የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጥቅማጥቅም ለማሻሻል ነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም መመሪያ አውጥቷል። መመሪያው ተመላሽ የማይደረግ ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ ተገዝቶ ለከፍተኛ ኃላፊዎቹ እንዲሰጥ ያዝዛል። የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከአንድ ወር በኋላ መመሪያውን ለማስፈጸም ፣ የሚገዙ የላፕቶፕና ሞባይል አይነቶችን ዝርዝርና የአፈፃፀም መመሪያን የያዘ ሰነድ ለፌዴራል ተቋማት አሰራጭቷል:: ምን ዋጋ አለው ? ማዘዝ እንጂ መታዘዝን የማያውቁ አንዳንድ ከፍተኛ ኃላፊዎች የአገርንና የህዝብን ሀብት መበዝበዣ አዲስ መንገድ አገኘን ብለው ገሰገሱበት::
ከስድስት ወራት በፊት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለአንድ የመንግሥት ባለስልጣን የመቶ ሺ ብር ተንቀሳቃሽ ስልክ ግዥ መፈጸሙን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጾ ነበር:: እኛም ህዳር አምስት ቀን 2012 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ በዚሁ አምድ “ባለስልጣን ይከለክላል እንጂ አይከለከልም” በሚል ርዕስ ባወጣነው ጽሑፍ ድርጊቱን በመኮነን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድበት አሳስበን ነበር፡፡
ከሰሞኑ የንዘብ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት አንዳንድ ተቋማት መመሪያውን በመጣስ በተጋነነ ዋጋ ግዢ መፈጸማቸውን ማረጋገጡን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጿል:: በወረደው መመሪያ መሠረት ግዢ መፈጸሙን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት … በአፈፃፀም መመሪያው ከተዘረዘረው ውጭ አይፎን ስልክና አፕል ላፕቶፖች ተገዝተው ተገኝተዋል:: መመሪያው ላይ በቀረበው ዝርዝር መሠረት የተገዙት የእጅ ስልኮችና ላፕቶፖችም ቢሆኑ ገበያው ላይ ካለው አማካይ ዋጋ አንጻር እጅግ በተጋነነ ዋጋ የተገዙ መሆናቸው ተገልጿል።
መመሪያው ግዢ በግልጽ ጨረታ መፈጸም አለበት ቢልም በማይታዘዙ አዛዣች ቀጭን ትእዛዝ በፕሮፎርማ ግዢ ተካሂዷል:: በመመሪያው መሰረት ስልክና ላፕቶፕ ከተገዛላቸው በኋላ በእጃቸው ላይ የነበረውን ለመመለስ አሻፈረኝ ያሉም ነበሩ:: አንዳንድ ተቋማት ደግሞ ጥቅማጥቅሙ ለማይመለከታቸው ኃላፊዎች ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ ገዝተው በመስጠት የመንግሥትን ሀብት “በሚገባ” ተጠቅመዋል።
ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ለኃላፊዎች የተጋነነ ግዥ በመፈፀም ግንባር ቀደሞቹ በትምህርቱ ዘርፍ በመሪነት የተሰማሩት መሆናቸው አግራሞትን ያጭራል::የትምህርት ዘርፉ እኒህን በመሰሉ የደሃ አገርን ሀብት በአግባቡ በሚጠቀሙ “ቆጣቢዎች” እየተመራ የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው::
ሳይማር ባስተማራቸው ያወቁ የተራቀቁ እርቃን አስቀሪዎች ሀብቱን የሚዘረፈው ህዝብ ግን አንጀት አይበላምን ? ይበለው ! “ሲሾም ያልበላ…” እያለ የሚተርት ማህበረሰብ ይህን ተረቱን እርም ካላለ ነጣቂዎቹ አያባሩም::እንዲያውም ላቡንና ደሙን መጥጠው ሲያበቁ ፣ ዶክተር ፍቃደ አዘዘ “አሻራ” በሚል ርዕስ በ1994 ዓ.ም ባሳተሙት የግጥም ስብስብ ገጽ 53 ላይ ያሰፈሩትን “ሽልማትና መስዋትነት” የተሰኘ ግጥም ተውሰው እንዲህ ይሉታል ፡-
ልንታዘዘው ሳይሆን ልናዝዘው የመጣንበት፤
አብረነው ልንሞት ሳይሆን እሱን ልንሸኝ የተሾምንበት፤
እሱ ራሱ ባስተማረን ከጫንቃው ላይ ወጥተንበት፤
ዳግመኛ ልንጭነው ማራገፉን ላንጠቅስለት፤
ለካስ ይሄው ነው መማር ለራስ መቆም ላንዲት አንጀት::
