እንደሀገር የገጠር ምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ1997 ዓ.ም ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ተጠቃሚዎችንና አካባቢዎችን ተደራሽ በማድረግ አራት ምዕራፎች አልፈው አምስተኛው እየተገባደደ ይገኛል። በዚህም ባለፉት ዓመታት ፕሮግራሙ ሽፋኑን በማሳደግ የተጠቃሚዎችን የኑሮ ደረጃ ለመለወጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይም በአራቱ ምዕራፎች በቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ፕሮግራም የታቀፉ ተጠቃሚዎችን በግብርና እና ከግብርና ውጪ ባሉ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የክህሎት ስልጠና በመስጠት እና የብድር አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በማገናኘት የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህንን ገንዘብ በመጠቀምም በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢና ጥሪት በመፍጠር ከሶስት ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች ከተረጂነት መላቀቃቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በአምስተኛው ምዕራፍም ካለፉት ዓመታት ልምድ በመቀመር ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተለይተው ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ በዘለለ በተለያዩ የልማት መርሃ ግብሮች ተሳትፈው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው። በዋናነትም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ባለው ‹‹ከተረጂነት ወደ ምርታማነት›› በሚለው ንቅናቄ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ይጠቀሳል። ይህም ከግለሰብ እስከ ሀገር ደረጃ በምግብ እህል ራስን በመቻል ሉአላዊነትን ለማስከበር ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል።
በዚህ ረገድም ክልሎች እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመቃኘት መርሃ ግብሩን ተግባራዊ እያደረጉ ሲሆን፤ በዋናነትም ያላቸውን እምቅ አቅምና የተፈጥሮ ፀጋን ያገናዘቡ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከእነዚህም ክልሎች መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው። በክልሉ በመርሃ ግብሩ እየተረዱ ያሉ ዜጎችን ከተረጂነት ለማውጣትና ምርታማ ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር በተመለከተ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምአን አነጋግረናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- በክልል ደረጃ በልማታዊ ሴፍቲኔት እየተረዱ ያሉ ዜጎች ከተረጂነት እንዲላቀቁ እየተሠራ ያለው ሥራ ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር ጋንታ፡- ዜጎች ከጠባቂነት አስተሳሰብ ተላቀው አምራች እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን። በአሁኑ ወቅት በክልላችን 52 ወረዳዎች ላይ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ባለፉት ዓመታት ቀለብ የስድስት ወር፣ በኋላም የአራት ወር ፣ ሌሎች ደግሞ የአስር ወር ሲያገኙ ነበር። ይህም ደግሞ በዋነኝነት አላማው የምግብ ክፍተታቸውን ለመሸፈን ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀለብ ካገኙ በኋላ በተመረጡ ማሕቀፎች ፣ በግብርና አልያም ከግብርና ውጪ በሆኑ ዘርፎች ላይ ስልጠና እንዲወስዱ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
በመቀጠልም የአዋጭነት እቅድ አዘጋጅተው፣ ካላቸው ላይ እንዲቆጥቡ እና ብድር አግኝተው በመረጡት መስክ እንዲሰማሩ የማድረግ እና ጥሪታቸውን የመገንባት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ይህም የሁሉንም ግለሰብ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፤ የገቢ አቅሙንም ጎን ለጎን ለመገንባት ያለመ ነው።
በተጓዳኝም በጉልበት ሥራዎች እና በካፒታል በጀት የማህበረሰቡን ጥሪት የመገንባት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሠራ ነበር። ይህም ሲባል የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በመሥራት የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ እንዲሁም ምንጮች እንዲጎለብቱ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል። በተያያዘም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ግለሰብ ጥሪት እንዲገነባ አቅም የሚሆኑ የማህበረሰብ ሥራዎች ናቸው በፕሮግራሙ ሲከናወኑ የቆዩት። ተፋሰሶች እንዲለሙ እና ምንጮች እንዲጎለብቱ ከማድረግ በዘለለ በተሠሩት ሥራዎች የአካባቢውን ጥሪት ማሳደግ እንዲቻል ነው ታሳቢ ተደርጎ ሲሠራ የቆየው። ማህረሰሰቡ ከዚህ ጥሪት ተጠቃሚ ሆኖ አቅሙን እንዲያሳድግ ጥረት እየተደረገ ነው። በአጠቃላይ እነዚህን ተግባራት በብቃት በመፈፀም ተረጂዎች ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን- ታዲያ እነዚህ ሥራዎች ምን ያህል ውጤት እያመጡ ነው?
