እንኳን አደረሰን፤ ለበዓለ ጥምቀቱ እንዲሁም ለዛሬዋ እለት። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና አስተምህሮ ጥምቀት ሰው ወደ ክርስትያን የአንድነት ማኅበር የሚቀላቀልበት ነው። በቅዱሱ መጽሐፍ የማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያው ምዕራፍም «የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ» ሲል ቀጥሎ ባለው ቁጥር የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት ነገር ያነሳል።
ቤተክርስቲያንም ለዘመናት ይህን የጥምቀት በዓል በልዩና ደማቅ ሁኔታ ስታከብርና ስታስብ ኖራለች፤ አሁንም እያከበረች ትገኛለች። በዓሉን በማስመልከትም መዝሙራት ይዘመራሉ፤ ምስጋና ይቀርባል። ያም ብቻ አይደለም፤ የበዓሉን ድርጊት በምሳሌ በተግባር ይታያል። ታድያ እኔ እህታችሁ ጨዋ ነኝና፤ ሃይማኖታዊ እይታውና ትውፊቱ ላይ ለመናገር አልደፍርም። በሁላችን ዐይን ግልጽ ሆኖ የሚታየውን እውነት ግን አውቃለሁና ዝም ልል አልወድም።
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ታቦታትን ከየማደሪያቸው የማውጣት ስርዓት የተጀመረው በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ መዛግብት ይነግሩናል። ይህም በአጼ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ነው። ከዛ ቀድሞ በየአብያተ ክርስትያናቱ ሕዝቡ ሰብሰብ ብሎ እዛው በየደብሩ አክብሮና በዓሉን አስቦ ነበር የሚለያየው።
ታድያ በአጼ ገብረመስቀል ጊዜ፤ ንጉሡ ታቦታት ከማደሪያቸው እንዲወጡ አሉ። አንድም ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን ያሳስባልና ነው። ይህ ከሆነ በኋላ ጥር 11 ቀን ታቦታት ከማደሪያቸው ወጥተው፤ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ማለትም የእለቱ ምስጋናና ጸሎት ሲጠናቀቅ፤ ታቦታቱ ወደማደሪያቸው እንዲገቡ ሆነ።
አንዱ በሠራው መልካም ስርዓት ላይ ሌላ በጎ ሥራን መጨመር የሚያውቁበት ነገሥታት፤ እንደ’ኛ «አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ» አይደሉም። እናም በንጉሥ ላልይበላ ዘመን «የሆነውስ መልካም ነው። ግን ታቦታቱ ለምን ብቻቸውን ይወጣሉ? ወደባህረ ጥምቀቱ ሲሄዱ ለምን በአቅራቢያቸው ካሉት ጋር በአንድነት አይሄዱም?» የሚል ጥያቄ ንጉሡ አነሱ።
ከዛ ቀጥሎ ባሉት ጊዜያት፤ እስከአሁንም ድረስ በዚሁ መሰረት በአንድ አካባቢ ካሉ አብያተ ክርስትያናት የሚወጡ ታቦታት በጋራ በመሆን ወደ አንድ ማደሪያ ያቀኑና ስርዓቱ ይፈጸም ጀመር። በዚህ አላበቃም፤ በንጉሥ አፄ ዘረ ያዕቆብ ንግሥና ዘመን የጥምቀት በዓል ተጨማሪ ስርዓት ታከለበት። እንዲህም ሆነ፤ ታቦታቱ በጥር ወር አስረኛው ቀን እንዲወጡና በማግስቱ በአስራ አንድ ወደማደሪያቸው እንዲመለሱ ፤ ያም ብቻ ሳይሆን ሀገሩን ሁሉ እንዲባርኩ፤ ለዛም ከተቻለ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ ስርዓት ወጣ።
ይህ ስርዓት ከዛን ዘመን አልፎና እስከዛሬ ቀጥሎ፤ እየደመቀና እያበበ፤ በዓለም መድረክ እይታን አግኝቶና ትኩረት ተሰጥቶት የሚናፈቅ በዓል ሆኗል። ስርዓቱ ለእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መንፈሳዊ አገልግሎት ነው።
