ጠባቂ አልባ ሱቆች

በእኩለ ሌሊት የሚቀመስ ነገር ለሻተ በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴዑል የሚገኙ ሱቆች በሮቻቸውን ክፍት አድርገው ይጠብቃሉ። እነዚህ ሱቆች 24 ሰዓት ነው የሚያገለግሉት። አንደኛው ሱቅ አይስ ክሪም ይሸጣል። የተለያዩ የአይስክሬም ዓይነቶችን የያዙ ማቀዝቀዣዎች ተደርድረዋል። ነገር ግን ሱቆችን የሚጠብቅም ሆነ ገንዘብ የሚቀበል ሰው የለም።

ሰዎች ወደ ሱቆቹ ገብተው የፈለጉትን ካነሱ በኋላ በታማኝነት ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ከፍለው ይወጣሉ። ከአይስ ክሬም ሱቅ በተጨማሪ የጽሕፈት አገልግሎት፣ የቤት እንስሳት ምግብ እንዲሁም ሱሺ የተባለውን ተወዳጅ የሆነ ምግብ የሚያቀርቡ ሱቆች አሉ።

ሁሉም አንድ ሠራተኛ የላቸውም። ሸማቹ ያሻውን አንስቶ ከመውጣቱ በፊት በማሽን ይከፍላል። በተጨናነቀው የከተማዋ ክፍል ሠራተኛ የሌላቸው መሸታ ቤቶችም አሉ። “እንዲህ ያለውን መጠጥ ቤት ለማስተዳደር ከ12 እስከ 15 ሰው ያስፈልገኛል። ነገር ግን ሁለት ሠራተኛ ብቻ ነው ያለኝ” ይላል ሱል 24 የተባለ መጠጥ ቤት ያለው ኪም ሱንግ-ሬ።

ኪም 24 ሰዓት የሚያገለግለው መጠጥ ቤት እንዳለ ሆኖ በጎን ሌላ ንግድ ያጧጥፏል። ከዚህ ቀደም እዚህ ገበያ ማዕከል ሌላ መጠጥ ቤት ነበረው። ነገር ግን ወጪ እና ገቢው አልመጣጠን ሲል ነው ሠራተኛ አልባ ‘ባር’ የከፈተው።

ላለፉት አስርት ዓመታት የኮሪያ የውልደት መጠን ማሽቆልቆሉ እና የሠራተኞች ክፍያ መጨመሩ እንደ ምክንያት ይቆጠራል። ደቡብ ኮሪያ በዓለማችን ዝቅተኛ የውልደት መጠን ካላቸው ሀገራት መካከል ናት። በአውሮፓውያኑ 2023 የውልደት መጠኑ 0 ነጥብ 73 ነበር። ነገር ግን ባለፈው ዓመት ወደ 0 ነጥብ 75 ከፍ ብሏል።

የሕዝብ ቁጥሩ የተመጣጠነ ሆኖ እንዲቀጥል የውልደት መጠኑ ወደ 2 ነጥብ 1 ከፍ ማለት አለበት። ደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲህ ያለ የውልደት መጠን ያየችው በአውሮፓውያኑ 1982 ነው። ይህ ማለት ለሥራ ወደ ገበያው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እጅጉን እየቀነሰ መጥቷል ማለት ነው። ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ የደቡብ ኮሪያ ዝቅተኛ ክፍያ በየዓመቱ ጭማሪ አሳይቷል።

እንደ ኪም ያሉ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ለሠራተኞቻቸው በሰዓት 7 ዶላር ይከፍላሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት አዲሱ ትውልድ በተለምዶ “3ዲ” የተባለውን ሥራ መሥራት አይፈልግም። ይህ ሥራ የሚያቆሽሽ፣ አደገኛ፣ ከባድ እና ብዙ የሚጠይቅ ነው ብሎ ያምናል።

እነዚህ ሥራዎች ፋብሪካዎችን፣ ግብርና እና የሸቀጥ ንግድ ሥራዎችን የሚመለከቱ ናቸው። እነዚህ ሥራዎች ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ መጥቷል።”ወጣቱ ትውልድ ከተማ መኖር ነው የሚሻው። የራሱን ሥራ መፍጠር እንጂ ተቀጣሪ ሆኖ መኖር አይፈልግም። አሊያም ደህና ደሞዝ የሚከፍል የቴክኖሎጂ ሥራን ይመርጣል” ይላሉ ቾ ጁንግ-ሁን።

ቾ የገዥው ፒፕልስ ፓርቲ አባል ሲሆኑ የትምህርት ቋሚ ኮሚቴ ውስጥም አሉበት። “እኔ እንደ ሌሎቹ ሕግ አውጪዎች አዲሱን ትውልድ መውቀስ አልፈልግም። የመረጠውን ነው የሚያደርገው። ቁጥሮች እንደሚያሳዩት በሚመጡት ዓመታት የሰው ኃይል እጥረት ይጠብቀናል። ከወዲሁ ውሱን የሆነውን የሰው ኃይል በጥንቃቄ ማከፋፈል አለብን” ይላሉ።

የኮሪያ ምጣኔ ሀብታዊ ጥናት ማዕከል እንደሚለው በሚቀጥሉት 20 ዓመታት 43 በመቶ ሥራዎች በማሽን ይተካሉ። ኩዎን ሚን-ጃይ ብራውኒ የተባለው የሠው አልባ ሱቆች አስተዳዳሪ የሆነው ድርጅት ኃላፊ ነው። ኩባንያውን ያቋቋመው ኮቪድ ማብቃት ሲጀምር ገደማ ነው። “ሠራተኛ አልባ የሆኑ የልብስ ማጠቢያ፣ አይስ ክሬም፣ ሸቀጣ ሸቀጥ፣ ካፌ እና ኤሌክትሮኒክስ ሲጋራ ሱቆችን እናስተዳድራለን” ሲሉ ይናገራሉ።

ምንም እንኳ ሱቆቹ ሠራተኛ አልባ ቢሆኑም ዕቃዎች ሲያልቁ መተካት፣ ማፅዳት እና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቃል። የኩባዎችን ኩባንያ እኒህን ሥራዎች ያከናውናል።”ይህንን ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች አሉን።

ደቡብ ኮሪያ በጣም ጥቂት የስርቆት ወንጀል ከሚፈጸምባቸው ሀገራት መካከል ናት። ለዚህም ነው ሰው አልባ ሱቆች ስኬታማ የሆኑት። “አንዳንድ ሰዎች ሳይከፍሉ ረስተው ይወጣሉ። ነገር ግን በኋላ ደውለው ይከፍሉኛል። ስለ ሌሎች ሱቆች ባላውቅም ወጣት ደንበኞች ዋሌታቸውን እና ስልካቸውን ጠረጴዛ ላይ ትተው ነው የሚንቀሳቀሱት” ይላል ኪም።

ነገር ግን በስርቆት ምክንያት ኪሳራ ሊመጣ እንደሚችል አይክድም። ቢሆንም ስርቆት የተለመደ ስላልሆነ የሚያሰጋ አይደለም ብሏል።

ሮቦት ማሠማራት ብዙ ገንዘብ እና ቦታ ይጠይቃል። ለዚህ ነው ኪም ሰው አልባ አሊያም አውቶሜሽን የተሰኘውን መንገድ የመረጥኩት ይላል።

በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ብዙ ሱቆች ሰው አልባ መሆን ጀመሩ። በዚህም ለሠራተኞች የሚከፍሉት ገንዘብ መቆጠብ ሲችሉ በወረርሽኙ ወቅት የነበረውን አካላዊ መራራቅም መጠበቃቸው የሚታወስ መሆኑን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You