ኢንጂነር ዳዊት እምሩ ካባ ከአዲስ አበባ ሕንጻ ኮሌጅ በኮንስትራክሽን ቴክኒዮሎጂ ማኔጅመንት እና በቢውልዲንግ ኢንጂነሪግ ተመርቀዋል።የራሳቸው የኮንስትራክሽን ደርጅት ያላቸው ሲሆን፤ የሕንጻ ስራ ተቋራጭም ናቸው።ብዙ ችግር ባለበት በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ መሰረታዊ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ቃለምልልስ አድርገው እንዲህ አቅርበነዋል ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡-በኮንስትራክሽን ውስጥ ደረጃ አንድ ኮንትራክተር ማለት የሚሸፍነው ምንድ ነው?
ኢንጂነር ዳዊት፡-ደረጃ አንድ ኮንትራክተር ማለት በአገሪቱ ትልቁ ደረጃ ተብሎ የሚጠቀስ ነው።መስፈርቶች ይወጡና ይሄን ያህል ማሽነሪ፤ ይሄን ያህል የሰው ሃይል እና ሌሎችም የሚዘረዘሩ መስፈርቶች አሉ።አንድ ሰው ይህን ሲያሟላ ወይም እዚህ ሲደርስ የሚሰጠው ደረጃ፤ ደረጃ አንድ ኮንትራክተር ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ደረጃውን የሚሰጠው ማነው ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- የከተማ ልማት ሚኒስቴር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሙያው ምን ያህል ጊዜና በኮንትራክተርነት የት የት ፕሮጀክቶች ላይ ሰሩ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- ትምህርቴን ጨርሼ እንደተመረቅኩ በቀጥታ የገባሁት ወደ ስራው ነው።1996 እና 1997 ዓ.ም በቤቶች ልማት ግንባታ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ገርጂ ከጂቲዜድ ጋር 32 ብሎኮች፤ ጀሞ 1 እና 2 ላይ 7 ብሎኮች፤ ጎተራ ኣካባቢ 4 ብሎኮች፤ መብራት ኃይል 4 ብሎኮች ሰርተናል።በብዙ ቦታዎች ተሳትፌአለሁ።
በአማራው ክልል የዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች ግንባታ እና የሆስፒታሎች ግንባታ፤ የኢትዮ ቴሌኮም ሀይ ሌብል ዌር ሀውስ ግንባታ፤ የባለሀብቶች ፓምፕ ፋብሪካ፤ አዳሚ ቱሉ የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ (ፍሪጎሪ ፊኮ ቦራን ፉድስ)፤ የውሃ ፋብሪካዎች ዋን ውሃ ሰበታ፤ አርኪ ውሃ ሱሉልታና የሁለቱ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች፤ የጫማ ሶል ፋብሪካ አቃቂ (ዳሚ ኢቲ)፤ የሻማ ፋብሪካ (አቢሰን ኢንደስትሪ)፤ የፓምፕ ፋብሪካና ጀኔሬተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ (ኢሙ ትሬዲንግ) ታጠቅ መስመር፤ ደቡብ ክልል በቤቶች ልማት ላይ በወላይታ ሶዶና በቡታጅራ ሌሎችም ብዙ ግንባታዎች ሰርተናል።
በአሁኑ ሰዓት የሶላር ፋብሪካ ግንባታ ደብረብርሀን (ኤል ስኮርፕ) ሴንት ጎበን ሞርታት ፕሮሰሲንግ ፕላንት፤ ኤልስ ዌዲ ትሬዲንግ ኬብል ማምረቻ በዱከም በኩል እነዚህን ግንባታዎች እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ደረጃ ያለውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ስራን የሚያዩት እንዴት ነው ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- በአጠቃላይ ከወሰድነው በአገር ደረጃ ያለው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ስራ ደስ የሚያሰኝ ነው።ከሴክተሩ ወጥቼ እንደ አንድ ግለሰብ ሳየው የሚደረጉት ግንባታዎች የሚዘረጉት መሰረተ ልማቶች የሚታቀዱት እቅዶች በነገይቱ ኢትዮጵያ ላይ የሚፈነጥቁ ናቸው።እጅግ በጣም ደስ ይላል።በአገር ደረጃ ተስፋ ሰጪነቱ ከፍተኛ ነው።