ኮሚሽነር ጋንታ፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት እነዚህ ሥራዎች ረጅም ጊዜ የቆዩ ሲሆን፤ አሁን አምስተኛውን ምዕራፍ እያገባደድን እንገኛለን። ልማታዊ ሴፍቲኔት እንደሚታወቀው አምስተኛ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። እንደመንግሥት በተያዘው መርህ አንደኛው እና ትልቁ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን ነው። እንዲሁም ደግሞ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ንቅናቄ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው።
በክልላችን እስከአሁን ባለው ሁኔታ ንቅናቄው ‹‹አባቶቻችን ምንም ሳይኖራቸው በወኔና ባህላዊ መሳሪያ ያስከበሯትን ሀገር እኛ ደግሞ ለስንዴ እጃችንን እየዘረጋን ሀገራችንን ዝቅ እንዳናደርጋት ተግተን መሥራት አለብን›› የሚል አስተሳሰብ ላይ መግባባት ተፈጥሮ እየተተገበረ ያለው ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ ይህ ንቅናቄ በፌዴራል ደረጃ በፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ሆኖ ወደ ክልል ሲወርድ የክልሉ ፕሬዚዳንት ወይም ደግሞ የመንግሥት ዋና ተጠሪ የሚመሩት ነው። የንቅናቄው መድረክ ደግሞ እስከ ቀበሌ ከወረደ በኋላ እቅዶች ታቅደው፤ በየጊዜው የሚገመገሙበት ሥርዓት ተበጅቷል።
በንቅናቄው ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እያንዳንዱ የክልሉ ነዋሪ በተለይም ከመንግሥትም ሆነ ከለጋሽ አካላት ድጋፍ እያገኙ ያሉ ተረጂዎች ራሳቸው “ከተረጂነት መውጣት እችላለሁ›› የሚለውን አስተሳሰብ መፍጠር መቻል አለባቸው። አባቶቻችን ሕይወታቸውን ሰጥተው ጠላትን እንዳንበረከኩት ሁሉ ዛሬ ላይ ያለነው ትውልዶች ባለን አቅም ተጠቅመን ድህነትን ማበርከክ መቻል አለብን።
በክልላችን ባለፉት ዓመታት ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ምቹ የአየር ፀባይ 13 ወራት በሙሉ ማምረት የሚያስችል እንዲሁም ደግሞ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከድህነት መውጣት እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ በመፍጠር መግባባት የመድረስ ሥራዎች ናቸው ሲሠሩ የቆዩት። መግባባት ከተፈጠረ በኋላ በአስቸኳይ የእለት ርዳታም ሆነ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የተካተቱ ሰዎች በመጀመሪያ በቂ ውይይት ከተደረገ በኋላ “በራሳቸው ከተረጂነት መውጣት አለብኝ” የሚል ውሣኔ ላይ መድረስ አለባቸው። ከዚያም ባለፈ ደግሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ሆኖ የመለየት ሥራ ሠርቶ በትክክል ሊደገፍ የሚገባው ሰው እንዲደገፍ ማድረግ ይገባል የሚል እምነት ተይዞ ነው ሲሠራ የነበረው።
የአዕምሮ ዝግጁነቱ ከተፈጠረ ወይም የእችላለሁ አስተሳሰቡ ከተገነባ በኋላ ደግሞ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አላግባብ የገባው ሰው ከወጣ በኋላ ያለውን ሰው እንዴት ደግፈነው በተለያዩ ፓኬጆች ማለትም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ እና በአትክልትና ፍራፍሬ አልያም በሌማት ቱሩፋት በመሳሰሉ ማሕቀፎች እንዲሰማራ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው። በዚህም