እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ለአገራችን እንግዳ የሆነው የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ረቂቅ አዋጅ ከሰሞኑ ብቅ ማለቱን ተከትሎ በቀደመው ሳምንት እትማችን በሕጉ ዙሪያ አንዳንድ ጉዳዮችን መዳሰሳችን ይታወሳል:: ተከታዩን ክፍል እነሆ::
ማህተም እና እማኞች በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጁ
ወረቀትን ማዕከል ባደረገው የግብይትና የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ የማህተምና የእማኞች ጉዳይ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው::
ማህተም አንድ ሰነድ ሕጋዊና አስተማማኝ ለመሆኑ ወሳኝ ማረጋገጫ ነው:: እማኞች ደግሞ በተለይም በግብይትና በአንዳንድ የመንግሥት አገልግሎቶች ውስጥ በሰነዶች ላይ የሚፈርሙ ሁነኛ ምስክሮች ናቸው::
የእጅ ስልክንና ኮምፒዩተርን ማዕከል ባደረገው በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ውስጥም ማህተምና እማኞች ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው::
በረቂቅ አዋጁ መሰረት ሕግ በሰነድ ላይ ማህተም እንዲያርፍ ግዴታ ከጣለ ሰነዱ በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ቅርጽ ከቀረበና በኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ (ቁጥር 1072/2010) መሠረት የዲጂታል ፊርማ ካረፈበት በሕግ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ ይቆጠራል።
እማኞችን በተመለከተም የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ከማህተም ጋር ተመሳሳይ ነው:: በዚሁ መሰረት ሕግ በሰነድ ላይ የእማኞች ፊርማ እንዲያርፍ ግዴታ ከጣለ ሰነዱ በኤሌክትሮኒክ መልዕክት መልክ ከቀረበና የእማኞች የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ካረፈበት በሕግ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ ነው የሚቆጠረው።
በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ዋና ቅጅ ምንድን ነው?
ወረቀትን ማዕከል ባደረገው የትራንዛክሽን ሥርዓት የሰነዶች ዋና ቅጅ (Original Document) እንዲቀርብና እንዲቀመጥ ይደረጋል።
የአንድ ሰነድ ዋና ቅጅ በዋናነት የጽሑፍንና የፊርማን ትክክለኛነት፣ የፈራሚውን ማንነት እንደዚሁም ፈራሚው የሰነዱን ይዘት ያጸደቀ መሆኑን ያረጋግጣል። ተዓማኒነት ያለውም ይኸው ዋና ቅጂ ነው::
በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንስ የዋና ቅጂ ጉዳይ እንዴት ይስተናገዳል የሚለው ታዲያ መሰረታዊ ጥያቄ ነው:: ኮምፒዩተርን ማዕከል በማድረግ የሚመነጩና ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ የሚላኩ ኢንፎርሜሽኖች ዋነኛ ባህርይ ሁሉም ኮፒዎች መሆናቸው ነው።
ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክ ደብዳቤ ጽፈን ስንልክ መልዕክቱ ተልኮ ሳለ በላኪው አድራሻ የመልዕክት ሳጥን ውስጥም የመልዕክቱ ቅጅ ቀሪ ሆኖ ተመዝግቦ ይገኛል።
ይህ ማለት አንድ መልዕክት ሲላክ በላኪና በተቀባይ ዘንድ ሁለት ተመሳሳይ የኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች ይገኛሉ ማለት ነው። ጥያቄው ታዲያ የትኛው ዋና ቅጅ ነው? የትኛውስ ቅጅ (ኮፒ) ነው? የሚለው ነው።
ከዚህ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶች ልዩ ባህርይ በመነሳት ረቂቅ ሕጉ ዋና ቅጅን በተመለከተ የሕግ ግምት (Presumption of Law) ያስቀምጣል።