በዘርፉ ውስጥ እንዳለ እንደ አንድ ኮንትራክተር ሆኜ ሳየው ደግሞ ምናልባትም ከስራው መቀዛቀዝ አንጻር በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ብዙ ድርጅት እየወደቁ ሲፈርሱ ይስተዋላል።በሌላ በኩል በጣም ተስፋ ሰጪ ነገር ጎልቶ ይታያል።መካድ የሌለበት በዘርፉ የመዳከም ስጋት አለ።የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከአገራዊ ኢኮኖሚው አንጻር ሲታይ ከግብርናው ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፉ ዘርፍ ነው።ተመልሶ እንደሚነቃቃና ስራዎች በተሻለ ሁኔታ እንደሚቀጥሉ ተስፋ አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ሰዎች የኮንስትራክሽን ስራቸውን ትተው ወደ ውጭ የሚሄዱት ለምንድ ነው?
ኢንጂነር ዳዊት፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉ ብዙና ውስብስብ ችግር ያለበት ነው።ወደ ችግሮቹ ስንገባ በመጀመሪያ ራሴን ብለህ ስታይ ከቢሮ አደረጃጀትህ ተነስተህ አመለካከቴ ምንድ ነው? መሄድ የምፈልገው ወዴት ነው? የማደርገው ምንድን ነው? በሚል አቅምህን ከመገንባት አኳያ የገንዘብና ብዙ ችግሮች ያሉበት ዘርፍ መሆኑን ታያለህ።
በአብዛኛዎቻችን ላይ ግልጽ የሆነ ራእይ የማስቀመጥ ችግር ይታያል።ወደውጭ ወደ መንግስት ስትመለከት ደግሞ ይሄን ችግር ለማቃለል ብዙ እገዛ የሚደረግበት ዘርፍ አይደለም።ተስፋ ቆርጠው ከኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚወጡም አሉ።ፈታኝ ዘርፍ ነው።ብዙ ፈተናዎች አሉበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄን ጉዳይ ማሕበራችሁ በተደጋጋሚ አንስቶታል።ብዙ ኮንትራክተሮች የሚያነሱት መሰረታዊ ችግር ነው።ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?
ኢንጂነር ዳዊት፡- በዘርፉ ማን ምን ያህል ስራ አለው? የሚለውን ከተማ ልማት ሚኒስቴር እንደ አገር ዳታ ሲስተም( የመረጃ ጥንቅር) የለውም።ምናልባት አሁን ገቢዎች ዳዊት የት አካባቢ ስራ አለው? አማራ ክልል ደብረብርሀን ወይስ ደሴ ወይንስ ስራ ያለው ደቡብ ክልል ነው? የሚለውን በተመለከተ ገቢዎች ሁሉም ዝርዝር መረጃ ይኖረዋል።ገቢያቸውን ለመሰብሰብ ስለሚፈልጉ በደምብ ሰርተውበታል።የእኛም የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ መረጃ (ዳታ) የሚያስፈልገው ነው።መረጃ መያዝ አለበት።ይሄ ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለሁሉም እንዲዳረስ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ፕሮጀክቶች ለመስራት አንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ ብዙ ቦታዎች ላይ ወሰደ እንበል።‹‹የሚሰራው የትኛውን ነው?›› ሲባል አቅሙና ጉልበቱ ብዙ ቦታ ላይ ስለሚበታተን አንዱን እንኳን በቅጡ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቶ ጨርሶ ማስረከብ አይችልም።የስራ ጫና ይበዛበታል።ድካሙ ከፍተኛ ነው።የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አንድ ላይ ማስተዳደር አይችልም።አንዱ ላይ ሙሉ ሀሳብን አድርጎ ግንባታውን በሚገባ እየሰሩ እየጨረሱ አስረክቦ ወደ ሌላው መሸጋገር ቢለመድ ይበጃል።
ይሄ ሁኔታ በተወሰነ ማእቀፍ ውስጥ ከተቀመጠና ገደብ ከተበጀለት ሁሉም ባለሙያ በተመጣጠነ መልኩ የመስራት እድሉን ያገኛል።ከተማ ልማት ሚኒስቴር ዳታ ሲስተም (የመረጃ ቋት አበጅቶ) ማን፤ የት፤ ስንት ፕሮጀክት አለው? የሚለውን እየተከታተለ ቢሰራበት ከፍተኛ ለውጥና ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ።ስራውንም በእኩልነት ለሁሉም ለማዳረስ ይረዳል።
አዲስ ዘመን፡-ይሄንን ችግር ለመፍታት ከመንግስት አካላት ጋር ተወያይታችኋል?
