበር ያለው ጥረት እና ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ በትግበራው ሂደት ችግሮችም አጋጥመውታል። እነሱም በፕሮግራሙ ዲዛይን መሰረት ከለጋሾች መቅረብ የሚገባው ሀብት ላይ ከፍተኛ መዘግየት እና የገንዘብ መጠን መቀነስ መኖሩ፣ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ፣ በኮቪድ እና ግጭት ምክንያት ለልማት መዋል ያለበት ሀብት ወደ እለት ደራሽ ምላሽ መዞሩ መርሀ ግብሩን በተሟላ መልኩ ለመተግበር እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጠቃሚዎች ጥሪት መመናመኑ፣ የዋጋ ንረት፣ በቤተሰብ ደረጃ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ኑሮ እንዲሻሻል ከማድረግ አንፃር ለልማት ሊውሉ የሚችሉ ያገገሙ ተፋሰሶችን ወደ ልማት ለማስገባት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን በዘርፉ ከታዩ ተግዳሮቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

‹‹በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ የስራ ዘርፍ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢና ጥሪት በመፍጠር ከፕሮግራሙ እንዲመረቁ ከማድረግ አንፃር በቂ የብድር አቅርቦት አለመኖሩ ሌላኛው ችግር ነበር›› ይላሉ። በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም በኃላፊነት ተጠያቂነት መንፈስ ስራቸውን አለማከናወናቸው ሌሎች ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

መንግሥት በዘርፉ ላይ በሁሉም ረገድ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የግብርና ሽግግር ለማምጣት ለዜጎች በቂ፣ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ። ይህንን እውን ለማድረግ የተረጂን ቁጥር እና የተረጂነትን ስሜት ወይም አመለካከትን መቀነስ ብሎም አደጋን የሚቋቋም ማህበረሰብ መፍጠር መቻል የሀገሪቱ እድገት አንዱ መገለጫ እንደሆነ ያነሳሉ።

ፕሮግራሙ የሚከናወነው በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች የጋራ ትብብር እና ስምምነት መሆኑን ወይዘሮ ሰዒዳ ገልጸዋል፤ ‹‹በአጋር አካላት ለሚደረገው ትብብር ሁሉ መንግሥትም ሆነ ተቋሙ ከፍተኛ ክብርና እውቅና ይሰጣሉ፤ ምክንያቱም ከላይ በየምዕራፉ እንደተጠቀሰው የህብረተሰቡን የምግብ ክፍተት በማሟላት እና በተለያዩ የዕድገት መርሀ ግብሮች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ በማድረግ ሊቆጠርና ሊታይ የሚችል ለውጦች እንዲመጡ አስተዋፅኦ አድርጓል›› ሲሉም ያስረዳሉ።

አሁን ሀገሪቷ ካስቀመጠችው የተረጂነት ቅነሳ መርሀ-ግብር አንጻር ሲታይ የተረጂነትን አመለካከት በማስተናገድና ርዳታን በመጠበቅ የእድገት ግቦችን ማሳካት እንደማይቻል አስገንዝበው፣ ‹‹በርከት ያለ ቁጥር ያለው ተረጂ ማህበረሰብንም ይዞ ሀገሪቷ ያስቀመጠቻቸውን ራዕይ ማሳካት አይቻልም›› ሲሉም አስታውቀዋል።

ስለሆነም የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በአካባቢው ባለው እምቅ ሀብትና ፀጋ ተጠቅሞ በልማት እንዲሳተፉ በማድረግ ኑሮአቸውን ማሻሻልና ከፕሮግራሙም በስፋት እየተመረቁ እንዲወጡ፣ የጠባቂነት አመለካከቶች ተወግደው የትርፍ አምራችነት ስሜት በተጠቃሚው የማህበረሰብ ክፍል እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በቅንጅት የመስራት ባህልን እንዲያጎለብት በኃላፊነት፣ በቁርጠኘነትና በተጠያቂነት መንፈስ መስራት እንደሚገባ አስታውቀው፤ ‹‹ይህንንም ለማረጋገጥ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ የሚታቀዱ እና የሚተገበሩ ስራዎች አሉ፤ ይህንንም ተመርኩዞ የቁልፍ አመለካከቶች አፈፃፀምን በየጊዜው በመገምገም ለውጥ ለማምጣት መስራት ግድ ይላል›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You