በዚሁ መሰረት አዋጁ “ሕግ ኢንፎርሜሽን በዋና ቅጅ እንዲቀርብ ወይም እንዲቀመጥ ግዴታ ከጣለ ኢንፎርሜሽኑ ያለመቀየሩን የሚያሳይ አስተማማኝ ዋስትና ካለ እና ኢንፎርሜሽኑ በማንኛውም በተፈለገ ጊዜ ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ተደራሽና የሚነበብ ከሆነ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ይህን ቅድመ ሁኔታ እንዳሟላ ይቆጠራል” በማለት ይደነግጋል።
እዚህ ላይ “… ኢንፎርሜሽኑ ያለመቀየሩን የሚያሳይ አስተማማኝ ዋስትና ካለ …” የሚለው የህጉ አነጋገር ግልጽ ሊሆን ያስፈልጋል::
ረቂቅ አዋጁ ለፓርላማው በቀረበበት ወቅት መንግሥት ካቀረበው ማብራሪያ ለመረዳት እንደሚቻለው “… ኢንፎርሜሽኑ ያለመቀየሩን የሚያሳይ አስተማማኝ ዋስትና ካለ …” ሲባል ኢንፎርሜሽኑ የመጨረሻውን ቅርጽ ይዞ በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ወይም በሌላ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመነጨበት ጊዜ አንስቶ ምሉዕ ስለመሆኑ የሚያሳይ አስተማማኝ ዋስትና ካለ ለማለት ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል::
የዚህ የሕግ ግምት ዋነኛ ክፍል የኢንፎርሜሽን ምሉዕነትን(Entirety/Complete)ማረጋገጥን ይመለከታል። ኢንፎርሜሽን ምሉዕ ነው ሲባል ደግሞ ከተቀናበረበት ጊዜ ጀምሮ፣ በማቆየት ሂደት እና ኢንፎርሜሽኑ በተላከበት ጊዜ በመንገድ ላይ በጠላፊዎች እጅ አልገባም፤ እንደዚሁም በእነዚህ ጠላፊዎች ይዘቱ አልተቀየረም ማለት ነው።
ክፍያና ደረሰኝ
መቼም በወረቀት ሥርዓት የክፍያና የደረሰኝ ጉዳይ የቱን ያክል ወሳኝ እንደሆነ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል:: ሽያጭ ወይም መሰል ግብይት ካለ ክፍያ መኖሩ የግድ ነው:: ክፍያ ካለ ደግሞ ደረሰኝ ያስፈልጋል::
በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ውስጥም ክፍያና ደረሰኝ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው:: በረቂቅ ሕጉ መሰረት ሕግ ክፍያ እንዲፈጸም ግዴታ የሚያስቀምጥ ከሆነ ክፍያው በኤሌክትሮኒክ መንገድ ከተፈጸመ እንደዚሁም ሌሎች መንግሥት ያስቀመጣቸው ግዴታዎች እስከተሟሉ ድረስ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ ነው የሚቆጠረው::
ደረሰኝን በተመለከተ ደግሞ ሕግ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ግዴታ የሚጥል ከሆነ በሕግ የተቀመጠው ግዴታ እንደተሟላ የሚቆጠርባቸውን ሁኔታዎች ዘርዝሮ አስቀምጧል::
እነዚህም የመጀመሪያው ደረሰኙ በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ቅርጽ የተዘጋጀ ከሆነ ነው:: የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ (ደረሰኙ) የወረቀት ደረሰኝ ይዘትን የሚያሟላ ከሆነ ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ነው::
ሶስተኛው የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ (ደረሰኙ) በቀጣይ ለማመሳከሪያነት መዋል እንዲችል ተደራሽና ሊነበብ የሚችል ከሆነ ነው:: እነዚህ ሶስት ሁኔታዎች በአንድነት ከተሟሉ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ተቆርጧል ማለት ነው::
የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ኮሙኒኬሽን
