‹‹እንኳን አደረሳችሁ››!

አዲስ አበባ ውስጥ የአንዳንድ ንግድ ቤቶች ጌጣጌጥ ለእንቁጣጣሽ ራሱ ይህን ያህል አልደመቁም። ለፈረንጆች አዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ እየተባባሉ ቀይ በቀይ ሆነዋል።

ትልልቅ የገበያ ማዕከላትና ሱቆች የ‹‹ሳንታ ክላውስ››ን ያህል በአደይ አበባ አሸብርቀው ነበር? አይመስለኝም!

ከአንዳንድ ሆቴሎች በር ላይ ደግሞ በእንግሊዘኛ ‹‹Merry Christmas›› ተብሎ በቀይ ቀለም በትልቁ ይጻፋል። ከሥር እንኳን የአማርኛ ጽሑፍ የለውም። እንደ ጣይቱ ሆቴል ያሉ ታሪካዊ ሆቴሎች ጭምር አድርገው አይቼ አውቃለሁ። ባህልና ሃይማኖትን የሚቀይር የውጭ ጠላት አይወረንም ብለው የታገሉትን፣ ባህልና ቋንቋቸውን ያስከበሩትን አሳነስንባቸው ማለት ነው። ‹‹እውን አባትህ አንተን ወለደ!›› አለ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ!

የቀን አቆጣጠራችን ነገር ዝብርቅርቁ የወጣ ሆኗል። አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ጥለን በውጭው ብቻ በቆጠርን ያሰኛል፤ ከሚዘበራረቅ ማለት ነው። እንደዚያ ቢሆን ደግሞ የሚፈጠረውን የባሰ መዘበራረቅ አስባችሁታል? ይሄን ሁሉ በዓላትና ታሪክ ገደል ከተትን ማለት እኮ ነው!

እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በፈረንጅ የቀን አቆጣጠር ብቻ የሚጠቀሙ መስሪያ ቤቶች አሉ። የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ብዙ የሀገር ውስጥ መስሪያ ቤቶች የውጭውን አቆጣጠር ይጠቀማሉ።

ወዲህ ደግሞ ሀታሪክ ተቆርቋሪ ነን ወደሚሉት ምሁራን እንምጣ! ጥናት ሰራን ብለው የሚያቀርቡት በፈረንጅ ቋንቋ በፈረንጅ የቀን አቆጣጠር የተሰራ ነው። እንግዲህ አቆጣጠሩን በሀገርኛ ማድረግ ካልቻሉ ታዲያ ምኑን ተመራመሩት? ጉዳዩ የውጭ ቢሆን እኮ ችግር አልነበረውም፤ ስለሀገር ውስጥ በሚሰራ ጉዳይ ‹‹እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር›› ይባላል።

እዚህ ላይ ግን የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሲያወሩ የሰማሁት ነገር ሁሌም ትዝ ይለኛል። በእርሳቸው ትዝብት ጥናቶች በፈረንጅ ቋንቋና አቆጣጠር የሚሆኑበት ምክንያት ለኩረጃ ስለሚያመች ነው። በቀላሉ ከበይነ መረብ ላይ ለቃቅሞ ማቅረብ ስለሚያስችል ነው፤ አቆጣጠሩን ወደ ኢትዮጵያ የመቀየር ሥራ እንኳን አይሰራበትም። ጥናቱ ሁሉ እንዲህ ስለሚሆን በይነመረብ ላይ በሀገር ውስጥ ቋንቋ ምንም ነገር ማግኘት አይቻልም፤ ከተገኘም ይሄው ብሔርን ከብሔር የሚያበጣብጥ የጥላቻ ጽሑፍ ነው። እናም እንግሊዘኛው ስለሚያመቻቸው ነው። በእውነት የፕሬዚዳንቱ ትዝብትማ ትክክል ነው።

በነገራችን ላይ ይሄ ‹‹እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር›› የሚባል ነገር ግን አይገባኝም፤ መላው ዓለም በዚህ አይደል እንዴ የሚጠቀመው? ለምን የአውሮፓውያን ብቻ ተባለ? ምናልባት እነርሱ ስለጀመሩት ይሆናል።

አያችሁ አይደል ግን ማንነት እንዴት እንደሚያስከብር? መላው ዓለም እየተጠቀመበት ‹‹እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር›› ተባለላቸው ማለት ነው። በእርግጥ በእንግሊዘኛው ‹‹ግሪጎሪያን›› ተብሎ ነው የሚገለጸው። ይሄም ቢሆን በአንድ አውሮፓዊ ቄስ የተሰየም ነው።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስታውስ ነገር የለም፤ አቆጣጠሩ በፈረንጅኛው ነው። ለዚህም ነው ከፈረንጅኛው ይልቅ ኢትዮጵያዊው ቀን የሚጠፋባቸው። ወዲህ ደግሞ የምንጠቀማቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች (ስልክ፣ ኮምፒውተር) የራሳቸው ሚና አላቸው።

የዚህ ሁሉ ውጤት ነው የሰሞኑን የፈረንጆችን አዲስ ዓመት ከእንቁጣጣሽ በላይ እንድናከበረው የሚያደርገን። ‹‹ከእንቁጣጣሽ እንኳን አልበለጠም›› እንዳትሉኝ፤ የበለጠበትን ምክንያት ልጨምርላችሁ። በእኛው አዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ የሚከበረውም በፈረንጅኛው የሰዓት አቆጣጠር መሆኑ ነው።