በመርሃ ግብሩ የሚደገፈው እያንዳንዱ የክልላችን ነዋሪ ጥሪቱን በመገንባት የራሱን የምግብ ክፍተት መሸፍን እና የምግብ ሉዓላዊነቱን አረጋግጦ እንዲወጣ የማድረግ ሥራ ፕሮግራሞችን በማቀናጀት የማስመረቅ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው። በዚህም መሠረት በበርካታ የክልላችን አካባቢዎች በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሌሎችም መስኮች ላይ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ራሳቸውን ችለው መውጣት የሚያስችሏቸው ሥራዎች ተጀምረዋል።
በተለይም በተያዘው በጀት ዓመት ከእቅድ ጀምሮ መሬት እስከሚወርድበት ጊዜ ድረስ ከክልል እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮቻችን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በዚህም መሠረት የስድስት ወር አፈፃፀማችን የክልላችን ፕሬዚዳንት በተገኙበት በቅርቡ ገምግመናል። በግምገማው በስድስት ወራት ውስጥ ብዙ የተገኙ ውጤቶችን መኖራቸውንም ለማየት ችለናል። እንደክፍተት የተለዩትንም አቅጣጫ አስቀምጠን በተጨባጭ ማሳካት በምንችልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረናል።
በመሆኑም በቀሪ ጊዜያት መጀመሪያ ተረጂዎችን የመለየት፤ ድጋፍና ክትትል የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በተጨማሪም ዘንድሮ ማስመረቅ የምንችላቸውን የሀብት ደረጃቸውን መዝግበናል። ከፍተኛ እና መካከለኛ ሀብት ያላቸውን ለይተን በብድርም ሆነ በርዳታ መልክ እያገዝናቸው፤ በቅተው እንዲሸጋገሩ የማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህንንም በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ የተደረገ ሲሆን፤ የዞን አመራሮች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ተገኝተው አመራር ተቀብለው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው። በጥቅሉ ግን በኅብረተሰብ ደረጃ ተረጂነትን የሚፀየፍና ወደ ልማት የመግባቱ ባህል እየጎለበተ መጥቷል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በሴፍቲኔት የሚደገፉ አርሶ አደሮችን ከድህነት ለማውጣት ያሉትን ፀጋዎች መጠቀም ላይስ የክልሉ መንግሥት ያከናወናቸው ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ማለት ይቻላል?
ኮሚሽነር ጋንታ፡- አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ክልላችን በጣም በርካታ ስነ-ምህዳር እና ሰፊ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ነው። ለአብነት ያህል እንኳን ብንጠቅስ ወደ ጌድዮ ዞን በእንሰት ፣ በቡና ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአግሮ ፎርስትሪ በጣም የበለፀገ ሀብት ያለበት አካባቢ ነው። በተመሳሳይ በወላይታ በጋሞና በሌሎቹም ዞኖች ያሉት ሀብቶች አይደለም ለእኛ ክልል ለሌሎችም የሚተርፍ ነው። በተቃራኒው ደግሞ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት በሚደርስ ችግር በርካታ ሕዝብ የመንግሥትና የለጋሽ አካላትን እጅ ለመጠበቅ የተገደደበት ሁኔታ ነበር። በመሆኑም በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት የክልላችንን ሕዝብ ከተረጂነት ለማላቀቅ በአካባቢው ያለውን ፀጋ ጥቅም ላይ የማዋሉ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ዘንድሮም ከጠባቂነት የተላቀቀ አምራች ዜጋ ለመፍጠር ያሉንን ፀጋዎች ያማከሉ ሥራዎች እየሠራን ነው።