ኢንጂነር ዳዊት፡- በኢንጂነር አምሀ ስሜ የሚመራው ማሕበራችን በጣም ብዙ ጊዜ ተወያይ ቶበታል።ይወያያልም።አሁንም እየሄዱበት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-የተገኘ መፍትሄ ወይስ የተወሰደ እርምጃ አለ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- ከአርክቴክቶች ማሕበር፤ ከስትራክቸራል መሐንዲሶች ማሕበር፤ ከኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች ማሕበር፤ ከተለያዩ ማሕበራት ጋር ሆነው በጋራ እየገፉበት እንደሆነ አውቃለሁ።አሁን የቱ ጋር እንደደረሱ ግን መረጃው የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- የኮንስትራክሽን ስራዎችን በተመለከተ የአገር ውስጥ ተጫራቾች እያሉ ለውጭ ሰዎች ይሠጣል የሚሉ አሉ።እንዴት ያዩታል ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- በፊት ባለስልጣኖች የሚያነሱት ነገር ነበር።እናንተን ሞክረናችሁ ስራ ሰጥተናችሁ ነበር።አልቻላችሁም ይላሉ።መልሰው ተስፋ ያደርጉና ለአገር ውስጡ ተቋራጭ ይሰጣሉ።በአራትም በአምስትም አመት እንደ ሕፃን ልጅ እዛው ዳዴ ከሆነ ለውጥ ሊያመጣ ካልቻለ ሌላ መጥቶ እንዲሰራ ሊደረግ ይችላል።አሁን ያለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው።የውጭ ተቋራጮች መጥተው ለምን ወሰዱ የሚል አመለካከት የለኝም።
ሲገቡ ግን በቴክኒዮሎጂ እውቀት ሽግግር፤ በአቅም ግንባታ ደረጃ በአገር ውስጥ ካለነው ጋር እንዴት መስራት አለባቸው የሚለውን በተመለከተ መንግስት በጣም ጠንክሮ በትኩረት መስራት አለበት።
የውጭ ኮንትራክተሮች አገር ውስጥ ገብተው አሸንፈው ስራ ሲወስዱ በአገር ውስጥ ላሉት ሰብ ኮንትራክት ይሰጣቸው ይባላል።በሕጉም ሰፍሮ ይገኛል። ለምሳሌ የአንድ ቢሊዮን ብር ስራ ቢወስዱ እስከ 25 በመቶ በሰብ ኮንትራት እንዲያሰሩ ተቀምጦላቸዋል።ነገር ግን ስራውን ሲሰጡህ የቴክኒዮሎጂ እውቀትና ልምድ ሽግግር የምታደርግበትን ዕድል አይሰጡህም።የአፈር ማንሳት ስራ ሊሰጡህ ይችላሉ።የሚሰጡት ተራ አይነት ስራዎችን ነው።በአገር ውስጥ ያሉ ሙያተኞች ወይንም ሰብ ኮንትራክተርስ ከውጪ ሰዎች የሚወስዱት የቴክኒዮሎጂ የእውቀትና የልምድ ሽግግር ዞሮ ዞሮ አገር ውስጥ ቀሪ ስለሆነ ዜጎች እውቀታቸውን አዳብረው የበለጠ የሚሰሩበትን ስራ የውጭ ኮንትራክተሮች እንዲሰጡ መንግስት የግድ ጫና ማድረግ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አገራችን መጥተው ሲሰሩ የቴክኖሎጂ የእውቀት የልምድ ሽግግር ለዜጎቻችን ማስተላለፍ ካልቻሉ ምን ትርፍ አለው?