በሕጉ በተሰጠው አንድምታ መሰረት የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ማለት በኤሌክትሮኒክ መንገድ ወይም በሌሎች ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት የመነጨ፣ የተላከ፣ የደረሰ ወይም የተከማቸ ኢንፎርሜሽን ነው::
ኢንፎርሜሽን የሚባለው ደግሞ ጽሑፍን፣ መልዕ ክትን፣ ዳታን፣ ድምጽን፣ የዳታ ቋትን፣ ቪዲዮን፣ ምልእክ ቶችን፣ ሶፍትዌርን፣ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችን፣ ኦብ ጀክት ኮድንና ሶርስ ኮድን እንደሚጨምር ሕጉ ይገልጻል::
ኮሙኒኬሽን ማለትም የውል አቀራረብና አቀባበልን ጨምሮ ሰዎች ከኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ጋር በተያያዘ የሚወስኗቸው ወይም ለውሳኔ የሚመርጧቸው ትዕዛዞች፣ ማስጠንቀቂያዎች፣ ጥያቄዎች ወይም መሰል መልዕክቶች ናቸው::
በዚሁ መሰረት የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ኮሙኒኬሽን በስልክ ወይም በኮምፒዩተር ኔትወርክ አማካኝነት በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ነው።
ረቂቅ አዋጁም የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ኮሙኒኬሽን ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል። ሕጉ በዋነኛነት የኤሌክትሮኒክ መልዕክት የአመንጪው ነው ተብሎ የሚወሰድበትንና የመልዕክቱ ተቀባይ መልዕክቱ የተላከው ከአመንጪው ነው ብሎ ግምት የሚወሰድበትን አግባብ ይደነግጋል።
በሕጉ መሰረት “አመንጪ” ማለት በራሱ ወይም በወኪሉ አማካኝነት የኤሌክትሮኒክ መልዕክት የላከ ወይም እንደ አግባቡ ከማከማቸቱ በፊት ያመነጨ ሰው ነው:: በኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ዙሪያ ያሉ የመሐል አገናኞች ግን አመንጪ ተብለው እንደማይቆጠሩ ሕጉ ይገልጻል::
“መልዕክት ተቀባይ” የሚባለው ደግሞ የመሐል አገናኞችን ሳይጨምር መልዕክቱን እንዲቀበል በአመን ጪው የተወሰነ ሰው ነው::
በሕጉ ትርጓሜ መሰረት “የመሐል አገናኝ” ማለት አንድን ሰው በመወከል የኤሌክትሮኒክ መልዕክትን የሚልክ፣ የሚቀበል፣ የሚያከማች፣ ወይም ከኤሌክትሮኒክ መልዕክት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያቀርብ ሰው ነው:: እናም የመሐል አገናኞች አመንጪዎችም ተቀባዮችም አይደሉም ማለት ነው::
በዚሁ መነሻ አንድ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት የአመንጪው ነው ተብሎ ግምት የሚወሰደው በራሱ በአመንጪው ወይም በወኪሉ አማካኝነት የተላከ ከሆነ ነው::
ከዚህ ሌላ መልዕክቱ የተላከው በአውቶማቲክ ሥርዓት ከሆነ የአውቶማቲክ ሥርዓቱ ፕሮግራም በተደረገው መሠረት አለመሥራቱ ካልተረጋገጠ በስተቀር መልዕክት በራሱ ጊዜ እንዲልክ ተደርጎ ፕሮግራም ተደርጎ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ በራሱ በአመንጪው ወይም በተወካዩ አማካይነት የተላከ ከሆነ የአመንጪው ነው ተብሎ ይወሰዳል።
ሕጉ አንድ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት የአመንጪው ነው ተብሎ የሚወሰድበትን አግባብ ከመደንገጉም በተጨማሪ የመልዕክቱ ተቀባይ በበኩሉ መልዕክቱ የተላከው ከአመንጪው ነው ብሎ ግምት የሚወሰድበትንም ሁኔታ አስቀምጧል።
በዚሁመሰረት የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ተቀባዩ መልዕክቱ የተላከው ከአመንጪው ነው ብሎ ግምት የሚወስድበት ዋነኛው ምክንያት መልዕክቱ ከኢንፎርሜሽን አመንጪው የተላከ መሆኑን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ስምምነት የተደረሰበት አሠራር ጥቅም ላይ ከዋለ ነው::
የመልዕክቱ ተቀባይ መልዕክቱ ከአመንጪው የተላከ እንዳልሆነ በጊዜ እንዲያውቅ ከተደረገና እርምጃ ለመውሰድም የሚያስችል በቂ ጊዜ የተሰጠው ከሆነ ወይም ተገቢ ጥንቃቄ በማድረግ ወይም በአመንጪውና በእርሱ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት የማረጋገጫ ዘዴ በመከተል መልዕክቱ ከአመንጪው እንዳልሆነ ካወቀ ወይም ሊያውቅ የሚችልበት መንገድ ካለ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ሕጋዊ ውጤት የለውም።
አመንጪውም የላከው መልዕክት ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትል በሚችል መልኩ የደረሰ ስለመሆኑ ተቀባዩን የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱን ስለመቀበሉ ማረጋገጫ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል።
እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ ታዲያ የመረጃ አመንጪው የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ሕጋዊ ውጤት የሚኖረው ከመልዕክት ተቀባዩ ማረጋገጫ ሲሰጠው እንደሆነ ገልጾ ከሆነ ተቀባይ መልዕክቱ ስለመድረሱ የላከው ማረጋገጫ ለአመንጪው እስከሚደርሰው ድረስ መልዕክቱ እንዳልተላከ ተደርጎ እንደሚቆጠር ነው።
የሸማቾች መብት ጥበቃ
የንግድ ሥርዓቱን በበላይነት በተቆጣጠረው ወረቀትን ማዕከል ባደረገው ግብይት የሸማቾች መብት ልዩ ጥበቃ የሚሰጠው ጉዳይ ነው:: ለዚህም የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ወጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል::
በዘመን-አመጣሹ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ውስጥም የሸማቾች መብት ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ነው:: በዚሁ መነሻ ረቂቅ አዋጁ የሸማቾች መብት የሚጠበቅባቸውን ሥርዓቶች ዘርግቷል::
ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አማካይነት ለሽያጭ፣ ለኪራይ ወይም ለልውውጥ የሚያቀርብ አቅራቢ በድረ-ገጹ ላይ ሊያስቀምጣቸው የሚገቡ በርካታ ኢንፎርሜሽኖችን ሕጉ ዘርዝሯል:: እነዚህንም ሸቀጦቹና አገልግሎቶቹ በሚቀርብበት ድረ-ገጽ ላይ እንዲያስቀምጥ ነው በአቅራቢው ላይ ግዴታ የተጣለው::
ከኢንፎርሜሽኖቹ በተጨማሪም ሸማቾች ውል ከመፈጸማቸው በፊት ሙሉ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽኑን እንዲገመግሙ አቅራቢው ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል:: ስህተቶችን የማስተካከል መብትም እንዳላቸውና ትራንዛ ክሽኑን ትተው እንዲወጡ ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባም በሕጉ ተደንግጓል።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላም ቢሆን ሸማቾች የገቡትን ውል በአስራ አራት ቀናት ውስጥ የመሰረዝ መብት ተሰጥቷቸዋል። ይሁንና ውል ማቋረጥ በመርህ ደረጃ የተፈቀደ ቢሆንም ይህ መርሕ ተፈጻሚ የሚሆነው የሸቀጦችን ባሕርይ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል::
በዚሁ መሰረት የሸቀጦቹን ባህርይ ታሳቢ በማድረግ (ለምሳሌ በቀላሉ የሚበላሹ ከሆኑ) ሸማቹ ያለምንም ምክንያትና ቅጣት ዕቃውን ከተቀበለበት ቀን ጀምሮ ወይም አገልግሎቶቹን መቀበል ከጀመረበት በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽኑን ሊሰርዘው ይችላል።
በሰባት ቀን ውስጥ ትራንዛክሽኑን የሚሰርዝ ሸማች ታዲያ የሚጣልበት ክፍያ ሸቀጡን ተመላሽ ለማድረግ የሚወጣ ቀጥተኛ ወጪ ብቻ ስለመሆኑ ነው ሕጉ የሚገልጸው።
ይህ ብቻ ሳይሆን ሸማቹ ትራንዛክሽኑን ከመሰረዙ በፊት ለሸቀጦቹ ወይም ለአገልግሎቶቹ ክፍያ ፈጽሞ ከሆነ ከላይ የተጠቀሰው ወጪ ከሙሉ ክፍያው ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ገንዘቡን የማስመለስ መብትም አለው::
የኤሌክትሮኒክ ነጋሪት ጋዜጣ መቋቋም
የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን የኤሌክትሮኒክ ንግድንና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎትን ያጠቃልላል:: በዚሁ መነሻ በረቂቅ አዋጁ የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶችን በተመለከተ ለመንግሥት አገልግሎቶች የተለዩ ባሕርያት አሏቸው የተባሉ ጉዳዮች ተለይተው ተቀምጠዋል።
በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሰነዶችን የሚቀበል፣ የሚያዘጋጅ፣ የሚያስቀምጥ፣ ፈቃድ የሚሠጥ፣ የክፍያ ሥርዓት የዘረጋ ማንኛውም መንግሥታዊ ተቋም ሰነዶችን፣ ፈቃዶችን ወይም የክፍያ ሥርዓቶችን በኤሌክትሮኒክ ቅርጽ ወይም መንገድ ሊቀበል፣ ሊያዘጋጅ፣ ሊሰጥና ሊዘረጋ እንደሚችል ተደንግጓል።
ከኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ዋነኛው ጉዳይ ሕጎችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ከማተም ጋር የተያያዘው ነው።
ሕጎችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ማተም በበርካታ አገሮች እየተለመደ የመጣ አዲስ አሠራር ስለመሆኑ ለፓርላማው የቀረበው ማብራሪያ ያሳያል።
ይህ አሠራር በየአገራቱ ቢዝነስ የሚሠራበት አግባብ እንዲሻሻል ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። በአገራችንም ይህንን አሠራር ማስገባት ፋይዳው እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ የፌዴራል የኤሌክትሮኒክ ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የፌዴራል የኤሌክትሮኒክ ነጋሪት ጋዜጣ በረቂቅ አዋጁ ተቋቁሟል።
ማንኛውም የፌዴራል መንግሥት ሕግ የሚወጣው በአዋጅ ቁጥር 3/1987 በተቋቋመው የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ አማካኝነት ነው:: ይሁንና ወጥነትና ተከታታይነት ባለው መልኩ በዚህ ጋዜጣ የሚታተሙት በፓርላማው የሚወጡት አዋጆች ናቸው::
በአንጻሩ በአስፈጻሚ አካላት የሚወጡ የበታች ሕጎች በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ስለማይወጡ በቀላሉ ተደራሽ አይደሉም:: በተለይም መመሪያዎችን ታትመው ማግኘት የማይታሰብ ነው::
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ታዲያ አዋጆችንና ደንቦችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ለማተም የፌዴራል የኤሌክትሮኒክ ነጋሪት ጋዜጣ ተቋቁሟል::
ከኤሌክትሮኒክ ነጋሪት ጋዜጣ በተጨማሪም የበታች ሕጎችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ በአዋጁ “የፌዴራል የኤሌክትሮኒክ ሕጎች መዝገብ” የተሰኘ ሕጎችን በኤሌክትሮኒክ ተደራሽ የማድረጊያ ሌላ የፌዴራል የሕግ ጋዜጣ ተቋቁሟል።
በዚሁ መሰረት ሁሉም የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት የሚያወጧቸው መመሪያዎች፣ አመላካች መመሪያዎች፣ ማስታወቂያዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ሰነዶች የሚወጡት በፌዴራል የኤሌክትሮኒክ የሕጎች መዝገብ ይሆናል ማለት ነው::
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
ከገብረክርስቶስ