የሴቶች ቦርሳ ፋሽን

ቦርሳ ከመታወቁ አስቀድሞ እናቶቻችን መቀነትን ለገንዘብ መያዣነት ይጠቀሙበት ነበር። መቀነት ወገብን ከመደገፍ በተጨማሪ ለገንዘብ መያዣነት ያገለግላል። በአሁኑ ጊዜም አንዳንድ እናቶች ገንዘብን በመቀነታቸው መያዛቸው የተለመደ ነው። ቀስ በቀስ በሂደት ገንዘብን በመሃረብ በመቋጠር ብብታቸው ስር ሽጉጥ ያደርጉ ነበር። እየቆየም ትንንሽ የእጅ ቦርሳዎች እየታወቁ መምጣታቸው ቦርሳን ለገንዘበ መያዣን መጠቀም ተጀመረ። የመጀመሪያዎቹ የእጅ ቦርሳዎች በጣም ትንንሽና በእጅ ጨበጥ ተደርገው የሚያዙ ናቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቦርሳ ጥቅም መታወቅ ጀመረ። በእጅ ጨበጥ ተደርጋ የምትያዝ ቦርሳ መጠኗ ከፍ እያለ ቁመቷ ረዘም ብሎ አፏ ጠበብ ባለው ተተካች።

ይህ ቦርሳ ከንፁህ ቆዳ የተሠራ ሲሆን ለየት ያለና ማራኪ ዲዛይን ነበረው። የቦርሳው መዝጊያ ሸምቀቆ ሲሆን በቀላሉ የማይከፈት ስለሆነ ለጥንቃቄ አመቺ ነው። ይህ ቦርሳ በክንድ ላይ ተንጠልጥሎ ሊያዝ የሚችል ነው። ይህ ቦርሳ ‹‹ጮጮ›› በመባል ይታወቃል። በተለያዩ እንደ ጨሌና ወርቀዘቦዎች ባሉ ጌጦች በማስጌጥ ልዩ ውበት በማላበስ ይሠሩ ነበር። እነዚህ ቦርሳዎች አሁን ላሉ ቦርሳዎች መፈጠር መሰረት ሆነዋል።

ቀስ በቀስ ቦርሳ ከገንዘበ መያዣነት ይልቅ በፋሽንነት ይደረግ ጀመር። የቦርሳ አሠራርም እድገትም ሆነ ጥበብ መታየት ጀመረ። የቦርሳ ፋሽን በየጊዜው የሚለዋወጥ ሲሆን ከወቅቱ፣ ከቦታውና ከአለባበስ ጋር የሚሄዱ ቦርሳዎች የጊዜው ፋሽን ይባላሉ።

የዘወትር ቦርሳ

ይህ ቦርሳ በሥራም ሆነ በተለያየ ቦታ በየቀኑ የሚያዝ ነው። ለዚህም ደግሞ ጠንካራና ምቾት ያለው እንዲሁም ማንገቻው ሰፋ ያለና የማይጎረብጥ ሊሆን ይገባዋል። ለጥንካሬ ከቆዳ ወይም ከሰው ሰራሽ ቆዳ ቢሠራ ይመረጣል።

አንዳንድ የቢሮ ሴቶች የምሳቃቸውን በቦርሳቸው ሲይዙ ይስተዋላል። ይህ ቦርሳ ቶሎ እንዲበጠስ እና ቅርፅ እንዲያወጣ ያደርገዋል። የምሣ ዕቃን በሌላ ቦርሳ መያዝ ለቦርሳ እድሜ መርዘምና ውበት ተመራጭ ነው።

የልጃገረዶች ቦርሳ ከ10-18 ዓመት ዕድሜ ክልል ላሉ ልጆች የሚሆን ቦርሳ ነው። ይህ ቦርሳ አነስ ብሎ የተወሰነ ዕቃ ብቻ መያዝ የሚችል ሲሆን ማንገቻው ረጅም ቢሆን ወይም በጀርባ ሊታዘል የሚችል አነስተኛ ቦርሳ ነው።

የግብዣ ቦርሳ

የግብዣ ቦርሳ ለግብዣና ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚደረግ ነው። ብዙውን ጊዜ ጌጥ የበዛባቸው እና ከተለያዩ ጨሌዎች፣ ዶቃዎች ፣ መስታውቶች ፣ ከሐር ጨርቆች እና ከቀላል ብረቶች የሚሠሩ ናቸው። በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ በመሆናቸው ውበታቸው ጎልቶ ይታያል። እነዚህ ቦርሳዎች በሚደረጉበት ጊዜ ለሚለበሰው ልብስና ጫማ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ከልብስና ከጫማ ቀለም ጋር አብሮ የሚሄድ ቦርሳም መምረጥ ያስፈልጋል። ከልብስ ወይም ከጫማ ቀለም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቦርሳ ካልተገኘ ጥቁር ቦርሳ መጠቀም ይመረጣል።

ይህም ጥቁር ቦርሳ ከማንኛውም ቀለም ጋር የሚሄድ ስለሆነ ነው። በፊት በፊት ሙሽሮች በሰርጋቸው ዕለት ነጭ ቦርሳ እንደ ፋሽን ይይዙ ነበር። የሙሽራ ቦርሳዎች በቆዳ፣ በሐር ፣ በነጭ ጨሌ የሚሠሩ ነበሩ። መጠኑን አነስ ብሎ ክንድ ላይ ይንጠለጠል ነበር። ቦርሳ ለሙሽሪት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ በጥሎሽ ላይ እንኳ ካልታየ ቅሬታ ይፈጥራል።

የዕረፍት ቀን ቦርሳ

የዕረፍት ቀን ቦርሳ በመባል የሚታወቁት ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተለመዱ መጥተዋል። ከሰኞ እስከ አርብ የምንይዘው ቦርሳም ለማሳረፍ ይጠቅማሉ። አሠራራቸውም ብዙውን ጊዜ ቀለል ያለና ክብደት የሌለው ነው፡፤ በዕረፍት ቀን ከሚለበሱ ጅንስና ቱታ ጋር አብረው ሲደረቡ ውበታቸው ጎልቶ ይታያል። ከጅንስ፣ ከሸራ፣ ከወፍራም ፕላስቲክና ከሳጠራ የሚሠሩ ሲሆን ብዙ ጊዜ ሰፋ ብለው ረዘም ያሉ ናቸው። ቀለማቸውም በአብዛኛው ልሙጥ ነው።

ፋሽንና ውበት

እነዚህ ቦርሳዎች ከሽርሽር ቦርሳዎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። በሳምንቱ መጨረሻ ዋና የምናዘወትር ከሆነ ቦርሳችን ውስጡ ፕላስቲክ ሊኖረው ይገባል። ምክንያቱም እርጥበት ያላቸው ነገሮች ለማስቀመጥ ይረዳናል። ቦርሳችን በእርጥበት እንዳይበላሽ ያደርጋል የጉዞ ቦርሳ ከሽርሽር ቦርሳ የሚመሳሰል ሲሆን በመጠን ከፍ ያለ ነው። የተለያዩ ዕቃዎችንም ለመያዝ የተለያዩ ኪሶች ሊኖሩት ይገባል። በጉዞ በሚቆዩበት ጥቂት ቀናት የሚቋጥሩትን ልብሶች የሚይዝ መሆን አለበት። ጠንከር ያለ እና ረጅም ማንገቻም ሊኖረው ያስፈልጋል።

ቦርሳው በጀርባ የሚታዘል ቢሆን ደግሞ ረጅም ማንገቻ ሊኖረው ያስፈልጋል። ጠቆር ያሉ ቀለማቸው በቶሎ አቧራ የማይቆሽሹ ተመራጭ ናቸው።

የሜካፕ ቦርሳ

ይህ ቦርሳ የተለያዩ መዋቢያ እቃዎችን ለመያዣነት የሚያገለግል ነው። ሜካፕ ቦርሳ ውስጥ እንዳይደፋና ቦርሳ እንዳይበላሽ እነዚህ ቦርሳዎች ይረዳሉ። ይህ ቦርሳ ከሐር ጨርቅና ከስስ ቆዳ ይሰራል። የሜካፕ ቦርሳ አነስ ያለ ሲሆን ቢቆሽሽ እንኳን በቀላሉ ሊታጠብ የሚችል ነው። የሜካፕ ቦርሳ የሌላት ሴት ገበሩ በኩል ፣ በሊፒስቲክ ፣ በፓውደር በተለያዩ ሜካፖች መበላሸቱ የማይቀር ነው። እንዲሁም ራስን ለማስዋብ የሚወስደውን ጊዜ ይቆጥባል። ስለዚህ ማንኛዋም ሴት የቦርሳ ደህንት ተጠብቆ እንዲቆይ የሜካፕ ቦርሳን ልትጠቀም ይገባል።

ልክ እንደ አለባበስ ሁሉ የምንይዘው ቦርሳ ተስማሚያችን መሆኑን በቅድሚያ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። አጭር ሴት ረጅም ማንገቻ ያለው ቦርሳ ልትይዝ አይገባትም። የቦርሳው ርዝመት ከወገቧ ማለፍ አይኖርበትም። አጭር ማንገቻ ያላቸው ቦርሳዎች ልትመርጥ ይገባል፤ የቦርሳው ስፋትም ሆነ ርዝመት መጠነኛ መሆን አለበት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You