አዲስ አበባ፡- በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደቱ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መቋረጡንና ላለፉት ዘጠኝ ቀናትም በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ተማሪዎች ወደክፍል አለመግባታቸውን ዩኒቨርሲቲው ገለጸ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በሁለት ቀናት ውስጥ በሚደርሰው ውሳኔ መሰረትም ችግሩን ለይቶ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድና ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚደረግበት ሂደት እንደሚፈጠርም አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በዩኒቨርሲቲው ለሁለተኛ ጊዜ የመማር ማስተማር ሂደቱ የቆመ ሲሆን፤ ላለፉት ዘጠኝ ቀናትም በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ተማሪዎች ወደክፍል አልገቡም፡፡ ይህ ክፍል ያለመግባት ሂደትም አመጽና ረብሻ የሌለበት ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲውም የሰላም ችግር የለም፡፡ ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ሆኖም ግን ተማሪዎቹ ወደ መማር ማስተማር ሂደት መግባት ስላለባቸው የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በሁለት ቀናት ውስጥ ውሳኔውን የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ አሁን የተስተዋለው ክፍል ያለመግባት አድማ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ቀደም ሲልም አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ቆሞ ነበር፡፡ በወቅቱም አሉን የሚሏቸውን ጥያቄዎች ማኔጅመንቱ ለመመለስ ሞክሯል፤ ከፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምር መጥተው አነጋግረዋል፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው እንዲሁም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታውም በየፊናቸው ለማነጋገር ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ተማሪዎቹ የተሰጠውን መልስ ለመቀበል ዝግጁ አልነበሩም፡፡ በዛ ሁኔታ መቀጠል ስለሌለበት መማር የሚፈልግ እንዲማር፣ መማር የማይፈልግ ደግሞ ግቢውን ለቅቆ እንዲወጣ በተወሰነው መሰረት እንደገና ምዝገባ ተካሂዶ ‹ከዚህ በኋላ ትምህርት አናቋርጥም፤ የዩኒቨርሲቲውንም ህግና ስርዓት እንከብራለን፤› የሚል ውል ፈርመው ወደ ትምህርት ተመልሰዋል፡፡
አሁን ደግሞ በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው ሦስት ልጆች ባልታወቀ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፎ በመገኘቱ ምክንያት ትምህርት አቁመዋል፡፡ በወቅቱ ምክንያታቸው የነበረው የተማሪዎቹ አማሟት እስከሚገለጽ የሚል ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ከሆስፒታል የመጣውንና የዞንና ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተላከለትን ውጤት ለጥፎ ተማሪዎች እንዲያውቁ በማድረግ በተረጋጋ ሁኔታ ክፍል ገብተው እንዲማሩ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከተማሪ ተወካዮች ጋር ጊዜ ወስዶ ለማናገር ሞክሯል፡፡ ከዚህ በኋላ የመጣ ጥያቄ ባይኖርም ተማሪዎቹ ግን ክፍል ከመግባት ተቆጥበዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም በመምህራኖቻቸው አማካኝነትም እንዲመከሩና እንዲጠየቁ የተደረገ ቢሆንም፤ «እንገባለን፣ እንማራለን» ከማለት ያለፈ ወደክፍል ሲሄዱ አልታየም፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ አሁን ላይ የተማሪዎቹ ትምህርት ማቆም ከምን ጋር የተገናኘ እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ይሁን እንጂ በእያንዳንዷ ቀን ብዙ ሃብት እየፈሰሰ እንደመሆኑ በዚህ መልክ እስከመጨረሻው መቀጠል አይቻልም፡፡ ያለ ምክንያት ተማሪ የዩኒቨርሲቲውን ሃብት እየተጠቀመ ግቢውስጥ ሆኖ ትምህርቱን የማይማር ከሆነ ወደ ውሳኔ መሄድ የግድ ስለሚሆን፤ በሁለት ቀናት ውስጥ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ተሰብስቦ ምን መደረግ እንዳለበት ይወስናል፡፡ ምናልባትም እሑድ እለት ለሚመለከተው የመንግሥት አካል፣ ለተማሪውና ለህብረተሰቡ በማሳወቅ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
በወንድወሰን ሽመልስ