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በእያንዳንዱ የክልላችን አካባቢዎች ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎችና አቅሞችን አስቀድመን በልዩ መልኩ አቅደንና አቅጣጫ አስቀምጠን ነው ወደ ተግባር የገባነው። እነዚህ አካባቢዎች የቡና ፓኬጆችን እንዲሁም ደግሞ በርካታ የእንሰት ችግኞች ከዚያ ስነምህዳር ጋር እንዲጣጣሙ ተደርጓል። በጓሮ እንሰት ወይም ቡና እንዲያለማ ከማድረግ ባለፈ ወዲያውኑ መጠቀም የሚያስችላቸው ከሰብልም፣ ከእንስሳትም ልማት ዘርፍ የተቀናጀ ፓኬጆችን መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
ወደ ጋሞ ዞን ብንመጣ ደግሞ እንደሚታወቀው ጋሞና አካባቢው በሙሉ የፍራፍሬ ማዕከል እየተባለ ነው የሚጠራው። እዚህ አካባቢ ፓፓያ በአጭር ጊዜ ነው የሚደርሰው፤ በተጨማሪም ሙዝ ፣ ማንጎና ሃብሃብ ያሉ ፍራፍሬዎችም በስፋት የሚመረትበት አካባቢ ነው። ከዚህም ባሻገር በዚህ ዞን ትልቅ እና ሰፊ የሆነ የእንስሳት ሀብት አለ። የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ በክልላችን በመኖሩ በዶሮ መሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ውጤታማ እንደሚሆን አጠያያቂ አይደለም። እንዲሁም ደግሞ ከግብርና ውጪ የሆኑ በርካታ የተጠኑ ፓኬጆች አሉ። እነዚህን አጥንተን በየዓመቱ ክለሳ የምናደርግባቸው እና በአዲስ መልክ የምናካትታቸውን በማከል ወደ ትግበራ ይሸጋገራሉ። ወደ ትግበራ ከመሸጋገሩ በፊትም ሥራውን ለማከናወን የተመረጠው ሰው በምን መልኩ መሥራት እንዳለበት ስልጠና ይወስዳል፤ ግብዓቶች ቀርበውለት የቴክኒክ ድጋፍ ይደረግለታል።
በሌላ በኩል በአርባ ምንጭ ዙሪያም ሆነ መስኖ-ገብ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በስፋት አትክልት እና ፍራፍሬ ላይ ሰፊ ጸጋዎች አሉ። በጥቅሉ ፓኬጆቸ እንደ ዞኑ እና ወረዳዎች ነባራዊ ሁኔታ እንዲቃኙ ተደርገዋል። አስተሳሰቡ የተቀየረ እና ለመሥራት የተዘጋጀ ከሆነ ድህነትን እና ተረጂነት የሚፀየፍ ሆኖ በሀገር ልማት ላይ የድርሻውን መወጣት እንዲችል የማድረግ ሥራ ነው ታሳቢ አድርገን እየሰራን ያለነው። እንግዲህ በዚህ መልክ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች መካከል 50 በመቶዎቹን በዚህ ዓመት ለማብቃት ቆርጠን ወደ ተግባር ገብተናል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ወደ ልማት የገቡ ተጠቃሚዎች ከቴክኖሎጂ አቅርቦትና ከገበያ ትስስር ጋር የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ፤ እኛም በጉብኝታችን በንብ ማነብ የተሰማሩ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች እንደ ማር ማጣሪያ፣ ሰም ማተሚያ ያሉ መሳሪያዎች ባለመኖራቸው እና የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው መቸገራቸውን ገልጸውልናል። የክልሉ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን እየሠራ ነው?
