የ“እመርታ” ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ በቅርቡ ይጠናቀቃል

ድሬዳዋ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራ በሆነው በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ እየተገነባ የሚገኘው የድሬዳዋ አስተዳደር የመደመር ትውልድ “እመርታ” ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የባህል ጥናትና ጥበቃ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ገበየሁ ወጋየሁ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የቤተ መጽሐፉ ግንባታ አፈጻጸም በአሁኑ ጊዜ 98 በመቶ ደርሷል። የቀረው ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መጻሕፍት መደርደሪያና መሰል ቁሳቁሶችን ማሟላት ነው። ይህም በአጭር ጊዜ ተሟልቶ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በመጪው ሰኔ ወይም ሐምሌ ወር ለአገልግሎት ክፍት መሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከመደመር ለትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘው ገቢ በቂ ስላልሆነ የድሬዳዋ አስተዳደር ተጨማሪ በጀት መድቦ እንደተጀመረ ያስታወሱት አቶ ገበየሁ፣ ቤተ መፅሐፉ አደረጃጀት ተሠርቶለትና አስፈላጊው ግብዓት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተሟላለት በኋላ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።

“ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነው የግንባታው አፈፃፀም እዚህ የደረሰው።” ያሉት አቶ ገበየሁ፣ ይህም ግንባታውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ትልቅ አቅምና ብቃት ፣ አስተዳደሩና ባለድርሻ አካላትም ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ አድርገው ከተቀመጠለት ጊዜ በፊት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ቤተ መጽሐፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ ፕሮጀክት በመሆኑም ልምድና ተሞክሮው በሌሎችም ሊስፋፋ ይገባል ተብሎ አቅጣጫ የተሰጠበት መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ተወካይ ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ ቤተ መጽሐፉ የተገነባበት አካባቢ በአቅራቢያው ዩኒቨርሲቲ፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አሉ። ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆንም ድሬዳዋ በመረጃና በዕውቀት የበለፀገ ትውልድ ለመፍጠር ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።

የድሬዳዋን የንባብ ባህል ያሳድጋል፣ በእውቀት የበለፀገ ትውልድ ይፈጠራል፣ በዚህም የትም ቦታ ሄዶ በዕውቀቱና በክህሎቱ ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ የሚሠራበት እድል ይፈጠራል ያሉት ተወካይ ዳይሬክተሩ፤ አስተዳደሩ ይህን እንደ ትልቅ እድል ወስዶ እየሠራ የሚገኘው ፕሮጀክት መሆኑንም አብራርተዋል።

ከ470 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለው ቤተ-መጻሕፍት በቀን በአንድ ጊዜ ከሦስት እስከ አራት መቶ ሰው የማስተናገድ አቅም እንዳለው ጠቁመው፤ አጠቃላይ ግንባታው በ2 ሺህ ካሬ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ቤተ-መጻሕፍቱ ባለ አራት ወለል ሕንጻ መሆኑንም ተናግረዋል።

በውስጡም የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል ሲሆን፣ ለአይነ ስውራን የብሬል አገልግሎት፣ የህፃናት ክፍል፣ የጥናትና ምርምር ክፍሎች፣ ለመጻሕፍት ቤቱ ሠራተኞች የህፃናት ማቆያ፣ አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ አገልግሎቶችና የመዝናኛ ቦታ ያለው እንደሆነ ተጠቅሷል። በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስትሮችና ባለድርሻ አካላት ፕሮጀክቱን መጎብኝታቸው ታውቋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You