በመዲናዋ ከ75 በመቶ በላይ ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነጻ ሆኑ

አዲስ አበባ ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከ75 በመቶ በላይ ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነጻ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ የዓለም ትንባሆ የማይጨስበት ቀንን በማስመልከት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲደረግ እንደተናገሩት፤ ባለሥልጣኑ ከተማዋን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ ኢኒሼቲቭ ሲያቋቋም የሕግ ተገዢነት ከ40 በመቶ በታች ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከ75 በመቶ በላይ ተቋማት ከትምባሆ ጭስ ነፃ ናቸው። ይህም የሕግ ተገዢነቱ ከ75 በመቶ በላይ መድረሱን ያሳያል ብለዋል።

እስከ አሁን በተከናወኑ የግንዛቤ ፈጠራና የቁጥጥር ሥራዎች የመጡ ተስፋ ሰጪ ለውጦች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በትምባሆ ጎጂነት እና ቁጥጥር ዙሪያ ከተማ አቀፍ የጋራ አጀንዳ መፈጠር መቻሉንም ተናግረዋል። በዚህም በትምባሆ ቁጥጥር ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተደራሽነት ማስፋፋትና ተባባሪ አካላት ማበራከት መቻሉን አመልክተዋል።

የትምህርት ማህበረሰቡ ግንዛቤው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱም ከትምባሆ ጭስ ነፃ ትውልድ እና የትምህርት ተቋማት ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት ማስመዝገቡንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትራንስፖርትና በታክሲ መጫኛ ቦታዎች እንዲሁም በሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ አመልክተው፤ አጠቃላይ በአዋጅ 1112/2011 የተቀመጡ ክልከላዎች ለህብረተሰቡ ከማስገንዘብ አኳያ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

አሁንም ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከልም በሚፈለገው ደረጃ እና የችግሩ ውስብስብነት በሚመጥን መልኩ ጠንካራ ቅንጅታዊና ተቋማዊ አሠራር ያለመዘርጋቱ፤ የትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ግብረ ኃይል በሁሉም የአስተዳደር እርከን አጀንዳ በማድረግ ተፈጻሚ እያደረገ አለመሄዱ፤ በአዋጅ 1112/2011 የተቀመጡ ክልከላዎች ወጥ በሆነ መንገድ አለመተግበራቸው እና ተጠያቂነቱ ጠንካራ አለመሆን፤ የቁጥጥር ሥራው በቀን እና በማታ ወጥ በሆነ መልኩ እና በተጠናከረ መልኩ ያለማስኬድ፤ ከትምባሆ አቅርቦትና ፍጆታ እንደዚሁም የሚያስከትለው ጉዳት ጋር ተያይዞ በከተማ ደረጃ በቂ ጥናቶች ያለመኖራቸው፤ የተወረሱ ሕገወጥ የትንባሆ ምርቶች ማስወገጃ ቦታ አለመኖር፤ የምሽት ቤቶች/መዝናኛ ቤቶች መስፋፋትና የቁጥጥር ሥራው በዚሁ ልክ ጠንካራ አለመሆኑ እንዲሁም የሕገወጥ የትምባሆ ምርት/ኢ-መደበኛ ንግድ መስፋፋት እንዲሁም በተለያየ ደረጃና ዓይነት የሚገለጽ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ-ገብነት ለአብነት የሚጠቀሱ ውስንነቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነፃ የሆነች ከተማ ለማድረግ የያዘውን የተቀደሰና ትውልድ አድን ፕሮግራምና እቅድ እንዲሳካ የከተማው ነዋሪ ከጎናችን በመሰለፍ ትውልዳዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You