የበለስ ማርማላት አምራቿ መውጫዎች

በትግራይ ክልል ሐውዜን ከተማ ነው የተወለደችው። ወላጅ አባቷ በሥራ ምክንያት ወደ ያኔዋ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ኤርትራ መዛወራቸውን ተከትሎ አብዛኛውን የትምህርት ዘመኗን በአስመራ ነው የተከታተለችው። የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲከሰት እሷም ሆነች መላው ቤተሰቧ ወደ ትውልድ ቀያቸው ለመመለስ ተገደዱ።

የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን ወይዘሮ ፀጋ ገብረኪዳን ከልጅነቷ ጀምሮ ፀሃፊ ወይም ተቀጣሪ ሰራተኛ የመሆን ሕልም እንደነበራት ትናገራለች። ይህንን ሕልሟን ለማሳካት ስትልም ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የኮምፒውተር ትምህርት ስልጠና ወስዳለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም በቀጥታ የግል ኮሌጅ ገብታ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች።

ዳሩ ግን ሕይወት እንዳሰበችው ቀላል አልነበረችምና በተማረችው ትምህርት ሥራ ማግኘት አልቻለችም። ከብዙ ልፋትና ጥረት በኋላ ማግኘት የቻለችው ሥራ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በፅዳትና ተላላኪነት ተቀጥሮ ማገልገል ብቻ ነበር። እሱንም ቢሆን አልናቀቸውም፤ መሸጋገሪያ ይሆነኛል በሚል ተስፋ ሰንቃ ማገልገሏን ቀጠለች። በዚሁ ተቋም ውስጥ እያገለገለች ሳለ ግን የሕይወት መስመሯን ሙሉ ለሙሉ መቀየር የሚያስችል የስልጠና እድል አገኘች። ይህም በአንዲት የውጭ ዜጋ አማካኝነት ያገኘቸው በበለስ ማርማላት መስራት የሚያስችል ክህሎት ነበር።

ከዚያ በፊት ግን በለስ በአካባቢያቸው ተወዳጅ የሆነ ፍራፍሬ ቢሆንም እሷም ሆነች ሌሎች ሰዎች የበሰለውን ልጠው ከመብላት ባሻገር በማርማላት መልኩ ተቀናብሮ ሊበላ እንደሚችል አታውቅም ነበር። ማርማላት ብቻም ሳይሆን ጁስና ወጥ መስራት እንደሚቻል እውቀት ቀሰመች። ይህ ስልጠና ደግሞ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ይመለከት የነበረውን ማንነቷን እንዳሰፋላት ታስረዳለች።

ከስልጠናው በኋላ ተቀጥራ ለመስራት ልቧ አልፈቀደምና ያገኘችውን ክህሎት በተግባር ለማዋል ቆርጣ ሥራዋን ለቀቀች። እናም ከወላጆቿ ባገኘችው አምስት ሺ ብር ለሥራ የሚያስፈልጋት ቁሳቁስ ገዛች፣ በተረፋት ቤት ተከራይታ የበለሱን ጭማቂ፣ ማርማላትና ወጥ ሰርታ በነጻ ቅመሱልኝ እያለች ለአካባቢዋ ሰዎች ሁሉ ማስተዋወቋን ጀመረች።

ጥቂቶች ምርቷን ቀምሰው ቢወዱትም፤ ምርቱ በተለይ በክረምት እንደልብ የሚገኝ በመሆኑ ምርቷ እንዳሰበችው ቶሎ ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም። ‹‹አንዳንዶቹ በጥሬው መብላት ስንችል ለምን በፋብሪካ የተቀነባበረ እንበላለን፤ እንደከብት ታሽጎ የቀረበ ቅጠል አንበላም›› የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶች ይሰነዘሩ እንደነበርም ታስታውሳለች። እሷ ግን ራዕይዋ ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ በላይ አሻግሮ የሚያይ በመሆኑ በአሉታዊ አስተያየቶቹ ተስፋ አልቆረጠችም፤ ይልቁንም ጆሮ ሳትሰጥ ምርቷን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ማስተዋወቁን ተያያዘችው።

ሆኖም ምርቷን አምኖ የሚገዛ በማጣቷ ለኪሳራ ተዳረገች፤ ተመልሳም ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ገባች።የበለሱ ማርማላት ሰው እያወቀውና እየለመደው ሲሄድ ተቀባይነት ያገኛል የሚል ተስፋ ስለነበራት የተወሰነ ገንዘብ አጠራቅማ ተመልሳ ማምረቷን ቀጠለች። በኤግዚቢሽኖችና በየገበያው እየዞረች ምርቷን ለማስተዋወቅ ጥረት አደረገች።

ከሽያጩ የምታገኘው ትርፍ በጣም አነስተኛ በመሆኑ የቤት ኪራይ መክፈል እየተሳናት ከሁለትና ሶስት ጊዜ በላይ ወደ ቤቷ እየተመለሰች፤ መልሳ እየወጣች ለሰባት ዓመታት ቆየች። ሥራው ለብቻ መስራት ከባድ መሆኑን ተገነዘበች። እናም አራት አጋሮችን ጨመረችና አቅማን አጎለበተች።

ከሥራ አጋሮቿ ጋር በመሆን ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው ፤ የመስሪያ ቦታም ከከተማ አስተዳደሩ አግኝተው በስፋት ወደ ማምረት ገቡ፤ የማስተዋወቁንም ሥራ ተቀናጅተው ይሰሩ ስለነበረም ተቀባይነታቸው እያደገ መጣ።

ወይዘሮ ፀጋ ይህንን ማየቷ ይበልጥ ለመስራት አነሳሳት፤ ምርቶቿ ከከተማ አልፎ በአዲስ አበባ ሱፐርማርኬቶችና የዓለም ትልልቅ ገበያዎች ላይ ማግኘት ትመኝም ስለነበር፤ ለዚያ ይረዱኛል ያለቻቸውን የመንግሥትና የግለሰብ ቢሮዎች ሁሉ አንኳኳች። ልፋቷ ከንቱ አልቀረም፤ እንዳሰበችውም ለመጀመሪያ ጊዜ የበለስ ማርማላቱ ኢትዮጵያን ወክሎ ጣሊያን ገበያ ላይ ዘልቆ መግባት ቻለ፤ ጥሩ ተቀባይነትም አገኘ። እነ ወይዘሮ ጸጋ ሥራቸው እየሰፋ ሲሄድ አሁንም በእነሱ ብቻ የሚሰራ አለመሆኑን ተገነዘቡና 20 የሚደርሱ ወጣቶችን በጊዜያዊነት ቀጥረው እስከማምረት ደረሱ።

በለስ በትግራይ በስፋት የሚገኝ ቢሆንም፣ የሚመረተው ግን በባኅላዊ ዘዴና መሳሪያ በመሆኑ ቀጣይነት ባለው መልኩ የማርማላት ምርቱን በስፋት በአዲስ አበባም ሆነ በዓለም ገበያ ለማቅረብ አለመቻላቸውን ይረዳሉ።‹‹የፋይናንስ እጥረት ስለነበረብን የምንፈልጋቸውን የማምረቻ መሳሪያዎች መግዛት አልቻልም›› የምትለው ወይዘሮ ፀጋ፤ ከአጋሮቿ ጋር በመመካከር ድርጅታቸውን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር ሕልም ሰንቀው ከሁለት ብድርና ቁጠባ ተቋማት አምስት መቶ ሺ ብር ተበደሩ።የጠርሙስ እጥረት ስለነበረባቸውም አክሲዮን ገዝተው በአካባቢያቸው ከሚገኝ ብርጭቆ ፋብሪካ ጋር ውል ፈፀሙ።

ይሁንና ሥራ ፈጣሪዋ ወይዘሮ ፀጋና ባልደረቦቿ ወደ ኢንዱስትሪ የማደግ ተስፋቸውን ከነጭራሹ የሚያጨልም ክስተት ገጠማቸው። ይኸውም በትግራይ የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት ነው፤ ‹‹በጦርነቱ ምክንያት ሼር የገዛንለት ብርጭቆ ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ ወደመ፤ የተበደርነውም ብር ጥቅም ላይ ሳናውለው አላግባብ ባከነ›› በማለት ቅስሟን የሰበረውንና ለኪሳራ የዳረጋትን አጋጣሚ ታስታውሳለች።ከሁሉ በፊት ሕይወትን ማዳን ይቀድማልና እሷም ሆነች አጋሮቿ ጦርነቱ እስከሚጠናቀቅ ያለሥራ ለመቀመጥ መገዳደቸውንም ትገልፃለች።

‹‹ ዋናው ሰላም ነው፤ ሰላም ካለ ሁሉንም እንደገና መመለስ ይቻላል›› የምትለው ወይዘሮ ፀጋ፣ እሷና አጋሮቿ ሃገር ስትረጋጋ እና በአካባቢያቸው የሰላም አየር መንፈስ ሲጀምር ያዘመመውን የንግድ ተቋማቸውን ዳግም ለማንሳት መከሩ፤ መክረው ብቻ አልቀሩም፤ ያለቻቸውን ጥሪት አሰባስበው ማምረታቸውን ቀጠሉ።

ልክ እንደ በፊቱ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በእሷ መሪነት ምርታቸውን በየኤግዚቢሽኑና ሱፐር ማርኬቱ ማስተዋወቃቸውን ቀጠሉ።በተለይም የምርታቸውን ጣዕም ቀምሰው በሚገባ ያጣጣሙት የአካባቢው ሰዎች በመስሪያ ቦታቸው በመምጣት እንደሚገዟቸው ትናገራለች።

በአሁኑ ወቅት የእነ ወይዘሮ ፀጋን ጥረት የተመለከተው የከተማ አስተዳደሩ የገበያ ትስስር ፈጠረላቸው፤ በዚህም ምርታቸው አዲስ አበባ ከሚገኝ ሱፐርማርኬት ተቀባይነት ማግኘቱን ታስረዳለች።

እነ ወይዘሮ ጸጋ አስር ያህል ሰዎችን በጊዜያዊት በመቅጠር ሥራቸውን እያስፋፉ ይገኛሉ።ሥራው አሁንም በእጅ (በማኑዋል) የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባሰቡት መጠንና ጥራት ልክ ማምረት አለማቻላቸውን ወይዘሮ ጸጋ ትገልጻለች።

‹‹በለስ በተለይ በትግራይ በብዛት ይመረታል፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህንን ምርት እንደ ሃብት ቆጥረነው አናውቅም ነበር፤ እንደ ሜክሲኮ ያሉ ሃገራት ከራሳቸው አልፈው ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እያገኙበት ነው›› የምትለው ወይዘሮ ጸጋ፤ በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል እንደሚባለው ሁሉ ይህንን ሃብት በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል ያለመቻሉ ሁልጊዜም ቁጭት ይፈጥርብኛል ትላለች።

‹‹በለስን በማርማላት መልኩ የማቀነባበሩ ሥራ አድካሚ መሆኑን እያወቅሁ ስለገባሁበት ባጋጠሙኝ ችግሮች ሁሉ ተስፋ ሳልቆርጥ ነው የቆየሁት›› የምትለው ወይዘሮ ፀጋ፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የለፋችበት የበለስ ማርማላት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ እውን እንደሚሆን፤ ለሃገርም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ እንደሚሆን እርግጠኛ ነች። ለዚህም ቀን ከሌሊት እየሰራች ትገኛለች፤ በተለይም በምንም ማዳበሪያ ወይም ሰው ሰራሽ ግብዓት የማይመረት መሆኑም በዓለም ገበያ ተፈላጊ እንደሚሆን አትጠራጠርም።

ለዚህም ዋስትና የሰጣት ከዚህ ቀደም ምርቱ በጣሊያን ቀርቦ የተገኘው መልካምና አበረታች ግብረ መልስ እንደሆነ ትናገራለች። በሌላ በኩልም ለማምረት ምንም አይነት ጥሬ እቃ ከውጭ ማስመጣት የማይጠበቅ መሆኑም ከተሰራበት በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ታምናለች።

‹‹ከቤቴ አጥር በሚገኝ ምርት ብቻ ማርማላቱ የሚመረት መሆኑ በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን የሚቻል ስለመሆኑ አልጠራጠርም›› ትላለች። ምርቱን በስፋት ማምረት ከተቻለ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ሃገራዊ ጥረት አጋዥ እንደሚሆንም ትገልፃለች።

ከዚህ ባሻገር ከውጭ የሚገባውን ማርማላት የመተካት አቅም ያለው በመሆኑ ሃገሪቱ ማርማላት ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በመታደግ ረገድ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ታስረዳለች። ‹‹ በአካባቢያችን ያለውን ምቹ እድልና ያለሥራ የተቀመጠ የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ከራሳችን አልፈን ለሌሎችም ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ያስችለናል›› ስትልም ታመለክታለች። ‹‹ከአሁን በኋላም የቱንም አይነት አስቸጋሪ ሁኔታና ፈተና ቢያጋጥመን ወደ ኋላ እንደማንመለስ እርግጠኛ ነኝ›› ትላለች። አሁን ላይ ቀድሞ የነበሩት አሉታዊ አመለካከቶች መቀረፋቸውን ጠቅሳ፤ ማርማላቱ ከተመረተ የገበያ ችግር ያጋጥማል ብላ እንደማታስብ ትናገራለች።

በቅርቡ ምርቱ ለአንድ ሱፐርማርኬት እየቀረበ መሆኑን ጠቅሳ፣ ምርቱን በሌሎችም የንግድ ማዕከላት በስፋት ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኗን ታስረዳለች። ከሁሉም በላይ ግን ራሱን የቻለ የበለስ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት መታቀዱንም ትናገራለች። ከማርማላት ጎን ለጎን ከበለስ የሚሰሩ የመዋቢያ ቁሳቁስ (ኮስሞቲክስ) ለመስራት ማሰቧን ጠቁማለች።ጥራቱን የጠበቀ የበለስ ምርት ወሳኝ በመሆኑ ለገበሬዎች ስልጠና በመስጠት ትስስሩን በማጠናከር ለሌሎች ማሳያ የሆነ ድርጅት እንዲኖራትም ትፈልጋለች።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ከሰጣቸው የማምረቻ ሼድ በተጨማሪ፤ ማርማላቱን ለማምረት የሚያስችሉ ባኅላዊ መሳሪያዎችና ቁጥራቸው ከ500 ያላቀ የተመረቱ ማርማላታዎችንና በጥሬው ያለውን ጥሬ ገንዘብ ጨምሮ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ካፒታል እንዳላቸው ትጠቁማለች። ይሁንና ካፒታላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ከአጋሮቿ ጋር ቀን ከሌት እየተጋች መሆኑንም ታመለክታለች።

ይህ ሕልሟ እንዲሳካ ግን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ትጠቁማለች።በተለይ የቴክኖሎጂ አማራጮች፤ የፋይናንስ ተቋማት እና የመንግሥት አካላት በለስ ለሃገር ያለውን ፋይዳ ተገንዝበው የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቃለች።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You