አሁን ወዳለንበት ጊዜ ስንመለከት፤ ከቀደሙት በትውፊት የተቀበልናቸው ስርዓቶች ቀጥለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለዘመኑ መስታወት መሆን የሚችሉ መልካም ተግባራት ታክለዋል። ለምሳሌ ከትናንት በስቲያ የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞችና እህቶች በጃን ሜዳ ተገኝተው ነበር። ለምን? ለጥምቀት በዓል የጃንሜዳን ጊቢ ሊያጸዱና መተባበርና ፍቅርን ሊያሳዩ። ሥራቸው ደግሞ ለይስሙላና ለካሜራ ፍጆታ እንዳይመስላችሁ፤ በሙሉ ልብና በስርዓት ነው ያደረጉት፤ እንዲህ ያለው በጎ ሥራ ጥምቀት በተለየና በድምቀት በሚከበርባት በጎንደር ከተማ እንደተከናወነም ሰምተናል፤ አይተናል።
በእርግጥ ይህ ከጊዜው ጋር አገናኝተን አነሳን እንጂ ወጣቶቹ የተለያዩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ እንዲህ ተምሳሌት በመሆን የሚችል ግብር ፈጽመዋል። ከእነዚህ ጋር የሚመሳሰሉ በዓላትና ሥርዓቶቻቸው፤ እንዲህ እንደዛሬው ጊዜ ማጣፊያው አጥሮ «የሰላም ያለህ!» በሚባልበት ሰዓት፤ ከሃይማኖታዊ ፋይዳቸው በተጓዳኝ ያለው ማኅበራዊ ጥቅማቸው ደምቆ ይታያል።
ሃይማኖቱ ወደሚነግረን መለስ እንበልና፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ወደ ባህረ ዮርዳኖስ ሲገባ ብዙ የታዩ ተዓምራት ነበሩ። ባህር ሸሽታለች፤ ከሰማይም ድምጽ ተሰምቷል። ቤተክርስትያንም የእምነቷ መሰረት የሆነውን የተዋህዶ ምስጢር ያገኘችው አንድም ከዛ ስፍራ ነው። መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል ሲያርፍና «የምወደው ልጄ ይህ ነው» የሚል ድምጽ ከሰማያት ሲሰማ።
ታድያ በዚህ በእኛ በዛሬው የጥምቀት በዓል የእነዚህ ወጣቶች እንቅስቃሴ ልክ እንደመንፈሳዊው ምስጢር ሁሉ የኢትዮጵያዊነት ኅቡዕ ትስስር የታይበት ነው። የሕግ ሁሉ ማሠሪያ የሆነው ፍቅር በዚህ ተገልጿል። ዛሬ እለቱን ተገን አድርገን ጥምቀትን አነሳን እንጂ፤ በኢድ ቀን ስታድየም እህት ወንድሞቻችን አባቶቻችን ለስግደት ሲወጡ የሚታየው ከዚህ የሚርቅ አይደለም።
እነዚህ ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የተሠሩ ስርዓቶች፤ ብሔርን እየጠራን ዘረኝነትን እየዘራን ላለን፤ «አስተውሉ!» የሚል ትልቅ ማሳሰቢያ ያለው ነው። በጥምቀት በዓል’ኮ ብሔር ሳይለይ፤ ቋንቋ ሳይመረጥ፣ መልክ ሳይታይ፣ የኑሮ ደረጃና የእውቀት ልክ ሳይመዘን፤ «ወረደ ወልድ…እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት» እያለ ሁሉም የሚዘምሩበት ነው። ሁሉም አንድ ዓይነት ድምጽ ኖሯቸው ነው እንዴ? አይደለም። ሁሉም በየራሱ ድምጽ ነው ዝማሬውን የሚያሰማው። ነገር ግን መዝሙሩ አንድ ነው።
የበዓሉ ተሳታፊ፣ «አላህ ታቦታቱን ጠብቆ በሰላም ይመልሳችሁ!» ብሎ የሚመርቀው አልያም በርቀት እያየ «ሲያምር!» ብሎ የሚያደንቀው፤ በጥቅሉ ሃይማኖተኛ በበዛባት አገር ላይ ስለምን ፍቅር በቶሎ አታሸንፍም? ሃይማኖተኛ የተባለ ሕዝብ ምን ቆርጦት «ምንድን ነው ዝም ብሎ መተቃቀፍ ብቻ!» ይላል? ቅዱሱ መጽሐፍም ሆነ ቁርዓን የሕግ ነው ወይስ የፍቅር ቃል በልጦ የሚገኝባቸው? እንዴት ለኢትዮጵያዊነት ይህን እምነታችንን ማሠራት አቃተን?
ለጥምቀት ያለውን ትብብር፤ ያለውን ፍቅርና ኅብረት ስታዩ ይህን ጥያቄ ሳትጠይቁ እንደማትቀሩ አምናለሁ። እንዳልኳችሁ ከትናንት በስቲያ ጃንሜዳ ተገኝተው ስፍራውን ያጸዱ እህቶችና ወንድሞቻችንን የማደንቃቸው ለዚህ ነው። በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ያለውን ፍቅርና መከባበር ማስታወሳቸው ወይም ማሳየታቸው ብቻ አይምሰላችሁ፤ መልካቸውም ደማቸውም አንድ ሆኖ ግን «ዘር» እያሉ ዘረኛ ለሆኑት መልዕክት ሊያስተላልፉ ነው።
የጥምቀት በዓል ስርዓቱ ውብ ሆኖ ውብ እንደሚያደርገን ኢትዮጵያዊነት ሆኖ ይታየኛል። ሁላችን ከፍ አድርገን የምናያት፤ ከእኛም ከሁላችን በላይ የሆነች አገር አለችን። አጅበን የምናደምቃት፤ የምናወድሳት፤ የምንዘምርላት አገር። ዝማሬአችን እኩል ላይሆን ይችላል፤ ግን አንድ ነው። ዓላማው አንድ መሆኑ ያመሳስለዋል።
አሁን አገራችን ያለችበትን ሁኔታ እናውቃለን። ለመዋደድ ካሉን እልፍ ምክንያቶች ይልቅ ለመጣላት አንዲት ሰበዝ የምንመዝ ሆነናል። መተማመን እየደበዘዘ ከመሄዱ የተነሳ፤ ለፍቅር ሲሉ የተቃቀፉ ሰዎች እውነታቸውን አይመስለንም። «እንወዳችኋለን» የሚሉን ሁሉ የሚዋሹን ይመስለናል። ሁሉም ነገር የፖለቲካ ቁማር ሆኖ ይታየናል። እውነተኛ መሆን ስላልቻልን፤ መልካም ቃል የሚናገሩ ሁሉ እያስመሰሉ እንደሆነ እናስባለን።
በክርስትናው ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ወደ ማስተማር ሲገባ፤ ሐዋርያቱን ሊመርጥ ሲነሳ፤ ያስቀደመው ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ መጠመቅን ነው። እንዳልኳችሁ ይህን ሊቃውንት ያብራሩታል፤ እኔ ግን እላለሁ ዛሬ ላይ እኛም ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ እንደመሄድ ያለ ጉዞ መጀመር አለብን። በፍቅርና በይቅርታ ተጠምቀን ወደ ኢትዮጵያዊነት ኅብረት የምንገባበት በር ያስፈልገናል።
በዮርዳኖስ በፍቅር ስንጠመቅ የእውነት የኢትዮጵያዊነታችን ምስጢር ይታያል፤ ያስተሳሰረን እውነት ይገለጣል። ወደ ዮርዳኖስ ሄደን በይቅርታ ስንጠመቅ፤ ቆሻሻ ታሪክ ከሰማው ጆሯችን ይልቅ እውነተኛ ፍቅር የሚያይ ዓይናችን ማመን እንጀምራለን። ወደ ዮርዳኖስ ሄደን በመዋደድ ስንታጠብ፤ ዘረኝነት ምን ያህል እድፍ ሆኖ ውብ ገላችንን እንደጋረደው እናያለን።
ወደ ዮርዳኖስ ሄደን «እኔ ብቻ» ጠባብነ ታችንን እንላቀቀው፤ ወደ ዮርዳኖስ አቅንተን በነገሩን እንጂ ባላየነው ታሪክ መጠላላታችንን እንጣላው። ዮርዳኖስ ሩቅ አይመስለኝም፤ በኢትዮጵያዊነት ስም ሁሉም ወደ ውስጡ ቢመለከትና ተረጋግቶ ለማሰብ ለራሱ ጊዜ ቢሰጥ፤ ኢትዮጵያዊነቱን ከውስጡ ያገኘዋል። «ምን ሆነው ነው!?» ብለው የሚወቅሱን ልጆች ሳይመጡ፤ «ምን ነክቶን ነው!» ብለን ዛሬ ወደ ዮርዳኖስ ብንሄድ ብዙ እናተርፋለን። መልካም በዓል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
ሊድያ ተስፋዬ