
– 89 በመቶ ሼድና የለማ መሬት በባለሀብቶች ተይዟል
አዲስ አበባ፡– በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ያለው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ከ60 በመቶ በላይ መድረሱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።በ13ቱም ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሼድና የለማ መሬት በባለሀብቶች የመያዝ ምጣኔ 89 በመቶ መድረሱ ተጠቁሟል።
የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እንደሀገር የተወሰዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ርምጃዎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ አድርጓል። በእዚህም ከአምስት በመቶ በታች የነበረው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎም ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል።
የተገኘው ውጤት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የተሠሩ ሥራዎችን ውጤታማነት የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ ዘመን፤ እንደሀገር የሚታሰበውን የኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር ዋነኛ ተዋናይ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ኢንዱስትሪያሊስት በማፍራት በኩልም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ከእዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ዞኖቻችን ውስጥ የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች በተለይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በአብዛኛው ዝቅተኛ እርከን ላይ የማሠማራት ሁኔታ ይስተዋል እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ወደ መካከለኛ አመራርነት ደረጃ ላይ ጭምር እየመጡ መሆኑንም አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የፖሊሲ፣ መመሪያና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን ማድረጉን አመልክተው፤ በእዚህ 80 የሚደርሱ የተለያዩ የሕግ ማሕቀፎች ክለሳ ተደርጓል ።በእዚህም ከእዚህ ቀደም ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት የነበራቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየታየባቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው 13ቱም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ ከእዚህ ውስጥ ቦሌ ለሚ እና አዳማ ልዩ ኢንዱስትሪ ዞኖች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች ተይዘዋል። አጠቃላይ የሁሉም ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የሼድና የለማ መሬት የመያዝ ምጣኔም 89 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።
የኢንቨስትመንት ፍሰቱም ከእዚህ ቀደም ከተለመዱት ቻይናና ሕንድ ባለፈ የጃፓን፣ ቬትናም፣ ደቡብ ምሥራቅ ኤስያ ሀገራት እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ባለሀብቶች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ ገብተው እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከውጭ ሲመጡ የነበሩ ባለሙያዎችንም በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እየተኩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
የኢንቨስመንት ፍሰቱን ለማሳደግም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢኮኖሚክ ዞኖች ምርቶችን ወደ ውጭ ከመላክ ባለፈ ገቢ ምርት መተካት ላይ ትልቅ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከውጭ ሲመጡ የነበሩ ወታደራዊ ደንብ ልብሶችንና የቢራ ገብስ ብቅልን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል። በሌሎች ዘርፎችም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ በቀጥታ ሥራ ከተፈጠረላቸው ዜጎች በተጨማሪ በየአካባቢው ላሉ በርካታ አርሶ አደሮች ቋሚ የገበያ ትስስር በመፍጠር በኩል ትልቅ ሥራ መሠራቱንም አቶ ዘመን ጨምረው ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና መካከል አስሩ ባለፈው ዓመት ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው ይታወቃል።
ከአፍሪካ ሀገራት ጋና፣ ሞሪሽየስ፣ ሴኔጋል እንዲሁም ሌሎች ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አቋቁመው በመሥራታቸው በዘርፉ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም