በበይነ መረብ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት

ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ የ12ኛ ክፍል የዓመቱ ሁለተኛ አጋማሽ ሞዴል ፈተና እየተሰጠ ይገኛል። ይሄ ፈተና ሲሰጥባቸው ከነበሩት መካከል አንጋፋው እና እንደ ሀገር የመጀመሪያ የሆነው የዳግማዊ ምኒሊክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይጠቀሳል። በትምህርት ቤቱ ፈተናው የሚዘልቀው እስከ ግንቦት 21/2017 እንደሆነ የትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር አበባው አበበ አንስተውልናል።

የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንዲሁም የእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ ፈተናው እስከ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 25/2017 እንደሚዘልቅ ነግረውናል። በሁለት መልኩ ስለሚሰጠው ስለ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓትና እያደረጉት ያለውን ዝግጅትም ገልፀውልናል። ከዚህ ከሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ጋር በተያያዘ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር አምና እና ዘንድሮ ለየት ያለ አሠራር መዘርጋቱ ይታወሳል። አሠራሩ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን የቃኘ ሲሆን ፈተናውን በበይነ- መረብ እና በወረቀት ጎን ለጎን ከመስጠት ጋር ይሰናሰላል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እየታተመ ለሚወጣው ዓመታዊ መጽሔት እንደገለፁት እንደ ሀገር ትምህርት ሚኒስቴር ወደ በይነ መረብ እና በወረቀት ፈተና አሰጣጥ አሠራር ሥርዓት ትግበራ የገባው ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ሚኒስትሩ እንዳሉት በ2016 የ12ኛ ክፍል ፈተና በበይነ-መረብ እና በወረቀት ነበር፤ ጎን ለጎን ተሰጥቶ የነበረው። ዘንድሮም ፈተናው እንዲሁ በበይነ-መረብ እና በወረቀት ይሰጣል። እንዲህ ዓይነቱ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ከአምና ተሞክሮ እንደታየው በፈተና አሰጣጥ ዙሪያ የትምህርት ዘርፉን ሲገጥሙት የነበረውን ችግር በዘላቂነት መፍታት አስችሏል። በቀጣይም የፈተና አሰጣጡ ከወረቀት ተላቆ ሙሉ በሙሉ ወደ በይነ-መርብ አሰጣጥ ሥርዓት ትግበራ ሲገባ ችግሩን ከአሁኑ በተሻለ በመቅረፍ አሠራሩን የበለጠ ዘላቂ ያደርገዋል ተብሎ የሚታመን መሆኑን ሚኒስትሩ ለዓመታዊ መጽሔት አዘጋጆቹ አስረድተዋል።

ከዚሁ ከ12ኛ ክፍል ፈተና አሠጣጥ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ አበራ (ዶ/ር) ዘንድሮም በበይነ- መረብ እና በወረቀት እንደሚሰጥ በዚሁ ገጽ መግለፃቸውን ማስነበባችን ይታወሳል። ዋና ዳይሬክተሩ ዘንድሮ ፈተናውን እንደ ሀገር ከ608 ሺ በላይ ተማሪዎች በዚሁ በፈተና አሰጣጥ ሥርዓት መልክ እንደሚወስዱትም ጠቅሰዋል።

ካለፈው ግንቦት 19 ጀምሮ እነዚህ ተማሪዎች የሙከራ ፈተና እየወሰዱ ይገኛሉ። በተለይ በበይነ- መረብ ከሚሰጠው ፈተና አንፃር በሙከራ ፈተናው ወቅት እና ቀደም ብሎ በየትምህርት ቤቶቻቸው ባሉ በአይሲቲ ማዕከላት አማካኝነት ልምምድ ሲያደርጉ ስለመቆየታቸው በርካታ በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አንስተዋል።

የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ ተማሪ ሀና ባይሳ አንዷ ነች። ተማሪዋን ያገኘናት ግንቦት 19/2017 ዓ.ም የሙከራ ፈተና (ሞዴል ወስዳ ) ከመፈተኛ ክፍል ስትወጣ ነው። እሷ እንደነገረችን በዕለቱ የወሰደችው ፈተና ጠዋት እንግሊዝ ከሰዓት ደግሞ ሂሳብ ሲሆን፤ ይሄም ዋናውን ፈተና ለመሥራት እንደሚረዳቸው ታምኖበት የተፈተኑት ነው። እሷን ጨምሮ በ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናው ለሁለተኛ ጊዜ በኦን ላይን በመሰጠቱ ምክንያት የበይነ-መረብ ሥርዓት (የኮምፒውተር ሲስተም) አጠቃቀም ችግር እንዳይገጥማቸው በቂ ልምምድ ሲያደርጉ ስለመቆየታቸውም አስታውሳለች። ፈተናውን የወሰዱት በወረቀት መሆኑን የጠቀሰችው ተማሪዋ ሆኖም በበይነ-መረብ ለሚወስዱት ለዋናው ፈተና በትምህርት ቤታቸው አይሲቲ ክፍል ልምምድ ሲያደርጉ ስለ መቆየታቸውም ተናግራለች።

‹‹እኔ የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ ነኝ›› የምትለው ተማሪዋ አብዛኛው ተማሪም የዘመናዊ ስልክ እንዲሁም እንደ ፌስ ቡክ፤ ቴሌግራም እና ዋትስ አፕ ያሉ ፈተናው ከሚሰጥበት ቴክኖሎጂ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቃሚ በመሆኑ በበይነ – መረብ አጠቃቀም ዙሪያ ልምምድ ባያደርግም ፈተናውን የሚሠራበት እውቀት እንደማይቸግረውም ታስረዳለች። ፈተናው በበይነ- መረብ መሰጠቱ የቀረውን ሰዓት ሳያቋርጥ ከማመልከት እና ተፈታኞችን ከማንቃት ጀምሮ ጊዜ ከመቆጠብ አኳያም ለተፈታኞች ተመራጭ ነው ብላ ማሰቧንም ተማሪዋ አጋርታናለች። ዋናውን ፈተና የሚወስዱትም አምስት ኪሎ በሚገኘው አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ እንደተነገራቸውም ገልጻልናለች። ለፈተናው መግቢያ የይለፍ ቃል እና ስም (ፓስ ወርድና ዩዜር ኔም) የተሰጣት መሆኑን፤ ይሄም የሙከራ ፈተናውን ከመሥራት ጀምሮ የጥናት ዝግጅት ማድረግ እንዳስቻላት ነው የተናገረችው።

ሌላው ያነጋገርኩት ተማሪ ደግሞ ፍሬው ሚሊዮን የዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ የማኅበራዊ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ተማሪውን ያገኘነው በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ የሙከራው ፈተና በተጀመረበት ግንቦት 19/2017 ዓ.ም በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የወሰደውን የእንግሊዝኛ የሙከራ ፈተና (ሞዴል ኤግዛም) ተፈትኖ በወጣበት ወቅት ነው። በዕለቱ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ሁለተኛውን የሂሳብ ፈተና ስለሚወስድ ብዙ ሳይርቅ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በጊቢው እያጠና ለመቆየት ወስኗል። እኛም በዚሁ አጋጣሚ ያገኘነው መሆኑን ያነሳው ተማሪው በሙከራ ፈተናው የነበረው ቁጥጥር እና ክትትል እንዲሁም አቀማመጥ ኩረጃን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ያለው መሆኑን ገልጾልናል። ትምህርት ቤቱ በበይነ መረብ አምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ለሚፈተኑት ፈተና ከወዲሁ በደንብ ልምድ እንዲያገኙ ማድረጉንም ነግሮናል። እሱ በበኩሉ ዘመናዊ ስልክ ያለው እና የዋትስ አፕ፤ የቴሌግራም እንዲሁም የፌስ ቡክ የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ቢሆንም አውቀዋለሁ ብሎ ዝም ሳይል ልምምዱን በአግባቡ እያደረገ መገኘቱንም አንስቷል። በግሉ ፈተናው ሀገር አቀፍ እንደመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ በማንበብ ዝግጅት ለማድረግ ይረዳሉ ያላቸውን በማካተት ሲያነብ መቆየቱን እና አሁንም በዚህ መልኩ የሚያደርገውን ጥናት መቀጠሉን ነግሮናል።

ሌላው ተማሪ ምስጋና ሄኖክ የቅድስት ስላሴ ካቴድራል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ተማሪዋ ቀደም ባሉት የመጀመሪያ ደረጃም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ ክፍሎች ጎበዝ የደረጃ ተማሪም እንደሆነች ነግራናለች። ከወር በኋላ የምትወስደውን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተናም በዚሁ ባልቀዘቀዘ ብቃቷ በጥሩ ሁኔታ ሰርታ የማለፍ ዕቅድ ሰንቃ ዝግጅት እያደረገች ስለመሆኗም ገልፃልናለች። ዋናው ፈተና በበይነ-መረብ እንደሚሰጥ የተነገራቸው መሆኑንም አንስታልናለች። ለዚሁ ፈተና የሚረዳ የበይነ-መረብ አጠቃቀም ቴክኖሎጂን አስመልክቶም በትምህርት ቤታቸው በአይሲቲ ማዕከል አማካኝነት ልምምድ ሲያደርጉ ስለመቆየታቸው ነግራናለች። እኛ አግኝተን ባነጋገርናት ዕለት ግንቦት 21/2017 ዓ.ም በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት በይነ-መረብ አጠቃቀሙ ዙሪያ ልምምድ ማድረጋቸውንም ገልፃልናለች። የ12ኛ ክፍል የኦን ላይን ፈተና ሂደት የሚያሳይ አስተማሪ ቪዲዮ ተለቋል፤ ተፈታኝ ተማሪዎች ይሄን ቪዲዮ ማየት ይችላሉም ብላለች። ‹‹ይሄ የበይነ መረብ-ፈተና አሰጣጥ ዘዴ ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር ተማሪውን አብሮ የሚያራመድ ዲጂታል ለመሆን እየሠራች ላለችው ሀገሪቱም ጠቃሚ ነው›› የምትለው ተማሪዋ ለአስኮራጅም ሆነ ለኮራጅ አመቺ ባለመሆኑ ኩረጃን በመቀነስ ረገድም አስተዋጾ የጎላ ስለመሆኑ ነው ያነሳችው። ማንበብ፤ በጥናት መዘጋጀት እንጂ ተማሪ መፍራት አይጠበቅበትም ስትልም መክራለች።

ዳግም አለማየሁ የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ዘንድሮ በበይነ መረብ ለመውሰድ መዘጋጀቱን እና ፈተናውን ሲሠሩ የሚቀራቸውን ሰዓት ማየታቸው በተለይ የሂሳብ ፈተናን አስበው ለመሥራት ስጋት ሊሆንባቸው ስለመቻሉ ያነሳል። ከዚህ በተረፈ ፈተናው በበይነ መረብ መሰጠቱን እንደወደደው እና በዚሁ ለመፈተን የሚያስችል ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱን በተጨማሪም፤ የፈተናውን ቀን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ነግሮናል።