ኢንጂነር ዳዊት፡- ለእኛ የሚጠቅመን በተለይ እውቀትና ልምዳቸውን መጋራቱ ነው።መንግስት በሕግ ደረጃ አስቀምጦታል።አሁንም ትልቅ ትኩረት መስጠት ተግባራዊነቱን መቆጣጠርና ጫና ማድረግ አለበት ያልኩትም ለዚህ ነው። በአብዛኛው አብረውን እየሠሩት ያሉት ቻይናዎች ናቸው።ዝም ተብሎ ከየት ተነስተው? የት ደረሱ እንዴት አደረጉ? ተብለው ቢታዩ በየከተሞቻቸው ያቋቋሟቸው የፈጠራ ስራ የሚሰሩበት የልህቀት ማእከል (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንሲ ) አላቸው።
ከተማችን ላይ ከጥቂት አመታት በፊት ይሰሩ የነበሩት ቤቶች በእንጨት የተማገሩ በጭቃ የተለሰኑ ነበሩ። እነሱ ከመጡ በኋላ እነዚህ ኤች ፒ የሚባሉትን ሌሎችንም ቴክኒዮሎጂዎች ስለሚገኙ ሲሚንቶና አሸዋ አብኩተን ተለሳኝ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።ትናንሽ የሚመስሉ ነገሮችን በጣም ይሰራሉ።እንዴት መስራት እንደሚቻል ያውቁበታል።
አሁን የኮሮና ወረርሽኙ ሲከሰት ችግሩን ለማስወገድ ስርጭቱን ለመግታት በፔዳል የሚመቱና ንክኪ እንዳይኖር የሚያደርጉ አሰራሮችን አምጥተዋል።እኛም ጋር ጭንቅላቱ አለ።ዋናው ነገር መንግስት መስመሩን ሰፋ አድርጎ ዜጎች ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ማድረግ ነው።ይህ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።ብዙ አገራዊ አስደናቂ አዳዲስ ግኝቶች፤ የፈጠራ ስራዎች ወደ አደባባይ ይወጣሉ።ኢትዮጵያ ውስጥ ታምቆ ያለ አደባባይ ያልወጣ የፈጠራ ስራ ችሎታና እውቀት እንዳለ አውቃለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-እኛ አገር ተገጣጣሚ ቤቶች፤ ፋብሪካዎች፤ ሆስፒታሎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ክሊኒኮች ወዘተ የሚሰሩ የመንግስት ወይንም የግል ፋብሪካዎች አሉ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- አዎን አሉ።ቻይኖቹ ፕሪ ፋብሪኬትድ የሆኑ ስራዎችን የሚሰሩ በጣም ግዙፍ ግዙፍ የሆኑ ወርክሾፖች አሏቸው።በመደበኛ አካሄድ ቢኬድ ቻይና በምትሰራው አይነት አንድን አነስተኛ ከተማ፤ ሆስፒታል፤ ቤት፤ ፎቅ በተአምር በ10 ቀን ውስጥ
መስራት አይቻልም።ተአምር እየሠሩ ያሉት አስቀድሞ ፕሪ ፋብሪኬትድ (ቀድመው የተመረቱ) እየመጡ የሚገጣጠሙ ብሎኮች ናቸው።በብዛትና በስፋት የሚሰሩ ለምሳሌ እንደ ኮንዶሚኒየም፤ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ሆስፒታሎች በፕሪ ፋብሪኬትድ (አስቀድሞ በተመረቱ ኤለመንቶች) መስራት ብንችል አንደኛ የሚፈለገውን ጥራት እንጠብቃለን፤ ሁለተኛ ብክነት እንቀንሳለን፤ ሶስተኛ በታቀደለት ጊዜ ፕሮጀክቱ አልቆ ወደሚፈለገው ስራ እንዲገባ ይደረጋል።መንግስት ይሄንን በስፋት ከሄደበት የግል ባለሀብቶች እነዚህን ግብአቶች በመጠቀም በጣም ሰፋ ያለ ስራ በመስራት ዋጋውን ማረጋጋት ይችላሉ የሚል እይታ አለኝ።
እኔ አሁን በስፋት የምሰራው ስቲል ስትራክቸር ፋብሪካ ላይ ነው።በስቲል ስትራክቸር የሚሰሩ ፋብሪካዎች ከመደበኛው በኮንክሪት ከሚሰራው ፋብሪካ ጋር በፍጹም አይገናኙም፡፡
አዲስ ዘመን፤- ስቲል ስትራክቸር ፋብሪካ ምንድ ነው ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- ስቲል ስትራክቸር ማለት ፋብሪካው ዲዛይን ተደርጎ ተሰርቶ ከውጭ ይመጣል።ኮሎኖቹ፤ ገርደሮቹ፤ ዲሞዎቹ ሁሉም ይመጡና እዚህ የሚሰራው ታች ያለውን የሲቪል ስራውን ብቻ ነው ማለት ነው።የሚገጣጠመው ያኛው በሙሉ ከመጣ በኋላ ነው።በእርግጥ በጣም ፕሪሳይስ (ትክክለኛ) የሆነ ስራ ይጠይቃል።ኢንች ፐርፌክት መሆን አለብህ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄ ቴክኒዮሎጂ አገራችን ከገባ ቆይቷል ?
ኢንጂነር ዳዊት፡-በሀገራችን አለ።ብዙ ግዜው ነው።እኔ ከአስራ አንድ አመት በላይ ሰርቼበታለሁ።
አዲስ ዘመን፡-በኢትዮጵያ ውጤታማ ነው ?
ኢንጂነር ዳዊት፡–በጣም ውጤታማ ነው። በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካዎች ላይ ውጤታማ ሆኗል።በዚህ መልኩ ትምሕርት ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ፎቆች፤ ሌሎችም ላይ ስቲል ስትራክቸርንም በመጠቀም መስ ራት ይቻላል።
በዚህ አይነት ተገጣጣሚ ቤቶች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ክሊኒኮች፤ ቤተመጽሀፍት፤ የመዝናኛ ቦታዎች፤ መሰብሰቢያ አዳራሾች፤ ሙዚየሞች፤ ፊልም ቤቶች፤ ድልድዮች ሌሎችም ሰፊ ነገሮችን ይሄን ቴክኒዮሎጂ ተጠቅመን ብንገነባ ብዙ ለውጥና እድገት ይመጣል።
የኢትዮጵያ ተገጣጣሚ ስራዎች ድርጅት የሚባል የመንግስት ድርጅት ቃሊቲ አካባቢ ድሮ ነበረ።ተገጣጣሚ ቤቶችን የሚሰራ ማለት ነው።ድርጅቱ አለ።አሁን እንደዚህ አይነት ስራዎችን ያመርታል አያመርትም አላውቅም።የምነግርህ እጅግ ፈርጀ ብዙ ለሆኑ ችግሮቻችን ፈጣን መፍትሄ የሚያስገኝ ስራ መሆኑን ነው።
ስራውን ስፔሲፊኬሽን ይወስነዋል።እየተለማመድን እንድንሄድ እንደዚህ አይነት ስራዎችን ለመስራት መንግስት በሩን በሰፊው መክፈት ቴክኒዮሎጂዎችን የሚጋብዝ የሚያዳብር መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡-የሚወጣው ስፔስፊኬሽን ይወስነዋል የሚለውን ቢገልጹልን ?
ኢንጂነር ዳዊት፡-ለምሳሌ አንድ ቤት ወይም አጥር ለመስራት አንተ በብረት መስራት ትፈልጋለህ።ሌላው በብሎኬት መስራት ይፈልጋል።ሌላው በድንጋይ ልስራ ይላል።ስፔስፊኬሽን በምንና እንዴት ይሰራ የሚለውን የሚገልጸው ነው።ወደዚህ አይነት ነገር እንዲሄዱ ነገሩ እጃችን ላይ ከሌለ ያንን ለመወሰን ይከብዳቸዋል።
በአሁኑ ሰዓት መንግስት ትላልቅ ነገሮችን እያቀደ ስለሆነ በዚህ መስክ የተገጣጣሚ ቤቶች የሚሰራበትን ፋብሪካ አንድ ጊዜ ቢገባበትና ቢያቋቁም ወይንም ይሄንን ሊያቋቁሙ የሚችሉ ባለሀብቶችን ቢጋብዝ እጅግ የላቀ ስራ ይሰራል ብዬ አምናለሁ።በሀገራችን ትልቅ ለውጥም ይመጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በስቲል ስትራክቸር አሰራር ከውጭ ዲዛይናቸው ተጠናቆ ተሰርተው የሚገቡ ፋብሪካዎችን እኛ የምንሰራው የመገጣጠም የቤዝመንት መሬት ላይ የመትከል ስራ ነው ብለዋል።ዲዛይኑ ከወጣ የፋብሪካዎቹ እቃዎች በሀገራችን ተሰርተው መገጣጠም አይቻልም ?
ኢንጂነር ዳዊት፡-ይቻላል።ስቲል ስትራክቸር አሁንም በሀገራችን እየተሰራበት ነው።ይሄን የሚሰሩ የግል ድርጅቶች አሉ።ልክ እንደ ስቲል ስትራክቸሩ ስራ በኮንክሪት ስትራክቸሩ ተገጣጣሚ የሆኑ ቤቶች ቢሰሩ፤ ግዙፍ ወርክሾፖች እንዲቋቋሙ ተደርጎ በዚህ አይነት ስራው ቢቀጥል ይሰፋል፤ ያድጋል ብዬ አስባለሁ።
መንግስት አነስተኛና ጥቃቅኖችን እንደሚያበ ረታታው ሁሉ የፈጠራ ችሎታ ላይ በጣም ብዙ ያዳበሩ ግለሰቦች አሉ። ለእነሱ ትኩረት ሰጥቶ ከያሉበት አሰባስቦ አቀናጅቶ እንዴት እንስራ የሚለውን አብሮ በጋራ ተቀምጦ መምከር ነው።ለምሳሌ በቅርቡ አንድ ጣሊያናዊ ወደ ላንጋኖ አካባቢ የሰራውን ቤት እያሣየኝ ነበር።ቤቱ ላይ ምንም ስንጥቅ የሚባል ነገር አይታይም።እንደዚህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው፤ ምንድነው ምስጢሩ ስለው አሁን በእኛ ልስን ለመለሰን የምናደባልቀው አሸዋና ሲሚንቶ ብቻ ነው።እሱ ትንሽ ኖራ ጨምሮበታል።ይሄንኑ ነገረኝ።ትንሽ ይምስላል ግን ትልቅ እውቀት ነው። አየህ እንደዚህ አይነት ነገሮች ጥራቱን የሚጠብቁ፤ አቅሙን የሚገነቡ፤ አንተን የማያስነቅፉ፤ በጊዜ ኢንቨስት የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው።ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉብን።አዎ አሉብን።ትልቁ ነገር እንዴት መሆን ያለበት እንፍታው የሚለው ነው።ነገን ብሩህ አድርገን ማሰብ ሀገራችንን ወደተሻለ የእድገት ምእራፍ በኮንስትራክሽኑም ሆነ በሌላው ዘርፍ ለማሳደግ ተግተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
መንግስት የልህቀት ማእከሎችን (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ) በየከተማው ቢያደራጅና በስፋት ቢሰራበት ሁለተኛ ደግሞ የተገጣጣሚ ቤቶችን ሊሰሩ የሚችሉ በጣም ግዙፍ የሆኑ ወርክሾፖችን በየቦታው ቢሰራ ቢያስፋፋ ለባለሀብቱ ለሕዝቡም ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።
በአንድ ወቅት መንግስት የአቅም ግንባታዎች ላይ በጣም ሰርቶ ነበር።ሲኖ ትራክ ከባድ መኪናዎች መጀመሪያ የመጡ ጊዜ ትንሽ ገንዘብ ተከፍሎ በረዥም ግዜ ክፍያ እንዲከፍሉ ያደርግ ነበር።እንዲህ አይነቱ ነገር ሊበረታታ የሚገባው ነው።አሁንም ቢቀጥል እኛን ቢያበረታታ ትልቅ ስራ እንሰራለን።
መንግስት ለግንባታ የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎችም ላይ ማበረታቻ ያደርግ ነበር።አሁንም ማሽነሪዎች የሚገቡት ከቀረጥ ነጻ ነው።መቶ ፐርሰንት የመክፈል አቅም የለም።ያኔ 15 በመቶ 20 በመቶ አስከፍሎ ያመጣና በረዥም ጊዜ እንዲከፍሉ ያደርግ ነበር።ይሄ ለዘርፉ እድገት እጅግ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ማበረታቻውን በተለያየ መልኩ ሊቀጥል ይገባዋል ብዬ አምናለሁ።ዘርፉ ከባድና በጣም አስቸጋሪም ስለሆነ የግድ የመንግስት ማበረታቻ ያስፈልገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የተሰሩት አብዛኛዎቹ የኮንስትራክሽን ስራዎች ጥራት ይጎድላቸዋል፤ ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም የሚሉ ባለሙያዎች አሉ።እርስዎ ምን ይላሉ ?
ኢንጂነር ዳዊት፡- በመጀመሪያ ደረጃ አንዳንዶች ስራዎች ሲሰሩ የነበሩት አዋጭ ነው አይደለም ከሚለው የፊዚቢሊቲ ጥናት ተነስቶ በደምብ ተጠንቶበት አይደለም።ለምሳሌ አሁን የቤቶች ልማትን ብትመለከት አዲስ አበባ ውስጥ ኮንዶሚኒየም የተሰራው አዋጭ ትክክልም ሊሆን ይችላል።ግን ርቀህ ሄደህ ገጠር ውስጥ ብትሰራ ተጠቃሚው በስፋት ከሌለ አዋጪ ሊሆን አይችልም። አንደኛ ነገር ስራው ራሱ የሚጀመረው ዲዛይኑ አልቆ አይደለም።እስከመጨረሻው ድረስ የማያልቁ አንዳንድ ዲዛይኖች አሉ። እየሰራህ የሚጎትቱህ ማለት ነው።
ሁለተኛው ነገር የተቀናጀ ነገር መኖር አለበት። ለውጥና እድገት የሚመጣው እየተሳሰቡ እየተግባቡ እየተናበቡ ሲሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡–ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።
ኢንጂነር ዳዊት እምሩ፡-እኔም በጣም አመሰግና ለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
ወንድወሰን መኮንን