የ2011 አዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማ ላይ ይመስለኛል። በዋዜማው በአንድ ዝግጅት ተጋብዤ የሆነ ሆቴል ሄጄ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ የነበረው ሽር ጉድ ከሌሊቱ 6፡00 የሚገባውን አዲስ ዓመት መቀበል ነበር። ባይሆን እንኳን ክርክሩ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሚገባው ማታ 12፡00 ነው ወይስ ጠዋት 12፡00 ነው የሚለው ነበር እንጂ ሌሊት ይገባል ብሎ የተከራከረ የሃይማኖት አባትም ሆነ የታሪክ ባለሙያ የለም። ይሄ ሙሉ በሙሉ ከፈረንጅ አቆጣጠር የተቀዳ ነው። በፈረንጆች ከሰዓት (PM) እና ጠዋት (AM) የሚቀያየረው በእኛ ሌሊት 6፡00 ላይ ነው፤ ልክ የእኛ ቀን 6፡00 ላይ እንደሚቀየረው ማለት ነው። እንግዲህ ይህን እንኳን ነው መለየት ያቃተን!

እሺ አሁን እንግዲህ ‹‹እንኳን አደረሰን!›› ነው ወይስ ‹‹እንኳን አደረሳቸው›› ነው የምንለው? እንደኔ እንደኔ ‹‹እንኳን አደረሳቸው›› እንጂ ‹‹እንኳን አደረሰን›› የምልበት ምክንያት የለኝም፤ ካልኩም ለገና በዓል እንጂ ለፈረንጆች ጥር 1 አይደለም። ስለዚህ መባል ያለበት ‹‹እንኳን አደረሳቸሁ›› ይመስለኛል።

እንኳን አደረሳቸሁ መባል እንዳለበት አምናለሁ፤ ምክንያቱም የዓለም ጉዳይ ጉዳያችን ነው። በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ብዙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አሉባት። እነዚህ ዓለም አቀፍ ጉዳዮቿ የተጻፉት በፈረንጆች አቆጣጠር ነው። ስለዚህ አይመለከተንም ብለን አንደመድምም፤ ታሪክ ስናነብም ሆነ ስንጽፍም ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በማጣቀስ ነው። የሌሎች ሀገራትንም ተሞክሮ እየወሰድን ነው። ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን በራሱ በውጭው ዐውድ እንጂ የኛው አቆጣጠር አድርገን መሆን የለበትም።

ሌላ ግን ግራ የሚገባኝ ነገር የኢትዮጵያንና የፈረንጆችን አቆጣጠር የሚያደበላልቁት! የምንጠቀምበት የራሱ ቦታ እኮ ነበረው። ለምሳሌ የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ዓመተ ምህረት ተጽፎ እናገኛለን፤ በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥ በፈረንጆች አቆጣጠር ተጽፎ እናገኛለን። ይገባኛል! በእንግሊዘኛ ጽሑፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ዓመተ ምህረት በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥም የፈረንጆች አቆጣጠር የሚያስፈልግበት አጋጣሚ ይኖራል። ይህ ሲያጋጥም ግን ጽሑፉ የእንግሊኛ ከሆነ ‹‹E.C›› የአማርኛ ከሆነ ‹‹እ.አ.አ›› የሚል መኖር አለበት። የምናየው ነገር ግን የተደበላለቀ ነው። አቆጣጠሩ በየትኛው እንደሆነ የሚያውቀው ሁነቱን የሚያውቅ ብቻ ነው። እንግዲህ ይህን ያህል ተደነባብረናል!

በውጭ የተጻፈውን እንኳን ወደኢትዮጵያ አቆጣጠር መመለስ ይቻላል እኮ። ለምሳሌ ከመስከረም እስከ ጥር ባለው ወር ውስጥ ከሆነ ከውጭው ዘመን ላይ 7 መቀነስ ነው። እነርሱ ጥር ላይ አዲስ ዓመት ስለሚቀበሉ ከጥር እስከ ነሐሴና ጳጉሜን ባለው ወር ውስጥ ከሆነ ደግሞ 8 መቀነስ ነው። ለቀንም እንደዚሁ። በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ያለን ልዩነት ይታወቃል። ለምሳሌ ዛሬ በፈረንጆች ታኅሳስ 30 ቀን 2024 ነው። ይህን በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር እናስቀምጠው ቢባል ቀኑ ታህሳስ 21 ዓመተ ምህረቱ ደግሞ 2017 ይሆናል። ምክንያቱም የእነርሱ የታኅሳስ ወር 31 ቀን ነው። ወራቸው 31 ሲሆን 9 እንቀንሳለን፤ ዓመተ ምህረቱ ደግሞ ከጥር በፊት ስለሆነ 7 እንቀንሳለን፤ ከጥር በኋላ ከሆነ 8 እንቀንሳለን። በዚህ ዘመን ግን ስማርት ስልኮች ለዚህ ምቹ ሆነዋል።

ሰሞኑን የፈረንጆች አዲስ ዓመት ስለሆነ ነው እንግዲህ ስለጉዳዩ ያወራነው። በዚያ ላይ ደግሞ ለእኛም ለእነርሱም የጋራ የሆነው ደግሞ የገና በዓል ነው። ምንም እንኳን የእነርሱን አከባበር እየተከተልን ቢሆንም ገናም የራሳችን የሆነ ባህላዊ አከባበር ያለው ነው።

ለእኛም ለእነርሱም መልካም በዓል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You