ኮሚሽነር ጋንታ፡– በክልላችን ቀደም ሲል በገጠርም ሆነ በከተማ የሥራ እድል ፈጠራ የተለየ ተቋም ነበር። አሁን ግን በአንድ ቢሮ ነው እየተመራ ያለው። ይህም በመሆኑ ከግብአትም ሆነ ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እያስቻለን ነው። ለምሳሌ ሰፊ የንብ ቀፎ ያስፈልገናል። ምንአልባት በዚህ ፓኬጅ ከ10 ሺ በላይ የሆኑ ቀፎዎችን ወደ ሥራ ልናስገባ እንችላለን። ስለዚህ ከተማ ላይ ቀፎ የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞች በአግባቡ ነው እንዲደራጁ የሚደረገው።
በተጨማሪም በስፋት ወደ ሥራ እንዲገቡ ፣ ዲዛይኑ ተሰጥቷቸው ወላይታ ሶዶ ላይ ባለን የገጠር ቴክኖሎጂ ማዕከል ስልጠና ወስደው በፍጥነት ወደ ሥራ ገብተው ቀፎ በብዛት ማምረት እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ለምሳሌ አንቺ ያነሳሽው ማር ማጣሪያ አንድ ሰው ብቻውን ሊኖረው የሚችል ባለመሆኑ በአንድ አካባቢ ያሉና የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ንብ አንቢዎች እየተደራጁ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ በቀጣይ ይፈጠራል። ከግብይት አንፃርም ከኅብረት ሥራ ማህበራትም ሆነ በተለይ አግሮ-ፕሮሰሲንግ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ማህበራትን ከማህበራት፣ ፕሮጀክቶችን ከፕሮጀክቶች ጋር በማስተሳሰር አንዱ ሌላውን ይዞ እንዲወጣ በማድረግ ችግሩን የመፍታት ሥራ እየሠራን ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- ለአደጋ የተጋለጡ የክልሉን ሕዝቦች ወደ ተረጂነት ሳይመጡ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ በምን መልኩ ነው የሚሠራው? ለምሳሌ አባያ ሀይቅ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የበርካታ አርሶአደሮች እርሻ በተደጋጋሚ ሲወድም ይታያል፤ ይህንን አስቀድሞ በመከላከል እና ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ እየተከናወነ ስላለው ሥራ ቢያብራሩልን?
ኮሚሽነር ጋንታ፡– በክልላችን ከአደጋ መንስኤዎች አንደኛው የተፈጥሮ አደጋ ነው፤ ከዚህ ውስጥ ትልቁ ናዳና ጎርፍ ነው። ይህም ጎርፍ የሚያጠቃው በተለይ አርባምንጭ ዙሪያ ፣ ምዕራብ አባያ አካባቢ ፣ ዳሰነች እና የመሳሰሉት አካባቢዎች ላይ ነው። ሌላው አደጋ ናዳ ነው፤ የእኛ ክልል በብዛት ተራራማ ነው፤ ጋሞ ዞን፣ ወላይታ ዞን፣ ጎፋ ዞን አብዛኞቹ አካባቢዎች ተራራማ ናቸው።
ከናዳ ጋር ተያይዞ ባለፈው ክረምት እንደሰማችሁት ጉዳት አድርሷል። ከዚያ ባለፈ ዳሰነች አካባቢ ውሃ ሞልቶ ከመውጣት ባለፈ አሁን ከቱርካና ሀይቅ ጋር በተያያዘ የመስፋፋትና ሰውን የማፈናቀል ሁኔታዎች ይታያሉ። እንግዲህ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አንደኛ ከናዳ ጋር ተያይዞ ካለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ጀምሮ በክልላችን የተከሰተውን ለመፍታት የተለያዩ ቀበሌዎችን ለይተናል። ‘ቀይ’ ብለን የለየንባቸው አካባቢዎች ላይ ያለው ሰው ወዲያውኑ እንዲወጣ እና ሌላ ቦታ መርጠን እንዲሰፍር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። መጀመሪያ የጀመርነው በወላይታ ዞን ኩንዲዲ ዳኤ ላይ ቀበሌ መርጠን፤ በወረዳው ሙሉ ያሉ ሰዎችን አውጥተን መኖሪያቸውን እንዲቀይሩ ተደርጓል። ይህንን አስፋፍተን በጋሞ ዞን፣ ጎፋ ዞን ላይም ተመሳሳይ ሥራ ሠርተናል።
ዘንድሮ እንዲያውም በአጋጣሚ እኛ አደገኛ ብለን ከለየነው ውጪ ያሉትንም ጭምር የማስፈር ሥራ ተሠርቷል። ይህንን ያደረግነው እኛ በወረዳ ደረጃ አደጋ ስጋት አለባቸው ብለን ከለየናቸው ውጪ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ነው። በመሆኑም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች አስቀድሞ ከአካባቢው እንዲወጡና ከስጋት ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።
ናዳ ሌላኛው የተፈጥሮ ሀብት ጋር ስለሚያያዝ ናዳ ባለፈው የተከሰተበት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት መልሶ ማገገም ሥራ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች እንዲሠሩ ግብርና ሚኒስቴር ጭምር እገዛ አድርጎ ሥራዎች ተሠርተዋል። አሁን ላይ ከወላይታ ወደ አርባ ምንጭ ሲመጣ የሚታዩ ተራሮች ለጎርፍ እና ለናዳ ተጋላጭ ስለሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ሁለቱንም ታሳቢ አድርገን ነው እየሠራን ያለነው።
ከጎርፍ አንፃር ለምሳሌ ዳሰነች አካባቢ እየተከሰተ ያለው እንዲሁ የሚገመት ነገር አይደለም። ስለዚህ ከዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት ጋር በጥምረት ጥናት እየተደረገ ነው። ሆኖም መጀመሪያ ሰዎችን ከስጋት ቦታ አውጥተናል። ውሃው ቀጥሎ አሁንም ሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አድርገናል። ነገር ግን ቱርካና ላይ እየተከሰተ ያለውና በቀጣይስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ነገር ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል። ለዚህም በፕሬዚዳንታችን የሚመራ ኮሚቴ ተደራጅተዋል፤ ይሄ ኮሚቴ ከጂኦሎጂ፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።
ከሀይቆች መስፋፋት ጋር የሚከሰቱ ጎርፎች አንዱ መንስኤ ከተፈጥሮ ሀብት መመናመን ጋር የተያያዘ ነው። ከጎርፍ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በእኔ እምነት ጎርፍ እየተከሰተ ያለው ውሃው በዝቶ ላይሆን ይችላል፤ ተራሮች ላይ ያለው አፈር መከላት ወይም በጎርፍ መወሰድ የሀይቆችን ጥልቀት ይቀንሳል። ይህ ሲሆን ውሃው ወደ ላይ ይወጣና እየሰፋ የሚሄድበት ሁኔታ አለ።
ስለዚህ አሁንም ቢሆን የተፈጥሮ ሀብት ላይ የምንሠራው ሥራ ይህንን ችግር ይፈታል ብለን ነው የምናምነው። በመሆኑም ተፋሰሱ ላይ ልዩ እቅድ ተዘጋጅቷል። በተለይም ጋንታ ተፋሰስ የሚባለውና አርባምንጭ አካባቢ የሚታየውና እንዲሁም የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ የሚባለው የኦሞ ጊቤ ተፋሰስ ላይ በየዓመቱ በንቅናቄ ከሚሠሩ ሥራዎች ጋር አስተሳስሮ በመሥራት ስጋቶችን ለመቀነስና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ከምግብ ዋስትና ጋር ተያይዞ ዋነኞቹ ተጎጂዎች ሴቶችና ሕፃናት ናቸው። በልማታዊ ሴፍትኔቱ ሴቶችን ከተረጂነት ለማውጣት በተለየ መልኩ እየተሠራ ያለ ሥራ ካለ ይጥቀሱልንና ውይይታችንን እናብቃ?
ኮሚሽነር ጋንታ፡- በክልላችን በፕሮግራሙ ታቅፈው ድጋፍ እያገኙ ያሉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው። አሁንም እንደ ፌዴራል ከታቀዱ አንፃር ለሴቶች የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል። በምን መልኩ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሴቷ ጋር የምንሠራው ሥራ ትልቅ ድርሻ ስላለው እስከ አሁንም ሥንሠራ የነበረው ባለን ውስን አቅም ልዩ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው። በተለይ ከጓሮ አትክልት ፣ ከዶሮ እርባታ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ሴቶች በቀላሉ ሊያመርቷቸው የሚችሏው ሥራዎች ናቸው። እነሱ ደግሞ ገቢያቸውን በተሻለ መልኩ መቆጣጠር የሚችሉ በመሆናቸው ለሴቶች ቅድሚያ ሰጥተን፤ ተደራሽ አድርገን ለመሥራት ነው ያቀድነው። ከዚያም ባለፈ ወጣቶች በልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ አባወራዎች አሉ፤ የተማሩትም ሆኑ ያልተማሩት በአቅማቸው መፈፀም ከሚችሉት አንፃር ለይተን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኮሚሽነር ጋንታ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም