አዲሱ የጋዛ የተኩስ አቁም እቅድና የሃማስ ጥያቄ

የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ፣ አሜሪካ ያቀረበችውን አዲሱን የጋዛን የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት እንደማይቀበለው አስታውቋል። አንድ የቡድኑ ከፍተኛ አመራር እንደተናገሩት፣ በአሜሪካ የቀረበው እቅድ በጋዛ ያለው ግድያና ረሃብ እንዲቀጥል ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ተናግረዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን ባለሥልጣናት ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ፣ አሜሪካ ያቀረበችው የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ የስምምነት ሃሳብ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እቅድን የያዘ ሲሆን፣ እስራኤል በእስር ላይ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን እንድትፈታ ሃማስ በሕይወት ያሉ አስር ታጋቾችን እና የ 18 ሟቾችን አስከሬን በሁለት ዙር እንዲያስረክብ ይጠይቃል።

የዋይት ሃውስ የፕሬስ ክፍል ኃላፊ ካሮሊን ሌቪት፣ እስራኤል ስምምነቱን እንደተቀበለች እንዲሁም የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ሰነዱን ለሃማስ እንዳቀረቡና አሜሪካ መደበኛ ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ ተናግረው ነበር። ሌቪት በመግለጫቸው፣ ‹‹ልዩ መልዕክተኛ ዊትኮፍ እስራኤል የደገፈችውን የተኩስ አቁም ሃሳብ ለሃማስ ማቅረባቸውን አረጋግጣለሁ። ይህ ሃሳብ ወደ ሃማስ ከመላኩ በፊት እስራኤል ስምምነቷን ገልጻለች። ውይይቶች መቀጠላቸውንም አረጋግጣለሁ፤ እናም በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረግ ተስፋ እናደርጋለን፤ ስለዚህ ታጋቾቹን በሙሉ ወደ ቤታቸው እንመልሳለን›› ሲሉ ተናግረዋል።

የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባሉ ባሰም ናኢም ግን የስምምነቱ እቅድ ጦርነቱን ማቆምን ጨምሮ የፍልስጤማውያንን ዋና ዋና ፍላጎቶች እንደማያሟላ ተናግረዋል። ‹‹የስምምነት ሃሳቡ አሁን ባለው ይዘቱ በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጭፍጨፋና የተከሰተውን ረሃብ የሚያስቀጥል ብቻ ነው። የድርጅታችን አመራር የስምምነቱን ሃሳቦች በሙሉ ብሔራዊ ኃላፊነትና ስሜት እየተመለከታቸው ነው›› በማለት ቡድኑ እቅዱን በጥልቀት እየተመለከተው እንደሆነ ገልፀዋል። ሃማስ የመጨረሻ ምላሹን ዛሬ እንደሚያሳውቅም ‹ሮይተርስ› ለጉዳዩ ቅርበት ካለው የቡድኑ ሰው መስማቱን ገልጿል።

የተኩስ አቁምና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ዝርዝር ይፋ ባይሆንም፣ የሃማስ ከፍተኛ አመራሩ ሳሚ አቡ ዙህሪ ለሮይተርስ እንደተናገሩት፣ የስምምነቱ እቅድ እስራኤል ጦርነቱን እንደምታቆም፣ ሠራዊቷንም ከጋዛ እንደምታስወጣና ርዳታ ያለገደብ እንዲገባ እንደምትፈቅድ የሚገልፅና ዋስትና የሚሰጥ ማረጋገጫን አላካተተም።

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ የስምምነት ሃሳቡ የ60 ቀናት ተኩስ አቁምን ጨምሮ በሕይወት ያሉና የሞቱ 28 እስራኤላውያን ታጋቾች በመጀመሪያው ሳምንት እንዲለቀቁ ይጠይቃል። ሃማስ በሕይወት ያሉትን ታጋቾችና የሞቱ እስራኤላውያንን አስከሬን ሲያስረክብ እስራኤል ደግሞ አንድ ሺህ 236 ፍልስጤማውያን እስረኞችንና የ180 ሟቾችን አስክሬን ታስረክባለች። ሃማስ ስምምነቱን በፈረመ ቅፅበት ርዳታ ወደ ጋዛ እንደሚገባም በስምምነቱ ላይ ስለመካተቱ የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

የእስራኤል መንግሥት ስለጉዳዩ የሰጠው ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የዊትኮፍን ጊዜያዊ የተኩ ማቆም እቅድ መቀበላቸውን ለታጋቾች ቤተሰቦች መናገራቸው ተዘግቧል። እስራኤላዊው የፖለቲካ ተንታኝ አኪቫ ኤልዳር፣ የእስራኤል በእቅዱ አስቀድማ መስማማቷ ያልተለመደ ነገር እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹እስራኤል ለመሰል ስምምነቶች ከሌላው ወገን አስቀድማ ይሁንታዋን መግለጿ ያልተለመደ ነገር ነው። ኔታንያሁ ይህን ያደረጉት ሃማስ ስምምነቱን እንደማይቀበል አስቀድመው ስለገመቱና ተኩስ ለማቆም ፍላጎት እንደሌለው በማስመሰል ጦርነቱን ለመቀጠል ስለፈለጉ ይሆናል›› ብለዋል።

ሃማስ ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ፣ ተደራዳሪዎቹ ከአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ጋር ባደረጉት ውይይት በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት አጠቃላይ ማሕቀፎችን እንደሚቀበልና ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ አስታውቆ ነበር። ‹‹ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ጠቅልሎ እንዲወጣ እና ሠብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዲገባ ከዊትኮፍ ጋር ተስማምተናል›› ብሎ ነበር። እንደቡድኑ መግለጫ፣ ስምምነቱ ተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ የጋዛን ጉዳዮች የሚከታተል ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚጠይቅ ሃሳብ እንደሚኖረው በዊትኮፍ ተገልጾለታል። ፕሬዚዳንት ትራምፕም በ60 ቀናት ውስጥ ተኩስ አቁም እንደሚሰፍንና የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንደሚወጣ በመልዕክተኛቸው በኩል ቃላቸውን እንደሰጡት ቡድኑ ገልፆ ነበር።

ሃማስ የአሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲሻሻል ጠይቆ 18 የሞቱ ታጋቾችን ጨምሮ በሕይወት ያሉ እስራኤላውያንን በመልቀቅ ፍልስጤማውያን እስረኞች እንደሚቀበል አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ስቲቭ ዊትኮፍ ሃማስ በመግለጫው ያሰራጨው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነ ገልጸዋል። ‹‹ሃማስ በመግለጫው ያነሳው የስምምነት ነጥብ በፍጹም ተቀባይነት የለውም›› በማለት እንዲህ ዓይነት የስምምነት ሃሳብ እንዳላቀረቡ ለሮይተርስ ተናግረዋል። ስማቸው ያልተገለጸ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ ሃማስ በመግለጫው ይፋ ያደረገው የስምምነት ይዘት የተሳሳተና የሚያበሳጭ እንደሆነ ገልፀዋል። አንድ እስራኤል ባለሥልጣንም ‹‹የሃማስ መግለጫ የሥነ ልቦና ጦርነትና ፕሮፓጋንዳ ነው›› ሲሉ ለ‹‹ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል›› ጋዜጣ (The Times of Israel) ተናግረዋል።

የሃማስ ከፍተኛ አመራር በኋላ እንደተናገሩት በስምምነቱ ላይ የተካተቱት ነጥቦች ቀደም ሲል በቡድኑ ተደራዳሪዎች እና በዊትኮፍ መካከል የተደረጉ ውይይቶችን የሚጻረሩ ናቸው። አመራሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ሃሳቡ ጊዜያዊው የእርቅ ስምምነት ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስለማምራቱ ዋስትና አይሰጥም። ባለፈው የተኩስ አቁም ወቅት በየቀኑ በመቶዎች በሚቆጠሩ የጭነት መኪኖች ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የፈቀደውን የሠብዓዊ ፕሮቶኮል መመለስን አላካተተም። ቢሆንም፣ ሃማስ ከአደራዳሪዎች ጋር ንግግሩን እንደሚቀጥል እና ምላሹን በጽሁፍ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈረንሳይ በእስራኤል ላይ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል አስጠንቅቃለች። እስራኤል ሠብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ካልፈቀደች ፈረንሳይ በእስራኤል ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናግረዋል። ሲንጋፖርን እየጎበኙ ያሉት ማክሮን ‹‹በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ለረሃብ አደጋ ተጋልጠው ሳለ፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዝም ብሎ ሊመለከት አይችልም። ሠብዓዊ ርዳታን በተመለከተ በቀጣዮቹ ቀናት ምንም ለውጥ የማናይ ከሆነ፣ በእስራኤል ላይ የጋራ አቋማችንን ማጠንከር ይገባናል›› ብለዋል። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የማክሮንን ሃሳብ ‹‹እውነታውን ያልተረዳ›› ብሎ አጣጥሎታል።

የማክሮን ማስጠንቀቂያ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ዘመቻ እንድታቆምና ሠብዓዊ ርዳታም እንዲገባ እንድትፈቅድ የሚሰማውን ዓለምአቀፍ ጥሪ የሚያጠናክር ነው ተብሏል። የበርካታ ሀገራትና ተቋማት መሪዎች እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም መጠየቃቸውን ቀጥለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ማክሮን ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። ማክሮን እስራኤል ጋዛን ለመቆጣጠርና ፍልስጤማውያንን ለማፈናቀል የያዘችውን እቅድ ካወገዙት ከኢንዶኔዢያው ፕሬዚዳንት ፕራቦው ሱቢያንቶ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ለእስራኤል ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ የፍልስጤም መንግሥት ምሥረታ የሞራል ግዴታና አስፈላጊ የፖለቲካ ተግባር ነው›› ብለዋል።

እስራኤል በአሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ አደራዳሪነት የተፈረመውና ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው የተኩስ አቁም አብቅቶ በመጋቢት ወር አጋማሽ ዳግመኛ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ እንዳሰበችው የቀሩትን እስራኤላውያን ታጋቾችን ማስለቀቅ አልቻለችም። ከእገታ የተለቀቀው ኢዳን አሌክሳደር የተባለው እስራኤላዊ-አሜሪካዊ ወታደር ብቻ ነው። ሃማስ ታጋቹን የለቀቀው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እያደረጉት ላለው ጥረት እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ገልጾ ነበር።

እስራኤል እና ሃማስ ተኩስ ለማቆም በየፊናቸው ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተራራቁ ሆነው ይታያሉ። እስራኤል ሃማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ ትፈልጋለች፤ ሃማስ በበኩሉ እስራኤል ጠቅልላ ከጋዛ እንድትወጣ ይፈልጋል። ይባስ ብሎም ከሦስት ሳምንታት በፊት የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ ጋዛን ለመቆጣጠር የቀረበውን ዕቅድ አፅድቋል። እቅዱ እስራኤል የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ‹‹ሃማስ›› መነኸሪያ በሆነችው በጋዛ ሰርጥ አዲስና የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ የሚያስችላት ሲሆን፣ በእቅዱ መሠረት የሀገሪቱ የጦር ሠራዊት በሃማስ ላይ የሚያካሄደውን የጥቃት ዘመቻ ያሰፋል።

የእስራኤል ወታደሮች በአዲስ አካባቢ ተሠማርተው በምድርና ከምድር በታች የሚገኙ ሁሉንም የሃማስ መሠረተ ልማቶችን ያወድማሉ። በዚህ የእስራኤል የዘመቻ እቅድ ምክንያት ተባብሶ በቀጠለው የጋዛ ጦርነት አስከፊ ሠብዓዊ ቀውስ እንደተከሰተም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You