የትምህርት ተቋማቱ ለአምስት የሥራ ኃላፊዎቻቸው ለላፕቶፕ 679 ሺህ ብር እና ለሞባይል 348 ሺህ 800 ብር ወጪ በማድረግ በድምሩ የአንድ ሚሊዮን 27 ሺህ 800 ብር ግዢ ፈጽመዋል።
የንዘብ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይሬክ ቶሬት ተቋማት የውስጥ ኦዲት አድርገው ግኝቱን እንዲልኩለት 137 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን በደብዳቤ የጠየቀው በየካቲት ወር ነው::እስካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ ምላሽ የሰጡት ተቋማት 58 ብቻ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ 42ቱ ተቋማት ለኃላፊዎቻቸው ግዥ የፈጸሙ ሲሆን፤ 16 ቱ ግዥ አለመፈጸማቸውን አሳውቀዋል። 63 ተቋማት ደግሞ ገና የኦዲት ሪፖርትም ሆነ ግዢ አለመፈጸማቸውን የሚገልጽ ምላሽ ለኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬቱ አላቀረቡም:: ምናልባትም አንዳንዶቹ ምላሽ ለመስጠት የዘገዩት ከመመሪያ ውጪ በተጋነነ ዋጋ ግዢ በመፈጸማቸው ምክንያት ሊሆን ስለሚችል የባሰ ነገርም ልንሰማ የምንችልበት ዕድል አለ::
አገራቸው የቋጠረችው ጥሪት በጠራራ ጸሐይ መጣራቱን የሰሙ ዜጎች ምን ይሉ ይሆን ? … አበራ ለማ “አውጫጭኝ” በሚል ርዕስ በ1994 ዓ.ም ካሳተሙት የግጥም መጽሐፉ ገጽ 51 ላይ “እኛ ጫማ ነን” በሚል ርዕስ የፃፉትን ግጥም ተውሰው እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡፡
እኛ ጫማ ነን ወደር የሌለን፤
ወጪ ወራጁ ሲጫማን –
ሰጥ ለጥ ብለን የታዘዝን፤
… እንደ ሰም ቀልጠን እንደ ብረት ተቀጥቅጠን፤
የወርቅ አምባር ያልማዝ ጉትቻ ቀለበት ሀብል ሆነን፤
ስንቱን ባለጊዜ አሳምረን አንቆጥቁጠን፤
ሳያልፍልን አሳልፈን ሽሮ ሳናይ ጮማ አብልተን፤
ቅራሪ ሳናይ ውስኪ ጠጁን አስጎንጭተን፤
ጎጆ ብርቄ እየተባልን እልፍኝ አዳራሽ አስመርጠን፤
ሁሉን ችለን ሁሉን ውጠን ያሳለፍን፤
እኛ’ኮ ጫማ ነን ወደር አቻ ያልተቸረን …
የመንግሥትና የህዝብ ሀብት በዚህ ደረጃ ሊባክን የቻለው መመሪያው በፈጠረው ክፍተት ነው::ለሚገዛው ላፕቶፕና ተንቀሳቃሽ ስልክ የዋጋ ጣሪያ መቀመጥ ነበረበት::መመሪያው አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ ካለበት ቦታ ተነስቶ በሌላ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሲመደብ እንደገና ግዢ እንዳይፈጸምለት አይከለክልም:: እንደ ሰንደቅ ዓላማ ጠዋት ወጥቶ ማታ የሚወርድ ተሿሚ በሚበዛበት አገር እንዲህ ያለ ክፍተት መፍጠር ከፍተኛ የሀብት ብክነት እንዲኖር በር ይከፍታልና ጥርቅም ተደርጎ መዘጋት ነበረበት::
ከዚህ ለጆሮ ከሚቀፍ ዜና ውስጥ የምንነጥቀው በጎ ነገር አላጣንም:: መንግሥት የሚያሳጣውን ነገር በራሱ እጅ አደባባይ ላይ ማስጣት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው:: የገንዘብ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት የኦዲት ግኝቶቹን ከመረመረ በኋላም ዘርፉን ለሚመራው የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ከግዥ መመሪያው ውጭ በመግዛት የህዝብና የመንግሥትን ገንዘብ ያባከኑ ከፍተኛ አመራሮች ሕግ ፊት እንዲያቆም ጠይቋል:: በተጨማሪም ገበያው ተጠንቶ የተጋነነ ግዥ የፈፀሙ ከፍተኛ አመራሮች ልዩነቱን ለተቋሙ እንዲመልሱ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። የጽሑፉ ትኩረት ሀብት አባካኝ ተቋማት ላይ ስለሆነ እንጂ፣ ለአንድ ላፕቶፕ 12 ሺህ 729 ብር እንዲሁም ለአንድ ሞባይል 7 ሺህ ብር 720 ወጪ በማድረግ ለኃላፊዎቻቸው ኃላፊነት በተመላበት መንገድ ግዢ የፈጸሙ ተቋማትም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
የትናየት ፈሩ