ከጓደኞቿ ጋር ከአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ስትወጣ ያገኘናት ደግሞ የእንጦጦ አምባ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ሰላም በሪሁን ናት። መጪውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ካለፈች የሕክምና ዶክተር የመሆን ምኞት በውስጧ በመሰነቋ ይሄንኑ ለማሳካት ከወዲሁ ለፈተናው ራሷን እያዘጋጀች ስለመገኘቷ ትናገራለች። እንደ እሷ አብርሆት ቤተ መጽሐፍት ከጓደኞቿ ጋር ተቀጣጥረው የተገናኙት ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ስለሆኑ እና ፈተናውን ትወስዳላችሁ የተባሉት በበይነ-መረብ በመሆኑ በቤተ መጽሐፍቱ ፈተናውን ለመሥራት የሚያስችላቸው ልምምድ ለማድረግ ነው። ተማሪ ሠላም ልምምዱ በኦን ላይን ስልጠና የታገዘ መሆኑን ትናገራለች። በስልጠናው ካገኘችውም ሆነ ቀደም ሲል ዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ እንደ መሆኗ ከነበራት ተሞክሮ ፤ በተጨማሪም አሁን ላይ አብዛኛው ተማሪ ዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ በመሆኑ ፈተናውን በበይነ-መረብ መፈተን አይከብድም እና አያስፈራም። የአሰራር ደረጃዎቹም ቢሆኑ እጅግ ቀላል ናቸው። ይሄም ውስጣዊ የራስ መተማመን ስሜት ፈጥሮባታል።

ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 25/2017 ያሉትን ሁለት የሙከራ (ሞዴል) ፈተናዎች በበይነ -መረብ ትፈተናላችሁ ስለመባላቸው እና ይሄም የሙከራ ፈተናውን በበይነ መረብ- በመፈተን ልምድ የማግኘት ተሞክሮ፤ ዋናውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ያለምንም ችግር ለመሥራት ይረዳናል ብላ እንደምታስብ አንስታለች።

በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርእሰ መምህር አበባው አበበ እንደሚናገሩት በትምህርት ቤቱ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን የሚወስዱት የቀኑ ክፍለ ጊዜ 320 ሴቶች እንዲሁም 366 ወንድ በድምሩ 686 ተማሪዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በማታው ክፍለ ጊዜ የሚማሩ 36 ወንድ እንዲሁም 23 ሴቶች በድምሩ ከቀን ተማሪዎቹ ጋር ሲዳመር 745 የማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ለፈተናው ይቀመጣሉ ።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ እንደሚናገሩት፤ በትምህርት ሚኒስቴር እና በፈተናዎች ምዘና አገልግሎት አማካኝነት ሁሉም የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በበይነ-መረብ በሁለት፤ በሁለት ዙር አምስት ኪሎ በሚገኘው በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንደሚፈተኑ ተነግሯቸዋል። በመሆኑም በትምህርት ቤቱ ባሉ 100 ኮምፒውተሮች አማካኝነት ተማሪዎቻቸው ዋናውን ፈተና በበይነ – መረብ ለመፈተን የሚያስችላቸውን ልምምድ እንዲያደርጉ አድርገዋል። በየኮምፒውተሮቹ «ሴፍ ኤግዛም ብሮውዘር » መጫኑንም አንስተዋል። ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት አካባቢ የኮሪደር ልማት እየተከናወነበት በመሆኑ ከኢንተርኔት ኔትወርክ እና መብራት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ዋይፋይ ተጠቅመው መለማመድ የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ ግብዓት ግዢ መፈፀሙንም አብራርተዋል።

ፈተናው በበይነ መረብ በመሰጠቱ ፍርሃት ያለባቸው ጥቂት ተማሪዎች መኖራቸውን ያነሱት አቶ አበባው የተማሪዎቹን ፍርሃት ለመቅረፍ የአይስቲ ባለሙያዎች በየክፍሉ በመዞር እንዲበረታቱ ግንዛቤ ማስጨበጫ ምክርና ተደጋጋሚ ስልጠና መስጠታቸውንም ያስረዳሉ። በኮምፒውተር (በበይነ- መረብ) አጠቃቀም ክህሎት አምና በኦን ላይን ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ ያለፉ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አበባው ፤በኮምፒውተር እጥረት ምክንያት ፈተናውን የማይሠራ ተፈታኝ እንደማይኖር እምነቴ ነውም ብለዋል። በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 5ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች 50 በመቶና በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ይታወሳል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You